ይደክማታል!
"የኔ ማር" ይላታል
"ወዬ" ትለዋለች ሰፍ ብላ
"ታላቁ ራሽያዊ የብዝሀህይወት ባለሙያ ኢቫኖቪች ሎቭኮቭ ገነት የነበረችው ኤስያ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም ምክንያቱም የመጀመሪያው አፕል የበቀለው እዚያ አካባቢ ስለሆነ ይላል..."
ይደክማታል! ማይመለከታትን ነገር ሲያወራት 'ምን አይነቱ ሞኝ ነው በሞቴ' ትላለች በውስጧ። ተነስታ ጥላው ለመሄድ ያሰኛታል ግን ደግሞ ትወደዋለች። ዝም ብላ ታየዋለች ይቀጥላል ወሬውን
"... እኔ ግን በእሱ ሀሳብ አልስማማም። ለምን አልሽኝ? ምክንያቱም ለእኔ ገነት ያለችው ሩቅ ሳይሆን እዚሁ አንቺ ከንፈር ላይ ነው"
አሁን ተሳበች.. ሙሉ ሰውነቷን ለንግግሩ ሰጠች
"ተው ባክህ?" እንደማፈር እየሞከራት
"አዎ ካላመንሽኝ..." ይጠጋታል ይጠጋታል ይጠጋታል ትታገሰዋለች እስኪደርስ ይርቅባታል ትንሽ ሲቀረው
"የኔ ማር"
"ወዬ" እየተናደደች
"ከሰውነታችን ጠንካራው ጡንቻ የቱ እንደሆነ ታውቂያለሽ?"
ይደክማታል! በረ.........ጅሙ ተንፍሳም አይቀላትም! ይቀጥላል አሁንም
"ምላስ ነው" ብቻውን ያወራል... ብቻዋን ትነጉዳለች
ድንገት አቋረጠችው
"እኔ እምልህ"
"እ"
"ለምን 'አርዳ' ተባልክ"
"ነግሬሽ የለ አባቴ ቱርካዊ ነው ብየ እሱ ነው ያወጣልህ ብለውኛል"
"ታዲያ ይሄ'ኮ በቂ መልስ አይደለም አባትህን ለምን 'አርዳ' አልከኝ አላልከውም?"
"ትልቅ ከሆንኩ በኋላ ነው አባቴን ያገኘሁትኮ"
"እና አልጠየቅከውም?"
"ተርኪኛ አልችልማ" በራሱ ቀልድ ይስቃል አብራው መሳቅ ይኑርባት አይኑርባት ግራ ይገባታል። የምር ይሄ ቀልድ ነው? ትላለች ለራሷ
ዝም ብላ ታፈጥበታለች ማውራቱን ቀጥሏል። ይሄኔ 3 ርዕስ አንስቶ አምስት ደግሞ ጥሎ ይሆናል። ትወደዋለች። ግን ምኑን እንደሆነ ግራ ይገባታል። ምኑ አምሮኝ ይሆን ግን ተስቤ የቀረሁት? ሉጫ ፀጉሩ አይሆንም መቼስ!
ድንገት ቀኝ ጉንጯን ሳማት ደንግጣ አየችው
ምንም እንዳልተፈጠረ ስለ አንድ ግሪካዊ ፈላስፋ ማውራት ጀመረ... 'ያመዋል እንዴ?' ትላለች ለራሷ
"የኔ ማር"
"ወዬ" ትለዋለች አሁንም ጓጉታ
"ግሪኮች ግን አይገርሙም?"
ይደክማታል! ተነስቼ ጥየው ልሂድ ወይስ ምን ላርግ እያለች ትምታታለች። መወሰን አለብኝ ጎኑ ሆኜም እንዳለሁ አይሰማውም! እንዲህ እንዳልል ደግሞ ለእኔ ብሎ ነው ያንንም ይሄንንም እያነሳ ሚያወራኝ... ትምታታለች። ያምታታታል! ይደክማታል!
"የኔ ማር" ይላታል
"ወዬ" ትለዋለች የተለየ ነገር እንደማይላት እያወቀችም መጓጓቷ ራሷን ያስገርማታል
"ዴዝዴሞናን ታውቂያታለሽ?"
"ኦቴሎ ላይ ያለችውን ከሆነ አዎ!"
"ሞናሊዛንስ?"
"አዎ"
"አያምሩም?"
በተሰላቸ መልክ በትክሻዋ 'እኔእንጃ' ትለዋለች።
"ለእኔ ግን አንቺ ከነሱ በላይ ውብ ነሽ! እነሱኮ ሼክስፒር እና ዳቪንቺ ምናብ ውስጥ የቀሩ ማይጨበጡ ቆንጆዎች ናቸው። አንቺ ግን ድንቅ እና ምርጥ የእግዜር ስራ"
ደስ ይላታል እንዲ ሲያወራት.. ሌላ ነገር እንዳያስብ ተመኘች
"የፀሀየ ዮሐንስ ዘፈን ላይም አለ ይሄ" አለችው
"ምን ሚለው?"
"በአለም አይገኝም አንቺን የሚመስል
ዴዝዴሞናም ታሪክ ሞናሊዛም ስዕል"
"ሀሳብ ግን አይገርምሽም? በተለያየ ሰአት እና ቦታ ሆነን እኔም ፀሀየም ይሄን ማሰባችን..."
አጠፋሁ ትላለች ለራሷ
"የኔ ማር"
"ወዬ"
"ሀሳብ ግን ላንቺ ምንድን ነው? ለእኔ ሀሳብ..."
ይደክማታል! መሄድ ያሰኛታል
'መጨከን አለብኝ መሄድ አለብኝ! አዎ መብሰል ይቀረዋል።' ትላለች መጨከን ደሞ ይከብዳታል። ይደክማታል!
ከራሷ ጋር እልህ ትጋባለች! እስከ 3 ቆጥሬ እነሳለሁ ትላለች።
1.... የምሬን ነው መሄድ ያለብኝ። አሁን ከሄድኩ መመለስ ብሎ ነገር የለም በቃኝ!
2.... ግንኮ አርዳ ጥሩ ሰው ነው። እንደሱ የሚሆንልኝ አላገኝም። እንደው ዝም ብየኮ ነው።
2... ( አውቃ እንደደገመችው ታውቋታል!) ግን ቢሆንም በቃ መሄድ አለብኝ። እሱጋ እንዲኖረኝ የምፈልገውን ያህል ቦታ አልሰጠኝም።
ሶስ...
"የኔ ማር" ይላታል... ድንገት ያሰበችው ፣ የተነተነችው ፣ ያሰለፈችው ነገር ሁሉ ብትንትኑ ሲወጣ ይታወቃታል
"ወዬ"
"በቃ የሚጠብቁኝ ሰዎች ስላሉ እኔ ልሂድ.. አንቺም ብቻሽን ብዙ አትቆይ እዚህ " ብሎ ግንባሯን እና ጉንጯን በስሱ ሳም አርጓት ይሄዳል።
ይደክማታል!
ለራሷ ይሄን አለችው።
እንደውም አልሄድም!😡
በአቤኒ የተጻፈ✒️✒️
(🤗እኔ-"ዮዳA"ወድጄዋለሁ 👌 አቤኒ ይችላል ! )
https://t.me/danutell