የሕጻናት ቆረቆር በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል የምርምር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገየዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕጻናት ቆረቆር በሽታ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችል የተቀናጀ የማኅበረሰብ አቀፍ የምርምር ፕሮጀክት ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ሚያዝያ 16/2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡
የምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ፕሮጀክቱ 1.75 ሚሊየን ብር የተበጀተለት የግራንድ ምርምር ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካትና ትግበራ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡና ትብብራቸው እንዳይለይ አሳስበዋል፡፡
የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ኮርፖሬት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን ዘርዶ የቆሮቆር በሽታን አስመልክቶ ማኅበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ችግር ያለ መሆኑን ጠቁመው ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ከዚህ ጋር የተገናኙና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የምርምር ፕሮጀክቱ ሲካሄድ ማኅበረሰቡን ያሳተፈና ያማከለ መሆን ይገባዋል ያሉት ዶ/ር ዘሪሁን በተለይ በፀጉር ቤቶች ዘንድ የሚታዩ ችግሮች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል፡፡
በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቆዳና አባላዘር ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የቆዳና አባላዘር በሽታ ስፔሻሊስት ሐኪምና የፕሮጀክቱ ዋና ተመራማሪ ዶ/ር ምህረት ተጫኔ የሕጻናት ቆረቆር በሽታ የሕጻናትን ጭንቅላት የሚያጠቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የ3 ዓመት ቆይታ ያለው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ምሕረት ከጥናት ባሻገር በጥናቱ ውጤት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ አቀፍ ትግበራ በት/ቤቶች፣ በፀጉር ቤቶችና በጤና ተቋማት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በበሽታው ዙሪያ ከቀረበው መግለጫ ብዙ ግንዛቤ ያገኙ መሆናቸውን ገልጸው ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር እና የበሽታው ተጠቂ የሆኑ ሕጻናት ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ከዞንና ከከተማ ጤና መዋቅሮች የተወጣጡ የበሽታ መከላከል የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪዎች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ ጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-ድረ-ገጽ -
https://www.amu.edu.et/ቴሌግራም -
https://t.me/arbaminch_universityፌስቡክ -
https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/ዩቲዩብ -
https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVAየሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት