ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎችን አስመረቀ።
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 560 የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመርቋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አማካሪ ሙሉቀን አዳነ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት አብዩ፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የተማሪ ወላጆች፤ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈው ለምርቃት የበቁ ተማሪዎችን፣ የተማሪ ወላጆችን እና የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እና ሠራተኞችን አንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎቹ በርካታ ችግሮች ሳይበግሯቸው ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለምርቃት የበቁ በመኾናቸው የፅናት ተምሳሌት ናቸው ነው ያሉት።
ወደፊትም ችግሮችን የመቋቋም ልምዳቸውን፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትን እና ክህሎት ተጠቅመው ለወላጆቻቸው፣ ለማኅበረሰባቸው እና ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ አማካሪ እና የምርቃቱ የክብር እንግዳ ሙሉቀን አዳነ (ዶ.ር) ዕውቀት እና ክህሎት ይዘው ለምርቃት የበቁ ተማሪዎች ሀገራቸውን የሚያሻግር ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ተመራቂዎች በዕውቀታቸው፣ በክህሎታቸው እና ጉልበታቸው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በስሜት ሳይኾን በስሌት እንዲሠሩ የሚያስችላቸውን ዕውቀት አግኝተዋል ነው ያሉት። ተመራቂዎች ለሀገራቸው የችግሮች መፍትሔ እንጅ የችግሮች ምንጭ መኾን እንደማይኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ
እንደ ሀገር የተጀመረውን የልህቀት እና የልዕልና ጉዞ ለማሳካት ትምህርት አይነተኛ ሚና አለው ብለዋል።
ለዚህም በዕውቀት እና በክህሎት የበቃ ዜጋ ለመፍጠር መንግሥት ትምህርት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በቀጣይ በተማሩት ሙያ ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ በየትምህርት መስኩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ፣ የሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዩኒቨርሲቲው በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ የትምህርት መስክ በከፍተኛ ውጤት የዋንጫ ተሸላሚ የኾነው ተመራቂ ታምሩ ተውቦ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በተለያዩ ችግሮች ቢፈተንም በፅናት ለውጤት እና ለምርቃት መብቃቱን ተናግሯል።
በቀጣይ በተማረበት ሙያ ሀገሩን እና ወገኑን ለማገልገል ዝግጁ መኾኑን ገልጿል።
ሌላኛዋ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ተመራቂ ቤተልሔም አበባው ከሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ኾናለች።
ተመራቂዋ በርካታ ችግሮችን ማለፋቸውን አንስታለች። ትምህርቷ በሽልማት በመጠናቀቁም ደስተኛ እንዳደረጋት ገልጻለች።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያገኘችውን ዕውቀት እና ክህሎት ተጠቅማ ሥራ ጠባቂ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ኾና ወገኗን እና ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ መኾኗንም ተናግራለች።
©️አሚኮ
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news