በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: Din


አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
Din
Statistika
Postlar filtri


▶️፲. "ይህንንም ነገር ተናግሮ ሳይጨርስ ስሙ ጥልምያኮስ የሚባል መልአከ ሞት ወርዶ ልቡን መታው በዚያችው ሰዓት ሞተ" ይላል (2ኛ መቃ.12፥13)። በመቃብያን ቀዳማዊ ላይ ግን  ጺሩጻይዳን የወባ ትንኝ ነክሳው እንደሞተ ነበር የተገለጸውና አይጋጭም?

✔️መልስ፦ አይጋጭም። በብሉይ ኪዳን ማንኛውም ሰው በማንኛውም በሽታ ቢታመምም ነፍሱ ከሥጋው የሚለየው ግን በመልአከ ሞት አማካኝነት ነበር። ስለዚህ ጺሩጻይዳን ወባ ነከሰችውና በጣም ታመመ። በእርሷ ምክንያት ለሞት ደረሰ። ነፍሱን ከሥጋው ደግሞ መልአከ ሞት ለየው። ስለዚህ ምንም የሚጋጭ ነገር የለውም። አንዱ ከአንዱ ጋር የተያያዘ ነውና። ሰው በበሽታ ታሞ ቢሞት የሞቱ መንሥኤ በሽታው ቢሆንም በኋላ ነፍስ ከሥጋ የሚለይ ግን መልአከ ሞት ነው። ስለዚህ የጺሩጻይዳንን ሞት መነሻ ምክንያት ሲያይ በወባ ትንኝ ሞተ ሲባል፣ ነፍሱን ከሥጋ የለየውን ሲያይ በመልአከ ሞት ሞተ ተብሏል።

▶️፲፩. "ሳምራውያን ግን ሥጋችን ትቢያ ይሆናልና አይነሣም ይላሉ" ይላል (2ኛ መቃ.14፥2)። በሌላ ደግሞ "ሰዱቃውያን ግን ነፍሳችን ከሥጋችን ከወጣች በኋላ ከሞቱ ሰዎች ጋራ አንነሣም ለሥጋና ለነፍስም ከሞት በኋላ መነሣት የላቸውም ከሞትንም በኋላ አንነሣም ይላሉ" የሚል አለ (2ኛ መቃ.14፥7)። የሁለቱ ሐሳብ ልዩነት ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ የሰዱቃውያን ትምህርት ሰው ሲሞት ነፍሱ እንደ ጉም ተና ትጠፋለች፣ ሥጋውም ፈርሶ በስብሶ ይቀራል የሚል ነው። የሳምራውያን ትምህርት ደግሞ ነፍስ ትኖራለች እንጂ አትጠፋም። ሥጋ ብቻ ነው ፈርሶ በስብሶ የሚቀር የሚል ነው።

▶️፲፪. 2ኛ መቃ.14፥16 ላይ "ሥጋህም ከነፍስህ ተለይቶ ከኖረ በኋላ እንደ አባታችን እንደ አዳም ሥጋ ሰባት እጥፍ ሆኖ የእግዚአብሔር የቸርነቱ ጠል ታስነሣሃለች" ያለው ቢብራራልኝ።

✔️መልስ፦ ሰባት እጥፍ የሚለው ፍጹም ለማለት ነው። እስመ ኍልቍ ሳብዕ ፍጹም በኀበ ዕብራውያን እንዲል። ስለዚህ በምጽአት ጊዜ ምንም ምን ሳይጎድል አካልህ ይነሣል ማለት ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን ይህን በጥሩ ተርጉመውታል። ግእዙ "ወሥጋከኒ ተአቲቶ ከዊኖ ምስብዒተ በከመ ሥጋሁ ለአቡነ አዳም ታነሥአከ ጠለ ምሕረቱ ለእግዚአብሔር" የሚለውን "ሥጋህም ከነፍስህ ከተለየ በኋላ እንደ አባታችን እንደ አዳም ሥጋ ፍጹም ሆኖ በእግዚአብሔር በቸርነቱ ጠል ይነሣል" ብለው ተርጉመውታል።

▶️፲፫. "ሥጋዎችም ሬሳቸው በወደቀባት ቦታ ይሰበሰባሉ ነፍሳት የሚኖሩባቸው ቦታቸውም ይከፈታሉ ነፍሳትም ቀድሞ ወደ ተለዩበት ወደ ሥጋ ይመለሳሉ" ይላል (2ኛ መቃ.14፥33)። በትንሣኤ ዘጉባኤ ነፍስና ሥጋ መጀመርያ በተለያዩበት ቦታ (ውሃ ያሰጠመውም ውሃ ውስጥ፣ አውሬ የበላውም የተበላበት ቦታ ላይ፣ ወዘተ) ይዋሓዳሉ ማለቱ ነው? እንደዚያ ከሆነ "በደብረ ጽዮን ከበጎቹ ጋር በቀኝ ያቁመን" የምንለው ጸሎት ምን ይሆን?

✔️መልስ፦ አዎ ቀጥታ የተገለጸው እንዲህ ነው። ሰው ሬሳው ከወደቀበት ሆኖ እንደሚነሣ በግልጽ ተጽፏል። "ወይትጋብኡ ሥጋት ውስተ መካናቲሆሙ ኀበ ወድቀ አብድንቲሆሙ" ያለው ለዚህ ነው። ቀሪ የትንሣኤን አፈጻጸም ስንደርስበት የምናውቀው ይሆናል። ከየወደቁበት ሆነው ከተነሡ በኋላ ጻድቃንን በቀኙ፣ ኃጥኣንን በግራው ያቆማቸዋል። ስለዚህ እኛንም በቸርነቱ በቀኙ ያቁመን እንላለን። በቀኙ ያቁመን ማለት የዘለዓለም ሕይወትን ይስጠን ማለት ነው። በግራ አቆማቸው ማለት ወደ ዘለዓለማዊ የመከራ ቦታ እንዲሄዱ ፈረደባቸው ማለት ነው። በደብረ ጽዮን እግዚአብሔር ነግሦልን ይኖራል ማለት በመንግሥተ ሰማያት ነግሦልን ይኖራል ማለት ነው።

▶️፲፬. 2ኛ መቃ.14፥1 አይሁድ በትንሣኤ ሙታን አያምኑም እንዴ? በተጨማሪ በኦሪት የተጻፉ ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚያትቱ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? (2ኛ መቃ.14፥25)።

✔️መልስ፦ መላው አይሁድ ባይሆኑም ዛሬ እንብላ እንጠጣ፣ ነገ እንሞታለን፣ በዚያም የምናየው የለም የሚሉ የአይሁድ ክፍሎች እንደነበሩ መጽሐፈ መቃብያን በግልጽ ጽፎልናል። በኦሪት ትንሣኤ ሙታን እንዳለ የሚያስረዱ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ከእነዚህም አንዱ የሣራ አርጅቶ መውለድ ነው። ይህን የመሰሉ ብዙ ምሳሌያዊ ትምህርቶች አሉ። ሙሉ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በመክብባቸው ኦሪት ስለሚላቸው ዳዊትም "እስመ ኢተኀድጋ ውስተ ሲኦል ለነፍስየ" ብሎ ሰውነቴን በመቃብር አትተዋትም ብሏል። በዚህም ትንሣኤ ሙታን መኖሩን አስረድቷል። በመጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ላይም በስፋት ትንሣኤ ስለመኖሩ ተገልጿል።

▶️፲፭. 2ኛ መቃ.14፥6 ጳውሎስ ያለው የትንሣኤ ሙታን አረዳድ ከፈሪሳውያን ጋር ተመሳሳይ ነውን? (የሐዋ.ሥራ 23፥6)።

✔️መልስ፦ አይመሳሰልም። ቅዱስ ጳውሎስ ፈሪሳዊ ነኝ ያለው በግብሩ ሳይሆን በትውልዱ ነው። እንጂ እርሱማ ትንሣኤ ሙታንን የሚያምን ስለትንሣኤ ሙታንም በስፋት ያስተማረ ታላቅ ሐዋርያ ነው (ዕብ.6፥2)።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 121 💙💙

▶️፩. 2ኛ መቃ.11፥6 "በሥጋና በነፍስ ሕያዋን ሳሉ ከከብቶቻቸውና ከድንኳኖቻቸው ጋራ ወደ ሲኦል አወረዳቸው" ይላል እንስሳት ሲኦል ይወርዳሉን?

✔️መልስ፦ ሲኦል መካነ ነፍሰ ኃጥእ ናት። በሲኦል የሚኖሩ የበደሉ ሰዎችና አጋንንት ናቸው። እንስሳት፣ አዕዋፋት፣ አራዊትና ሌሎችም ደማውያን ፍጥረታት ሲኦል አይኖሩም። ከዚህ ጥቅስ "በሥጋና በነፍስ ሕያዋን ሳሉ ከከብቶቻቸውና ከድንኳኖቻቸው ጋራ ወደ ሲኦል አወረዳቸው" ያለው ወደ መቃብር ወረዱ ማለት ነው። መቃብርን ሲኦል ስለሚለው ነው። ከነቤታቸውና ከነእንስሳቸው ስለሚቀበሩ መቃብሩን ሲኦል ብሎት መሆኑን ያስተውሉ።

▶️፪. "በምድር ላይ ብዙ ዘመን ከመኖር በገነት አንዲት ቀን መደሰት ይሻላል" ይላል (2ኛ መቃ.13፥4)። ከዚህ አያይዤ መጠየቅ የፈለኩት ሰማዕትነትን በተመለከተ ነው። አንድ ክርስቲያን የሞት ሰማዕትነትን ቢሸሽ ወይም ከሞት ሸሽቶ ቢሰደድ እንደ ኀጢአት ይቆጠርበታል? በሃይማኖት ምክንያት ከሚመጣ ሞት ወይም መከራ ሸሽቶ ከአካባቢ ርቆ ለመኖር ቢወስንስ ኀጢአት ነው?

✔️መልስ፦ ኃጢአት አይሆንበትም። በክርስትና ሁለት ዓይነት ሕይወት አለ። ሁለቱንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳይቶናል። አንደኛው ሞትን ከፈራን መሰደድ እንደምንችል የሚያሳይ ነው። ጌታ ወደ ግብጽ የተሰደደ ለሚሰደዱት አብነት ለመሆን ነው። ኢየሱስ ስዱድ ተስፋሆሙ ለስዱዳን እንዳለ ደራሲ። በእርግጥ እርሱ አርአያ ለመሆን ተሰደደ እንጂ ፈርቶ አልተሰደደም። ከፈራን እንድንሸሽ ራሱ ጌታ "በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ" ብሎ ገልጾልናል (ማቴ.10፥23)። ሁለተኛው ለመሞት የቆረጠ ካለ ደግሞ ሰማዕት እንዲሆን ጌታ በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ አሳይቶናል።

▶️፫. "ስሙ ጥልምያኮስ የሚባል መልአከ ሞት ወርዶ ልቡን መታው" ይላል (2ኛ መቃ.12፥13)። ይህ መልአክ ቅዱስ ነው ርኩስ? መልአከ ሞትስ ቁጥሩ አንድ ነው?

✔️መልስ፦ መልአከ ሞት የሚባል ራሱ ሰይጣን ነው። ሰይጣን ደግሞ ርኩስ ነው እንጂ ቅዱስ አይደለም። ሰይጣን የሚባሉ በሰይጣን ስም የሚጠሩ አጋንንት ሁሉ ናቸው። ስለዚህ ቁጥራቸውም ብዙ ነው። መጽሐፍ ግን በግብር አንድ ከሆኑ ዘንድ በአንዱ የሁሉን ግብር ይገልጻል። ለምሳሌ ሰይጣን የብርሃን መልአክ እንደሚመስል ሲጻፍ ለአንዱ ብቻ የተነገረ ሳይሆን ለሁሉ የተነገረ ነው። ቃል በቃል መልአከ ሞትን ሰይጣን ሲለው "እስመ ደቂቅ ተሳተፉ በሥጋ ወደም። ውእቱኒ ተሳተፎሙ በዝንቱ ወከመ ቢጾሙ ኮነ ሎሙ። ከመ በሞቱ ይስዐሮ ለመልአከ ሞት ዘውእቱ ሰይጣን" ይላል (ዕብ.2፥14)። ትርጉሙም "ልጆች በሥጋና በደም አንድ ናቸውና እርሱ ደግሞ በዚህ ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነ። ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው። መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ ይኸውም ሰይጣን ነው" ማለት ነው።

▶️፬. "የተናገረው ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይደረግለት ነበር" ይላል (2ኛ መቃ.11፥6)። ለሙሴ እግዚአብሔር እንዲናገር ተናግሮት ሳለ "እንደ እግዚአብሔር ቃል ይደረግለታል" ማለት ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ የእግዚአብሔር ቃል ከተነገረ ይደረጋል። እግዚአብሔር ተናግሮ ሳይደረግ የቀረ የለም። ሙሴም በጸጋ ከእግዚአብሔር ቃልን (ትምህርትን) ስለተቀበለ እግዚአብሔር በባሕርይው ሁሉን እንደሚያደርግ ሁሉ ለሙሴም በጸጋ ሁሉ ይደረግለት ነበር ማለት ነው።

▶️፭. "ካህናቱን ይሾማቸዋልና በእነርሱ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር አስመሰለው" ይላል (2ኛ መቃ.11፥5)። በእነርሱ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር አስመሰለው ሲባል ትርጓሜው ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ እግዚአብሔር በባሕርይው እንደሚከበር፣ ካህናትንም እንደሚሾም ሁሉ ሙሴ ደግሞ ከእግዚአብሔር በተቀበለው ጸጋ አሮንንና ካህናትን መሾሙንና በካህናት ዘንድ በጸጋ መከበሩን ለመግለጽ እንደ እግዚአብሔር አስመሰለው ተብሏል።

▶️፮. "በሞትህ ጊዜ የተያዝክባት የሲዖል ገመድ በአንገትህ አለችና ሳትወድ ይፈረድብሃል" ይላል (2ኛ መቃ.14፥11)። ከዚህ ከዘላለማዊ ፍርድ አያይዤ ለፍርድ ዙፋን የሚቀርቡት አምነው ምግባር ያልሠሩት ብቻ ናቸው ወይስ ያላመኑትም ናቸው?

✔️መልስ፦ ሰው የሆነ ሁሉ በዕለተ ምጽአት ይነሣል። ሰው ሆኖ ትንሣኤ የሌለው የለም። ሃይማኖት ያልነበራቸው ከሓድያንም፣ ሃይማኖት ኖሯቸው ምግባር ያልሠሩ ኃጥኣንም፣ ሃይማኖት ኖሯቸው ምግባር ትሩፋት የሠሩ ጻድቃንም ሁሉም ይነሣሉ።

▶️፯. "በአንገትህ የታሠረች ያች ገመድ ለእናትህ ማሕፀን ከሲኦል ግንድ ለአንተ ትበቅላለች። አንተም ባደግህ ጊዜ እርሷም ታድጋለች" ይላል (2ኛ መቃ.14፥12)። ከዚህ ጋር አያይዤ
በእናታቸው ማሕፀን እያሉ የሚሞቱ ትንሣኤ ሙታን ያገኛሉ? ለፍርድስ ይቆማሉ? ከቆሙስ እንዴት ባለ መልኩ?

✔️መልስ፦ ተሥዕሎተ መልክእ የተፈጸመለት ሁሉ በትንሣኤ ጊዜ ይነሣል። ሳይወለዱ በውርጃ የወረዱ ሕፃናት ሁሉ ይነሣሉ። ነፍስ የነበረው ሰው ሁሉ ይነሣል። ማንኛውም የሰው ጽንስ ገና ሲጸነስ ከእናትና ከአባቱ ሥጋን እንደሚነሣ ሁሉ ነፍስንም ይነሣል። ስለዚህ ከጽንስ ጀምሮ ነፍስ ያለው ሰው ስለሆነ ይነሣል። ክርስቶስን ሰው ሆነ የምንለው በተጸነሰ ጊዜ ነው። የተጸነሰበትን ቀን ማለትም መጋቢት 29ን ዕለተ ትስብዕት (ሰው የሆነባት ዕለት) ብለን እናከብራታለን። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከተጸነሰ በኋላ ሰው ስለሚባል ሳይወለድ ቢሞት እንኳ በትንሣኤ ጊዜ ይነሣል። እንዴት ባለ መልኩ ይነሣሉ ለሚለው ያኔ ስንደርስ እናውቀዋለን። መጽሐፍ ሁሉም ወንድ የሠላሳ ዓመት ቁመና ኖሮት ሴት የአሥራ አምስት ዓመት ቁመና ኖሯት ይነሣሉ ብሎናል።

▶️፰. "ያን ጊዜ በነፋስ ውስጥ ያለ ነፋስ ባሕርይህም ቢሆን፥ በውኃ ውስጥ ያለ ውኃ ባሕርይህም ቢሆን፤ በመሬት ውስጥ ያለ መሬት ባሕርይህም ቢሆን፤ በእሳት ውስጥ ያለ እሳት ባሕርይህም ቢሆን ይመጣል። በአንተ ያደረች በጨለማ የምትኖር ነፍስም ብትሆን ትመጣለች" ይላል (2ኛ መቃ.14፥19)። የዚህ ንባብ ትርጓሜ ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሥጋው ትለያለች። ተለይታም ኃጥእ ከነበረ ሲኦል ይቆያል። ጻድቅ ከነበረ ገነት ይቆያል። ሥጋችን ደግሞ ከአራቱ ባሕርያት የተገኘ እንደመሆኑ የመሬት ባሕርይ ወደ መሬትነት፣ የነፋስ ባሕርይ ወደ ነፋስነት፣ የእሳት ባሕርይ ወደ እሳትነት፣ የውሃ ባሕርይ ወደ ውሃነት ይመለሳል። በዕለተ ምጽአት በዳግም ትንሣኤ ጊዜ ሙታን ሲነሡ አራቱ ባሕርያት ከሞት በፊት ወደነበሩበት የሰውነት ማንነት ይመለሳሉ። የኃጥእ ነፍስም ከጨለማ ከሲኦል ወጥታ ከአራቱ ባሕርያት ጋር ተዋሕዳ ትነሣለች። የጻድቅ ነፍስ ደግሞ ከብርሃን ከገነት ወጥታ ከአራቱ ባሕርያት ጋር ተዋሕዳ ትነሣለች። ከዚያ ዘለዓለማዊ ፍርድ ይደረጋል ማለት ነው።

▶️፱. "በሙሴ ወንበር ተቀምጠህ በቃልህ የሙታን ትንሣኤ የለም ትላለህ" ይላል (2ኛ መቃ.14፥24)። በሙሴ ወንበር ተቀምጠህ ሲል ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ የሙሴን መጻሕፍት ተቀብለው የሚያስተምሩ ሰዎች በሙሴ ወንበር የተቀመጡ ይባላሉ። ፈሪሳውያን፣ አይሁድ፣ ሳምራውያን፣ ሰዱቃውያን ሁሉ የሙሴን መጻሕፍት ተቀብለው ነገር ግን በመጻሕፍቱ መሠረታዊ ፍሬ ሐሳብ የማያምኑ ስለነበሩ በሙሴ ወንበር ተቀምጣችሁ ትንሣኤ ሙታን የለም ትላላችሁ ተብለው ተገሥጸዋል (ማቴ.23፥2)።


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 120 💙💙

▶️፩. "ወደ አራስና ሳትነጻ በደሟ ወዳለች ሴት መሄድ" እንደ ኀጢአት በብሉይ ኪዳን ተቆጥሯል (2ኛ መቃ.9፥21)። አንዲት ሴት ስትወለድ ማን ያርሳታል ወይስ ራሷ እንድትሠራው ነው? በሐዲስ ኪዳንስ ያለው እንዴት ነው?

✔️መልስ፦ ወደ አራስና ሳትነጻ በደሟ ወዳለች ሴት መሔድ አይገባም ብሎ የገለጸው ከዚህ በአራስነቷ ወይም በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግንኙነት አይገባም ማለት ነው እንጂ እንኳን ማርያም ማረችሽ ለማለት አራስን ለመጠየቅ መሔድ አይገባም ማለት አይደለም። በእርግጥ በብሉይ ኪዳን አራስ ቤተ መቅደስ እስከምትገባና ሌላም ሴት በወር አበባዋ ወቅት ሳለች እንደ ርኵስት ትታይ ነበር። እና እርሷን ሰላም ማለትና መንካትም ያረክስ ነበር። በሐዲስ ኪዳን ግን ሰላምታም አይከለከልም። መስቀል መሳለምም ትችላለች። ቤተክርስቲያን ውስጥ መግባትና መቁረብ ብቻ አይፈቀድላትም።

▶️፪. እግዚአብሔር እስራኤላውያን ሲበድሉ የአሕዛብን ነገሥታት አስነሥቶ ያስማርካቸዋል። መልሶ ደግሞ የአሕዛብን ነገሥታት በዚያ ድርጊታቸው ይኮንናቸዋል ይሄ ነገር እንዴት ይታያል?

✔️መልስ፦ ማንኛውም ሰው በደለኛ ከሆነ በበደሉ ይቀጣል። አንድ ጻድቅ ሲያጠፋ እግዚአብሔር በኃጥእ እጅ ሊጥለው ይችላል። ይህም ተጸጽቶ ንስሓ እንዲገባ ነው። ኃጥእ ራሱ ግን ባደረገው በደል ይቀጣል። ለምሳሌ ይሁዳ ጌታን በሠላሳ ብር የሸጠው ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ነው። ንጹሕ ሰውን አሳልፎ መሸጥ ኃጢአት መሆኑን ይሁዳም ያውቅ ነበር። ብሩ በልጦበት እስከ መካድ ደረሰ። አሁን በዚህ ጊዜ ተሰቅሎ ዓለምን ማዳን የጌታም ፈቃዱ ስለሆነ የይሁዳን ክፋት እርሱ ለሌሎች መዳኛ አድርጎ ለውጦታል። ይሁዳ ግን ክፋትን ስለሠራ ተጠያቂ ሆኖ በበደሉ ተቀጥቶበታል። የአሕዛብ ነገሥታት እስራኤላውያንን እየማረኩ ሲበድሏቸው ኖረዋል። አሕዛብ ክፋትን ስላደረጉ በክፋታቸው ይቀጣሉ። እስራኤላውያንም በክፋታቸው ይቀጣሉ። ክፋት ሆኖ የማያስቀጣ ነገር እንደሌለ ሁሉ መልካም ሥራ ሆኖ የሚያስጎዳም የለምና።

▶️፫. አንደኛ መቃብያን ላይ ያለው መቃቢስ ታሪኩ አልተገለጸም ነበር። ሁለተኛ መቃብያን ላይ ነው የተገለጸው። እንደዚህ ከሆነ ለምን ከሁለተኛ መቃብያን አልጀመረም? አንደኛና ሁለተኛ መቃብያንስ ልዩነቱ ምንድን ነው? ታሪኩ ስለተመሳሰለብኝ ነው ።

✔️መልስ፦ ምንም እንኳ ታሪካቸው ተቀራራቢ ቢሆንም ሁለቱም መጻሕፍት የተጻፉት ስለተለያዩ ሰዎች ነው። አንደኛ መቃብያን የተጻፈው ስለመቃቢስ ዘብንያምና ስለ ልጆቹ ሲሆን ሁለተኛ መቃብያን የተጻፈው ደግሞ ስለ መቃቢስ ዘሞዓብ ነውና።

▶️፬. "ክሣደ ልቡናውን በማጽናትና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን እምቢ እንዳለ" ይላል (2ኛ መቃ.9፥3)። ይሄ ንባብ ምን ለማለት ነው?

✔️መልስ፦ ቅዱሳን መላእክት አዳም በእግዚአብሔር አርዓያና መልክ የተፈጠረ መሆኑን ሲሰሙ እግዚአብሔር በባሕርይው ስለማይታይ አምሳሉን አዳምን ለማየት ይጓጉ ነበር። እናም ቅዱሳን መላእክት አዳምን አይተው ሲያከብሩትና ደስ ሲሰኙ ሰይጣን ግን ክፉ ቅንዐትን ቀንቷል። የዲያብሎስን አለመደሰትና አለማክበር አለመስገድ ብሎ ገልጾታል።

▶️፭. "አሳዝነውታልና ክፉ ሥራ የሠሩ ሰዎችንም አስነሥቶ ፈርዶ ወደ ገሃነም ይወስዳቸዋል" ይላል (2ኛ መቃ.9፥16)። መቼም ፍርድ ሲባል የመጨረሻው ቀን (ምጽአት) ነው። መምህር እዚህጋ አንድ ነገር ግልጽ ቢያደርጉልኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞቶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ከዲያቢሎስ አገዛዝ (ባርነት) ነጻ አወጣ። አንዳንድ መመህራን "ሲኦል ተመዘበረች ባዶ ቀረች" ይላሉ። ከሲዖል ያወጣቸው በስሙ (በእግዚአብሔር  አምላክነት) አምነው የሞቱትን የአዳም ልጆች ብቻ ነው ወይስ በአምላክነቱ ሳያምኑ የሞቱትን አሕዛብንም ጭምር ነው? ለዘለዓለም ወደ ገሃነም የሚገቡ ሲኦል ውስጥ የቀሩ ነፍሳት ነበሩ?

✔️መልስ፦ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ከዚያ በፊት የነበሩ ሕዝብና አሕዛብን በጠቅላላው የአዳም ልጆችን አድኗል። መድኃኔዓለም መባሉ አንዱ በዚህ ነው። ስለዚህ ከዚያ በፊት አምነው የሞቱትም ሳያምኑ የሞቱትም ከሲኦል ወጥተው ወደ ገነት ገብተዋል። እንጂ ያን ጊዜ ሲኦል የቀሩ ነፍሳት አልነበሩም። በመቅድመ ወንጌል ወኀደጎሙ ለእኩያን የሚለውን ሲያትት አጋንንትን በሲኦል እንደተዋቸው ይናገራል። የሰው ልጆች ግን ሁላቸውም ወጥተዋል። ከስቅለት በኋላ ያለን ሰዎች ደግሞ አምነን በመጠመቅና መልካም ሥራን በመሥራት ወደ ገነት እንድንገባ ነጻ ፈቃድ ተሰጥቶናል። ነጻ ፈቃዳችንን ለበጎ እንጠቀምበት። ከስቅለት በኋላ ግን ክፋት ሠርቶ ሲኦል የሚገባ ሰው በኋላ ዘመን ወደ ዘለዓለማዊ ገሃነም እንደሚገባ ተገልጿል (ማቴ.25)።

▶️፮. መቃብያን ማለት ምን ማለት ነው? የመጽሐፈ መቃብያን ጸሓፊስ ማን ነው?

✔️መልስ፦ መቃብያን ማለት የመቃቢስ ዘሮች ማለት ነው። የእነርሱን ታሪክ ስለሚናገር የመጽሐፉ ስም በእነርሱ መቃብያን ተብሏል። የመጽሐፈ መቃብያን ጸሓፊ ከዚሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማን እንደሆነ አልተገለጸም። በሌላ የታሪክ መጽሐፍ ካለ ከዚያ ይፈልጉት። ያስጻፈው መንፈስ ቅዱስ ለመሆኑ ግን መጻሕፍት አምላካውያት ከሚባሉት በመመደቡ ታውቋል (ፍት.ነገ.2)።

▶️፯. በለዓም ንጉሡ ባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት ብዙ እጅ መንሻ ቢያቀርብለትም የእግዚአብሔርን ቃል በማክበር ጥያቄውን እንዳልተቀበለ ተገልጿል (2ኛ መቃ.10፥12)። ብዙ ጊዜ ትምህርት ሲሰጥ ግን በለዓም በበጎ ጎን ሲነሣ አልሰማም። በአሉታዊ ሁኔታ በበለዓም መንገድም ሄደዋልና ተብሎም ሌላ ስፍራ ላይ ተጠቅሷል እንጂ። ይህ ሀሳብ እንዴት ይታረቃል?

✔️መልስ፦ በለዓም ጠንቋይ ነው። እስራኤላውያን ሊረግም ሲሄድ እንኳ እግዚአብሔር አፉን ከፍቶ ፊቱን ጸፍቶ ነው አልረግምም ያሰኘው። ፈርቶና ተገዶ ነው እንጂ የእግዚአብሔርን ቃል አክብሮና በእግዚአብሔር አምኖ አልነበረም አልራገምም ያለ። ክፉና ተንኮለኛ ሰው እንደነበረ የሚያሳየን ባይራገም እንኳ ክፉ ምክር መክሮ እስራኤላውያን እንዲጎዱ በማድረጉ ነው።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


💝 ሁለተኛ መጽሐፈ መቃብያን ክፍል 3 💝

💝ምዕራፍ ፲፩፡-
-ሙሴ ሕዝቡን ሲመራ እንዳልተበሳጨ መገለጡ
-የእግዚአብሔርን ቃል ካልተላለፍን ፈቃዳችንን እንደሚያደርግልን መገለጡ

💝ምዕራፍ ፲፪፡-
-የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማያደርጉ ሰዎች ወዮታ እንዳለባቸው
-ክፋትን የሚሠሩትን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው
-ጺሩጻይዳን እንደሞተ

💝ምዕራፍ ፲፫፡-
-ይህ ዓለም እንደሚያረጅና እንደሚያልፍ ተድላውም ለዘለዓለም እንደማይኖር ዐውቀው ያመኑ የመቃቢስ ልጆች ለጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት አንበላም በማለታቸው በሰማዕትነት ሰውነታቸው ለሞት እንደሰጡ
-ከንጉሥ ቁጣ የእግዚአብሔር ቁጣ እንደሚከፋ መነገሩ

💝ምዕራፍ ፲፬፡-
-ስለ ፈሪሳውያን፣ ስለ ሳምራውያን እና ስለሰዱቃውያን አስተምህሮ መነገሩ

💝ምዕራፍ ፲፭፡-
-ጻድቃን በዳግም ምጽአት ጊዜ በደስታ እንደሚኖሩ መገለጹ
-በዕለተ ምጽአት ሁሉ እንደ ሥራው እንደሚከፈለው
-ኃጥኣን በዕለተ ምጽአት ቀድሞ በሠሩት ክፉ ሥራ እንደሚጸጸቱና እንደሚያለቅሱ

💝💝💝የዕለቱ ጥያቄዎች💝💝💝
፩. እኛ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንፈጽም እግዚአብሔር ለእኛ ምን ያደርግልናል?
ሀ. መልካም ፈቃዳችንን ያደርግልናል
ለ. በመከራችን ጊዜ ቸል አይለንም
ሐ. ኃጢአታችንን ያስተሠርይልናል
መ. ሁሉም
፪. ጺሩጻይዳንን የገደለው ማን ነው?
ሀ. መቃቢስ ዘይሁዳ
ለ. መቃቢስ ዘሞዓብ
ሐ. ጥልምያኮስ የተባለ መልአከ ሞት
መ. መብክዩስ
፫. ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ይህች ዓለም የምታልፍና የምታረጅ ናት ተድላዋም ለዘለዓለም አይኖርም
ለ. የመቃቢስ ልጆች መከራ ሲጸናባቸው የጣዖት መሥዋዕትን በልተዋል
ሐ. በምድር ላይ ብዙ ዘመን ከመኖር በገነት አንዲት ቀን ደስ መሰኘት ይሻላል
መ. እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው
፬. ከሚከተሉት ውስጥ በትንሣኤ ጊዜ ሥጋችን ትቢያ ይሆናልና አይነሣም ነፍሳችን ግን ትነሣለች የሚሉት የትኞቹ ናቸው?
ሀ. ፈሪሳውያን
ለ. ሳምራውያን
ሐ. ሰዱቃውያን
መ. ሀ እና ለ

https://youtu.be/YErG3SRvW6w?si=LNRHXlMbYejy4GyZ


💛 ሁለተኛ መጽሐፈ መቃብያን ክፍል 2 💛

💛ምዕራፍ ፮፡-
-የእግዚአብሔር ጠላት ጺሩጻይዳን የሐሰት ካህናትንና የጣዖታቱን አገልጋዮች እንደሾመ፣ እነዚህም ለጣዖታት መሥዋዕትን ይሠዉ እንደነበር
-የመቃቢስ ልጆች ለጣዖታት አንሰግድም በማለታቸው እንደታሰሩና እንደተሰደቡ
-የመቃቢስ ልጆች በሰማዕትነት በእሳት ተቃጥለው እንደሞቱ

💛ምዕራፍ ፯፡-
-ሰማዕት ከሆኑ በኋላ የመቃቢስ ልጆች ለጺሩጻይዳን በራእይ ተገልጠው እንዳስፈራሩት

💛ምዕራፍ ፰፡-
-ጺሩጻይዳን በኩራትና በልብ ተንኮል እንደሄደ

💛ምዕራፍ ፱፡-
-ሰው ነገ መሬትና አመድ የሚሆን እንደመሆኑ መኩራት እንደማይገባው መነገሩ
-ኃጥኣን በጻድቃን ምክር ይኖሩ ዘንድ እንደማይወዱ መገለጹ
-ጻድቃን እግዚአብሔር ከማይወደው መንገድ ሁሉ እንደሚርቁ መነገሩ

💛ምዕራፍ ፲፡-
-ነገሥታትና መኳንንት በሰይጣን ጎዳና መሄድ እንደማይገባቸው መገለጹ
-ነገሥታትና መኳንንት እግዚአብሔርን መፍራት እንደሚገባቸው መገለጹ

💛💛💛የዕለቱ ጥያቄዎች💛💛💛
፩. የመቃቢስ ዘሞዓብ ልጆች ለጣዖት አንሰግድም ስላሉ ምን ተደረገባቸው?
ሀ. በጣዖታውያን ተሰደቡ
ለ. በጣዖታውያን ታሰሩ
ሐ. በእሳት ተጥለው ሰማዕት ሆኑ
መ. ሁሉም
፪. ስለጺሩጻይዳን ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ለድኻ አይራራም ነበር
ለ. እግዚአብሔርን ያመልክ ነበር
ሐ. ለጣዖት ይሰግድ ነበር
መ. ትዕቢተኛ ነበር
፫. ከሚከተሉት ውስጥ የኃጥኣን መንገድ የተባለው የቱ ነው?
ሀ. ፍቅርና ሰላም
ለ. ቅሚያና ክዳት
ሐ. ጾምና ጸሎት
መ. ትሕትናና የውሃነት

https://youtu.be/aAD-FgWCdMM?si=yZS0O3KKZPHg7-Yy


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 119 💙💙

▶️፩. "መስጊዳቸውን፣ ጥንቆላቸውንና ጣዖቶቻቸውን" ይላል (2ኛ መቃ.3፥20)። "መስጊዳቸውን" የሚለው ቃል በዚህ መጽሐፍ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት (ካልተሳሳትኩ)። ይሄ ደሞ መጽሐፉ መች ነው የተጻፈው የሚል ጥያቄ ይወልዳል? እስልምና ከመነሣቱ በፊት መስጊድ ነበር?

✔️መልስ፦ በግእዝ ሰገደ ከሚለው ቃል ምስጋድ የሚል ባዕድ ዘር ይወጣል። ትርጉሙ መስገጃ፣ መሰገጃ ማለት ነው። ይህንን ዐረብኛው መስጊድ ይለዋል። ስለዚህ እስልምና ከመነሣቱ በፊትም ጣዖታዊ ሰው ለጣዖት የሚሰግድበት ልዩ ቦታ ስለነበረው ያን ቦታ መስጊድ ማለት የተለመደ ነበር። ስለዚህ እስልምና ከመነሣቱ በፊትም ለጣዖት የሚሰገድባቸው ብዙ ቦታዎች ስለነበሩ እነርሱን ለመግለጽ የብሉይ ጸሓፊዎች መስጊድ ብለዋቸዋል።

▶️፪. "እርሱ ልዩ ሞዓባዊ ሲሆን አይሁድ የሚከለክሉትን ምግብ ይከለክል ነበር" ይላል (2ኛ መቃ.4፥15)። "ልዩ ሞአባዊ" ሲል ምን ማለቱ ነው? በሐዲስ ኪዳን አንድ ሰው ወደ ክርስትና ቢመጣ ቀድሞ የነበረውን የምግብ ሥርዓት መተው አለበት?

✔️መልስ፦ መቃቢስ ልዩ ሞዓባዊ መባሉ ሞዓባውያን ጣዖት ሲያመልኩ እርሱ በኋላ ተለይቶ በእግዚአብሔር ያመልክ ስለነበረ ነው። በሌላ አተረጓጎም በነገድ ከእስራኤላውያን የተለየ ሆኖ ሳለ በአምልኮ እንደ እስራኤላውያን ሆኖ ስለተገኘ ልዩ ሞዓባዊ ተብሏል። በሐዲስ ኪዳን አንድ ሰው ወደ ክርስትና ቢመጣ ክርስትና ከሚከለክላቸው ምግቦች መከልከል ግዴታው ነው። ክርስትና ለጣዖት የታረደን፣ ደምን፣ ሞቶ ያደረን፣ ጥሬ ሥጋን መብላትን ይከለክላል። ስለዚህ ከእነዚህ መከልከል ግዴታው ነው። ሌላው ግን የባህል ጉዳይ ስለሆነ እንደየባህሉ የመቀጠል ነጻ ክርስቲያናዊ ፈቃድ አለው።

▶️፫. "ከዚህም በኋላ የከለዳውያን ንጉሥ ጺሩጻይዳን መጣ። ሀገራቸውንም ሁሉ አጠፋ" ይላል (2ኛ መቃ.5፥4)። እስካሁን ባነበብነው እስራኤሎች በባዕድ እንዲወረሩ የሚሆነው እግዚአብሔርን በረሱበት ዘመን ነበር። በዚህ ታሪክ የመቃቢስ ልጆች በሥርዓት እየኖሩ አልነበረም ወይ? እግዚአብሔር እንዴት አሳልፎ ሰጣቸው?

✔️መልስ፦ መከራ በሁለት መልኩ ይመጣል። አንደኛው ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ ለተግሣጽ እግዚአብሔር መከራን የሚያመጣባቸው ጊዜ አለ። እስራኤላውያን ሲበድሉ የተለያዩ መከራዎች ይደርስባቸው የነበረው በዚህ አግባብ ነው። ሁለተኛው ሰዎች ምንም በደል ሳይበድሉ ጸጋቸው ይበዛ ዘንድ እግዚአብሔር የሚያመጣባቸው መከራ ነው። የመቃቢስ ልጆች የደረሰባቸው መከራ ይህ ነው። ሰማያዊ ዋጋቸው ይበዛ ዘንድ ነው መከራ የመጣባቸው። መከራን በትዕግሥት ቢቀበሉት የጸጋ ምንጭ ይሆናልና።

▶️፬. "አሁን ስለወለድካቸው ልጆችህ እግዚአብሔር ኀጢአትህን ይቅር አለህ" ይላል (2ኛ መቃ.3፥5)። የመቃቢስ ልጆች እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር?

✔️መልስ፦ መቃቢስ ስለወለድካቸው ልጆችህ እግዚአብሔር ኃጢአትህን ይቅር አለህ መባሉ ልጆቹ በኋላ ሰማዕት ሆነው እንደሚያርፉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለሚያውቅ በእነርሱ የኋላ ግብር ይቅር እንዳለው የሚያመለክት ቃል ነው። ምክንያቱም መቃቢስ ልጆቹን ያስተማራቸው ንስሓ ከገባ በኋላ ነው። እነርሱም ኖሩ የተባለው አባታቸው ባስተማራቸው ሥርዓት ነውና (2ኛ መቃ.5፥1)። ስለዚህ ይህ ቃል መቃቢስ ካመነ በኋላ ልጆቹም እንዳመኑ ያመለክታል።

▶️፭. መቃቢስ ቀድሞ እግዚአበሔርን የማያመልክ እንደነበረ ይታወቃል። እስካሁን ባነበብናቸው የእስራኤል ታሪኮች እግዚአብሔር መከራ ሲያመጣባቸው ከመከራ እንዲድኑ በንስሐ ወደ እርሱ እንዲመለሱ የእስራኤልን ሕዝብ ነበር የሚያስጠነቅቀው። በዚህ ታሪክ ግን መቃቢስ በባለ ራእዩ ራእይ ሲገሥጸው አይተናል ለምን ሕዝቡን ንስሓ አስገብቶ ከመከራ አላዳናቸውም ነበር?

✔️መልስ፦ እግዚአብሔር በመግቦቱ ለሁሉም የንስሓ ጊዜን ይሰጣል። ስለዚህ ለሕዝቡም ብዙ ጊዜ ነቢያትን እየላከ ከበደላቸው እንዲመለሱ አስተምሯል። ምክሩን ሰምተው ተግባራዊ ያደረጉት ግን በየዘመኑ ጥቂቶች ናቸው። ከዚህም መቃቢስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ አምኖ ንስሓ ገብቶ አርፏል። ስለዚህ እግዚአብሔር የእነርሱን መታመን አይቶ ያዳናቸው አሉ። በክፋታቸው በጸኑት ደግሞ መከራን አምጥቷል።

▶️፮. "ስለ እነዚህ ልጆች ከአንተ ጋር ያለውን ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ" ይላል (2ኛ መቃ.3፥10)። "ካንተ ጋር ያለውን ቃል ኪዳኔን" ሲል መቃቢስ ቃል ኪዳን ነበረው? መቃቢስ በቀድሞ ሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚያመልክ ነበር?

✔️መልስ፦ መቃቢስ በቀድሞ ሕይወቱ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አልነበረም። በኋላ ግን ንስሓ ገብቶ እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሆኗል። እግዚአብሔርም ለመቃቢስ ቃል ኪዳን የገባለት ከተመለሰ በኋላ ነው። እግዚአብሔር ለመቃቢስ የገባለት ቃል ኪዳን እንዳለ በዚሁ ተገልጿል። ምን የሚል ቃል ኪዳን እንደነበረ ግን መጽሐፍ ቅዱሱ ዝርዝር ጉዳዮችን ስላልጻፈልን አለማወቅ ይገድበናል።

▶️፯. 2ኛ መቃ.1፥9 ላይ "ኢየሩሳሌምንም እንደ ተክል ጠባቂ ጎጆ አደረጓት በውስጧም ድምፅ አሰማባት" ሲል ምን ለማለት ነው?

✔️መልስ፦ በገጠር ተክል የሚጠብቅ ሰው ጊዜያዊ ጎጆ ሠርቶ ይጠብቃል። ተክሉ ከተሰበሰበ በኋላ ጎጆዋን ያፈርሳታል። ስለዚህ የተክል ጠባቂ ጎጆ ማለት ሁልጊዜ የማትኖር ቶሎ የምትፈርስ ማለት ነው። ኢየሩሳሌምን እንደ ተክል ጠባቂ ጎጆ አደረጓት ማለት አፈረሷት ማለት ነው። በውስጧም ድምፅ አሰማባት የሚለው እግዚአብሔር የማይወደውን ሥራ አደረገባት ማለት ነው።

▶️፰. 2ኛ መቃ.5፥6 "አውሬ የነከሰውንና ደሙን፣ በክቱን አባላ መትተው የጣሉትን" ይላል። አባላ ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ አባላ መትተው የጣሉትን ማለት አንገቱን ወይም ቋንጃውን ቆርጠው የጣሉትን እንስሳ ሥጋውን መብላት አይገባም ማለት ነው።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


Video oldindan ko‘rish uchun mavjud emas
Telegram'da ko‘rish


፩. አንዳንድ ቀን የሞቱ ሰዎችን የfacebook ገጽ አያለሁ። ከዕድሜያቸው ቀንሰው ዋጋ ሰጥተው የጻፉት ምን ነበር? ያ ያደረጉት ነገር ከሞት በኋላ ላለው ሕይወት አንዳች ቁም ነገር ኖሮት ይሆን? ለሰው ጠቅሞ ይሆን? እግዚአብሔር የሚወደው ነበር ይሆን?

፪. አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሞቱ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ እሰማለሁ። ዋጋ ሰጥተው የተናገሩት ነገር ከዘለዓለማዊው ሕይወት ጋር ግንኙነት ነበረው ይሆን? ለምን ነበር በዚህ ምድር የደከሙት? ቃለ መጠይቃቸው ላይ ትኩረት ያደረጉት በምን ጉዳይ ነበር? ያ ጉዳይ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ አሁን ለሄዱበት ዓለም አዎንታዊ ሚና ነበረው ይሆን?

፫. የሞቱ ሰዎችን መጻሕፍትና የምርምር ውጤቶች (Researches) አነባለሁ። በዚህ ዓለም የደከሙለት ጉዳይ ከዘለዓለማዊው ሕይወት ጋር የተገናኘ ነበር? የትኩረታቸው ዋና ማዕከል ምን ነበር?

፬. ቤተክርስቲያን ስትሔዱ የብዙዎችን መቃብር አስባችሁት ታውቃላችሁ? አንዳንዶቹ ዕቅዳቸውን ሳይቋጩ ያረፉ ናቸው። አንዳንዶቹ ለምን እንደሚኖሩ ሳያውቁ ያረፉ ናቸው። አንዳንዶች አሁን እኛ ባለንበት ሁኔታ (መጥፎ ወይም መልካም) ሆነው ያረፉ ናቸው።

ሰው ሞትን መዘንጋት የለበትም። ስለዚህ እስካለ ድረስ ለሰው በጎ አስተዋጽኦ አበርክቶ ቢያልፍ መልካም ነው። እግዚአብሔር አድርጉ ያለንን አድርገን ለማለፍ ሕጉን በየዕለቱ እያነበብን እየተገበርን ብንኖር መልካም ነው። ለመሞት አንድ ቀን እንደቀረው ሰው ሆነን እንኑር። ሰውን እንደራሳችን እንውደድ። የእግዚአብሔርን ሕግ እንጠብቅ። ጎበዝ ዕድሜያችንን ለቁም ነገር እናውላት። ሁሉም ኃላፊ ነውና የማያልፈው ላይ ትኩረት እናድርግ። መሞታችን ካልቀረ ደግ ሥራ እየሠራን እንሙት።

© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


🧡 ሁለተኛ መጽሐፈ መቃብያን ክፍል 1 🧡

🧡ምዕራፍ ፩፡-
-ሞዓባዊው መቃቢስ እስራኤልን ከሌሎች አሕዛብ ጋር ሆኖ እንዳጠፋቸው
-እስራኤላውያን ቢበድሉ መቃቢስ ዘሞዓብን እንዳስነሳባቸው
-መቃቢስ ዘሞዓብ እግዚአብሔር የማይወደውን የክፋት ሥራ ሁሉ እንዳደረገ

🧡ምዕራፍ ፪፡-
-ንስሓ ካልገባ በመቃቢስ ዘሞዓብ የልብ በሽታና የተለያዩ መከራዎች እንደሚደርሱበት ነቢይ መናገሩ
-መቃቢስ ስለኃጢአቱ ማቅ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት እንዳለቀሰ

🧡ምዕራፍ ፫፡-
-እግዚአብሔር የመቃቢስን ንስሓ ተቀብሎ ይቅር እንዳለው
-ንስሓ የሚገቡ ሰዎች ብፁዓን እንደሆኑ መገለጹ

🧡ምዕራፍ ፬፡-
-እግዚአብሔር በተለያዩ ሰዎች እያደረ እስራኤላውያንን ይረዳቸው እንደነበረ
-መቃቢስ በጎ ሥራን መሥራት እንደጀመረና መንገዱን ያቀና እንደነበር

🧡ምዕራፍ ፭፡-
-መቃቢስ እንደሞተና ልጆቹ በሥርዓት እንዳደጉ፣ ገንዘባቸውን ለድሆች ይመጸውቱ እንደነበር

🧡🧡🧡የዕለቱ ጥያቄዎች🧡🧡🧡
፩. ሞዓባዊው መቃብስ ስለሠራው ሥራ ትክክል የሆነው የቱ ነው?
ሀ. ከሴቶች ሆድ ያለውን ፅንስ አውጥቷል
ለ. እግዚአብሔር የማይወደውን ክፉ ሥራ ሠርቷል
ሐ. ሀ እና ለ
መ. መልስ የለም
፪. መቃቢስ ዘሞዓብ በሠራው ክፉ ሥራ ምክንያት ንስሓ ካልገባ የልብ በሽታ፣ እከክና ቁርጥማት እንደሚመጣበት የተናገረው ማን ነው?
ሀ. ሚክያስ
ለ. ረአይ የሚሉት ነቢይ
ሐ. ዮናስ
መ. ናሆም
፫. ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል የሆነው የቱ ነው?
ሀ. የሚጠራጠሩ ሰዎች ንስሓ ለመግባት አይጨክኑም
ለ. በፍጹም ልቡናቸው ንስሓ የሚገቡ ሰዎች ብፁዓን ናቸው
ሐ. ከሳቱ በኋላ ንስሓ የገቡ ሰዎች የእግዚአብሔር ናቸው
መ. ሁሉም
፬. መቃቢስ ዘሞዓብ ንስሓ ከገባ በኋለ ምን አደረገ?
ሀ. ከቤቱ ጣዖትን አስወገደ
ለ. ሟርተኞችን፣ ጠንቋዮችንና ጣዖት የሚያመልኩ ሰዎችን አስወገደ
ሐ. የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ሥርዓቱንና ሕጉን ጧትና ማታ ይመረምር ነበር
መ. ሁሉም
፭. ስለ መቃቢስ ዘሞዓብ ልጆች ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ስሙ ብኤል ፌጎር የሚባል ጣዖትን ያመልኩ ነበር
ለ. እግዚአብሔርን ይፈሩት ነበር
ሐ. ገንዘባቸውን ለድኾች ይመጸውቱ ነበር
መ. ባልቴቶችንና የሙት ልጆችን እየረዱ ያረጋጓቸው ነበር
፮. ብኤል ፌጎር ስለተባለው ጣዖት ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ይበላና ይጠጣ ነበር
ለ. ትንፋሽና ዕውቀት የሌለው የሰው እጅ ሥራ ነው
ሐ. መልካምም ክፉም አያደርግም
መ. ለ እና ሐ

https://youtu.be/LOHKuokmjRw?si=6IEk7GL2SEJx7qbA




ዜና PDF በዚሁ የቴሌግራም ቻናሌ (ቀጥሎ)
አንደኛ መቃብያን ላይ የጠየቃችሁኝ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በPDF ቀጥሎ ተለቋል። ማንበብ ትችላላችሁ።

ነገ ሁለተኛ መቃብያን ይቀጥላል።
የንባቡ ሥርዓት በቀን አምስት አምስት ምዕራፍ ማንበብ፣ ከዚያ ካነበባችሁት አምስት ምዕራፎች ያልገባችሁን ማናቸውንም ጥያቄ መጠየቅ ነው። ለማንበብ ጊዜ ያጠራችሁ ካላችሁ እየሠራችሁ ማዳመጥ እንድትችሉ በማሰብ በAudio (በድምፅ) በዩቲይብ ቻናሌ እለቀዋለሁ።

በእግዚአብሔር ቸርነት ሁለተኛ መቃብያን ደረስን። እግዚአብሔር ቢያኖረን እስከ ራእየ ዮሐንስ በዚህ መልኩ እንቀጥላለን። በየዕለቱ ከሚነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውጭ ሌላ ጥያቄ እንደማልቀበል ደግሜ አሳውቃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ካለቀ በኋላ የፈለጋችሁትን ጥያቄ መጠየቅ ትችላላችሁ።

© በትረ ማርያም አበባው

✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 118 💙💙

▶️፩. "የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሁሉን ያውቃል" ይላል (1ኛ መቃ.34፥15)። የቅዱሳን ዕውቀት ምን ዓይነት ነው? ቅዱሳን ሰዎች ከመላእክት ጋር ዕውቀታቸው እኩል ነው?

✔️መልስ፦ የቅዱሳን ዕውቀት የጸጋ ዕውቀት ነው። በባሕርይው ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። የፍጡራን ዕውቀት የጸጋ ዕውቀት ነው። ስለሆነም ወሰን አለበት። ከዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሁሉን ያውቃል ሲል ከሌሎች በተለየ ብዙ ያውቃል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ሁሉ ማለት የተለመደ ነውና።

▶️፪. "በጎ ሥራ የሚሠሩትን ግን እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ እንደ ጠበቀው እንደ ኢዮብ" ይላል (1ኛ መቃ.36፥16)። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው የኢዮብ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ይመስላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ቅደም ተከተላቸው ምንን መሠረት ያደረገ ነው?

✔️መልስ፦ አዎ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው ከኢዮብ መነሣት በኋላ መሆኑ በዚህ አገላለጹ ይታወቃል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቅደም ተከተላቸው መደብ ተኮር ነው። ይኸውም መጀመሪያ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ብሎ ከመደበ በኋላ ብሉይን አስቀድሞ ሐዲስን ያስከትላል። ከዚያ ብሉይ ኪዳንን ደግሞ የሕግ (የኦሪት)፣ የታሪክ፣ የመዝሙርና የጥበብ፣ የትንቢት ብሎ ከፍሎ በቅደም ተከተል መጀመሪያ የሕግን አስቀድሞ የታሪክን ይቀጥላል። ከታሪክ ቀጥሎ የጥበብ ይቀጥላል። ከዚያ መጨረሻ ላይ የትንቢትን አድርጎ ይጽፋል። ስለዚህ ቅደም ተከተላቸው መደብን የተከተለ ነው እንጂ የተጻፉበትን ጊዜ የተከተለ አይደለም።

▶️፫. "የሮም መንግሥት በመቄዶንያ መንግሥት ላይ ትጸናለች። የኢትዮጵያ መንግሥትም በእስክንድርያ መንግሥት ትጸናለች" ይላል (1ኛ መቃ.34፥1-2)። ይህ ንባብ ትንቢት ነው ወይንስ መጽሐፉ በተጻፈበት ዘመን የተፈጸመ ነው? መጽሐፉስ ከየትኛው የመጽሐፍ ክፍል ይመደባል (የታሪክ የሥርዓት ወይስ የትንቢት?)።

✔️መልስ፦ "ትጸናለች" ብሎ በትንቢት አንቀጽ (ካልኣይ አንቀጽ) በመገለጹ መጽሐፈ መቃብያን ከተጻፈ በኋላ የሚሆን ጉዳይ መሆኑን ያመለክተናል። ይህ ትንቢት ይፈጸም አይፈጸም ግን የተገለጸ ነገር አላገኘሁም። መጽሐፈ መቃብያን ቁጥሩ ከታሪክ መጻሕፍት ነው። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሕግ፣ የታሪክ፣ የጥበብ፣ የትንቢት ተብለው ቢከፈሉ እንኳ በጸናው መናገር ነው እንጂ ሁሉ ከሁሉ አለ። ከሕግ መጻሕፍት ላይ ሕግም፣ ታሪክም፣ ጥበብም ይገኛል። ለምሳሌ ስቅልተ ትሬእያ እስራኤል ለሕይወትከ የሚለው በሕግ መጽሐፍ ያለ ቢሆንም ስለክርስቶስ የተነገረ ትንቢት መሆኑን ማስተዋል ይገባል። የኦሪት መጻሕፍት የሕግ መጻሕፍት ቢሆኑም ከአዳም ጀምሮ የነበሩ አበውን ታሪክም የያዙ መሆናቸውን መረዳት ይገባል። ከታሪክ መጻሕፍትም ጥበብ፣ ትንቢት፣ ሕግ ይገኛል። ከጥበብ መጻሕፍትም ሁሉም ይገኛሉ። ስለዚህ ምንም እንኳ መጽሐፈ መቃብያንን በብዙ ነገሩ ከታሪክ መጻሕፍት ብንመድበውም ትንቢትንም፣ ሕግንም፣ ጥበብንም የያዘ መጽሐፍ መሆኑን መረዳት ይገባል።

▶️፬. 1ኛ መቃ.36፥4 "አንተም ይስማኤላዊ የባርያ ልጅ አንገትህን ለምን ታስረዝማለህ?" ይላል። ይስማኤላውያን በዚያ ዘመን መኖሪያቸው በየት ነበር?

✔️መልስ፦ ይስማኤላውያን በዚያ ዘመን የትና ከየት እስከ የት ይኖሩ እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጽ አላገኘሁም። መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ጉዳዮች ላይ እንጂ በእያንዳንዱ ጉዳይ ዝርዝር ጉዳዮችን የማይገልጽበት ሁኔታ አለና።

▶️፭. 1ኛ መቃ.32፥3 የበግ ወተት በብሉይ ዘመን ይፈቀዳልን?

✔️መልስ፦ በሀገራችን ስላልተለመደ ነው እንጂ የበግ ወተትን መጠጣት ምንም ዓይነት ርኵሰት የለውም። በግም በብሉይ ኪዳን ንጹሕ ከሚባሉት እንስሳት አንዷ ነች እንጂ ርኩስ ከሚባሉት አይደለችምና።

▶️፮. 1ኛ መቃ.32፥3 እንደ እስራኤል ልጆች ሲል የአንደኛ መቃብያን ተደራስያኑ እስራኤላውያን አይደሉም ወይ?

✔️መልስ፦ ከዚህ ላይ የመጽሐፈ መቃብያን ቃል በመላው ዓለም እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ነገሥታትና መኳንንት የተነገረ ነው። ከላይ በርእሱ "እናንተም ነገሥታትና መኳንንት ቃሌን ስሙ" ብሎ የነገሩን ባለቤቶች ገልጾልናል። ስለዚህ ቀድመው ጣዖትን ያመለኩ እነ ኢዮርብዓም ወልደ ናባጥንና ሌሎችንም እንደ ሸማ ጠቅልሎ የእስራኤላውያንን ክፋት መሠረት አድርጎ እንደእነርሱ አትሁኑ ብሎ ገልጿል። ተደራሲያኑ ከዚህ ምዕራፍ በተለዩ ነገሥታተ ዓለም፣ መኳንንተ ዓለም ናቸው።

▶️፯. 1ኛ መቃ.33፥1 ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ ያለው ዳዊት (መዝ.77፥24-25) መላእክት መና ይመገባሉ እንዴ? አይ የመላእክት እንጀራ የተባለው ምስጋና ነው እንዳንል አንደኛ መቃብያንም ሆነ መዝሙረ ዳዊት መና ነው የሚል። መላእክት እንደማይበሉ ደግሞ መጽሐፈ ጦቢት እና የማቴዎስ ወንጌል ላይ ተጽፏል።

✔️መልስ፦ መላእክት ረቂቃን ፍጥረታት ስለሆኑ ምድራዊ ምግብን አይበሉም። መና ብሎ በግሥ የተናገረውም ምስጋናን ነው። ሰዎች እንደ መላእክት አመሰገኑ ማለት ነው። ኅብስተ መላእክት ያለው ውስጠ ወይራ ነው። ውዳሴ መላእክት፣ ስብሐተ መላእክት፣ መዝሙረ መላእክት ማለት ነው። በዚህ ጊዜ መልአክ ለአከ ላከ ከሚለው የግእዝ ቃል ወጥቶ መልአክ ባዕድ ዘር ውስጠ ዘ ይሆናል። ከእግዚአብሔር የሚላክ ማለት ነው። በሌላ አተረጓጎም ተመልአከ አለቃ ሆነ ከሚለው የግእዝ ቃል መልአክ የሚል ዘር ውስጠ ዘ ይወጣል። በዚህ ጊዜ መልአክ አለቃ ሲሆን መላእክት አለቆች ተብሎ ይተረጎማል። ስለዚህ አለቆች ነገሥታት፣ አለቆች መሳፍንት፣ አለቆች መኳንንት የሚመገቡትን ምግብ ሌላው ሕዝብም ተመገበው ማለት ነው።

▶️፰. 1ኛ መቃ.34፥7 እግራቸው በሚሰነካከልበት ቀን የሚለው የትኛውን ቀን ነው?

✔️መልስ፦ እግራቸው በሚሰነካከሉበት ቀን ማለት በሚቸገሩበት ቀን ማለት ነው። በኃጢአታቸው ምክንያት መከራ በሚደርስባቸው ቀን ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቀድመው በዚህ ምድርም ሳሉም በኋላ በምጽአትም ይተረጎማል።

▶️፱. 1ኛ መቃ.34፥15 የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሰው እንዴት ነው ሁሉን አዋቂ (omniscient) የሚሆነው በጸጋ ነው እንዳይባል በጸጋስ ቢሆን ሁሉ ይገለጽለታልን?

✔️መልስ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ የሚለው ቃል ብዙ ተብሎም ይተረጎማል። ከሌላው ሰው በተሻለ ብዙ ያውቃሉ ማለት ነው እንጂ እንደ አምላክ በባሕርይ ሁሉን ያውቃሉ ማለት አይደለም። ብዙውን ሁሉ ማለት ልማደ መጽሐፍ ቅዱስ ነውና።

▶️፲. ረዓይታዊው ጎልያድ (1ኛ መቃ.31፥4) ሲል ጎልያድ በንፍር ውሃ ከጠፉት ረዓይያት ዝርያ ነው ማለት ነው?

✔️መልስ፦ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ረጃጅም ሰዎችን "ረዓይት" ይላቸዋል። ጎልያድም ከሌላው ሰው በተለየ ስድስት ክንድ ያህል ርዝመት ስለነበረው ረዓይት ተብሏል እንጂ በማየ አይኅ ከጠፉት ወገን ስለሆነ አይደለም።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


❤ መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ክፍል 7 ❤

❤ምዕራፍ ፴፩፡-
-ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ነገሥታት እንደማይነግሡ መነገሩ

❤ምዕራፍ ፴፪፡-
-እግዚአብሔር ነገሥታትን ቃሌን ጠብቁ ማለቱ

❤ምዕራፍ ፴፫፡-
-እስራኤላውያን አምልኮቱን ቢተዉ መከራ እንደደረሰባቸው

❤ምዕራፍ ፴፬፡-
-ወንድም በወንድሙ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሣ መነገሩ

❤ምዕራፍ ፴፭፡-
-የሚሰክሩ፣ ፍርድን የሚያዳሉና በመዳራት የሚኖሩ ሰዎች ወዮታ እንዳለባቸው

❤ምዕራፍ ፴፮፡-
-ትምክህት እንደሚያስቀጣ መነገሩ፣ መልካም የሠሩ ወደ ዘለዓለም ሕይወት ክፉ የሠሩ ወደ ዘለዓለም ቅጣት እንደሚሄዱ መነገሩ

❤❤❤የዕለቱ ጥያቄዎች❤❤❤
፩. ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል የሆነው የቱ ነው?
ሀ. ነገሥታት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አይነግሡም
ለ. እግዚአብሔር ትእዛዙን የሚጠብቁ መኳንንትንና ነገሥታትን ይወዳቸዋል
ሐ. እግዚአብሔር ለደጋግ ነገሥታት ኃይልንና ድልን ይሰጣቸዋል
መ. ሁሉም
፪. ከሚከተሉት ውስጥ ዳግም ምጽአት ሲቃረብ ይሆናሉ ከተባሉት መካከል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ሰላምና ፍቅር ይበዛል
ለ. ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሣል
ሐ. ክርክር፣ ሰልፍ፣ ቸነፈር ይሆናል
መ. ለ እና ሐ

https://youtu.be/Rt1f_YGCUV0?si=P4AtKKw_VZ3-vkFP


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 117 💙💙

▶️፩. "በስድስተኛዪቱም ቀን ከብቶችንና አውሬዎችን ሌሎችንም ፈጠረ ሁሉንም ፈጥሮ አዘጋጅቶ አዳምን በምሳሌውና በመልኩ ፈጠረው" ይላል (1ኛ መቃ.27፥11)። መምህር በደንብ ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር አለ። እግዚአብሔርን በባሕርይው  መላእክትስ እንኳን ቢሆኑ ማንማ ያየው የለም ይባላል። ሰው ደሞ የተለያየ መልክ አለው። ግን ሀሉም ሰው (ነጩም ጥቁሩም) እግዚአብሔርን ይመስላል ይባላል። ታዲያ አዳምን በምሳሌውና በመልኩ ፈጠረው ስንል ምሳሌና መልክ ሲባል ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ እውነት ነው እግዚአብሔርን በባሕርይው ያየው አንድስ እንኳ የለም። ወደፊትም የሚያየው የለም። አዳምን በምሳሌውና በመልኩ ፈጠረው የሚለው በዋናነት እግዚአብሔር በባሕርይው የሚገዛውን ፍጥረት አዳም በጸጋ እንዲገዛው አደረገው ማለት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው ምሳሌ ከሚመሰልለት ያነሰ ስለሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይመስላል ሲባል በገዢነት ይመስለዋል ማለት ነው። በተጨማሪም እግዚአብሔር በባሕርይው ለባዊ፣ ሕያው፣ ነባቢ እንደሆነ ሁሉ ሰው ደግሞ በጸጋ ለባዊ ነባቢ ሕያው ነውና በዚህ ይመስለዋል። ሌላው የእግዚአብሔር አካል በሁሉ ያለ ረቂቅ ቢሆንም የሰውን አካል ይመስላልና ይኸውም ለእግዚአብሔርም እጅ እግር፣ ራስ፣ ዓይን እና የመሳሰሉት ሌሎችም አካላት እንዳሉት ተጠቅሷልና ነው። ለሰውም በጸጋ እነዚህ ነገሮች ስላሉት እግዚአብሔርን ይመስላል ተብሏል።

▶️፪. "እግዚአብሔር በአባታችን በአዳም ተቈጣ ከገነትም አስወጥቶ ሰደደው። ያርሳት ዘንድ ጥሮ ግሮም የድካሙን ዋጋ ይበላ ዘንድ ትእዛዙን ባፈረስ ጊዜ ስለእርሱ ረገማት። አሜከላና እሾህን የምታበቅል ያችንም ምድር ሰጠው" ይላል (1ኛ መቃ.27፥19)። አሜከላና እሾህን የምታበቅል ያችንም ምድር ሰጠው ሲል እሾህና አሜከላ አዳም ከመበደሉ በፊት ቀድመው እንደ ሌሎች ዕፀዋት በሦስተኛው ቀን የተፈጠሩ ነበሩ እንዴ? ወይስ አዳም ስለበደለ ብቻ ከበደል በኋላ መሬት ያበቀለቻቸው ናቸው?

✔️መልስ፦ በዚህ ዙሪያ ሁለት እይታዎች (Speculations) አሉ። አንደኛው የዕፀዋት እሾህ ባሕርያዊ የሆነና ከዕለተ ፍጥረታቸው ጀምሮ ያለና የነበረ ሲሆን ስለዚህ እሾህና አሜከላ ያብቅሉብህ ማለት ፍትወታት እኩያት (ክፉ ምኞቶች) ይሠልጥኑብህ ማለት ነው የሚል ነው። ሁለተኛው የብሉይ መተርጉማን እንዳለ ወስደው የተረጎሙት ነው። ይህም ማለት ዕፀዋት አስቀድሞ እሾህ አልነበራቸውም። ከዚህ ርግማን በኋላ እሾህ እንዳወጡ ተናግረዋል ማለት ነው። አንድም በሰው ሆድ ውስጥ ተሐዋስያን ይኑሩ ማለት ነው ብለውታል። ሁለቱንም እይታዎች አክብረን እንይዛለን።

▶️፫. "አዞዎችንና ዓሣ ነባሪዎችን አሽኮኮዎችና ጉማሬዎችን አቆስጣንም" ይላል፡፡ አቆስጣ ማለት ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ አቆስጣ ከአራዊት ወገኖች የሆነ የሚናከስ ፍጥረት ነው።

▶️፬. "ዳግመኛ ደግ ልጅ ሴት ተወለደ። አዳም ስድሳ ልጆችን ወለደ ከነእርሳቸው ደጋጎች ሰዎችና ክፉዎቸ ሰዎች አሉ" ይላል (1ኛ መቃ.28፥6)፡፡ አዳምና ሔዋን የወለዷቸው ልጆች ብቻ ናቸው ስድሳ?

✔️መልስ፦ አዎ አዳም ከሔዋን በጠቅላላ የወለዳቸው ልጆች ስድሳ (ስሳ) ናቸው።

▶️፭. "በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር በምድር ላይ አትክልቱን ሥሩን ሁሉ እንጨቶችንም በየወገናቸው የሚያፈሩ ፍሬዎችንም ሲያዩት ያማረ የደኅንነት እንጨትንም ፈጠረ" ይላል (1ኛ መቃ.27፥6)። የደኅንነት እንጨት ሲል ምን ዓይነት እንጨት ነው?

✔️መልስ፦ የደኅንነት እንጨት የሚለው ዕፀ ሕይወትን ነው። ግእዙ በደንብ ገልጾታል። "ወዕፀ ሕይወት ዘሠናይ ለርእይ" እንዲል።

▶️፮. "ወንድሙን አቤልን ስለ ገደለ እግዚአብሔር በቃየል ፍርድን ፈረደ ደሙንም ስለ ጠጣች እግዚአብሔር ምድርን ተቈጣት" ይላል (1ኛ መቃ.28፥3)። የበደለ ቃኤል ብቻ ሆኖ እያለ ደሙንም ስለ ጠጣች እግዚአብሔር ምድርን ተቈጣት ለምን አለ?

✔️መልስ፦ የምድር መረገም ጉዳቱ ለሰው ስለሆነና ምድርን መርገም ቃኤልን የመርገም አንድ አካል ስለሆነ ነው እንጂ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።


© በትረ ማርያም አበባው

✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 116 💙💙

▶️፩. "ደስታቸው እንደምትበር ወፍ ነውና" ይላል (1ኛ መቃ.25፥15)። ትርጓሜው ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ የምትበር ወፍ ፈጥና እንደምትሄድ (እንደምታልፍ) ሁሉ የኃጥኣንም ደስታቸው ፈጥና ታልፋለች አትጸናላቸውም ማለት ነው።

▶️፪. "እርሱ ሕያዋንንና ሙታንን ከኖባና ከሳባ ከኢትዮጵያና ከሕንደኬ" ይላል (1ኛ መቃ.25፥9)። ሳባና ሕንደኬ ይለያያሉ? ከኢትዮጵያና ሕንደኬ ሲልስ የተለያዩ ሀገሮች ናቸው እንዴ?

✔️መልስ፦ ሕንደኬ የሚላት ሕንድን ነው። ሳባ የሚላት ደግሞ የመንን ነው። ኢትዮጵያ የሚላት ደግሞ ሀገራችንን ነው። ስለዚህ የተለያዩ ሀገሮች ናቸው። የመን የኢትዮጵያ አካል የነበረችበት ዘመን ግን እንደነበረ በትውፊት ይነገራል።

▶️፫. 1ኛ መቃ.24፥8 ላይ"ክፉ ሰዎች ልብሳቸውን ለውጠው ይመጣሉ። ከመብላት ከመጠጣት በብርና በወርቅም ከማጌጥ እግዚአብሔርም የማይወደውን ሥራ ሁሉ በኃጢአት ጸንቶ ከመኖር በቀር በነእርሳቸው ዘንድ ሌላ ሕግ የለም"ይላል።  በዚህ ንባብ "ልብሳቸውን ለውጠው ይመጣሉ" ሲል ምን ለማለት ነው?

✔️መልስ፦ በሌላ ክፉ ሥራ ይመጣሉ በክፋት ላይ ክፋት ይጨምራሉ ማለት ነው። ይህም እንደ አንዳንድ ሌቦች ነው። ሰርቀው ወዲያው ሌላ ልብስ ቀይረው ይመጣሉ። ይህም ሌባ ሆነው ሳለ ሌብነታቸው እንዳይታወቅ ነው።

▶️፬. "የዓለምንም ገንዘብ በሰሙ ጊዜ በዐይናቸው ሳያዩት የራሳቸው ገንዘብ ያደርጉታል። በዐይናቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለምና በዐይናቸው ባዩት ጊዜ በአፋቸው የበሉት ይመስላቸዋል" ይላል (1ኛ መቃ.24፥12)። የዚህ ንባብ ትርጓሜ ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ ይህ ደግሞ ስስታምነታቸውን ለመግለጽ ነው። በዐይናቸው ባዩት ጊዜ በአፋቸው የበሉት ይመስላቸዋል ማለት አንዳንዱ ሰው ምግብ ቀርቦለት ምንም ሳይበላው ገና በዐይኑ ቀውለል ቀውለል እያለ ስስታምነቱን ያሳያል ማለት ነው። የዓለምንም ገንዘብ የራሳቸው ገንዘብ ያደርጉታል የተባለው የእነርሱ ያልሆነን ገንዘብ እየሰረቁ ኃጢአት ይሠራሉ ማለት ነው።

▶️፭. "እኔ እግዚአብሔር ከአድማስ እስከ አድማስ ምሉእ ነኝና ፍጥረቱም ሁሉ በሥልጣኔ ተይዟልና በሰማይና በምድር በጥልቅና በባሕርም ከሥልጣኔ የሚያመልጥ የለም" ይላል (1ኛ መቃ.25፥4)። መምህር ስለአድማስና ናጌብ ሰፋ አድርገው ቢያብራሩልኝ። ከአድማስ እስከ አድማስ ሲል ከአድማስ ባሻገር እግዚአብሔር በሥልጣኑ የሚገዛው ሌላ ፍጥረት (ዓለም) የለም እንዴ?

✔️መልስ፦ ናጌብ የሚባለው በመሬት ዙሪያ ያለ እስከ ሰማይ የማይደርስ ከሰማይ ዝቅ ያለ ተራራ (ቅጽር) ነው። ከናጌብ ቀጥሎ ዐቢይ ውቅያኖስ የሚባል አለ። ይህም ከዓለም የተሰወረ ዓለም ያልደረሰበት ዓለም ነው። ግዙፋኑ ፍጥረታት እነ ሌዋታን የሚኖሩበት ክፍለ ምድር ነው። ከዚያ ቀጥሎ አድማስ አለ። አድማስ ሰማይና ምድር የሚገናኙበት ቦታ ነው። እግዚአብሔር ከአድማስ እስከ አድማስ ይገዛል ማለት በምድር ያሉ ፍጥረታትን ሁሉ ይገዛል ማለት ነው። ከአድማስ ባሻገር ዓለም እንዳለ የሚገልጽ መጽሐፍ አላገኘሁም። ከአድማስ በኋላ ያለ እግዚአብሔር ነው። በሰማያት ያሉትንም በምድር ያሉትንም ሁሉንም ፍጥረታት የሚገዛ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ይተርፋታል እንጂ አትተርፈውምና። ስለዚህ በያዛት ዓለምም ህልው ሆኖ ከያዛት ዓለም ውጭም በምልአት ኖሮ ፍጥረታትን ሁሉ ይገዛል ያስተዳድራል።

▶️፮. "ከአዜብ ነፋሰ ይነሣል በመስዕም ያለ ድርቅ ይጸናል ኋላ በፍጻሜ ዘመን ወደእርሷ የሚመጣ ከእግዚአብሔር መፈራት ገናንነትም የተነሣ የኤርትራ ባሕር ተሰምታ ትጠፋለች። በእርሱ የሞቱትንና ያሉትን ሰዎች ይገዛልና ከሳባ እና ከኖባ ከሕንደኬና ከኢትዮጵያም ወሰናቸውና አውራጃቸውም ጋራ ሁሉ ተሰምታ ትጠፋለች" ይላል (1ኛ መቃ.25፥8-9)። የዚህ ንባብ ትርጓሜው ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ ይህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረ ነው። በእርሱ የሞቱትንና ያሉትን ሰዎች ይገዛልና የተባለ ክርስቶስ ነው። በስሙ አምነው የሞቱትንና ያሉትን የሚገዛ እርሱ ነውና። ሌሎችን እርሱ የማይገዛ ሆኖ አይደለም። የሁሉ ፈጣሪ ነውና። እግዚአብሔር በሚወዳቸው መጠራት ደስ ስለሚለው ነው። የሁሉ አምላክ ሆኖ ሳለ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅ አምላክ የያዕቆብ አምላክ ነኝ እንዳለው ያለ ነው። የኤርትራ ባሕር በእግዚአብሔር ግርማ ፊት መቆም እንደማትችል ለመግለጽ ትጠፋለች ተብሏል። ምድር ከቃሉ የተነሣ ትንቀጠቀጣለች እንደሚለው ያለ ነው።

▶️፯. "የክፉ ሰዎች ዐመፃቸው እንደ ጥቅል ነፋስ የበደለኞች ጉባኤያቸውም እንደ ጉም ሽንት ነውና ይልቁንም በየጊዜው ወደሱ የሚለምኑ የንጹሓንን ልመና ይቀበላል" ይላል (1ኛ መቃ.25፥14)። ጥቅል ነፋስና የጉም ሽንት ብሎ የገለጻቸው ምንን ለማመልከት ነው?

✔️መልስ፦ ጥቅል ነፋስ ለአንድ አፍታ ብዙ መስሎ ቢታይም ትንሽ ቆይቶ እንዳልነበረ ይሆናል። ጉምም ብዙ ቢመስልም ከዘነበ በኋላ ወዴት እንደሄደ አይታወቅም ይጠፋል። ክፉ ሰዎችም ያለን ቢመስላቸውና ብዙ ቢመስሉም እንደ ጉም ሽንትና እንደ ጥቅል ነፋስ ወዲያው ይጠፋሉ ማለት ነው።

▶️፰. "የሌላውን ገንዘብ ይበሉ ዘንድ ከጠላታቸው የዘረፉትን ገንዘብ በልተው ይጠግቡ ዘንድ እንስሳትን በጎችንና ላሞችንም ይዘርፉ ዘንድ የሌላውንም ማዕድ ይበሉ ዘንድ የጠላቶቻቸውንም ልጆች ምርኮ ይወስዱ ዘንድ ደስ ያሰኘዋል" ይላል። የጠላትን ገንዘብ መውሰድ (መማረክ) በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን እንዴት ይታያል?

✔️መልስ፦ በጦርነት ገጥሞ የጠላትን ገንዘብ መማረክ በብሉይም የነበረ በሐዲስም ያለ ነው። ሰው መጀመሪያውን ባይጣላና በሰላምና በፍቅር ቢኖር መልካም ነበር። ነገር ግን አለመግባባት አይሎ ወደ ጦርነት ቢያድግ በፍትሕ ሥጋዊ (በነገሥታት አስተዳደር) ምርኮ ሊፈቀድ ይችላል። ይህ በራሱ ሕግ የሚዳኝ ስለሆነ ኃጢአትነት የለውም። በፍትሕ መንፈሳዊ (በካህናት አስተዳደር) ግን መታረቅና ሰላም መፍጠር እንጂ ምርኮ የለም።

▶️፱. "ከጉድጓዱ እንደ ወጣ ፍለጋውም እንደማይገኝ ወደ ቤቱም እንደማይመለስ አሽን ፈጥነው ይጠፋሉና በሕይወታቸውም ሳሉ በጎ ሥራን ስላልሠሩ እግዚአብሔር ተቈጥቶ በያዛቸው ጊዜ ለሰውነታቸው ወዮላት" ይላል። አሽን ማለት ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ አሸን የሚባለው ክረምት ሊገባ ሲል ከመሬት የሚወጣ ሁለት ክንፍ ያለው አካሉ ምስጥ የሚመስል ፍጥረት ነው።

▶️፲. 1ኛ መቃ.23፥2 ቃኤል ወንድሙን አቤልን የገደለው በሴት ቀንቶ ነው ይላል። ነገር ግን በዘፍ.4፥1-8፣ ኩፋ.5፥9፣ ዕብ.11፥4 እና 1ኛ ዮሐ.3፥12 ባለው እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት ስለተቀበለና የቃኤልን ስላልተቀበለው እንደገደለው ያስረዳል። ቢብራራልኝ።

✔️መልስ፦ ሁለም ትክክል ነው። አቤልና ቃኤል መጀመሪያ በሚስት ተጣሉ። አዳም የአቤልን መንትያ ለቃኤል፣ የቃኤልን መንትያ ለአቤል አጋብቷቸው ነበር። ነገር ግን የአቤል ሚስት የነበረችው የቃኤል መንትያ በጣም ውብ ስለነበረች ቃኤል የእኔን ውብ መንትያ ለምን ለአቤል ይሰጠዋል ብሎ ተቆጣ። ይህን ጊዜ አዳም መሥዋዕት ሠዉና መሥዋዕቱን እግዚአብሔር የተቀበለለት ይሁን አላቸው። ከዚያ መሥዋዕት ሠዉ። መሥዋዕት ሲሠዉ ቃኤል እግዚአብሔር አይበላ ምን ይሠራለታል ብሎ ግርድ ግርዱን አቀረበ። አቤል ደግሞ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ስለሆነ ንጹሕ ነገር ይፈልጋል ብሎ ቀንዱ ያልከረከረ፣ ጸጕሩ ያላረረ የዓመት ጠቦት አቀረበ። እግዚአብሔርም የአቤል የልቡን ንጽሕና ተመልክቶ የአቤልን መሥዋዕት ተቀበለ። ወነጸረ እግዚአብሔር ላዕለ አቤል


💟 መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ክፍል 6 💟

💟ምዕራፍ ፳፮፡-
-የሰው ራሱ የጽድቅ ፍሬ እንደሆነ እና ፍሬ የሌለው በጎ ሥራ እንደሌለ መገለጹ

💟ምዕራፍ ፳፯፡-
-እግዚአብሔር ዓለምን እንደፈጠረ፣ ምድርን በውሃ ላይ እንዳጸናት

💟ምዕራፍ ፳፰፡-
-ከአዳም ደጋግ ልጆች ነቢያት ነገሥታትና ክፉዎች ልጆች እንደተወለዱ

💟ምዕራፍ ፳፱፡-
-እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ቸል እንደሚላቸው መገለጹ

💟ምዕራፍ ፴፡-
-እግዚአብሔር እንደ ሕጉ የማይሄዱ ነገሥታትን ልጆች ከመንግሥትነት እንደሚከለክላቸው መናገሩ
-እግዚአብሔር ያላከበሩኝን፣ ሕጌንም ያልጠበቁትን ከሰጠኋቸው ስጦታ እለያቸዋለሁ ማለቱ

💟💟💟የዕለቱ ጥያቄዎች💟💟💟
፩. ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል የሆነው የቱ ነው?
ሀ. ፍሬ የሌለው በጎ ሥራ የለም
ለ. ሰው ጽድቅን ሲሠራ ቅንነትን ያፈራል
ሐ. እግዚአብሔር ለሚጸልይ ሰው የአንደበቱን ዋጋ ይሰጠዋል
መ. ሁሉም
፪. ስለ ልዑል እግዚአብሔር ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ መሓሪና ይቅር ባይ ነው
ለ. ለፈጠራቸው ደማውያን ፍጥረታት ሁሉ ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው
ሐ. ሀ እና ለ
መ. መልስ የለም

https://youtu.be/2dQxH87vVC0?si=hAR4ZRyT0cL-3MP9


እንኳን ለሰማዕቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ።

የሰማዕቱ በረከት ይደርብን።

ሰማዕት ማለት እውነትን በመመስከር እስከ ሞት የታመነ ማለት ነው። ሰማዕትነትን ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ባርኮ ሰጥቶናል። ቅዱሳን ፍቅረ እግዚአብሔርን እስከ ሰማዕትነት ደርሰው ገለጹ።

ሰማዕታት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ የደረሰባቸውን ምድራዊ መከራ ሁሉ ናቁት። የዚህን ዓለም ክብር ናቁት። አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም። ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ። ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት። ስለመንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሡ (ቅዱስ ኤፍሬም፣ ውዳሴ ማርያም)።

ሰማዕትነት ፍኖተ ክርስቶስ ነው። ሰማዕትነት መስቀለ ክርስቶስን መሸከም ነው። ዓለሙ ሁሉ ወዶን እግዚአብሔር ከሚጠላን ዓለሙ ሁሉ ጠልቶን እግዚአብሔር ቢወደን ይሻላል። ነገራችንን ምን ያህል ሰው ይወደዋል ብሎ ከመናገር ይልቅ እግዚአብሔር የሚወደው ነወይ የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።

እንደ ሰማዕታት
ለእውነት
በእውነት እንኑር

© በትረ ማርያም አበባው


💜 መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ክፍል 5 💜

💜ምዕራፍ ፳፩፡-
-ዳዊት በእግዚአብሔር በመታመኑ ከሳኦልና ከሌሎችም ጠላቶቹ እጅ እንደዳነ መነገሩ
-ድል መንሣት ከእግዚአብሔር እንደሆነ መገለጡ
-እግዚአብሔር ሕጉን በማይጠብቅ ሰው ላይ መከራን እንደሚያመጣበት መገለጡ

💜ምዕራፍ ፳፪፡-
-በእውነት መፍረድ፣ ቸር፣ የዋህና ቅን መሆን እንደሚገባ መገለጹ

💜ምዕራፍ ፳፫፡-
-በቃየል መንገድ መሄድ እንደማይገባ

💜ምዕራፍ ፳፬፡-
-ጌዴዎን እግዚአብሔርን በመታመኑ በጥቂት ሠራዊት ብዙ የአሕዛብን ሠራዊት ድል እንደነሣ

💜ምዕራፍ ፳፭፡-
-ፍጥረታትን ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛና የሚያስተዳድር እግዚአብሔር እንደሆነ
-ደም ግባት፣ ገንዘብ ኃላፊ እንደሆነ መገለጹ

💜💜💜የዕለቱ ጥያቄዎች💜💜💜
፩. ከሚከተሉት ውስጥ ትክክል ያልሆነው የቱ ነው?
ሀ. ድል መንሣት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው
ለ. በእግዚአብሔር መታመን ከጠላት ያድናል
ሐ. በእግዚአብሔር ከመታመን በሠራዊት መታመን ይሻላል
መ. በእግዚአብሔር የታመነ በሕይወት ይኖራል ይከብራልም
፪. እግዚአብሔር ሕጉን የማይጠብቅን ሰው ምን ያደርገዋል?
ሀ. በጠላቱ እጅ ይጥለዋል
ለ. ፍሬያትን በመስጠት ደስ ያሰኘዋል
ሐ. ዝናምን በጊዜው ያዘንምለታል
መ. ለ እና ሐ
፫. ጌዴዎን በጥቂት ሠራዊት በጣም ብዙ የሆኑ የአሕዛብን ሠራዊት ለማሸነፍ የረዳው ምንድን ነው?
ሀ. በእግዚአብሔር መታመኑ
ለ. ለጣዖታት መሥዋዕትን መሠዋቱ
ሐ. ኃይለኛና ጉልበታም መሆኑ
መ. ለ እና ሐ

https://youtu.be/VDY0NiNL-vs?si=rOAjlK3DROrTS4f9


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 115 💙💙

▶️፩. 1ኛ መቃ.18፥7 ከጥፋት ውሃ በኋላ ከ120 ዓመት በላይ የኖረ አለ አይደል?

✔️መልስ፦ አዎ አለ። ነገር ግን ከጥፋት በኋላ ጥቂቶች ብቻ እንጂ አብዛኛው ከ120 ዓመት በላይ አልኖረም። በብዙው ተናግሮ ነው። ከጥፋት ውሃ በፊት ግን አብዛኛው ከ120 ዓመት በላይ ይኖር ነበር።

▶️፪. "በኪሩቤል ሠረገላ የሚቀመጥ እጅግ የብዙ ብዙ የሆኑ መላእክት በፊቱ የሚቆሙ የሠራዊት ጌታ የሚመሰገንባት የእግዚአብሔርን ከተማ ለማጥፋት ተባብረዋልና" ይላል (1ኛ መቃ.16፥9)። ያች የእግዚአብሔር ከተማ የተባለችው ማን ናት?

✔️መልስ፦ በብሉይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ከተማ የሚላት የዳዊት የመንግሥቱ መቀመጫ የነበረችውን ጽዮንን (ኢየሩሳሌምን) ነው።

▶️፫. "አባቶቻቸው መላእክት ሳሉ ከመላእክት ጋር በሰማይ ያመሰግኑ ነበር" ይላል (1ኛ መቃ.18፥3)። የዚህ ንባብ ትርጓሜ ምንድን ነው? መላእክት ሳሉ ሲልስ ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ ደቂቀ ሴት በመልካም ሥራ ጸንተው ይኖሩ ስለነበር መላእክት እስከመባል ደርሰው ነበር። ስለዚህ መላእክት ሳሉ ማለት በግብረ መላእክት በመልካም ሥራ ጸንተው ሳሉ ለማለት ነው።

▶️፬. አጋንንት ከደቂቀ ሴት የሚለዩት በምንድን ነው? አንዳዴ ሲወራ ጋኔን ልጇን አዝላ አየን ሲሉ ይሰማልና ከዚህ 1ኛ መቃ.18፥4 ካለው ጋር ያለውን ግንኙነት ያስረዱኝ? እንዲሁም የቃየን ልጆች በበዙ ጊዜ ከበሮና በገናን ሳንቲንና መሰንቆን ሠሩ ዘፈንና ጨዋታውንም ሁሉ አደረጉ ይላልና ሳንቲ ምንድን ነው? (1ኛ መቃ.19፥1)።

✔️መልስ፦ ደቂቀ ሴት ሰዎች ናቸው። መጀመሪያ በመልካም ሥራቸው መላእክት እስከመባል ደርሰዋል። ቀጥለው ክፉ ሥራ በመሥራታቸው አጋንንት ተብለዋል (ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት) ማለት ነው። ደቂቀ ሴት ሥጋ ያላቸው በክፋታቸው ምክንያት አጋንንት የተባሉ ናቸው እንጂ ከመጀመሪያውም ረቂቃን ሆነው የተፈጠሩ አይደሉም። ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት ይወልዳሉ ይዋለዳሉ ስለዚህ ልጅ አዝለው ሊታዩ ይችሉ ይሆናል። ሳንቲ የሚባለው ዋሽንት ነው።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።


💙💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 114 💙💙

▶️፩. "ክሣደ ልቡናውን የሚያጸና የሚመካ ፈጣሪውን የማያውቅ ሐሳዊ መሲሕ ከእነርሱ ይወለዳልና ወዮላቸው" ይላል (1ኛ መቃ.13፥2)። ሐሳዊ መሲሕ የሚወለድበት ወገን በእውኑ ይታወቃል እንዴ? ከገዳም ይወጣል የሚሉ ሰዎችም አሉና በአጠቃላይ ስለሐሳዊ መሲሕ ስፋ አድርገው ቢያብራሩልኝ።

✔️መልስ፦ ሐሳዊ መሢሕ ከነገደ ዳን እንደሚወለድ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጿል። አንዲት ሴት መነንኩ ብላ ወደ ገዳም ስትሄድ ከመቃብረ አረሚ አግኝቷት አንድ ጎልማሳ ይደፍራታል። በዚህ ጊዜ ትጸንሳለች። እርሷም ትዕቢት ይዟት በድንግልና ጸነስኩ ብላ ትዋሻለች። ልጁ ይወለዳል። የሚወለደው ልጅ ላይኛው ከንፈሩ ትልቅ፣ ዓይኑን ደም የሰረበው ነው (ዘላዕላይ ከንፈሩ የዐቢ እንዲል)። ይህም ሰው በሰይጣናዊ ምትሐት እየታገዘ የተለያዩ ተአምራትን እያደረገ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር (ለ42 ወር) ብዙ ሰዎችን ያስታል። ከዚያ በኋላ እነ ኤልያስ እነ ዕዝራ እነ ሄኖክ ከብሔረ ሕያዋን መጥተው ሐሰተኛነቱን ይነግሩታል። እርሱም ይገድላቸዋል። ሰማዕት ይሆናሉ። ከዚያ በኋላ ጎግ ማጎግ የሚባሉ ኃያላን ሠራዊት የዓለምን ሕዝብ በጦር ይጨርሱትና ጥቂት ሰዎች ይቀራሉ። እነዚያ ለጥቂት ዘመን በዚህች ምድር ከኖሩ በኋላ ዳግም ምጽአት ይሆናል። ጻድቃን ወደ ዘለዓለም ደስታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ። ኃጥኣን ወደ ዘለዓለም ኀዘን ወደ ገሃነመ እሳት ይገባሉ።

▶️፪. 1ኛ መቃ.13፥8 ላይ "ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እኔ ፈርጄ አጠፋለሁ ብሏልና ከምጽአት በኋላ ግን ለዲያብሎስ ሥልጣን የለውም" ሲል በምን ላይ ነው ሥልጣን የሌለው? ከምጽአት በኋላ ከእርሱ ጋር በገሃነመ እሳት በሚኖሩት ላይ ሥልጣን የለውም እንዴ?

✔️መልስ፦ ዲያብሎስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የቻለውን ያህል ለማሳሳት ይሞክራል። ከምጽአት በኋላ ግን ማንንም አያሳስትም። እርሱና በእርሱ ትምህርት የተሳሳቱት ሁሉ በገሃነመ እሳት እየተቃጠሉ ይኖራሉ። በገሃነመ እሳት እርሱም ከሚቃጠሉትና ከሚሰቃዩት አንዱ ሆኖ ይኖራል እንጂ ለእርሱ የተለየ ሥልጣን አይኖረውም።

▶️፫. "እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት ላይ ኮርቷልና ፈጥኖም የወደደውን ሁሉ በአንድ ሰዓት አድርጓልና ታናሽ ጠላት ዲያብሎስን የጌታ ሞት ያጠፋዋል" ይላል (1ኛ መቃ.13፥7)። በፈጠረው ፍጥረት ላይ ኮርቷልና፣ በአንድ ሰዓት አድርጓልና ሲል ምን ለማለት ነው?  ይሄ ንባብ ቢብራራልኝ።

✔️መልስ፦ የወደደውን በአንድ ሰዓት አድርጓል ማለት አንድ ጊዜ ክዷል ማለት ነው። በካደ ጊዜ የሆነውን ድርጊት ለማስታዎስ ነው። በፈጠረው ፍጥረት ላይ ኮርቷልና ማለት እግዚአብሔር ከፍ አድርጎ ቢፈጥረው ሌሎችን ፍጥረታት እኔ ፈጠርኳችሁ ብሎ መታበዩን መግለጽ ነው። ኩራት የትዕቢት መገለጫ ነውና።

▶️፬. 1ኛ መቃ.12፥1 ላይ ያለው በየትኛው የትንቢት ክፍል ተጽፏል?

✔️መልስ፦ ኢየሩሳሌም በበደሏ ምክንያት እንደምትማረክ ነቢያቱ እነኤርምያስን ጨምሮ ተናግረዋል። ከዚህ ላይ የመቃብያን ጸሓፊ ነቢይ ብሎ ቢገልጽም ስሙን ግን አልነገረንም። ኢየሩሳሌም በበደሏ ምክንያት እንደምትማረክ ግን ኤርምያስ "በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ። ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ። ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ። ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ" ብሏል (ኤር.23፥14)።

▶️፭. 1ኛ መቃ.12፥7 ላይ "የወይናቸው ተክል የሲዖል ውኃን ጠጥቷልና ሐረጋቸውም በሐሩር ነፋስ ፀንቷልና" ሲል ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ ጉዳዩ ቀጥታ ስለወይንና ስለተክል ለመናገር ሳይሆን ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። የሲኦል ውኃ ያለው ክፋትን ነው። የሲኦል ውሃን ጠጥቷልና ሲል ክፋትን ሠርቷልና ማለት ነው። በሐሩር ነፋስ ጸንቷል ያለው የሐሩር ነፋስ በጣም ሞቃት ስለሆነ ተክልን ያደርቃል። በዚህ ምክንያት ተክሉ ልምላሜ ፍሬ አይገኝበትም። ስለዚህ ምግባር የላቸውም መልካምነት አይገኝባቸውም ማለት ነው።

▶️፮. "ክፉ ሰዎች የማረኩትን ምርኮ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ደጋጎች ይካፈላሉ" ይላል (1ኛ መቃ.12፥4)። የንባቡ ትርጓሜ ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ ክፉ ሰዎች በክፋታቸው ብዙ ገንዘብ ቢሰበስቡ እንኳ ያንን ገንዘብ ሳይበሉት ያልፉና ሌሎች ደጋግ ሰዎች ወርሰውት ይኖሩበታል ማለት ነው።

▶️፯. "ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ኃይሌን እገልጽ ዘንድ ለቁጣዬ አምሳል አደረግሁት" ይላል (1ኛ መቃ.13፥2)። "ለቁጣዬ አምሳል አደረግሁት" ሲል ትርጓሜው ምንድን ነው?

✔️መልስ፦ በቁጣ የሚመጣ ቅጣት ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ የቁጣ አሞሳል ማለት እገሌን ቢያጠፋ እግዚአብሔር ተቆጥቶ እንዲህ አደረገው እኛም ብናጠፋ እንዲህ ያደርገናል እንድንል የሚያደርግ ማለት ነው። ሌላው የቁጣውን ውጤት አይቶ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ የሚያደርግ ስለሆነ የቁጣ አምሳል ተብሏል። እግዚአብሔር ቁጣውን በእኛ ላይ ክፉ ሰዎች ሲነግሡ ዝም በማለት ሊገልጽ ይችላል። በዚህ ጊዜ እነዚያ ክፉ ነገሥታት የቁጣ አምሳል ይባላሉ።

▶️፰. "ምሥጢር እንዳያዩ ዓይነ ልቡናቸው ታውሯልና እንዳይሰሙ እግዚአብሔር የሚወደው ፈቃዱንም እንዳያደርጉ ጆሯቸውም ደ*ንቁ-ሯልና በሥራቸው እግዚአብሔርን አላወቁም ልቡናቸውም አንደ ሰዶም ሕግ ማደሪያ ነው። ወገናቸውም የጣፈጠ ፍሬን የሚያፈራ የገሞራ ወይን ወገን" ይላል (1ኛ መቃ.12፥2)። የጣፈጠ ፍሬን የሚያፈራ የገሞራ ወይን ሲባል ምን ማለት ነው?

✔️መልስ፦ የገሞራ ወይን (ወይነ ገሞራ) ያለው ውስጠ ወይራ ነው። ወይን ብሎ በግሥ ተናገረው እንጂ የገሞራ ክፋት ማለት ነው። የጣፈጠ ፍሬ ማለቱም ኃጢአት ሲሠሩት የጣፈጠ እንደሚመስልና ቆይቶ ግን መራራ መሆኑን ለማሳየት ነው።


© በትረ ማርያም አበባው


✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።

🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.