ጥበቃ... [Expectation]
___
["Blessed is he who expects nothing, for he shall never be disappointed." — Alexander Pope]
___
መጠበቅን መሰላል እንደመውጣት ነው የማስበው፤ በጣም ትጠብቃለህ ማለት በመሰላሉ ከፍተኛ እርካብ ላይ አለህ ማለት ሲሆን ጥበቃህ ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ነው ማለት ደግሞ የመሰላሉን ተመሳሳይ ቦታ ይዘሃል ማለት ነው...
እንግዲህ መሰላል የወጣ ሰው ዕጣፈንታ ሁለት ነው... ወይ እንዳወጣጡ ይወርዳል፣ አልያም ከደረሰበት ነጥብ እርካብ ከድቶት ይወድቃል...
[የመጠበቅ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው መሰላሉ ላይ በሰቀለህ እውነታ ነው... ብዙውን ጊዜ ግን ጥበቃ ከእጅ ካለው የታወቀ ሁኔታ ይልቅ ባልተጨበጠ ተስፋ ላይ የሚመሰረት ይሆንና መውደቅን ውጤቱ ያደርጋል...]
በመስተጋብራችንም ሆነ በግል ልምምዳችን ውስጥ እጅግ አደገኛው ስሜት መጠበቅ ሲሆን አስከፊ ውጤቱ ደግሞ የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር የሚፈጠረው ስብራት ነው...
ይህ ጥበቃ የታክሲ ሰልፍ ወይም የቦኖ ወረፋ አይደለም... ጊዜ ሲደርስ የምትደርስበት ወይም የመሆን ዋስትና የጨበጠ አይደለም... የስሜት ዕዳ ነው... የቅጽበት ክስተት... ቀጥሎ ምን እንደሚሆን የማይታወቅባት ዓለም ዕዳ...
እኛ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሕይወት ጋር በጸጥታ የምንገባው ውል አለን... ኮሽታ ሳናሰማ በተስፋ፣ በህልም፣ በምኞት በመፃኢ ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንፈጽማለን... በአዕምሮአችን ውስጥ ጥንቅቅ ብለው የተሰደሩ በርካታ ውብ ስዕሎች አሉን... ጠንክረን ስለሰራን፣ አጥብቀን ስላፈቀርን፣ ተግተን ስለጠበቅን ሕይወትም በዚያው መሰረት ምላሽ እንደምትሰጠን እናስባለን - እናምናለንም... ግና ምኞትና እውነታ ሁሌ አይሰምሩም... ያንጊዜ ደግሞ የመንፈስ ስብራት ይገጥመናል...
ስብራት ያልሰመረ ጥበቃ ውጤት ነው... ብዙ የለፉለት ግንኙነት ምላሽ ሲያጣ፣ ለረጅም ጊዜ የጠበቁት ዕድል ቅዠት ሲሆን፣ እንደ ጣልንባቸው ተስፋና እንደ ሰጠናቸው ቦታ ሰዎች ሳይከውኑ ሲቀሩ ህመም ይገጥመናል... ህመሙ ግን ስለ እጦታችን ብቻ አይደለም... ከእጃችን በሌለ ነገር ላይ የገነባነው ተስፋ ከፊታችን ብን የማለቱ ሃቅ ብሎም ለርሱ ብለን ያጠፋነው ጊዜ የሚፈጥረው ቁጭትም እንጂ...
“Disappointment is a sort of bankruptcy—the bankruptcy of a soul that expends too much in hope and expectation.” — Eric Hoffer
[ነገሩን በምሳሌ እናፍታታው...]
ያፈቀርካት ልጅ ከልብህ የቀለስክላትን ጎጆ አክላ እንድትከሰትልህ ትጠብቃለህ - በእርሷ ልብ ውስጥ ዳስ የተጣለለት ተፈቃሪ ሊኖር መቻሉን ግን ትዘነጋለህ...
[እናም - 'አይሆንም' አለችኝ በሚል ሰበብ ልብህ እንክት ትላለች...]
___
ሃሳብህን ሰው ሁሉ እንዲረዳልህ ትጠብቃለህ - ግና ሁሉም ሰው በየራሱ ንሸጣ፣ በየራሱ መንገድ እንጂ ባንተ መንገድ ብቻ ነገርህን ሊገነዘብ እንደማይችል ትዘነጋለህ...
[በዚህ ምክንያት ድብርት ትከናነባለህ...]
___
ሰዎች ሁሌም በበጎ ቃልና በፈካ ፊት እንዲቀበሉህ ትጠብቃለህ - ሆኖም በብዙ ዓይነት የስሜት መዋዠቅ ውስጥ እንደሚያልፉ፣ ያም ቀናነታቸውን እንደሚያደበዝዘው ትዘነጋለህ...
[በዚህ ምክንያት ቀንህን አስረክበህ ትውላለህ... አንዳንዴም ቂም ቋጥረህ ግንኙነትህን ታበላሻለህ...]
___
ሎተሪ እንዲደርስህ ትጠብቃለህ - ሆኖም ከብዙ ሚሊዮኖች ጋር የሚደረግ ውድድር መሆኑን ትዘነጋለህ...
[በዚህ ሰበብ ዩኒቨርሱን በአድሎ ፈፃሚነት ትከሳለህ...]
___
በድካምህ ልክ ሹመት፣ በጥረትህ ልክ ሽልማት ትጠብቃለህ - የሰዎች ሚዛን ያለው ራሳቸው ጋ መሆኑን ግን ትዘነጋለህ...
[እናም ይህን ሰበብ አርገህ የስራ ሞራልህን ትገድላለህ...]
___
ብዙ ድካምና ሃብት ያፈሰስክበት ቢዝነስ ፈጥኖ ውጤታማ እንዲሆን ትጠብቃለህ - የጊዜና የሁኔታዎችን ምቹነት የማጤን አስፈላጊነት ግን ትዘነጋለህ...
[በዚህ ምክንያት የሚያድግ ወረትህን ትቀብራለህ፣ ሌላ የመጀመር ድፍረትህንም ትሰዋለህ...]
___
በችግራቸው ጊዜ አለሁ ያልካቸው ሁሉ ኑሮ ሲፈትንህና ምርግ ሆኖ ሲጫንህ እንዲደርሱልህ ትጠብቃለህ - ከጓዳቸው ያደፈጠ፣ ከገመናቸው የተሻጠ ምስቅልቅል ሊኖር እንደሚችል ግን ትዘነጋለህ...
[አዎን - በዚህ ተቀይመህ ሰው ትርቃለህ... የልብህንም ሰዎች ታጣለህ...]
___
ወዳጆችህ በሃዘንህ ጊዜ ጎንህ ተገኝተው እንባህን እንዲጠርጉ፣ በክፉ ጊዜህ ገመናህን እንዲሸሽጉ፣ በደስታህ ጊዜ ድግስህን እንዲያደምቁ ትጠብቃለህ - ከእነርሱ ታዛ ሰው የማይደርስበት ለቅሶና ምሬት፣ በሳቅ የሚከልሉት ችግርና ብሶት ሊኖር እንደሚችል ግን ትዘነጋለህ...
[እናም በዚህ ሰበብ ሰው የምታይበት ዓይን፣ የምታቀርብበት ወሰን፣ የምታርቅበትም ሚዛን ይዥጎረጎራል...]
___
"We are all prisoners of our expectations." — Georges Bernanos
___
[ታዲያስ?...]
እንግዲህ ጥበቃ የአዕምሮ ቅኝት ነውና ይቆጣጠሩታል እንጂ አያስቀሩትም... ይመጥኑታል እንጂ አልቦ አያደርሱትም...
ማግስቱን ለድብርት፣ ከርሞ ለስብራት ምክንያት እንዳይሆን ግን ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል...
___
[ሦስት መላዎች ይታዩኛል...]
___
፩) Flexibility - 'ይህን ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ' ከማለት ይልቅ 'ይህ ባይሆን ያንን አሳካለሁ' ብሎ ማሰብ... ችክ አለማለት... አማራጮችን ማየት... አንዳንድ ጊዜ ያጣነው በመሰለን አንድ ነገር ፈንታ ያልጠበቅነው እልፍ ስጦታ ሊደርሰን ይችላል... የጠበቅነው የሚጎዳን፣ የሚሰጠን የሚያስደስት ሊሆንም ይችላል...
፪) እንዲሆን የሚፈልጉት ነገር ላይ what if መቀላቀል... ባይሆንስ ብሎ ማሰብ... ቢቻል የጉዳዩን ተጨባጭነት ማጤን፣ አልያም ጥበቃን ማመጣጠን...
[በመሰላሉ ግርጌ ላይ መቆየት... ነገሩን የሚያመጣው ወይም የሚያስቀረው ጥበቃው ሳይሆን የጉዳዩ ተጋጋዥ ሁኔታዎች ሕብር ነው... ሊመጣ ያለን - ባለመጠበቅ አታጣም፣ የማይመጣንም በመጠባበቅ አትወልድም...]
፫) መቀበል... የሆነውን እንደመሆኑ ማስተናገድ... ስለ ጉዳዩ ከመብሰልሰል ይልቅ ክስተቱን እንደሁኔታው ተቀብሎ ወደፊት መጓዝ... ባለፈው ጎርበጥባጣ የባከነ ጉልበትህን ሳይሆን ቀሪው አቅምህ የሚያስወጣህን አቀበት ማስተዋል... Let it go!
___
"We must accept finite disappointment, but never lose infinite hope." — Martin Luther King Jr.
___
መልካም አሁን!!
___
@bridgethoughts