EOTC TV (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ድርጅት)


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: Din


Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
Din
Statistika
Postlar filtri






ቅዱሳን በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምንጊዜም ይሠራል፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፤ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድኾች እንድንመጸውት፣መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፣ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፣ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐጽማቸውን፣ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐጽማቸውን፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕረፍታቸውን በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
የኢትዮጵያዊው ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጸሎታቸው እና አማላጅነታቸው አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
✍️ ገድለ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ
✍️ መጽሐፈ ስንክሳር
✍️ የቤተክርስቲያን ታሪክ


ስባረ ዐጽሙ ለተክለ ሃይማኖት ጻድቅ
በመ/ር ጌታቸው በቀለ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያዊውን ጻድቅ ሐዲስ ሐዋርያ ፀሐይ ዘኢትዮጵያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስባረ ዐጽማቸውን ጥር ፳፬ ቀን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ጥበብ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም ተወለዱ /ገድለ ተክለ ሃይማኖት/፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው “አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው” በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም “ፍሥሐ ጽዮን” የሚል ሲሆን “ተክለ ሃይማኖት” ደግሞ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያወጣላቸው ስም ነው፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡
ሐዲስ ሐዋርያ
አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድ ቀን ለአደን ወደ ጫካ በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሰደረባቸው፤ እንደዚሁም “ሐዲስ ሐዋርያ” ብሎ ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ነገራቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም “ተክለ ሃይማኖት” እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደ ሆነ አስረዳቸው፡፡ ከዚህ በኋላም ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ” በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡
ጥር ፳፬ የኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ስባረ ዐጽማቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በታላቅ ድምቀት አክብራ የምትውልበት ታላቅ ቀን ነው። ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለዓመታት ከቆሙበት ሳይቀመጡ፣ ከፊት፣ ከኋላ ከጐን እና ከጐን ምንም ሳይደገፉ በአንድ ቦታ በመወሰን ለ፳፪ ዓመታት ደብረ ሊባኖስ በሚገኘው ደብረ አስቦ ዋሻ ውስጥ ሲጸልዩ ከመቆም ብዛትም እግራቸውን አጥተዋል። ከዚያም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ጸሎታቸውን ቀጠሉ። ስለ ክብራቸውም ከእግዚአብሔር ክንፍ ተሰጥቷቸዋል። በአጠቃላይ ለ፳፱ ዓመታት በጸሎት ቆይተዋል። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንም በየዓመቱ ጥር ፳፬ ደግሞ ስባረ ዐጽማቸውን (ለ፳፪ ዓመታት ቆመው ሲጸልዩ ከመቆም ብዛትም እግራቸውን አያጡበትን ወይም የተቆረጠበትን) ቀን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች።
እንደ ማጠቃለያ
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው፣ ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በብሕትውና ኖረዋል፡፡ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

































20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.