አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜንኅዳር 12-ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር ንሥረ አርያም የሚባል ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ ንዑድ ክቡር የሆነ ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ዕለት ነው፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል፡- ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ' ካ-ከመ' ኤል-አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ ‹‹መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው›› ማለት ነው፡፡ አንድም ለእግዚአብሔር አሸናፊ ድል አድራጊ የቸርነትና የርህራሄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው፡፡
ገናናው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስን ወደ ጥልቁ ጥሎት በእርሱ ምትክ ከሁሉ የበላይ ሆኖ በተሾመበት በዚህ ዕለት በበዓሉ መታሰቢያ በኅዳር 12 ቀን የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክንፎቹን ወደ ሲኦል ያወርዳል፣ ኃጥአንንም ወደ አዲሲቱ ምድር ያወጣቸዋል ይኸውም የመላእክት አለቃ የሚካኤል ሠራዊት ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸውና ምሕረት አግኝተው በአንድ ጊዜ በክንፉ ያወጣቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡
ቅዱስ ሚካኤል በየዓመቱ በኅዳር 12 ቀን እንዲህ እያደረገ እልፍ ነፍሳትን ያወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ወገኖች የሆኑትን ሁሉ እንደሥራቸው ወደ ምሕረት ቤት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አብ መጋረጃ ውስጥ ይገባል፣ በዚህች ዕለት ምድራዊትና ሰማያዊት ስለሆነች ምሕረቱም ከመንበሩ በታች ይሰግዳል፡፡ ስለውኃ ምንጮች፣ ስለ ወይን ቦታዎች፣ ስለ ምድር ፍሬዎች በምድርም ላይ ስለሚኖሩ ስለ ሰው ልጆች ነፍስ ሁሉ፣ ስለ እንስሳትም፣ ስለ ሰማይ ወፎችም፣ ስለ ባሕር ዓሣዎችም፣ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የምሕረት ባለቤት ከሆነ ከአብ ዙፋን በታች ሁልጊዜ በማመስገን ይሰግዳል፤ ልመናውንም እስኪሰማውና የምሕረትንም ቃል እስኪያስተላልፍለት ድረስ ከእግረ መንበሩ ሥር አይነሣም፡፡
ለዚህ ዓለም ምሕረትን የሚለምኑ ቅዱሳን መላእክትም በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀንበእግዚአብሔር የዙፋኑ ዓውደ ምሕረት ዙሪያ ተሰብስበው ስለ ሰውና ስለ እንስሳትም ሁሉ ምሕረትን የሚለምን ቅዱስ ሚካኤል ከአብ መጋረጃ ውስጥ በወጣ ጊዜ ቸርና መሐሪ አብ ለቅዱስ ሚካኤል የሰጠው ልብሱን እነዚያ መላእክት ይመለከታሉ፣ ይቅርታን የማግኘት ምልክታቸው ነውና፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ምሕረት እንደተደረገ ሰውንም እንስሳትንም ይቅር እንዳለ በዚህ ዓለምም የሚሆነውን ሁሉ አይተው ቅዱስ ሚካኤል በለበሰው ልብስ አምሳል ያውቁታል፡፡
ስንክሳሩ እንደሚለው ይህ እጅግ የከበረ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋራ በመሆን ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የሚያጽናናቸውና የዘወትር ጠባቂአቸው ሆኖ የሚራዳቸው እርሱ ነው፡፡›› የብዙዎቹንም ቅዱሳን ገድል ስንመለከት የዘወትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
ቅዱሳን በሕይወት ሳሉ ይህ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ረዳትና የዘወትር ጠባቂ፣ እንደጓደኛም አማካሪ ሆኖ የተበቃቸውን ስንቱን ቅዱሳን ዘርዝረን እንቸላለን፡፡ እርሱ ያልረዳው ቅዱስ የለም፡፡ መከራውን ያላስታገሰው ሰማዕት የለም፡፡ ለቅዱሳኑ እንዲህ እንደጓደኛቸው ሆኖ ሲጠብቃቸው ይኖራል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ለኃጥአንና አምላካቸውን ለካዱ ሰዎች ደግሞ በቁጣ ለመቅሰፍት ይመጣባቸዋል፡፡
ሰናክሬም በእግዚብሔር ላይ ክፉ በመናገሩ በአንዲት ሌሊት ብቻ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) ሠራዊቱን ቅዱስ ሚካኤል በብርሃን ሰይፉ ፍጅቷቸው አድሯል፡፡ 2ኛ ነገ 19፡35፣ ኢሳ 37፡36፡፡
እግዚአብሔርን ለሚወዱና እርሱንም ለሚያከብሩት መታሰቢያውንም ለሚያደርጉለት ግን ከሚፈልጉት ነገር ከቶ አያሳጣቸውም፣ ዘወትርም ይጠብቃቸዋል፣ በኋላም በአማላጅነቱም ከሲኦል እሳት ያድናለቸዋል፡፡
እነሆ ይህ ገናና ክቡር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- ‹‹የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ነገር ግን ወደቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡
ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ 300 የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ›› አላቸው፡፡
እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፡፡
የከበረ ገናናው መልአክም ‹‹ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፡፡ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡››
የመላእክት አለቃ ቅዱስ የሚካኤል ጥበቃው አይለየን! ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!
@ewuntegna@ewuntegna