✍
ከመልካሞች አንደበት ስሞታ ሳይሆን ውለታ ነው የሚሰማው!! ነብዩላህ ዩሱፍ
ﷺ ከህፃንነቱ ጀምሮ ሙሉ ዕድሜው በስቃይ የተሞላ መራራ ሕይወት እንጂ ሰላም እና ዕረፍት ያለው የሕይወት ገፅታ ለማየት አልታደለም ነበር። ከመሆኑም ጋ: በንግግሩም ይሁን በተግባሩ ሁሌም ውለታን ሲጠቅስ እንጂ ስሞታ ሲዘረዝር ታይቶ አይታወቅም ነበር።
ለምን???? የዚህን ጥያቄ መልስ የታሪኩ መጨረሻ ላይ እናገኘዋለን። {…
وَقَدْ أَحْسَنَ بِي…} ሲል። ያንን ሁሉ መከራ እና ሰቃይ ሲፈራረቅበት ጌታው እሱ ላይ የዋለው ውለታ እና አዘኔታ መሆኑን እንጅ ሌላ አይታየውም ነበር።
ለምሳሌ፦
እነዝያ ሁሉ ዓመታት በግፍ ታስሮ ከእስር ሲወጣ: በበደል በመታሰሩ ማዘን እና ስሞታ ማቅረብ ሳይሆን ከእስር በመፈታቱ ጌታው የዋለለትን ውለታ ይጠቅሳል………
{…وَقَدْ أَحْسَنَ بِي إِذْ أَخْرَجَنِي مِنَ السِّجْنِ…}
{…(ጌታዬ) ከእስር ቤት ባስወጣኝ ጊዜ በእርግጥ ውለታ ውሎልኛል።…} ወንድሞቹ እንደዛ ጠልተው አሰቃይተው ከሸጡት በኋላ: እነርሱን ሲገናኝ ስለ ሰሩበት በደል ስሞታ ከማቅረብ ይልቅ በድጋሚ በሰላም ከእነሱ እና ከወላጆቹ እንዲገናኝ አላህ የዋለለትን ውለታ ይጠቅሳል………
{…وَجَاءَ بِكُم مِّنَ الْبَدْوِ مِن بَعْدِ أَن نَّزَغَ الشَّيْطَانُ بَيْنِي وَبَيْنَ إِخْوَتِي…}
{…ሸይጣን በእኔና በወንድሞቼ መሃል ካበላሸ በኋላ, እናንተን ከገጠር ወደ እኔ ሲያስመጣችሁም (ጌታዬ) በእርግጥ ውለታ ውሎልኛል።…} ያቺ ኣመፀኛ ሴት እንኳ ለብልሽት ስትጠራው: እሷ እንዲማግጥበት የፈለገችው ባልዋ ለእሱ ባለ ውለታው መሆኑን ይጠቅሳል………
{…قَالَ مَعَاذَ اللَّهِ إِنَّهُ رَبِّي أَحْسَنَ مَثْوَايَ…}
{…በአላህ እጠበቃለሁ: እሱ (ባልሽ) መኖሪያዬን ያመቻቸልኝ ዐለቃዬ ነው አላት።…} ሁሉም ዐይነት ፈተናም ይሁን መከራ ሲገጥመው: አላህ የሚውልለት ውለታ እንጂ ሰዎች ለፈፀሙበት በደል ወይም አላህ ላይ ተማሮ ስሞታ ሲያቀርብ አይታይም።
የንፁህ ልብ ባለቤት የሆኑ ደጋጎች ሁሌም እንዲህ ናቸው። ተቆጥሮ የማያልቅ ውለታ ለጋሽ የሆነው ጌታቸው ከማመስገን የሚመልሳቸው ክስተት የለም። በመሆኑም ጌታቸው የዋለላቸው ሰፊ ውለታ ሁሌም ስለ ሚያስታውሱ: ሁሌም ለጌታቸው ተገዢ እና አጎብዳጅ ታማኝ ባሪያ ይሆናሉ።
ነብዩላህ ዩሰፍ
ﷺ የአላህን ውለታ ብቻ የሚያስታውስ አመስጋኝ ባሪያ በሆነ ጊዜ: አላህም ከሰፊው ቱሩፋቱ ጨምሮ ጨማምሮ ከመስጠት አልተቆጠበም። በዚህም ሂደት ነው ባሪያ ተደርጎ በመሸጥ የጀመረው ሕይወት ንጉስ እና መሪ ሁኖ የተጠናቀቀው።
ሁላችንም ቀን ከሌት በአላህ ፀጋ እና ውለታ የምንገለባበጥ ባለ ፀጋዎች ነን፤ ይህንን አውቆ የሚያመሰግን ልብ ግን አጣን።🖊
ሐምዱ ቋንጤ ከፉርቃን ሰማይ ስር!!https://t.me/hamdquante