#የምርመራዘገባ አለም ባንክ በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ለኢትዮጵያ የሰጠው 200 ሚልዮን ዶላር ምን ላይ እየዋለ ነው?
- በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ስር በግል አማካሪነት በአመት 120 ሺህ ዶላር የሚከፈለው ግለሰብ አለ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ይፋ ተደርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2013 ዓ/ም ነበር። በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ብሄራዊ ኮሚቴ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ሆኖ መንቀሳቀስ የጀመረው።
ፋውንዴሽኑ ዋና አላማው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የህዝብ ተቋማት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ዝርጋታ፣ የብሄራዊ መታወቂያ ስራ፣ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማትን አቅም መገንባት በስራው ውስጥ የተካተቱ ነበሩ።
እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ በመንግስት በይፋ ቢገለፅም አንዳንድ አነጋጋሪ ድርጊቶች ግን መታየት ጀምረዋል።
ለምሳሌ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ከሚገኙት መሀል ዶ/ር ስሜነው ቀስስ ሲሆኑ የትምህርት መስካቸው የእንስሳት ህክምና ቢሆንም በዚህ የዲጂታል ዘርፍ በአማካሪነት ተቀጥረው በአመት 130,000 ብር በአማካሪነት እንደሚከፈላቸው ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።
በሌላ በኩል አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ወይም ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ 'ቴክ ቶክ' በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ በተመሳሳይ በማማከር ቅጥር በአመት 120,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጠሩ አነጋጋሪ እንደሆነባቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል፣ ሰለሞን በአመት በርካታ ወራትን በአሜሪካ የሚያሳልፍ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "Internet Exchange Point" በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
"አይቲ ፓርክ" ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ እነዚህ ምንጮች ያስረዳሉ።
"በሸገር ከተማ ቡራዩ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 'የቴክኖሎጂ ክህሎት ስልጠና ለመስጠት' በሚል ፋሪስ ለተባለ ድርጅት 21 ሚልዮን ብር በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ተከፍሏል" የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ይህም የተከናወነው በጨረታ ስም ሆኖ ሌሎች አቅም ያላቸው ተቋማት ገለል ተደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።
የፋሪስ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ የቴስላ 'ሳይበርትራክ' መኪና ካለቀረጥ ወደ ሀገር በማስገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህን መኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ባለቤቱ አቶ ኤልያስ ይርዳው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለሀገሪቱ ትልቅ "የኢኖቬሽን" እምርታ ብሎ የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።
በዚህ ዙርያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶ/ር በለጠ ሞላን እንዲሁም የዲጂታል ፋውንዴሽን ሀላፊውን አቶ ተሰማ ገዳን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
መረጃን ከመሠረት!
@MeseretMedia