«ይችላል ወይስ አይችልም?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
15፥45 አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡ وَكَانَ اللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ مُّقْتَدِرًا
አምላካችን አሏህ ስለ እርሱ ኑባሬ በሦስተኛ መደብ ሲናገር፦ "አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው" በማለት አለመቻል በእርሱ ቻይነት ላይ እንደሌለበት ይናገራል፦
15፥45 አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡ وَكَانَ اللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ مُّقْتَدِرًا
ነገር ግን ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ፦ "አምላክ ሁሉን ማድረግ ይችላል ወይስ አይችልም? በማለት ይጠይቅና መልሱ "ይችላል" ከሆነ "መውለድ እና መወለድ አይችልም ወይስ ይችላል? የሚል ስሑት ጥያቄ ይጠይቃል።
፨ሲጀመር "ማድረግ" "ማስሆን" እና "መደረግ" "መሆን" ልዩነት አላቸው። ለምሳሌ፦ "መላእክት ወንድ ናቸው ወይስ ሴት? ተብሎ ቢጠየቅ ከመነሻው ጥያቄው ስሑት ጥያቄ ነው፥ ምክንያቱም ሴት እና ወንድ ፆታ ላለው ተፈጥሮ እንጂ ፆታ ለሌላቸው ለመላክእት አይሆንም። "መውለድ" እና "መወለድ" ደግሞ "መሆን" እንጂ "ማስሆን" አይደለም፥ "መደረግ" እንጂ "ማድረግ" አይደለም። በአሏህ ባሕርይ ውስጥ "ማስሆን" እንጂ "መሆን" ወይም "ማድረግ" እንጂ "መደረግ" የሚባል ባሕርይ የለም፥ እርሱ "ነው" እንጂ "ሆነ" አይባልም። እርሱ የሚያስሆን እና የሚያደርግ እንጂ የሚሆን እና የሚደረግ አይደለም፥ መውለድ ወላዲ መሆን መወለድ ተወላዲ መሆን ስለሆነ እርሱ የሚያስሆን እንጂ የሚሆን አይደለም።
አሏህ ከወለደ ከአንድ ወደ ሁለት ይባዛል፥ ከተወለደ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ ፍጡር፣ ሟች፣ ደካማ፣ እንቅልፋም፣ ባሪያ ይሆናል። ስለዚህ ከፍጥረት ውጪ ጊዜ እና ቦታን ያካበበ ፈጣሪ በአንድነቱ ሁለትነት የለውም፥ "አሏህ "መሆን" ይችላል ወይስ አይችልም?" ተብሎ የሚጠየቀው የዐላዋቂዎች ጥያቄ ሁለት ስሑት ቀጠና"false dichotomy" ነው። ይህም ሥነ-አመክኗዊ ሕፀፅ"logical fallacy" አለበት፥ ምክንያቱም "መሆን" እና "አለመሆን" የፍጡር ባሕርይ እንጂ የፈጣሪ ባሕርይ ስላልሆነ ሌላ "ማስሆን" የሚባል ሦስተኛ ቀጠና"trichotomy" አለ።
፨ሲቀጥል መውለድ መንስኤ ሲሆን መወለድ ውጤት ነው፥ አብ አስገኝ ወልድ ተገኚ ከሆነ በመካከላቸው ድብን አድጎ መሽቀዳደም አለ። ይህም የመንስኤ እና የውጤት መቀዳደም ነው፥ ወላዲ አስገኝ በመሆን አስጀማሪ ሲሆን ተወላዲ ተገኚ በመሆን ተጀማሪ ስለሚሆን በመካከላቸው የመንስኤ እና የውጤት መቀዳደም አለ።
በመቀጠል፦ "እግዚአብሔር የማይችለው አንድ ነገር ነው፥ እርሱም አለመቻልን ነው" ይለናል፥ እንደ እርሱ ስሑት ሙግት እግዚአብሔር አለመቻልን ካልቻለ ሁሉን ቻይ አይደለም ማለት ነው። "አምላክ ሁሉን ነገር ማድረግ ከቻለ አለመቻል መቻል እንዴት ያቅተዋል? ለምሳሌ፦ "ፈጣሪ ሁሉን ቻይ "አለመሆን" ይችላል ወይስ አይችልም?" ብንል "ይችላል" ካልን ሁሉን ቻይ አይደለም፥ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ አለመሆን መቻሉ ሁሉን ቻይ አያስብለውም። "አይችልም" ካልን ሁሉን ቻይ አይደለም፥ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ አለመሆን አለመቻሉ ነው።
ስለዚህ ጥያቄው ሥነ-አመክኗዊ ሕፀፅ አለበት፥ ሦስተኛ ቀጠና ግን ከመሆን እና ከአለመሆን ነጻ የወጣ "ማስሆን" የሚባል ባሕርይ ስላለ "አሏህ ሰው "ማስሆን" "ማድረግ" ይችላል ወይስ አይችልም?" ወይም "አሏህ ሰው እንዲወልድ እና እንዲወለድ "ማስሆን" "ማድረግ" ይችላል ወይስ አይችልም?" ተብሎ መጠየቅ አለበት! መልስ አሏህ ነገርን ሁሉ "በማድረግ" እና "በማስሆን" ቻይ ነው።
ክርስቲያኖች ሆይ! የሚገዳደረው ወደረኛ፣ የሚቀናቀነው ተቀናቃኝ፣ የሚተካከለው እኩያ፣ የሚፎካከረው አቻ፣ የሚመስለው አምሳያ የሌለውን አንዱን አምላክ አሏህን በብቸኝነት እንድታመልኩት ጥሪአችን ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።»
©:ከዐቃቤ እሥልምና ወሒድ
የቴሌግራም ቻነሉን ተከታተሉት፦
https://t.me/Wahidcom