#ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሩፋኤል (#ታኅሣሥ_13)
ታኅሣሥ ዐስራ ሦስት በዚህች ቀን በዚህች ዕለት ፈታሄ ማህጸን ሊቀ መልአክት ቅዱስ ሩፋኤል ቅዳሴ ቤቱና ተአምር ያደረገበት ዕለት ነው፡፡ ሰማያውያን ከሆኑ ከመላአክት አለቆች ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ 3ተኛ ነው፡፡ "ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ ጦቢት 12፡15፡፡ ሩፋኤል የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል መልአከ የሰላምና የጤና መልአክ ይባላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፡3፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ ሄኖክ 10፡13፡፡ ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ በማኅፀን ላለ ችግርና ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት በማሕፀን እያለ ማለትም በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሠቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል ጦቢት 3፡8-17፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ሄኖክ 3፡5-7፡፡ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሄኖክ 2፡18፡፡ ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘረጋቸዉ ይህ ታላቅ መልአክ ነዉ፡፡
የምህረትና የረድኤት መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሥራዎቹ አንፃር በተለያየ ስም ይጠራል፡፡ "ፈታሄ ማህጸን" ይባላል-እናቶች ሲወልዱ ምጥ እንዳይበዛባቸዉ የሚራዳ መልአክ ስለሆነ አያሌ ክርስቲያኖች ማርገዛቸዉን ካወቁ ጀምሮ ድርሳኑን በማንበብ መልኩን በመድገም ጠበሉን በመጠጣት ሰዉነታቸዉን በመቀባት ይለምኑታል፡፡ እንደ እምነታቸዉ ጽናት ይደረገላቸዋል፡፡ ዳግመኛም "ዐቃቤ ኖኀቱ ለአምላክ" ይባላል-ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠበቅ ስለሆነ ነው፡፡ ዳግመኛም "መራሔ ፍኖት" ይባላል-ጦቢትን በቀና መንገድ መርቶታልና ነው፡፡ እንዲሁም "መላከ ክብካብ" ይባላል-ጦቢያና ሣራን ያጋባ ጋብቻቸዉን የባረከ በመሆኑ ነው፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያደረገው ተዓምር ይህ ነው፡፡ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በዓል እስኪፈፀም ድረስ በከበረ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎፍሎስ ዘመን በምድረ ግብጽ ውስጥ ከእስክንድርያ ውጭ በታናፀች አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከአሳ አንበሪ ላይ የታነፀች ነበር፡፡ ነገር ግን በወደቡ አጠገብ ከነበረ ግዙፍ አንበሪ ጀርባ ላይ መታነጿን ቀድሞ ያነጿት ሰዎች ቢሆኑ ከካህናትም ቢኾን ያወቀ አልነበረም፡፡
ያ አንበሪም የቤተክርስቲያኑ ህንጻ በከበደው ጊዜ ፈጽሞ ተንቀሳቀሰ፡፡ ከአሸዋማው መሬት ላይ በባህሩ ዳርቻ የታነፀች ይህች ቤተ ክርስቲያንም ከመሰረቷ አናወጻት፡፡ ያን ጊዜ ትልቁም ትንሹም ወንዱም፣ ሴቶችም፣ የተሾሙ ዲያቆናት፣ ካህናት፣ ሕዝቡም ሁሉ ደነገጡ ታወኩ፡፡ አሣ አንበሪው ግን መንቀሳቀሱን አልተወም፡፡ በመንቀሳቀሱም የቤተ ክርስያኗ ሕንፃ እኩሌታ ይሰነጠቅ ዘንድ ጀመረ፣ ምድርን ተናወፀች፣ ንጉስና፣ ሊቀ ጳጳሳቱም፣ ካህናቱም፣ ዲያቆናቱም፣ ህዝቡም፣ ሁሉም ካሉበት በባህሩ ወደብ ከተሰራች ከዚህች ቤተ ክርስቲያን መናወጥ የተነሳ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላያቸው ወረደ፡፡ ያ አንበሪ ግን በባህሩ ውስጥ ወደፊት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗም በጀርባው ላይ ነበረች፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሉትም ሁሉ ያ አሳ አንበሪ ወደ ባሕሩ ውስጥ ሊያሰጥመን ነው ሲሉ አሠቡ፡፡ ያን ጊዜም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ስዕል ፊት በጽኑ አለቀሱ፡፡ በአንድ ቃልም "ገናናው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ሆይ ርዳታህ ፈጥኖ ይደርስልን ዘንድ በቅድስት ቤተክርስቲያን ወደተሰበሰብን ወዳጆችህ ተመልከት" እያሉ ይጸልዩ ጀመር፡፡ ያንጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ ያችን ቤተክርስቲያን በብሩሃት ክንፎቹ እንደደመና ጋረዳት፡፡ በእጁ በተያዘ የብርሃን በትረ መስቀሉ ያን ኣሣ አንበሪ ወገቶ "በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል ከቦታህ ሳትንቀሳቀስ እስከትውልድ ፍፃሜ ዘመን ለዘለአለም ትኖር ዘንድ አዝዝሃለሁ" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያኗን ከነመዓዘኗ ከግርግዳዎቿ ከመሠዊያዋ በውስጧ ተተክለው ካሉት ሁሉ ጋር ከጀርባው ላይ እያለች ያንን አሳ አንበሪ ወግቶ በያዘበት ብርሃናዊ በትረ መስቀሉ ወደቀድሞው የባሕሩ ወደብ ጎተተው፡፡ ያንጊዜም ግንቡ ቦታውን ሳይለቅ እርስ በእርሱ ተጣበቀ፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አሣ አንበሪውን በቀድሞ ሥፍራው ያቺን ቤተክርስቲያን በቀደመ መሠረቷ ላይ አጽንቷቸዋልና፡፡ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤልም አዳኝ የሆነ የጌታው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጠርቶ ከሞት እንዳዳናቸው ሁሉም አስተዋሉ፡፡ በድንቅ ተዓምራቱ የዳኑ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በሊቀመላእክቱ ቅዱስ ሩፋኤል ላይ አድሮ ድንቅ ተዓምራቱን ስለገለጸላቸው የቅዱስ ሩፋኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዚህች ቤተክርስቲያን ታሪክም በዓለም ሁሉ በየአውራጃዎቹም ተሰማ፡፡ የቅርብም የሩቅም ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው ታላቁ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የለመኑትን ሁሉ ያደርግላቸው ዘንድ የነገሩትን ያማልዳቸው ዘንድ በውስጧ ይጸልያሉ፡፡ በዚችም ቤተክርስትያን ብዙ ውስጥ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ታኅሣሥ 13 ቀንም ተአምራቶቹ ከተፈጸመባቸው ዕለታት አንዷ ናት፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በዚሁ ዕለት ተከናውኗል፡፡
የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ጥበቃው አይለየን።