ጥር ፲፮ /16/
በዚችም ቀን የከበረ አባት ተጋዳይ የሆነ ጰላድዮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከዋሻው ሳይወጣ የሴቶችን ፊት ሳያይ ሃምሳ ዓመት ኖረ ድንቆች ተአምራቶችን የማድረግና የትንቢት መናገር ሀብት ተሰጠው ዜናውም በቦታው ሁሉ ተሰማ።
በምስር አገር አንድ ነጋዴ በመርከብ ተጭኖ ሲሔድ ማዕበልም ተነሥቶበት ለመሥጠም ደረሰ ከሞት ከዳነም መቶ የወርቅ ዲናር እንደሚሰጥ ስለት ተሳለ ቅዱሱም አዳነው።
ከዚህም በኋላ ነጋዴው የተሳለውን ወርቅ ይዞ ወደ ቅዱሱ በዓት ሔደ። አንድ ሞሪት የሚባል ሰው አግኝቶ ሁሉንም ነገር ነገረው ሞሪትም ከቅዱሱ ዘንድ አደረሰው። አባ ጰላድዮስም አይቶ ባረከው እንዲህም አለው በዚህ ወርቅ ፍላጎት የለኝም ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ጠቃሚ እንዲሆንህ ሒደህ ለድኆችና ለችግረኞች በትነው አለው ነጋዴው ግን ይቀበለው ዘንድ ከእግሩ ሥር ወድቆ ማለደው ጥቂትም ወሰደለትና እንዲህ አለው ለበረከት ይህን ተቀብየሃለሁ የቀረውን እንዳዘዝኩህ አድርገው አለው።
ነጋዴውም ወርቁን ይዞ ተመለሰ ሞሪትም ሰይጣን አስቶት ነጋዴውን ገሎ ወርቁን ወሰደ በድኑንም ከቅዱሱ በዓት ጣለው። በማግሥቱም ወደ አገረ ገዥ ሒዶ ስለ ሟቹ ነገረው።
መኰንኑም አባ ጰላድዮስን አሰረውና ስለሟቹ ይመረምረው ጀመር። አባ ጰላድዮስም እርሱ እንዳልገደለው ተናግሮ በሟቹ ላይ ቢጸልይበት ነጋዴው ተነስቶ ሞሪት እንደገደለው ተናገረ። መኮንኑም ተጸጽቶ ሞሪትን ሊገድለው ወደደ አባ ጰላድዮስም አስተወው። ከብዙ ተጋድሎም በኋላ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝቶ አገልግሎ በመልካም ሽምግልና አረፈ።
@sebhwo_leamlakne