❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ እንኳን #ለጌታችን_ለአምላካች_ለመድኃኒታችን #ለኢየሱስ_ክርስቶስ ለንዑስ በዓል ለአንዱ #ለስብከት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በፍቅር አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፪ "#ወልዶ_መድኅነ_ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፣ አዝ፤ #አክሊለ_ሰማዕት_ሠያሜ_ካህናት ወተስፋ መነኰሳት #ወልዶ_መድኅነ_ንሰብክ ወልዶ መድኅነ ንሰብከ"። ትርጉም፦ ቅድመ ዓለም በክብር በጌትነት የነበረ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር #መድኃኒት_ልጁን_እንሰብካለን እርሱም #የሰማዕታት_ዘውድ_ነው_የካህናት_ሿሚ_ነው፣ የመነኰሳት ተስፋ ነው። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው።
✝ ✝ ✝
❤ #ስብከት፦ ይህች ዕለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት "ስብከት" ትባላለች:: ስብከት ማለት በቁሙ "የምስራች አዲስ ዜና መንገርን" የሚመለከት ሲሆን ዋናው ምሥጢር ግን ከነገረ ድኅነት (ከመዳን ትምሕርት) ጋር የተገናኘ ነው።
❤ በዚህ ዕለት (ሳምንት) ሁሉም ነቢያት ከነ ትንቢታቸው ይታሰባሉ። ዘመነ ስብከትም ከታኅሣሥ 7 እስከ 13 ያለውን ይይዛል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ በአንዱ እሑድ በሚውለበት ቀን ማኅሌት ተቁሞ ስብከት ተብሎ ይከበራል።
❤ ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሀብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ። በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ፤ በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። በኋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው።
❤ ከዚህ በኋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር። ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር፤ ሱባኤ ይቆጠር፤ ምሳሌም ይመሰል ገባ።
❤ ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ። ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል። ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት/ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል።
❤ ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም፤ በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል። እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል። መድኅን ክርስቶስም ተወልዶ አድኗቸዋል::
❤ ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር)፤ መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው። ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል። እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ።
❤ ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም። በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ። (የሐዋ ሥራ 11፥27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ፣ ይገስጻሉ።
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር፤ ወተናጸሩ ገጸ በገጽ፤ መንፈስን ንጹሕ በማድረግ ነቢያት እግዚአብሔር አይተውታልና ፊት ለፊት ተያይተዋልና"። እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።
❤ የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ፤ አንዳንዶቹም በእሳት፣ አንዳንዶቹም በሰይፍ፣ አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል። ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል።
❤ ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ፤ እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል። ዮሐ. 4፥36
❤ ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል፣ ሽተዋልም። "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል። (ማቴ. 13፥16፣ 1ኛ ጴጥ 1፥10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው፤ ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ።
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት 15ቱ አበው ነቢያት፣ 4ቱ ዐበይት ነቢያት፣ 12ቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ።
❤ "15ቱ አበው ነቢያት" ማለት፦
1 ቅዱስ አዳም አባታችን
2 ቅዱስ ሴት
3 ቅዱስ ሔኖስ
4 ቅዱስ ቃይናን
5 ቅዱስ መላልኤል
6 ቅዱሴ ያሬድ
7 ቅዱስ ኄኖክ
8 ቅዱስ ማቱሳላ
9 ቅዱስ ላሜሕ
10 ቅዱስ ኖኅ
11 ቅዱስ አብርሃም
12 ቅዱስ ይስሐቅ
13 ቅዱስ ያዕቆብ
14 ቅዱስ ሙሴና
15 ሳሙኤል ናቸው።
❤ "4ቱ ዐበይት ነቢያት"
1 ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
2 ቅዱስ ኤርምያስ
3 ቅዱስ ሕዝቅኤልና
4 ቅዱስ ዳንኤል ናቸው።
❤ "12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
1 ቅዱስ ሆሴዕ
2 ቅዱስ አሞጽ
3 ቅዱስ ሚክያስ
4 ቅዱሴ ዮናስ
5 ቅዱስ ናሆም
6 ቅዱስ አብድዩ
7 ቅዱስ ሶፎንያስ
8 ቅዱስ ሐጌ
9 ቅዱስ ኢዩኤል
10 ቅዱስ ዕንባቆም
11 ቅዱስ ዘካርያስ
12 ቅዱስ ሚልክያስ ናቸው።
❤ "ካልአን ነቢያት" ደግሞ፦
1 ቅዱስ ኢያሱ
2 ቅዱስ ሶምሶን
3 ቅዱስ ዮፍታሔ
4 ቅዱስ ጌዴዎን
5 ቅዱስ ዳዊት
6 ቅዱስ ሰሎሞን
7 ቅዱስ ኤልያስ
8 ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው።
❤ ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ፦
1 የይሁዳ (ኢየሩሳሌም)
2 የሰማርያ (እሥራኤል)
3 የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ።
❤ በዘመን አከፋፈል ደግሞ፦
1 ከቅዱስ አዳም እስከ ቅዱስ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት)።
2 ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ እስከ ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)።
3 ከቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)።
4 ከቅዱስ ዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ። ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ ፔጅ።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ፈኑ እዴከ እምአርያም። አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ። ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር"። መዝ 143፥7። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 1፥1-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 3፥1-10 እና የሐዋ ሥራ 3፥17-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 1፥44-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የስብከት በዓልና የነቢያት (የገና) ጾም ለሁላችንም ይሁንልን።
@sigewe https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKwL https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886