🖤ይምረኝ ይሆን
✨ክፍል 1
✍አይመኒ
💭ቢንት ኡሚሃ
🎈በድሮዋ ፐርሺያ በአሁኗ ኢራን ውስጥ ተወልጄ በእርሷ መዳፍ ላይ በልቼ ጠጥቼ በሰፋፊ የሲፊን መንደር ሜዳዎች እየወደቅሁ እየተነሳሁ በሳቅ እና ለቅሶ ዜማ ተናውዤ ኹራሳን ውስጥ ኖሬአለሁ።
" ሂልዋ ጃን " የሚል ድምፅ ከእነባባ ክፍል በኩል ሲጠራኝ እንባዬን እየጠራረግሁ ወደ ተጠራሁበት ክፍል ገባሁ፡ ባባ ወደ ፍሪሞንት አሜሪካ በዚችው ሌሊት ለመብረር ሻንጣውን ሸክፎ ከሰፊው ኢራን ሰራሽ አልጋ ላይ አስደግፎታል፡ አይን አይኖቼን እያየ" ነይልኝ እንጂ ሂልዊ ጃን(ውዴ) እኔኮ እንድትከፊብኝ አልፈልግም ትንሽ የስራ ግዜ አሳልፌ እመጣለሁ አለቀ ከዛ " ሲለኝ ዘልዬ ተጠምጥሜ አለቀስኩበት "በጣም ነው የምትናፍቀኝ ባባ "
። ወደ ኤርፖርት የሚያመራው ከሌሊቱ 11 ሰዐት ላይ ስለነበር ያቺን ሌሊት እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር አደርኩኝ፡፡
ከሱብሂ አዛን ቀደም ብሎ ነበር የባባን"ኸረ ለይላ ውዴ ከልጆቹ ልትብሺ ነው እንዴ በቃሽ አሏህ ያቃልኮ" የሚል ማስተዛዘኛ ስሰማ የክፍሌን በር እንደ በረገገ የጦይባ ግመል በርግጄው የወጣሁት፡ እነባባ ክፍል ስደርስ ፈርሃን እና ሀሰን ባባ ላይ ተጠምጥመው ነበር የሁለቱም ታላቅ ብሆንም በዚያች ቅፅበት ግን ከሁሉም ታናሽ የሆንኩ መስሎ ተሰማኝ፡፡
ባባ ሁላችንንም አንድ በአንድ ጉንጫችን እስኪቀላ ከሳመን በኋላ ወደ ኡሚ ተጠግቶ በቅጡ ያልሰማሁትን ወሬ አንሾካሾከላት ፡ እጆቹን በችኮላ ከትከሻዋ ላይ አሳርፎ ግንባሯን ስሟት ወደ መውጪያው በር አመራ፡ " አሏህ ይጠብቅህ ዐሊይ ውዴ..." ነበር የእናቴ ሲቃ አዘል መልስ፡ በኹራሳን ከተማ አነስ ያለች የፖለቲካዊ ፉክቻ ምክንያት ነበር ባባን እስከ ኤርፖርት ድረስ እንዳንሸኘው ያደረገን ።
ባባ ከተናበተን በኋላ ፈርሃን እና ሀሰንን "ኡሚ ብቻዋን እንዳትሆን ዛሬ እነባባ ክፍል እናድራለን፡ የሌሊት ልብሳችሁን አርጋችሁ ኑ" አልኳቸው በትዕዛዛዊ አንደበት ፡ ኡሚን ኩርምት ብላ ነበር ያገኘኋት " ኡሚ ሁሉም አሏህ ያለው ነው ብሎሻልኮ ባባ ለምንድነው ምታዝኚው" ፡ " የኔ ቆንጆ ሂልዋ አላዘንኩምኮ ትንሽ ብቻ ነው የደበረኝ" ብላ አቀፈችኝ፡ ጉንጯን ወደ ኋላ የተበተነው እንደ ቱርክ ሒና የደመቀው ፀጉሬ ላይ አንተርሳ እንዳነባች ግን አልረሳውም፡፡
እናቴ ለይላ ልቅም ያለች የፐርሺያዋ ጨረቃ ናት ምንም እንከን የማይወጣላት ፡አይኖቿ ሀዘል አረንዴ እና የሚያበሩ አፍንጫዋ ስልክክ ብሎ የተተከለ የታችኛው ፊቷ እንደ ሰይዲና ዐሊይ ዙልፊቃር ሰይፍ የተሳለ ነበር ፡ ባባ እቺን የመሰለች እንቁ ማግኘቱ እደለኛነቱን ያሳብቃል ፡እሷም ብትሆን ባባን ያንን ደግ የኢራን ጉብል ማግኘቷ ሰዐዳ መሆኗን ያሳያል፡ ግን ምን ዋጋ አለው እናቴ እኔን ከወለደችበት ግዜ አንስቶ የሚያሰቃያት አንድ በሽታ ነበር።
ፈርሀን እና ሐሰን ፒጃማቸውን ለብሰው ወደ ክፍሉ ሲገቡ ነበር ኡሚ እንባዋን ገታ አድርጋ" ነይ ፈርሂ አንቺ መሀል ተኚ ሐሱ ደግሞ ከኔ በስተቀኝ ሁን ምን መጣብህ ከነዚህ ትላልቅ ፍጥረቶች አጠገብ" ብላ ፈገግ አለች፡ ሁላችንም እርስ በእርስ ተቃቅፈን ሰፊው ንጉሳዊ የመሰለ ሰሪር ላይ ወደቅን. .... ኡሚ ጥንታዊ የፋርስ እሳት አምላኪዎችን የሞኝ ስራ እና እምነቶችን እየነገረችን ነበር የተኛነው....እንቅልፍ ፈርሂን ሀሱን እማን እያለ በመጨረሻም የእኔን አይኖች ከደነ.......
1980 ኢራን ሲፊን መንደር
በመስኮቱ በኩል የሚገባው የወፎች ዝማሬ ነበር ከእንቅልፌ ያነቃኝ " ሂልዋ ተነሺ እንጂ ቀድ ሐደረ ጦዐም " የኡሚም ድምጽ ከሲፊን ወፎች እንጉርጉሮ የሚተናነስ አይደለም ፡ የዝነኛውን ካህሊል ጂብራን እና የሃፊዝ ካፕሌቶችን በፐርሺያዊ ለዛ ስታዜማቸው የቴህራንን ወይኖች ያጣጣምኩ ያህል ደስ የሚል ስሜት ይወረኛል፡፡
ሰላም አለይኩም ኡሚ ካልኳት በኋላ ያስቀመጠችልኝን ጣፋጭ ሃልዋ እና እንደ ህፃን ጉንጭ የለሰለሰ ነአን አጣጥሜ ወደ መድረሳ ለመሄድ ተነሳሁ ፡ " አበባዬ አንችኮ የኔ ዛህራ ነሽ በርቺልኝ እሺ ቁርዐን ፊፍዝሽን ስትጨርሺ ማደርግልሽን አታውቂም" ብላኝ አፍም ሳታስከፍተኝ የቆዳውን ቦርሳዬን አስይዛ እስከ መውጪያው በር ሸኘችኝ! ትላንት ባባ እኛን ጥሎ የከነፈባት የእንጨት በር!
ልቤን አንዳች ነገር እንዳስጨነቀኝ ቢሰማኝም ናቅ አድርጌ ትቼው ስለታናናሾቼ ሁኔታ ማሰብ ያዝኩ" ፈርሃንስ እሺ እንደስሟ ደስታ የሚያሳድዳት፡በትላቅ የአረም ማሳ ላይ አፈንጋጭ አረጓዴ ተክል የሚታያት እድለኛ ልጅ ናት ሀሰን ግን ያለዐቅሙ ነው ሚያስበው ባባ ትላንትና ኡሚን ያንሾካሾከላት ስለ ሐሰን ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም" እያልኩ ከልቤ ጋር እያወራሁ ነበር ኢስቲቅላል መድረሳ የደርስኩት፡
በር ላይ እንደተለመደው ግርግር ይታያል፡ ኪታብ የሚሸጡ ሽማግሌዎች ኢስቲቅላል መድረሳ በር ላይ ተኮልኩከዋል ከበሩ ራቅ ብሎ ደግሞ ኹፍ፡ሲዋክ ሙሰበሃ የመቭለዊይ ኮፊታዎች እና ኢራን የምትኮራባቸው አፍንጫ የሚያናውዙ አድሩሶችን የሚሸጡ ወጣት እና አሮጊት ቅልቅል ፍጥረታት የጦፈ ወሬ ይዘው ተደርድረዋል
ከዋናው መንገድ ተሻግሮ የመድረሳችን ኡስታዞችና ጎበዝ ጧሊቦች የሚሰበሰቡባት "ኢናያ መፃህፍት ቤት" በመድረሳው ትይዩ ቀጥ ብላ አፍጥጣ ቆማለች፡፡ ወደ በሩ ስጠጋ " ሰላም አለይኩም ሂልዋ " የሚሉ ብዙ ድምጾች ተስተጋቡ" ወአለይኩሙሰላም ወራህማ" ምትለዋን እየደጋገምኩ ኢስቲቅላልን ዘለቅኋት።
በዚህች ግቢ የእኔ ስም ከነኢማም አል ገዛሊ እኩል ሊጠራ ደርሷል ብል ማጋነን አይሆብኝም፡ከኡሚ ከወረስኩት ሀዘል አረንጓዴ አይን እና የሚበር ፋልኮን ከመሰለው ቅንድብ በላይ አስደማሚ የመድረሳ ውጤቴ አነጋጋሪ ሆኗል ፡ገና በአስር አመቴ ቅዱስ ቁርዐንን ለማኽተም 5 ጁዝኦች ብቻ ቀርተውኛል፡ "ሚኣህ አሃዲስ አነበዊይ" የተሰኘውን ባላመቶ የረሱል ሐዲስ እንደ ስሜ እያቀላጠፍኩ እዘግባለሁ ፡የቅኔ እውቀቴም ልጅኛ አይመስልም ጀላሉዲን አል ሩሚ፡ ሰዐዲይ፡ሃፊዝ እና ሌሎችም የፋርስ ባለቅኔዎች ሙሉ መዛግብታቸውን ባላካልልም ከባህራቸው ቀማምሼአለሁ፡ ለዚህም ነው የግቢው ዋና ሙዲር ሸይኽ ጢብሪዝ" ሁመይራእ" እያሉ የሚጠሩኝ፡ የረሱላችን ሚስት እመት አኢሻእ ተቀፅላ ፡፡
🎈
🎈 በአሏህ ፍቃድ ይቀጥላል
✨
@WISDOMISM1 👈