🚨
“ የሚላስ የሚቀመስ የለም ” - የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ
🔴
“ ችግር እንዳለ ይታወቃል ” - የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በምግብ እጥረት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተጎዱ፣ በተለይ ጨቅላ ህፃናት የከፋ ስቃይ ላይ እንደሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
“ ጉዳዩ በጣም አሳዛኝ ነው። በእኛ ቦታው ያልሆነ ሰው አይገባውም ” ሲሉም የሁነቱን አስከፊነት አስረድተዋል።
ስሜ ከመነገር ይቆይ ያሉ የመረጃ ምንጭ በበኩላቸው፣ “ በቡግና ወረዳ ጉልሃ ቀበሌ አንድ ህፃን በምግብ እጥረት ሞቷል ” ብለዋል።
የቡግና ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል አለሙ በበኩላቸው፣ በክልሉ ባለው ግጭትና ተፈጥሯዊ ተፅዕኖ ምክንያት ወረዳው ለድርቅና ለምግብ እጥረት በመጋለጡ ህፃናትን ጨምሮ ከ10 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን ሰሞኑንን ለቢቢሲ አማርኛ መናገራቸው አይዘነጋም።
በወረዳው በተከሰተ የምግብ እጥረት በተለይ ጨቅላ ህፃናት ስለተጎዱ ነዋሪዎቹ የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸውን በመግለጽ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ የጠየቀው የቡግና ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት፣ “ እኛ ጋር ስራ የለም ” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥቷል።
ጽሕፈት ቤቱ፣ “ እውቅናው የለኝም ” ያለ ሲሆን፣ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ነዋሪዎች መናገራቸውን ብንገልጽለትም፣ “ እስካሁም ምንም አይነት በሪፓርትም የመጣ ነገር የለም ” ብሏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቡግና ወረዳ በተጨማሪም ለአማራ ክልል ስጋት አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ችግሩ መኖሩን አምኗል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ፍቅሬ ሙሉጌ በሰጡን ቃል፣ “ ጉዳዩ በኛ ቁጥጥር ውስጥ ነው። ከእኛ አቅም ውጪ የሆነ ነገር የለም ” ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፣ “ ችግር እንዳለ ይታወቃል። ድጋፍ እየቀረበ ነው። ምንም የተለዬ ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ የአምናውን ድርቅ ችግር ተቋቁመናል አሁን እንዲያውም ጥሩ ነው ምርት አምርተዋል ” ሲሉ ተናግረዋል።
ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሆነ ምን ያክል ድጋፍ ተደርጓል ? ሰሞኑን ያደረጋችሁት ድጋፍ ነበር ? በተለይ ሰሞኑን ህፃናቱን የሚመግቡት እንደተቸገሩ ነዋሪዎቹ እየገለጹ ነው፣ ስንል ለወ/ሮ ፍቅሬ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበናል።
እሳቸውም በምላሻቸው፣ “ በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው በተለመደው አግባብ (ድጋፉ የሚሰጥበት ቀመር አለው) ድጋፍ እየደረሳቸው ነው ” ከማለት ውጪ የችግሩን አስከፊነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ነዋሪዎቹ የላኳቸው ፎቶዎች ህፃናቱ በምግብ እጥረት እንደተጎዱ የሚመሰክሩ እንደሆኑ ገልጸን፣ ድጋፍ ካለ ጉዳዩ እንዴት በዚህ ልክ ጉዳት እንዳደረሰ ማብራሪያ እንዲሰጡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ኃላፊዋን ጠይቋል።
በዚህም፣ “ ይለካል እኮ ማልኑውትሬሽን፣ ሞዴሬት የሆኑት እየተለካ ምግብ ሁሉ ይሰጣቸዋል ለእናቶች፣ ለህፃናት ” የሚል ምላሽ ሰጠተዋል።
“ ለዩኒሴፍም ይቀርባል። ለአዋቂዎች ደግሞ እህል ይቀርባል። የገንዘብ ደጋፍም ይሰጣልና ክትልትል እየተደረገ ነው ” ያሉት ወ/ሮ ፍቅሬ፣ “ በመሀል ደግሞ በህመምም በምንም ጉዳት ሊያጋጥም ይችላል ” ነው ያሉት።
የቡግና ወረዳ ኮሚዩኒኬሽንና ኮሚሽኑ ይህን ይበሉ እንጂ የቡግና ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ግን ለቢቢሲ አማርኛ በሰጠው ቃል፣ “ ማህበረሰቡ ምርት ባለማግኘቱ እናቶች ልጆቻቸውን ባግባቡ መግበው የተሻለ የጤና እድገት እንዳይኖራቸው አድርጓል ” ብሏል።
በሌላ በኩል ፤ የሰሜን ወሎ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ይመር ዛሬ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል " አካባቢው በፋኖ ታጣቂዎች ስር በመሆኑ ለተከሰተው የምግብ እጥረት መንግሥት በቶሎ ምላሽ መስጠት አልቻለም " ብለዋል።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በአደረጉት ጥረትም አሁን ላይ የርዳታ እህል ወደ ስፍራው እየተጓጓዘ መሆኑን አስታውቀዋል።
የወረዳው ነዋሪ ያለበትን የምግብና የጤና ችግር ለፋኖ ታጣቂዎችና ለመንግሥት አካላት ለማስረዳት ከተመረጡት 18 ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበርኩ ያሉት ቄስ ገብረ እግዚአብሔር ዝናቤ ይርዳው " በአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት መድኃኒቶችንና አልሚ ምግቦች ወደ ወረዳው እየገቡ ነው " ብለዋል።
የኤሪካ ኤምባሲ ደግሞ ፤ የምግብ እጥረት ቀውስ ሰለመኖሩ የወጡ ሪፖርቶችን እየተከታተለ እንደሆነ አመልክቷል።
ቀውሱ መወገዱን ለማረጋገጥ እንደሚሠራም ጠቅሷል።
ኤምባሲው ቀውሱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን አላካተተም።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመደገፍ ፣ አጋሮቹ በአሁኑ ሰዓት በችግሩ በተጠቁት አብዛኞቹ ስፍራዎች የምግብ እና አልሚ ንጥረ ምግቦች ስርጭትን ያጠናከሩ መሆናቸውን አክሏል።
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia