"ጌታውን ደስ ያሰኘ ታማኝና ቸር አገልጋይ ማነው?"ቅዱስ ያሬድ
በዲያቆን ግዛው ቸኮልመጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ክፍል ሁለት
በዚህ ዘመን ለምንኖር አገልጋዮች አገልግሎታችንን የሚያዳክሙ ነገሮች ምንድን ናቸው?
፩.የመንፈሳዊ ሕይወታችን መዛል፡-መንፈሳዊ ዝለት በሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንደኛው ያለ አቅም የተጀመረን መንፈሳዊ ተግባር ቀስ በቀስ ማቋረጥና ወደቀድሞው ሥጋዊ ሕይወት መመለስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀስ በቀስ ያደገን መንፈሳዊ ሕይወት የሚጠይቀውን መንፈሳዊ አኗኗር ከመሰልቸት የሚመጣ ነው፡፡
በሁለቱም መንገድ በሕይወቱ ወደኋላ የተመለሰ ሰው ለአገልግሎት (ለመታዘዝና ለመታመን) የነበረው ፍቅር ይቀንስና ሁልጊዜ መጸጸትን ብቻ ሥራው ያደርጋል፤ "የነበርኩ" ሕይወትንም ይለማመዳል፡፡
፪.ምቹ ሁኔታዎችን መሻት፡-ሰዎችን መርጦ መታዘዝና ማገልገል ቀላል ነው፤ሰው ሲመቸው ማገልገል ሳይመቸው ከቤተክርስቲያን መቅረትንም ገንዘቡ ያደረጋል፡፡
ነገር ግን እስከ መጨረሻው ጸንቶ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ደግሞ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ሰማዕትነትን መክፈል ያስፈልጋል፡፡
ካልሆነ የአገልግሎትን ጣዕም አንረዳውም፡፡
"በዝግታ ቆመህ በጊዜውም ያለጊዜውም ቃሉን ስበክ፤ በሁሉም እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ገሥጽ፤ ዝለፍ፤ ፈጽመህ አጽናና፤" ያለውን የሐዋርያውን ቃል ማሰብ ጠቃሚ ነዉ፡፡ ፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪
፫.ዓላማን መርሳት፡-መታዘዝም ሆነ መታመን ትርጒም የሚኖረው በዓላማ ሲፈጸም ነው፡፡ ኃላፊነትን መርሳት ከመስመር ያርቀናልና ሁልጊዜ የመጣንበትን ዓላማ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ
ነገር ግን ከተመሠረተው በቀር ሌላ መሠረት ሊመሠርት የሚችል የለምብሎ እንደተናገረው መሰባሰባችንን ለሌላ ዓላማ መጠቀምም ሆነ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ፩ኛ ቆሮ. ፫፥፲፩
፬.ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ፡-በእርግጥ ለጽድቅ የሚያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ የእኛ በጎ ምግባር ብቻ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነቢዩ ኤርምያስም
ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምናበማለት ተናግሯል፡፡ ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ ራስ ወዳድነት ከመሆኑም በላይ ድርሻንም አለመገንዘብና አለማወቅም ጭምር ነው፡፡
ባለአንዱ መክሊት ድርሻውን ስላልተወጣ የተፈረደበት ለዚህ ነው፡፡
"በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል" በማለት መጽሐፍም ያስረዳናል፡፡
ሰቈ ኤ. ፫፥፳፪፣ ሐዋ ፲፬፥፳፪
በጎ አገልጋይ ለመሆን ምን እናድርግ?፩. መታዘዝ፡-የሰው ልጅ በፈጣሪው አርአያና አምሳል ሲፈጠር የሚያዝም የሚታዘዝም ሆኖ ነው፡፡
አገልግሎት (መንፈሳዊነት) መታዘዝ ነው ስንል እንደ ባለአምስቱና ባለሁለቱ አገልጋዮች ያለምንም ማጉረምረም ከኃጢአት በስተቀር ሁሉንም ተቀብሎ ማከናወን ማለት ነው፡፡
አብርሃም "ልጅህን ሠዋልኝ" የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥያቄና ትእዛዝ የተቀበለው በጸጋም በደስታም ነው፡፡
ነቢያት፣ ሐዋርያት ኃላፊውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጠው መንፈሳዊ ተልእኮን እንዲወጡ ለእግዚአብሔር ቃል ሲታዘዙ በደስታ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም የአባቶቻችንን መታዘዝ መታዘዛችን ልናደርግ ይገባናል፡፡
፪.በትጋት ማገልገል፡-ከዘመነ አበው ጀምሮ የእግዚአብሔር ወዳጆች እየተባሉ የሚጠሩ ሁሉ የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫቸው ትጋታቸው ነበር፡፡
መንፈሳዊ ሕይወት ከትጋት ውጭ መለኪያ የለውም፡፡ ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተመረጡት ከሥራ ቦታቸው ነው፡፡
ጌታችን ሲመርጣቸውም እጅግ በጣም ትጋትን ለሚጠይቅ ተልእኮ ነበር፡፡ ዋጋን ለመቀበል ከጠዋት እስከ ማታ በአገልግሎት መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌ
"በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው"በማለት ትጋት የመንፈሳዊ ዋጋ መጠበቂያ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ማቴ. ፲፥፩-፲፬፣፳፥፩-፲፪፣ ምሳ.፲፰፥፱
፫. በተስፋ የተመላ ትጉህ አገልጋይ መሆን፡-የሰው ልጅን በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመሩ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ከሌላው ሥነ-ፍጥረታት የተለዩ የሚያደርጋቸው ተስፋ ነው፡፡
የተወለደው የማደግ ተስፋ፣ ያደገው የመኖር ተስፋ፣ በኃጢአት የወደቀው በንስሓ የመነሣት ተስፋ፣ ቤተክርስቲያንን የማገልገል ተስፋ፣ መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ ተስፋ ለሰው ልጆች በተለይም ለእኛ ለክርስቲያኖች የተሰጠን ተስፋችን ነው፡፡
ነቢያትን በትንቢት ያጸናና መከራውን እንዲታገሡ ያደረጋቸው፣ ሐዋርያትን በሐዋርያነት ያጸናና በሰማዕትነት ያጠነከራቸው፣ ከዘመነ አበው እስከ ዕለተ ምጽአት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስተሳስሮ የሚኖር ኅቡእ ሰንሰለት ተስፋ ነው፡፡አባቶቻችን
"የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን" ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡
በአጠቃላይ እኛም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ነግደን እንድናተርፍበት ከጌታችን የተሰጠንን መክሊት በግዴልሽነት፣ በትዳር፣ በትምህርት እና በቦታ ርቀት ምክንያት አንዳችን ካንዳችን ባለመስማማት ለራሳችን ሰበብ እየፈጠርን እንደ ባለአንዱ አገልጋይ ከቀበርነው ቆይተናል፡፡
ጌታችንም የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ስለማናውቅ ከቀበርንበት አውጥተን ልናተርፍበት ይገባናል።
"እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን ዛሬ ነው"እንዳለ ሐዋርያው አትርፎ መገኘት ለእኛ ለክርስቲያኖች የግድ ያስፈልገናል፡፡
፩ኛ ቆሮ. ፮፥፪
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም
"መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ፤ በጎ ሥራ እየሠራ ጌታው ያገኘው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማነው?"እንዳለ ታማኝነት እና መታዘዝ ከሌለን፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ከራቅን፣ በጌታችንም ፊት መሾም መሸለም፣ ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ መግባት አይኖረንም፡፡
ስለዚህ በተሰጠን ስጦታ፣ ሀብት፣ አቅም፣ ጊዜ፣ ቦታና ዕድሜ ሥጦታውን ለሰጠን እግዚአብሔር ታምነንና በአገልግሎት ጸንተን ወጥተው ወርደው አትርፈው ከተሾሙት ወገን እንዲደምረን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይፍቀድልን፤
አሜን።
ቃለሕይወት ያሰማልን
~ተፈጸመ~
╭══•|❀:✧๑♡๑✧❀|: ══╮
@yamazemur_getemoche ╰══•ೋ•✧๑♡๑✧• ══╯