ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha


The best fiction is far more true than any journalism
📢 ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ፤ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ በሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ
👉 በፌስቡክ ገፆቻችን https://www.facebook.com/simon.dereje.56
👉 https://www.facebook.com/mik0Man

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Statistika
Postlar filtri


በየቀኑ ከ20 በላይ አዳዲስ የአእምሮ ጤና ህክምና ፈላጊዎችን እያስተናገደ መሆኑን የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ

ሆስፒታሉ በ2017 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ102 ሺ በላይ ተገልጋዮች በአእምሮ ህመምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ህክምና እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

በ2017 በጀት ዓመት ለ124,800 ዜጎች በአእምሮ ህመምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአእምሮ ህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እቅድ ይዞ በ9 ወራት ውስጥ በአስተኝቶ የአእምሮ ህክምና 1,421 በተመላላሽ የአእምሮ ህክምና 98,803 እንዲሁም በድንገተኛ የአእምሮ ህክምና 2,380 በአጠቃላይ ለ102,604 የአእምሮ ህመም ታካሚዎች ህክምናውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አብዩ የኔአለም ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ከማሻሻል አኳያ የተመላላሽ ህክምናን አገልግሎት ጥራት ማሻሻል የሚገኝበት ሲሆን የተመላላሽ ታካሚ የቆይታ ጊዜ ከ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 49 ደቂቃ ወደ 38 ደቂቃ  ማድረስ መቻሉንም አስታውቃል፡፡በየዕለቱ ህክምና ሳያገኙ የሚመለሱ ህሙማን ቁጥርን በመቶኛ 0 ማድረስ ያቀደው ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ እቅዱን መተግበርም መቻሉንም አቶ አብዩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል  በሆስፒታሉ አማካኝ የአስተኝቶ የቆይታ ግዜ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረው 36 ቀን በ2017 በጀት ዓመት በ9 ወራት ውስጥ ወደ 33  ቀን ማድረስ  የተቻለ ሲሆን የአልጋ የመያዝ ምጣኔም 84 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ጥራት ማሻሻልን በተመለከተ ደግሞ በ5 ደቂቃ የህመምተኞች ልየታ የመስራት  እቅዱን መቶ በመቶ ማራካቱን አስታውቋል።

በትግስት ላቀዉ
#ዳጉ_ጆርናል


አሜሪካ በሱዳን ጦርነት የኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሏል አለች

👉 አሜሪካ ከጁን 6 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ማዕቀብ በሱዳን ላይ ልትጥል እንደምትችል ይጠበቃል


አሜሪካ በሱዳን ላይ እኤአ በ2024 የኬሚካል ጦር መሳሪያ መጠቀሟን ካረጋገጠች በኋላ በሀገሪቱ ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ አስታውቋል። እ.ኤ.አ. በ 1991 በኬሚካል እና ባዮሎጂካል የጦር መሳሪያዎች ቁጥጥር እና ጦርነት ማስወገጃ ህግ (CBW Act) ላይ መሰረት ያደረገው ውሳኔ ሱዳን አካል የሆነችበትን የኬሚካል የጦር መሳሪያ ኮንቬንሽን (ሲደብሊውሲ)ን የማቴቴታከብር መሆኑን ከማረጋገጡ ጋር ተያይዞ ለኮንግረሱ ቀርቧል።

የመምሪያው ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ በሰጡት መግለጫ “ዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን መንግስት ሁሉንም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች መጠቀም እንዲያቆም እና በCWC ስር ያሉትን ግዴታዎች እንዲወጣ ትጠይቃለች" ብሏል። የ15 ቀን የኮንግረስ ማሳወቂያ ጊዜን ተከትሎ፣ በፌደራል መዝገብ ላይ ማስታወቂያ ከታተመ በኋላ፣ ማዕቀቡ ከጁን 6፣ 2025 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። እርምጃዎቹ ዩኤስ ወደ ሱዳን የምትልካቸው ምርቶች ላይ እና የአሜሪካ መንግስት የብድር መስመሮችን የማግኘት ገደቦችን ያካትታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ለኬሚካል ጦር መሳሪያ መስፋፋት አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን በድጋሚ የገለፀች ሲሆን የሱዳን ኬሚካላዊ የጦር መሳሪያዎች መጠቀም ምርመራ የተደረገውም ሪፖርቶችን ተከትሎ ነው ተብሏል።

በጥር 16 2025 ላይ የወጣው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሱዳን ጦር ሀገሪቱን ለመቆጣጠር በሚዋጋው የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሀይሎች ቡድን ላይ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ኬሚካላዊ የጦር መሳሪያ ተጠቅሟል ይላል። የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ጥቃቱ ከመሀል ሱዳን ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ በሰፈሩ የአር.ኤስ.ኤፍ ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበርም ተዘግቧል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 3 በመቶ ለሚሆነዉ ህዝብ ብቻ ነዉ ተባለ

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጰያ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መኖራቸዉ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ የህይወት መድን አገልግሎት የሚሰጡት 13ቱ ብቻ ናቸዉ ተብሏል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2013 ዓ.ም ባደረገዉ ጥናት ከኢትዮጰያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች 55 በመቶ የሚሆኑት ቅርንጫፎቻቸዉ የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነዉ ።

እነዚህም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 3 በመቶ ለሚሆነዉ የሀገሪቱ ህዝብ ብቻ በመሆኑ ፍትሃዊ የሆነ የመድን ሽፋን እየተሰጠ አለመሆኑን የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀነራል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ ገድለጊዮርጊስ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትብብር የተሠራ አንድ ግዙፍ ጥናት እንደሚሳየው  ኢትዮጵያዊያን የህይወት መድን ከማይገዙባቸዉ በርካታ ምክንያቶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የግንዛቤ እጥረት መሆኑን ጥናቱ ያሳያል ።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እና ቅርንጫፎቻቸዉ በአቅራቢያ ማግኘት አለመቻል ሌላኛዉ ምክንያት ነዉ።በዚህም የተነሳ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጋራ ሰርተዉ ለንብረት ነክ ፣ለህይወት እና ጤና መድን የሰጡት የኢንሹራንስ ሽፋን ከ7 በመቶ ለማይበልጥ የኢትዮጰያ ህዝብ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል


የአፍሪካ ህብረት ፍልስጤማውያንን ወደ አፍሪካ ለማፈናቀል በሚደረገው ጥረት ደስተኛ እንደማይሆን አስታወቀ

የአፍሪካ ህብረት ፍልስጤማውያንን ወደ አፍሪካ ለማባረር በሚደረገው ሙከራ ደስተኛ ሊሆን አይችልም ሲሉ የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴቴ አንቶኒዮ ተናግረዋል። "በእርግጠኝነት የሁለት መንግስታት መፍትሄ፣ ሁለት መንግስታት ጎን ለጎን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎችን እንጠብቃለን ሲል አንቶኒዮ ከአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ይህው የተነገረው በብራሰልስ ሶስተኛውን የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ነው።

እኛ ለክልሉ ቅርብ ነን እናም ቢያንስ ለእነዚያ ሰዎች ስቃይ ግድየለሾች አይደለንም ብለዋል። አንቶኒዮ “የአፍሪካ ህብረት መርህ ሁል ጊዜ ግጭት በሚፈጠርበት ቦታ ሁሉ እና ለፍልስጤም ህዝብ ጎን ይቆማል” ብለዋል ። የአፍሪካ ህብረት ለጉባኤው ብቸኛ ቋሚ ተጋባዥ የፍልስጤም ባለስልጣን ሊቀመንበር መሆኑን ገልፀው ለህብረቱ "የፍላጎት ጥያቄ ፣ ትልቅ ጉዳይ" ነው ብለዋል ። ካላስ በበኩሏ በአፍሪካ የሳህል ክልል ያለው ሁኔታ የአውሮፓ ህብረትን "በጣም ያሳስበዋል" በማለት ህብረቱ "በአዲሱ የሳህል ስትራቴጂ" ላይ እንደሚወያይ ተናግራለች።

እኔም የሁለትዮሽ ስብሰባዎችን አድርጌያለሁ፣ ከአፍሪካ ሀገራትም የእነርሱን አስተያየት ጠይቄያለሁ  ስትል የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ተናግራለች። በአህጉራዊ የሽምግልና ጥረቶቹ ለአፍሪካ ህብረት ድጋፉን ገልጻለች። እነዚህ ሁሉ ሂደቶች በአፍሪካም የአፍሪካ መሪ እና የአፍሪካ ባለቤትነት አላቸው ብላለች።፣ ካላስ በተጨማሪም በየቦታው "ውጊያ" አለ እናም "የተሳሳቱ መረጃዎች ሩሲያ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ከምትጠቀምባቸው መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ ነው" በማለት ገልፀዋል ። አክለውም “የተሳሳቱ መረጃዎችን እና የውጭ መጥፎ ተጽዕኖዎችን ሁል ጊዜ መዋጋት አለብን” ብለዋል ።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል፦

1. ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆርስን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤
2. ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
3. ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስን የሐዲያ ሀ/ስብከትን እንደያዙ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
4. ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዘኮሎራዶን የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፤
5. ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ሚኒሶታን እንደያዙ የኮሎራዶ ሀ/ስብከትን እንዲመሩ፤
6. ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የደቡብ አፍሪካ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳ ጳስ፤
7. ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምን የገዳማት መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲመሩ፤
8. ብፁዕ አቡነ ሙሴ አውስትራልያን እንደያዙ የግቢ ቅዱስ ገብርኤልና የበዐታ ለማርያም ገዳም ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲመሩ ወስኗል።

#ዳጉ_ጆርናል


የኒውዮርኳ ዜና አምባቢ በምጥ ላይ ሳለች የሁለት ሰዓት ርዝመት ያለው የመረጃ ሰዓት መርታ መጨረሷ ግርምትን ፈጥሯል

መገኛውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረገውን WRGB-TV ጋዜጠኛ የሆነቺው ኦሊቭያ ጃኵት የረቡዕ ማለዳ የዜና አምባቢ በነበረችበት ወቅት 12 ሰዓት አየር ላይ ከመውጣቷ አስቀድሞ 10:15 ላይ የእንሽርት ውሃዋ መፍሰሱ ተነግሯል።

በዚህም ምንም እንኳ እንስቷ ወደ ህክምና ተቋም መወሰድና የወሊድ ሂደቷን መጀመር የነበረባት ቢሆንም እንደዛ ሳይሆን ይቀራል።

የቀጥታ ስርጭቱም አብራት ዜና ለማንበብ በተሰየመቺው ጁልያ ዱን የተጀመረ ሲሆን ጁልያም አስቀድመን የምንነግራቹ ሰበር መረጃ አለን የባልደረባየ ኦሊቭያ የእንሽርት ውሃ ፈሷል ልጇን ልትወልድ ነው ስትል ነበር የቀጥታ ስርጭቱን ያስጀመረቺው።

ታድያ ኦሊቭያ ምንም እንኳ ባልደረቦቿ ወደ ሀኪም ቤት እንድትሄድ ቢነግሯትም እሷ ግን ምጧ የመጣው ያለጊዜው እንደሆነ በመግለፅና የመረጃ ሰዓቱን እንደጨረሰች ወደ ሆስፒታል እንደምትሄድ በመግለፅ በቀጥታ ወደ ዜና ማንበቧ መግባቷ ተነግሯል።

ነገር ግን የእርግዝና ቀኗን እና የመውለጃ ቀኗን ያውቁ የነበሩት የስራ ባልደረቧቻ በቴሌቪዥን ስክሪኑ ጫፍ ላይ ኦሊቭያ መውለድ ከነበረባት ሁለት ቀናት እንዳሳለፈች የሚያሳይ መግለጫ ለጥፈው ታይተዋል።

እንስቷ በዚህ ሁኔታ ለሁለት ሰዓታት ገደማ የመረጃ ሰዓቱን ከባደልደራባዋ ጋር በመሆን ስትመራ የቆየች ሲሆንም ስርጭቱ እንደተጠናቀቀም ከባልደረቦቻ ብሎም ከዳይሬክተሯ አድናቆትና ምስጋና ትችሯታል። ከስርጭቱ መጠናቀቅ በኃላ መልእክቱን ያስተላለፍ የፕሮግራሙ ዳይሬክተርም ኦሊቭያ ለተመልካቾችና ለሞያዋ ልዩ ክብር ያላት ጋዜጠኛ ነች ዛሬም እሱን ነው ያሳየችን ሲል ተደምጧል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል


በአማራ ክልል ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ተነገረ

የዩኒቨርስቲ ምሁራን በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብ በማፍለቅ  የድርሻቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ጋር ውይይት መካሄዱን ብስራት ሬዲዮ ከደብረብርሃን መንግስት ኮሙኒኬሽን  ያገኘው መረጃ አመላክቷል። በክልሉ የተከሰተው ግጭትም  አውዳሚ እና የሚያሳስብ መሆኑን በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

ችግሩ ከዚህ የበለጠ ውድመት ከማስከተሉ በፊት በውይይትና በድርድር እንዲፈታ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል።የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አማካሪ ባዬ አለባቸው እንደገለጹት እየደረሰ ያለውን ጉዳት የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ተረድቶ የመፍትሄው አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደብረብርሃን ከተማ  ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በማጠቃለያው እንደተናገሩት በክልሉ በተከሰተው ችግር በርካታ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት መድረሱን ዘርዝረዋል፡፡ በክልሉ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው የትውልድ ክፍተት መፈጠሩንም  አመልክተዋል፡፡ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት የችግሩን ስፋትን በመገንዘብ ለዘላቂ ሰላም ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የተከሰተውን የትውልድ ክፍተት የሚሞሉ  በዕውቀት፣በክህሎትና በመልካም ስነ ምግባር የታነጹ ምሩቃንን የማፍራት ተልዕኮ ዩኒቨርስቲው በትጋት እንዲወጣም ከንቲባ በድሉ ማሳሰባቸውብ ብስራት ሬዲዮ ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

#ዳጉ_ጆርናል


47 የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

👉 የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ በሀገራችን ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፣ በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ 47 የጤና ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት ጀምሯል፡፡ 

እነዚህ ተጠርጣሪዎች የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እንደሽፋን በመጠቀም ሕገ-ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፤ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ለአድማ በማነሳሰት፣ የታካሚዎች ሕይወት ለሞትና ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ ናቸዉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ የጤና ተቋማት የአድማ መረቦችን በመዘርጋት፤ የጤና ባለሙያ ያልሆኑ አካላትን ነጭ ጋዋን በማስለበስ የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተዉ ሁከት እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ ያልተገባ ወሬ በመንዛት እና በተለያየ መንገድ ሰላማዊ የሕክምና ሂደትን በማደናቀፍ የሕሙማንና የጤና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ፣ በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት እና ትምህርት በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል አድርገዋል፡፡

እንዲሁም ሙያቸውን አክብረው በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ከማድረስ ባለፈ ሁከት እንዲፈጠር ሙከራዎችን አድርገዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በመረጃና በማስረጃ በመለየት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጤና ባለሙያዎቹ የሙያው ሥነ-ምግባርና ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ለሞትና ለአደጋ በማጋለጥ ሥራ ማቆም፣ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ማነሳሳት እና ማስፈራራት፣ የወንጀል ተግባር መሆኑን እየገለፀ ሌሎችም ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ ያሳስባል። 

በዚህ አጋጠሚ ሕዝባቸውን እና ሕግ አክብረው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ እያረጋገጠ፤ ከዚህ ውጭ ሁከትና ብጥብጥን ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳውቃል።

#ዳጉ_ጆርናል


ከውድቀት ማግስት የመዓርግ እድገት ያገኙት የፓኪስታን ጦር ኢታማጆር ሹም እያነጋገሩ ነው

👉 የሀገሪቱ መንግስት የጦር አዛዡን የፊልድ ማርሻልነት መዓርግ ቢሰጣቸውም የሀገሬው ሰው ግን የከሸፉ ማርሻል "ፌይልድ ማርሻል" ሲል እየጠራቸው መሆኑም ተነግሯል።


ከህንድ ጋር ገብተውበት የነበረው ግጭት ጋብ ካለ በኃላ የፓኪስታን መንግስት የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ለሆኑት ለጀነራል አሲም ሙኒር የፊልድ ማርሻልነት መአርግ ቢሰጥም ጀነራሉ ግን አዲሱ መአርግ ለትችት ዳርጓቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስተር ሸህባዝ ሻሪፍ የሚመራው የፓኪስታን ካቢኔ የጄነራሉን ሹመት ያፀደቀ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ይህንኑ የፊልድ ማርሻልነት ማዓርግ ያገኙ ሁለተኛው ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በፓኪስታን ለመጀመርያ ጊዜ የፊልድ ማርሻልነት ማዓርግ የተሰጣቸው ሞሀመድ አይብ ከሓን በመባል የሚታወቁት የጦር አዛዥ ሲሆኑ ጊዜው ደግሞ እኤአ በ1959 ነበር።

ታድያ ከአምስት አስርት ዓመታት በኃላ በቅርብ ጊዜው ጦርነት የላቀ የአመራር በቃትና አፈፃፀም አስመዝግበዋል የተባሉት ጀነራል ሙኒር በተለይ የሲንዶር ዘመቻን የመሩበት መንገድ ይህንን የፊልድ ማርሻልነት መዓርግ አሰጥቷቸዋል ተብሏል። ነገር ግን በርካቶች በአስር ቀናት ውግያ ሊፈረካከስ ከጫፍ ደርሶ የነበረን ጦር የመራን ጀነራል የመዓርግ እድገት መስጠት ስድብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም ጀነራሉ ፊልድ ማርሻል የተባሉት መሬት ላይ ባልታዩ ስኬቶች ወይም በሐሰተኛ ሪፖርት ነው ብለዋል።

የጀነራሉን ሹመት ተከትሎ በተለይ ኤክስ ላይ መነጋገርያ ለመሆን የቻለ ሲሆን እራሱን በራሱ ነው የሾመው መንግስት ከማፅደቅ ውጭ ምንም ለማለት አቅም የለውም ቢኖረው ጦርነቱ ወቅት ለተፈጠሩ ድክመቶች ተጠያቂ ሊያደርገው ነበር የሚገባው የሚሉ አስተያየቶችም ተስተጋብተዋል።

ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ምንም እንኳ ፓኪስታን በአስር ቀናት ጦርነቱ ሙሉ የበላይነት ተወስዶባት የነበረ ቢሆንም የሀገሪቱ መንግስት ግን ራሱን እንደ ድል አድራጊ አድርጎ ይቆጥራል ለዚህም ነው የጦር አዛዡን ፊልድ ማርሻል ሲል የሰየመው እውነታው ግን ጀነራል ሙኒር ፊልድ ማርሻል ሳይሆኑ ፌይልድ ማርሻል ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልክን በመጠቀም ብቻ የህይወት መድን ለመግዛት የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ አ.ማ ከሉሚና ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግ.ማ ጋር በመሆን  '' ሉሚና '' የተሰኘ ዲጂታል የህይወት መድን መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል ።

ሉሚና በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንኛውም ሰዉ ስልኩን በመጠቀም ብቻ የህይወት መድን መግዛት የሚያስችል መተግበሪያ መሆኑን የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጀኔራል ኢንሹራንስ ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽመልስ ገድለጊዮርጊስ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።

የሉሚና መተግበሪያ ለአጠቃቀም ምቹ ፣ቀላልና ቀልጣፋ ሲሆን ሌሎች ሀገራት በደረሱበት ቴክኖሎጂ ታግዞ የበለፀገ ነዉ  ተብሏል ። መተግበሪያዉ ከፋይዳ ብሔራዊ የመታወቂያ ቁጥር አገልግሎት የመረጃ ቋት ጋር የተገናኘ በመሆኑ ማንኛውም ሰዉ መለያ ቁጥሩን ብቻ በማስገባት ሁሉንም ግላዊ መረጃ ከነፎቶግራፍ በማዉጣት ያለምንም ድካም በራሱ የሚሞላ ነዉ ።

ለዘመናት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ ተወስኖ የኖረዉን የመድን ፖሊስ ወደ አማርኛ ፣አፋን ኦሮሞ ፣ሶማሊ እና ትግረኛ  በመተርጎም ማንኛውም ሰዉ የመድን ዉሉን አንብቦ በመረዳት ከ100 ሺህ እስከ 750ሺህ ብር የህይወት መድን እንዲገዛ ለማድረግ ታስቦ የበለፀገ መሆኑ ተነግሯል ።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለ3.2 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የግለሰብ የህይወት መድን ሽፋን በመስጠት የሞት ስጋትን እንደሚፈታ እና ከ13ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በተዘዋዋሪና በቀጥታ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ።

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል


በአዲስ አበባ ከተማ 11 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን አላገኙም ተባለ

በአዲስ አበባ ከተማ በወሊድ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 11 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን እየፈለጉ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታውቋል።በቢሮው የተዋልዶ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ቡድን መሪ ሲስተር አስቴር ለታ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በአዲስ አበባ መተግበር ከጀመረ ቆየት ቢልም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ግን ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም።

ይህን አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚረዳ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያበረክት መሆኑ ተገልጿል። ቀደም ሲል በተደረጉ ጥናቶች መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ እድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሚሆኑና በመውለድ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 11 በመቶ ሴቶች አገልግሎቱን ማግኘት ፈልገው እንደማያገኙ ማረጋገጥ ተችሏል ያሉት ቡድን መሪዋ የወጣት ሴቶች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።

ወጣት ሴቶች ስለ ጉዳዮ በቂ እውቀት ስለሌላቸው አገልግሎቱን ላያገኙ እንደሚችሉ የተነገረ ሲሆን እናቶች እንደወለዱ በሚሰጣቸው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ዙሪያም ፍላጎቶቻቸው የማይሟላበት ሁኔታ መኖሩ ተጠቅሷል።ይህን ችግር ለመፍታት እናቶች የሚፈልጓቸውን የመድሀኒት አማራጮች በአግባቡ የሚያገኙበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባ ሲስተር አስቴር ገልፀው አገልግሎቱን ውጤታማ ለማድረግ በቂ በጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የተለያዮ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል።

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል


የእንግሊዝ ፍርድ ቤት የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሸስ ለማስረከብ የተደረገውን ስምምነት አገደ

የብሪታኒያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ መንግስት የቻጎስ ደሴቶችን ሉዓላዊነት ወደ ሞሪሸስ እንዳያስተላልፍ ለጊዜው አግዶታል።ሐሙስ እለት የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ትእዛዝ የሰጠዉ ፍርድ ቤቱ ስምምነቱ ከሞሪሸስ መንግሥት ተወካዮች ጋር ይፈረማል ተብሎ ከመጠበቁ ከሰዓታት በፊት ነበር።

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተቀባይነት ያገኘው በቻጎስ በሚገኘው በዲያጎ ጋርሺያ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ በተወለዱ ሁለት የእንግሊዝ ዜጎች በሆኑት በርናዴት ዱጋሴ እና በርትሪስ ፖምፔ ደሴቶቹ በብሪታንያ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ከጠየቁ በኃላ ነዉ። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጁሊያን ዝይ የብሪቲሽ መንግስት ማንኛውንም “የሚያጠናቅቅ ወይም ህጋዊ አስገዳጅ እርምጃ እንዳይወስድ ለጊዜው አግዶት የነበረው የብሪቲሽ ህንድ ውቅያኖስ ግዛት፣ እንዲሁም የቻጎስ ደሴቶች በመባልም የሚታወቀው ለውጭ መንግስት” ማዛወርን በሚመለከት ድርድሩን ለመደምደም ነዉ።

ከ1814 ጀምሮ ክልሉን የተቆጣጠረችው እንግሊዝ በ1965 የቻጎስ ደሴቶችን ከሞሪሸስ በመለየት የብሪቲሽ የህንድ ውቅያኖስ ግዛትን መፍጠር ችላለች። እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ መንግስት በትልቁ ደሴት ላይ ለሚገኘው የዲያጎ ጋርሺያ አየር ማረፊያ መንገድ ለማድረግ ወደ 1,500 የሚጠጉ ነዋሪዎችን ወደ ሞሪሸስ እና ሲሸልስ አስወጥቷል።

በጥቅምት ወር መንግስት ደሴቶቹን ለሞሪሸስ ለማስረከብ እና ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በ99 አመት የሊዝ ውል መሰረት የዲያጎ ጋርሺያ ቤዝ መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችል ረቂቅ ስምምነት አስታውቋል።በስምምነቱ ላይ ምክክር በማድረግ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አፅድቆታል። ይሁን እንጂ ስምምነቱን ማጠናቀቅ ያልተቻለ ሲሆን በሞሪሸስ የመንግስት ለውጥ የተነሳ ዘግይቷል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ኪሎ ኮረሪማ ከ2 ሺህ 600  እስከ 2 ሺህ  700መቶ  ብር እየተሸጠ ነው

በአዲስ አበባ በተለያዩ የንግድ መደብሮች ላይ ለምግብ ማጣፈጫ ጥቅም ላይ የሚዉለዉ ኮረሪማ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ብስራት ሬዲዮ ባደረገው ቅኝት ማወቅ ችሏል፡፡

ነዋሪዎች ለጣቢያችን እንደገለፁት በተለይም ካለፉት አስራ አምስት ቀናት  ጀምሮ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጰያ ህዝቦች ክልል ከፋ ዞን በ17 ወረዳዎች የኮረሪማ ምርት በዋናነት የሚመረት ሲሆን በተጨማሪም በቤንች ሸኮ፣ በምዕራብ ኦሞ እና በሸካ ዞኖች  በብዛት ይመረታል፡፡

ካፋ ዞን በብዛት የኮረሪማ ምርት የሚመርትበት ቢሆንም ከሰሞኑ በዞኑ ከ1ሺህ 500 መቶ እስከ 1ሺህ 700 እየተሸጠ መሆኑን እና ታይቶ የማይታወቅ ጭማሪ ማሳየቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡

ኮረሪማ ከተተከለ ከ3 እስከ 5 ዓመት ቆይቶ ምርት መስጠት የሚጀምር ሲሆን አርሶ አደሮች፣ ምርት መስጠት ከጀመረ በኋላ ከ7 እስከ 10 ዓመታት በየአመቱ ከ1 ሄክታር በአማካይ ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በአዲስ አበባ በተለይም ካለፉት አስራ አምስት ቀናት ወዲህ የኮረሪማ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋው የጨመረበትን ምክንያት ብስራት ሬዲዮ የሚመለከታቸውን አካል አናግሮ በቀጣይ  ምላሽ ይዞ ይመለሳል፡፡

በሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል


በካርቱም ያጋጠመው የውሃ ቀውስ ተከትሎ በሱዳን የኮሌራ ወረርሺኝ መባባሱ ተገለፀ

የሱዳን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኦምዱርማን ካራሪ አካባቢ እና ከካርቱም በስተደቡብ በምትገኘው ጃባል አውሊያ የኮሌራ በሽታ መከሰቱን አስታውቋል። በካርቱም ግዛት ውስጥ ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት ችግር ያጋጠመ ሲሆን ግንቦት 14 ቀን የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች በኦምዱርማን ሶስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ላይ ጥቃት በመፈፀሙ በመዲናዋ መብራት እንዲቋረጥ ካደረገ በኋላ ቀውሱ ተባብሷል።

የካርቱም ነዋሪዎች ንፁህ ካልሆኑ ምንጮች ለምሳሌ ጥልቀት ከሌለው ጉድጓዶች ወይም በቀጥታ ከአባይ ወንዝ ውሃ ቀድቶ በመጠቀም ለበሽታዎች መስፋፋት አስተዋጽኦ አደርጓል ተብሏል። "በሦስት ሳምንታት ውስጥ 51 ሞትን ጨምሮ 2ሺ323 አዳዲስ የኮሌራ በሽታዎች ተመዝግበዋል የሚለው የሱዳን ጤና ሚኒስቴር ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በካርቱም ግዛት በተለይም በካራሪ እና ጄቤል ኦሊያ ናቸው" ሲል የጤና ሚኒስቴር የአደጋ ጊዜ ኦፕሬሽን ማእከል በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ሱዳን በክልሎች የተለያዩ የኢንፌክሽን እና የሞት አደጋዎችን ጨምሮ የዴንጊ ትኩሳት፣ ወባ፣ ሄፓታይተስ፣ ኩፍኝ እና ዲፍቴሪያን ጨምሮ ሌሎች የጤና ችግሮች እንዳጋጠሟት ገልጿል። የጤና ሚኒስቴር በሽታን የመከላከል ዘዴዎችን በማስተማር የቤት ውስጥ ጉብኝት በማድረግ፣ ቲያትር እና ተንቀሳቃሽ ሲኒማ እንዲሁም የማህበረሰብ ውይይት በማዘጋጀት እና በመገናኛ ብዙሃን የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል።

መግለጫው አክሎም ከ 50 በመቶ በላይ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች እና ለወረርሽኝ በሽታዎች የፍጆታ እቃዎች በብሔራዊ የሕክምና አቅርቦቶች ፈንድ መጋዘኖች ውስጥ ይገኛሉ ያለ ሲሆን በተጨማሪም፣ አንዳንድ ድርጅቶች በተወሰኑ ግዛቶች ውስጥ የራሳቸው አቅራቢዎች አሏቸው ብሏል። በግጭት ዞኖች ውስጥ እስከ 80 በመቶ የሚደርሱ እና 45 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የጤና ተቋማት በአቅርቦት እጥረት፣ በመብራትና በውሃ እጥረት እና የህክምና ባለሙያዎች ስራ በማቆማቸው ሳብያ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ተብሏል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የስነምግባር ጥሰቶችን የፈፀሙ 26 ሞያተኞች ከስራ እስከማሰናበት የሚደርስ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

በ2017 በጀት ዓመቱ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ለመሰብሰብ የታቀደው ገቢ 3 ቢሊየን 672 ሚሊየን 186ሺ 772 ብር ነበር ሲሉ በጉራጌ ዞን ገቢዎች መምርያ የታክስ ትምህርት ድጋፍ ባለሞያ የሆኑት አቶ ይረፉ አባተ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት በዘጠኝ ወራት ከ2 ቢሊዮን 754 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከዚህም ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ቢሊየን 322 ሚሊየን መሰብሰብ መቻሉን እና  ከታቀደው  84.34 በመቶ የሚሸፍን ማሳካት መቻሉን አቶ ይረፉ አባተ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር መምርያው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 26 ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ የነገሩን ባለሞያው፤ ሞያተኞቹ በተለያዩ የስነምግባር ጥሰቶች በመሳተፍ እርምጃ የተወሰደባቸው ናቸዉ፡፡ ከ26ቱ አስሩ የቃል ማስጠንቀቅያ፣ ለሰባት ሞያተኞች የፅሑፍ ማስጠንቀቅያ፣ ሶስት ሞያተኞች ከስራ ሲሰናበቱ አንድ ሰራተኛ በደመዎዝ፣ አንዱ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ ብሎ እንዲሰራ የቅጣት ውሳኔ ተሰጥቷል::አራት ጉዳዮች ደግሞ በሂደት ላይ ያሉ መሆናቸው ገልፀዋል።

ያለ ምክንያት ከስራ ቦታ መጥፋት፣ በተደጋጋሚ ከስራ ቦታ መቅረት፣ በደረሰኝ የተሰበሰበ ገቢ እጅ ላይ ማቆየት፣ ያለ ደርሰኝ ገቢ መሰብሰብ፣ የተሰጠን ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትና የተሰጣቸው የስልጣን እርከን ተላልፈው ጉዳይ መፈፀም የመሳሰሉ የዲስፒሊን ጥሰቶች ለቅጣቶቹ ዋነኛ መንስኤዎች ናቸው።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምርያ ከሞያተኞቹ በተጨማሪ በግብር ከፋዮች ላይ እንደየ ጥፋት መጠናቸው የተለያዩ የእርምት እርምጃዎች ወስዷል፡፡ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይንት ሲፈፅሙ የተገኙ 92 ግብር ከፋዮች ላይ በወሰደው እርምጃ በዘጠኝ ወሩ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን 685 ሺ ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን  አቶ ይረፉ አባተ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።

በሰብል አበበ
#ዳጉ_ጆርናል

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.