ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy


Kanal geosi va tili: Efiopiya, Amharcha
Toifa: ko‘rsatilmagan


"Strong minds discuss ideas, average minds discuss events, weak minds discuss people."
Rinu Ruzvelt

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Efiopiya, Amharcha
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri


ያልታዩ ነገሮች - በርክሌ

ምንጭ ፦ ፍልስፍና ከዘርዐያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ
ፀሀፊ ፦ ፍሉይ አለም

በጥቅጥቅ ጫካ መሃል አንድ ዛፍ ወደቀ፤ ሆኖም በጫካው ውስጥ ማንም አልነበረም፡፡ ዛፉ ሲወድቅ እና መሬቱን ሲመታው ድምጽ ያሰማልን? የሆነ የሚሰማ አካል ሳይኖር ድምጽ ማውጣት ማለት ምን ማለት ነው? ያልተሰማ ድምጽ ምን አይነት እንደሆነ ማሰብ እንችላለን? በሃሳብህ ለማሰብ ሞክር፡፡ በአእምሮህ ውስጥ ምን አለ? ምን ይመስላል?

ይህ ሃሳብ የአስራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን አይሪሻዊ ፈላስፋ የሆነው ጆርጅ ባርክሌ የሃሳባዊነትን (Idealism) ፍልስፍና
እንዲመራመር አደረገው፡፡

ፈላስፎች እንግዳ ወደሆኑ ስፍራዎች ይጓዛሉ፤ ከሚጓዙባቸው ቦታዎች መሃል ሃሳባዊነት አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ጓደኛህ ከአንተ አእምሮ ውጪ በውኑ ዓለም እንዳለ አረጋግጥልኝ?

ምናልባትም ወደ እርሱ በጣቶችህ ልትጠቁመኝ አልያም እየነካህ ልታሳየኝ ትችላለህ፡፡ “ይኸው እዚህ ጋር አለ፤ እንደዚህ አድርጌ በጥፊ ስመታው ያመዋል፣ ምላሽም ይሰጣል” ልትለኝ ትችላለህ።

ለበርክሌ ጓደኛህን መንካትህ ብቻውን በቂ ማስረጃ አይደለም፡፡ አዎ... ዓለምን የምትረዳበት የራስህ የስሜት ህዋሶች አሉህ ሆኖም ይህ ማለት እውነታውን ያረጋግጡልሃል ማለት አይደለም፡፡ ዳክዬ ማየትህ ብቻ ዳክዬ እንዳለች ማረጋገጫ አይሆንህም፡፡ ምናልባትም የተመለከትከው ዳክዬ መሳይ ነገር ይሆናል። ምናልባትም የምትኖርበት ዓለም ሁሉ በህልምህ ያለ ዓለም ሊሆን ይችላል፤ ጓደኛህም የህልም ዓለምህ አካል ይሆናል። በመንገድ ስትጓዝ የአእምሮ እክል ያለባቸው ሰዎች አጋጥመውህ አያውቅም? ልክ በራሳቸው ዓለም እንዳሉ ሆነው ይንቀሳቀሳሉ፣ ከማይታዩ ሰዎች ጋር ያወራሉ፣
ለብቻቸው ይስቃሉም---

የሰው አእምሮ ስለ ዓለም ያለው እውቀት የተገደበ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ “መስሎኝ _ ነበረ” እንላለን፡፡ ነገሮችን የምናይበትም መንገድ ነገሮቹን በትክክል ይገልጻቸዋል” ማለት አንችልም፡፡ በዳክዬዋ እና በአንተ መካከልም እውቀትህን የሚገድብ ወንዝ አለ፡፡

ባርክሌ በሃሳብህ አንድ ነገርን አስብ ይልሃል፤ ለምሳሌ ብርቱካንን በሃሳብህ ሳል አሁን ደግሞ ብርቱካንን እንደማታየው ሆነህ ስለ ብርቱካን አስብ... ይህን ማድረግ በጥቂቱም ቢሆን ይከብዳል፤ ግን ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ አይንህን ጨፍነህ ብርቱካንን በእጅህ እየነካካኸውና ሽታውን እያሸተትከው ወይም እየቀመስከው እንደሆነ ማሰብ
ትችላለህ።

አሁን ደግሞ ብርቱካኑ ያለ ሽታ እና ያለ ጣዕሙ፤ ያለ መዳሰስ ወይም ያለ መታየት ምን እንደሚመስል አስብ... ክብደቱ በእጅህ ላይ አይሰማህም፣ ስለ ቀለሙ እና ቅርጹ ማሰብ አትችልም፣ ጣዕሙን መቅመስ አልያም ሽታውን ማሽተትም አትችልም፡፡ ከሰውነት ህዋሳቶችህ ውጪ ሆነህ ብርቱካን ይህን ይመስላል ብለህ ግለጽልኝ?

አትችልም..... ብርቱካኑን የምትገልጽበት ምን ቀረህ? ምንም!

ይህንን ነው ባርክሌ ሲያጠቃልለው esse est percip ያለው። ሃረጉ የተፈጠረው ከላቲን ቃላት ሲሆን፣ ትርጓሜውም “መሆን ማለት ማስተዋል ነው፡፡” ወንበር በውኑ ዓለም ላይ ያለ ነገር ለመሆን የግድ የሚያስተውለው አካል ያስፈልገዋል። የሚዳስሰው አልያም የሚመለከተው ሰው ከሌለ ወንበሩ በውኑ ዓለም አለ ማለት አንችልም። በጫካ ውስጥ የወደቀው ዛፍ ሰሚ ከሌለው ድምፅ አያሰማም፣ ጓደኛህም አንተ ካላየኸው ወይም ካልነካኸው በውኑ ዓለም አለ ማለት አንችልም፡፡

የእውኑ ዓለምም የሚፈልቀው ከአንተ አእምሮ በመነሳት ነው፡፡ ህንጻዎችን ስትመለከት፣ የአበባ መዓዛን ስትምግ፣ ትኩስ ቡና ምላስህን ሲያቃጥለው እነዚህ ሁሉ በአእምሮህ ያሉ የውኑ ዓለም መገለጫዎች ናቸው፡፡ የውኑ ዓለምም የሚያየው (የሚያስተውለው)
አካል ሳይኖር ሲቀር መኖሩ ያበቃለታል፡፡

ሆኖም ግን ሰው (ወይም ሌላ አስተዋይ) በማይደርስበት በረሃ ላይም እኮ ዛፎች፣ ተራሮች፣ ድንጋዮች አሉ ... ይህ ስለምን ሆነ? ለምንስ እነርሱም አልተሰወሩም።

የባርክሌ ምላሽ ቀላል እና አጭር ነው፤ “እግዚአብሔር አለ!” ተመልካች በሌለበት ሁሉ፣ በአጽናፈ አለሙ በሙሉ እግዚአብሔር ተመልካች ነው፡፡ ለዛም ነው የተከልናት አበባ ወደ ቤታችን እስክንመለስ ድረስ ሳትሰወር የምትጠብቀን፤ ለዚህም ነው በጥቅጥቅ ደን መሃል የወደቀ ዛፍ ድምጽ የሚያሰማው፡፡

ይህ የባርክሌ ሃሳብ ከላይ ለሚያየው ቀልድ ይመስላል፤ ሆኖም በዘመናዊው የሳይንስ ዓለምም ቢሆን የባርክሌ ሃሳብ ከፊል እውነትነት አለው፡፡ ለምሳሌ እጅህን ብቆነጥጥህ የቱ ጋር ነው ህመሙ የሚሰማህ? “እጄ ላይ ነዋ” ትለኝም ይሆናል፡፡ ግን አይደለም። ሰዎች ለምን ፓራላይዝ የሚሆኑ ይመስልሃል? በብዛት የሚታወቀው ምክንያት ከአእምሯቸው ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የአእምሯቸው (ወይም የህብለሰረሰራቸው) የሆነ ክፍል ላይ እክል የገጠማቸው ሰዎች ከአካል ክፍላቸው አንዱ ይደነዝዛል ወይም ፓራላይዝ ይሆናል፡፡ እጁ ፓራላይዝ የሆነ ሰው ላይም የፈላ ውሃ ብታፈስበት አያቃጥለውም። ምክንያቱም የማቃጠል ስሜት ያለው በአእምሮ ውስጥ እንጂ፣ በእጁ ላይ ወይም በሻዩ ላይ አይደለም፡፡ ጣዕምም፣ ድምጽም፣ ቀለማትም ሁሉም በአእምሮ ውስጥ ያሉና አእምሮ የእውኑን ዓለም ለመረዳት የሚጠቀምባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy


እብዱ ዮሐና
ከካህሊል ጂብራን እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው
Credit to ትረካ ቲዩብ

መልካም ሰንበት🙏
@zephilosophy




-ዛሬም የሚያስፈልጉን ነፃነቶች
-ቁልፍ እና ድልድይ
-ውይ ሴቶች!!
ተራኪ-አንዱአለም ተሰፋዬ
@Zephilosophy
@Zephilosophy




#ሰውና_ተፈጥሮው
አዲስ መጽሐፍ

👉5ት ድንቅ ትምህርቶችን እነሆ ለቅምሻ፦

The Laws of Human Nature የተሰኘው የሮበርት ግሪን ድንቅ መጽሐፍ #ሰውና_ተፈጥሮው በሚል ርእስ በቅርብ ቀን በገበያ ላይ ዋለ ።

ታዋቂውን 48 Laws of POWER የተሰኘውን መጽሐፍ 48ቱ የኃያልነት ሕጎችን በሚል በተረጎመችው #ሃኒም_ኤልያስ የተተረጎመ ሲሆን፣ ልክ እንደ #የኃያልነት_ሕጎች_መጽሐፍ ጥፍጥ ብሎ ከተዘጋጀው #ሰውና_ተፈጥሮው አዲስ መጽሐፍ ላይ ለቅምሻ 5ቱን ድንቅ ትምህርቶች እነሆ ብለናል፦


#አንድ
#መርዛማ_ሰዎችን_አስወግድ

ከመርዛማ ሰዎች ጋር አብዝተን የምንገናኝ ከሆነ በአካልም ሆነ በአእምሮ ሊጎዱን ይችላሉ ይለናል። እነዚህ ከልክ ያለፈ ትችት የሚሰጡ፣ ምቀኛ፣ ትዕቢተኛ፣ ጠበኛ ወይም ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን ያጠቃልላል።  እነዚህን ባህሪያት በራሳችን እና በሌሎች እንዴት መለየት እንዳለብን እና ራሳችንን ከእነሱ እንዴት ማራቅ እንዳለብን ያስተምረናል።

#ሁለት
#ስሜታዊነትህን_ተቆጣጠር

ስሜታችን ምን ያህል በጥልቅ እንደሚገዛን እና ውሳኔዎቻችንን እና ድርጊቶቻችንን እንዴት እንደሚነካ አናውቅም። ምክንያታዊነትን በማዳበር እነዚህን ስሜታዊ ተፅእኖዎች እንዴት መቋቋም እንደምንችል ማወቅ የግድ ይለናል። እራሳችንን ጠንቅቆ ማወቅ፣ ስሜቶቻችንን ከሥሮቻቸው መፈተሽ፣ የምላሽ ጊዜያችንን ማዘግየት፣ የአስተሳሰብ እና የስሜታዊነት ሚዛንን ማግኘትን የመሳሰሉ ስልቶችንም ሮበርት ግሪን በመጽሐፉ ይጠቁመናል።

#ሶስት
#ከጓደኞችህ_ጋር_አብረህ_ወደ_ገደል_አትግባ

ከሌሎች ጋር ለመስማማትና ብቻችንን ላለመሆን ብለን የሌሎችን አስተያየት ወይም ግምት ከልክ በላይ እንዳንቀበል ያስጠነቅቀናል።  ይህ ግለሰባዊ አቅማችንን እንድናጣ እና ለቡድን አስተሳሰብ እንድንጋለጥ ሊያደርገን ይችላል።

#አራት
#ሳታቋርጥ_የተሻለ_ነገርን_ፈልግ

ባለን ነገር እንዳንረካ እና ሌላ ቦታ ያለን የበለጠ ደስታን የሚሰጥ ነገር እንድንፈልግ ይገፋናል። ከመጠን በላይ የሆነ ምሬትም ወደ ብስጭት፣ ጭንቀት፣ መሰላቸት ወይም ሱስ እንደሚመራን፣ ከዚህ ይልቅም እስካሁን ያገኘነውን በምስጋና ተቀብለን፣  ራሳችንን በማሻሻል ላይ ማተኮር እንዳለብን ያሳየናል።

#አምስት
#በሰዎች_ጭምብል_ስር_ምን_እንዳለ_ተመልከት

ሮበርት ግሪን፣ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እውነተኛ ሀሳባቸውን እና ስሜታቸውን ከራስ መተማመናቸውና ከአካላዊ ውበታቸው ስር  እንዴት እንደሚደብቁ ያሳየናል።  በሌሎች ቃላት እና ድርጊቶች ውስጥ ያሉ የማታለል ምልክቶችን እንዴት መለየት እንደሚቻል ያብራራልናል። እንዲሁም በሰዎች ፊት ሀቀኝነታችንን እና ታማኝነታችንን ሳናጣ እንዴት መጫወት እንዳለብንም ያስረዳናል።

#ሰውና_ተፈጥሮው መጽሐፍ በቅርብ ቀን በገበያ ላይ ይውላል።

👉ሌሎች የሮበርት ግሪን ምርጥ የእንግሊዝኛ መጽሐፍት እጅግ በጥራት ታትመው በገበያ ላይ፦

#The_Laws_of_Human_Nature


@Zephilosophy
@Zephilosophy


ነገ  ዘረኝነት በባህላዊነት ይተካ ይሆናል። በቀደመው ጊዜ 'የኛ ዘር የተለየ ነው' ብለው ያመኑቱ ዘራቸውን ለመጠበቅ ዋጋ ከፍለዋል። ሌሎችን ዝቅ አድርገዋል። እስከመገዳደልም ደርሰዋል። አዶልፍ ሂትለር አይሁዳውያንን ለመጨፍጨፍ የዘር ካርድ መዟል። ይህን የእብድ ሃሳብ ፊደል የቆጠሩቱም ደግፈዋል።
ትላንት የተማሩ፥ የተመራመሩ ወገኖች የዘራቸውን ምርጥነት በሳይንሳዊ ማስረጃ ለማስደገፍ ታትረዋል።በዚህ ዘመን ግን 'የኔ ዘር የተለየ ተፈጥሮ አለው' ብሎ የሚሟገት ቂል ቢመጣ ሳይንስ በቀላሉ ሙግቱን ፉርሽ ያደርግበታል። ጥቁሮች ከነጭ ያነሰ ተፈጥሮ  እንደሌላቸው ግልፅ ሆናል።  እንዲህ ያለ ጨዋታ ሳይንሳዊ አይደለም።

ዛሬ ዛሬ ዘረኝነት በባህላዊነት እየተለወጠ ይመስላል። ካልቸሪዝም ገንግኖ በሬሲዝም መንበር ለመቀመጥ እያደባ ነው።

ኹሉም ወገን የራሱን ባህል ልዩ መሆን ይሰብካል። የባሰው ነገር ደግሞ ባህልን ከመጤ ባህል መጠበቅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነገር ሆኗል። ትላንት "በዘር  የተለየን ነን" ብለው ያሰቡቱ በአመራር ደረጃ የከበረ ዘራቸውን "ከብክለት እንጠብቅ" ብለው ደም አፍስሰዋል። ምናልባት ደግሞ ነገ ምርጡን ባህል ከመጤ ባህል ለመጠበቅ በሚል የሰው ልጅ ደም ይፋሰስ ይሆናል።

በእርግጥም የሰው ልጅ ኢምክንያታዊነት የማይናቅ ጉልበት አለው!

ከ #ነገን_ፍለጋ መፅሐፍ የተወሰደ
ተስፋብአብ ተሾመ


እሳት፣ ውሀ፣ አየር እና መሬት
The fourth element

እሳት

እሳተ ሥሪቱ ፍጹም የእንከንየለሽነት፣ የምኅረትየለሽነት መሆኑ እሙን ነው፡፡ የእሳትንም ያህል ፍጹም ቅን፣ ገር እና በስነተፈጥሮው ቀጥተኛ ነገር መኖሩን አላውቅም፡፡ እሳት ከብሉያት፣ ነብያት፣ ወንጌላዊያን፣ ከአፈታሪኮች እና ባለቅንያት ዘመን ጀምሮ ብዙ የተባለለት መለኮት አከል ረቂቅ ክንውን ሆነ፡፡
የሰው ልጅ ከተሰራባቸው አራቱ የስጋ ባህሪያት ውስጥ ምናልባት ከአየርም በላይ እጅግ ረቂቁ ይኸው እሳት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እሳት ሲፈጅ፣ ሲበላ እንጂ ሲያርፍ ማደሪያው የት፣ ሲግለበለብ መከሰቻው ከወዴት እንደሆንስ ስንኳ የሚያውቅም የለም፡፡ እሳት የነካውን ሁሉ የሚያነጻ (purifying) ወይም የሚያገረጣ (terrifying) አቅም አለው፡፡ ቁም ነገሩ ለየትኛው አሰልጥነነዋል የሚለው ብቻ ነው፡፡

እሳት ንጹህ ነው፡፡ ቅን ነው፡፡ ገር ነው፡፡ ግን ደግሞ አውዳሚ፣ ጨራሽ፣ ፈጅ፣ ቀሳፊ፣ ቁጡም ነው፡፡ የዚህ ረቂቅ የነበልባል ፍጥረት ጥሪ እና ምሪት ሰብዓዊነትን ማበልጸግ መሆኑ ጥንት ከአፈታሪክ፣ ከነፕሮሚተስ ዘመን ጀምሮ ይታወቃል፡፡ ሁላችንም ውስጥ ስንረሳው እንደ ዶርማንት ቮልካኖ, ወይ በተኛበት ሳር እንደሚበቅልበት ዘንዶ ሊያንቃላፋበጎሬያችን ተወሽቀን እንድናጎላጅ ሊያሰንፈን፣ ስናነቃው ግን ከራሳችን አልፎ ለዓለሙ በሙሉ ሲትረፈረፍ የሚያስችል እሳታዊ ኃይል በውስጣችን አሸልቧል፡፡ የረቂቁ መንፈሳዊ ሽግግር ጠበብት አልኬሚስቶች የሰው ልጅን እሳታዊ ባህሪይ ራስን ከመግዛትና ለራስ ከሚሰጥ ዋጋ ጋር ያይዙታል፡፡

የእሳት ገዥ ሥነ ባህሪ (fire dominant form of energy) ያላቸው ግለሰቦች ለሚከውኑት ማንኛውም ተግባር ጥልቅ ፍቅር (passion) ይኖራቸዋል፡፡ የኃይል ባለቤቶችና እና አንደተ ርቱዓን ናቸው፡፡ ሆኖም የሚንቀለቀል ነበልባላዊ ፍላጎታቸውንና ጉልበታቸው በጊዜ መግራት ካልቻሉ ደፋርነታቸው፣ እንግዳነታቸው እንደ ብልግና (arrogancy) ሊቆጠርባቸው ይችላል፡፡


ውኃ

ውኃ  ሕይወት ነው፡፡ ንቅናቄ (movement) ፍሰት፣ ደግሞ ይሄን የሕይወትነት ጸጋውን ያድስለታል፡፡ የወንዝ ውኃ ከኩሬ መብለጡ ንቅናቄ ሕይወት ቢሆን አይደለምን? ውኃ ያድሳል፤ ያነጻል፤ ይፈውሳል፤ ያሻግራል፡፡ ግን ደግሞ ይሸረሽራል፤ ይበረብራል፤ አለት ይሰባብራል፡፡ ቅርጸ ተለዋጭነቱም (በጠጣር፣ በፈሳሽና በትነት መልክ መከሰት መቻሉ) ተሻግሮ አሻጋሪነቱን ይገለጣል፡፡ አካላችን የሚያድሰው ዋነኛው ኃይል እሱ ነው፡፡
አፍሪካዊው እና መላው ጥንታዊ ሕዝቦች የውኃ አካላት፣ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ኩሬዎች እና ባህራት የመናፍስት ማደሪያ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ለጥንታዊ ሕዝቦች ውኃ በስነተፈጥሮው ቅዱስ ነው፡፡
የውኃ ገዥ (Dominant) ሥነ ባህሪይ ያላቸው ሰዎች የተረጋጉ፣ ጸጥተኞች፣ በሰከነ ከባቢ ሳይቀር ገለል ማለትን የሚመርጡ ቁጥቦች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ብልሆች፣ ጥልቆች፣ ረቂቆች፣ በራስ መተማመን ያላቸው፣ ፈተናን መቋቋም የሚችሉ ይሆናሉ፡፡


መሬት

መሬት ከአራቱ የአካል ባህሪያተ በላይ የመስከን፣ የመርጋት፣ ስር የመያዝ ምልክትነት አለው፡፡ የመሬት መሪ ሥነ ባህሪ ያላቸው ሰዎች መጋቢ (በመንፈስ፣ በደመነፍስ)፣ አበልጻጊ፣ ተንከባካቢዎች፣ ታማኞች፣ ቅኖች፣ ጽኑዎች ናቸው፡፡ ጥንታዊ ሕዝቦች ሁሉ ነገራቸው ከመሬት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ቢዘሩ፣ ቢለቅሙ፣ ቢያድኑ፣ ቢቆፍሩ፣ ቢተከሉ... ከመሬት!


አየር

አየር ከደመነፍስ፣ ከመንፈስ (spirit) ጋር የተያያዘ ስነ ባህሪ ነው፡፡ ለሥነ-ሕይወት መፈጠርና መቀጠል ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ ረቂቅ ስለሆነ አይያዝ፣ አይታይ፣ አይጨበጥም፡፡ ሆኖም በዙሪያ ገባው ላይ በሚፈጥረው ተሻጋሪ ተጽዕኖ በቀላሉ እንረዳዋለን፡፡ ረቂቅ ቢሆንም ቅሉ እንደአንዳች፣ ወይ እንደ ጠባቂ መልአክ ዘወትር አጠገባችን መሆኑን በውል እንገነዘባለን፡፡ እንደ እሳት እና ውኃ ሁሉ የለውጥ አቀጣጣይ (catalyst)፣ እንደ ውኃ ሰጋር (ተንቀሳቃሽ) ባህሪይነት አለው፡፡
የአየር ገዥ (Dominant) ሥነ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ቅን፣ ቻይ፣ ሰዎችን መመዘን የማይወዱ ነጻ ሰዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም አየር የዕውቀት የመብቃት ሥነ ባህሪ ነው፡፡


መፅሀፍ -በፍም እሳት መቃመስ
ደራሲ- ያዕቆብ ብርሀኑ
@Zephilosophy






በፍም እሳት መቃመስ
በያዕቆብ ብርሀኑ

ተፈጥሮ ህብሯ፣ መገለጫ መልኳ (manifestation) እልፍ ነው፡፡ ውሉን ካገኘኸው፣ ከውሻ ጩኸት፣ ከውኃ እናት እንቅስቃሴ ትማራለህ፡፡ ከቴሌስኮፕና ማይክሮስኮፕ በላይ ደመነፍስህን ታምነዋለህ፡፡ የተፈጥሮን ውል ካገኘኸው ስለሁሉም ነገር ለመማር ዓይኖችህን መጨፈን ብቻ እንደሚበቃህ ይገባሃል፡፡ ዝም ረቂቅ ጸሎት፣ ዝም በመንፈስ መገናኘት እንደሆነ ይገለጥልሃል፡፡ ረቂቁ ነገር ያለው ያልተጻፈው፣ ያልተነገረው ፈጽሞ ሊጻፍ የማይችለው ውስጥ (in the inexplicable) መሆኑን ትቀበላለህ፡፡ ከቀኖና ይልቅ ኅሊና በላጭ መሆኑ ፍንትው ይልልሃል፡፡

ዝሙን መለማመድ፣ የተፈጥሮን ረቂቅ ውል ማሰስ ረቂቅ መንፈሳዊ ፍለጋ (mysticism) ነው፡፡ ሚስቲሲዝምን ከምሥራቁ ዓለም የሐይማኖት እና አስተሳሰብ ጽንፍ ጋር ብቻ አያይዘው የሚያስቡ ሰዎች ያስቁኛል፡፡ አፍሪካዊ የቮዶ (vodooo) አማኞችን ጠይቋቸው.. ‹‹ነጮች ወደ ቤተክስትያን ሄደው ተሰባስበው ስለመለኮት ይጮሃሉ፡፡ እኛ ግን እንዲሁ በመደነስ ብቻ መለኮታዊያን እንሆናለን›› ይሏችኋል፡፡ (The white poeple go to church and speak about God, but we simply dance and become God.)

ሚስቲዚም የትም አለ፡፡ ስህተተኛው ታናሽ ወንድማችን የሚሉትን ዘመናዊውን የሰው ልጅ ሽሽት በኮሎምቢያ አይደፈሬ የተራራ ሰንሰለቶች የሚኖሩት የኮጊ (Kogi) ጥንታዊ ቅዱስ ሕዝቦችም አኗኗርም ሆነ በእናትህ ዓይኔ ተርገበገበ ማንን ሊያሳየኝ ይሆን? ብሂል ውስጥ ሚስቲሲዝም አለ፡፡ አያቶችህ ወፍ መለሰችኝ፤ ‹ስቅ አለኝ ማን አነሳኝ፤ እጄን አሳከከኝ ምን ላገኝ ይሆን?› ሲሉ ምን ማድረጋቸው መሰለህ? በስግብግቡ የሰው ልጅ አእምሮ ምሪት በምክንያታዊነት ከማይደረስበት ከረቂቁ ተፈጥሮ ጋር ሲመሳጠሩ እኮ ነው!

ቢሆንም ዝሙን ጭጩን በምልዓት ለመዋረስ የተዘጋጀን ስላለመሆናች (since we are incapable of being_silent) ከማይነገረው ከዝምታው ጥልቅ ጥቂት ሀቲቶችን ለማፍካት መውተፍተፋችን ጤንነት እንደሆነ ተቀብለን እንቀጥላለን...

መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ‹‹እሁድ በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት ፬ቱን ባህሪያት ውኃ፣ መሬት፣ አየር፣ እሳት) ካለመኖር (እምኅበ አልቦ ሀበቦ) ሰራቸው ይለናል፡፡ እነዚህ የሰው ልጅ አካል የተቀመረባቸው አራት የስጋ ወይም የአካል ባህሪያት እሳት፣ ውኃ፣ መሬት እና አየር የረቂቁ የአልኬሚ ጽንሰ ሀሳብም መሰረታዊ ትዕምርቶች (symbols) መሆናቸውን ልብ ማለት ያሻል፡፡ ውኃ፣ እሳት፣ አየር፣ መሬት በየትኛውም የዓለም ክፍል፣ በየትኛውም ቋንቋ፣ ዘመን፣ መንገድ መንፈሳዊ ሐሰሳ የሚያደርጉ ‌መሰጠቱ ያላቸው ሁሉ የሚጨባበጡባቸው ስጋችን የታነጻባቸው ባህሪያት ስለመሆናቸው በብዙ ታትቷል፡፡

ረቂቃዊያን (mystics) ደግሞ መቃተት፣ መቃበዛቸው የቱንም ያህል ሰርቦላ ቢሆን ዞሮ ዞሮ ያው ስሪታቸው የወል (communal) የውኃ፣ አየር፣ የመሬት እና የእሳት ነው... ሕልማቸውም ልዩነት የለውም፡፡ በየትኛውም መንገድ ያምልኩ ያመስግኑ ዞሮ ዞሮ ራስን ማብቃት፣ የሰውን መለኮታዊ ማንነት ማንቃት፣ የሰውን ልጅ ከራሱ ደመነፍሳዊ እስራት ነጻ ማውጣት፣ ከስሜት - ከስግብግብነት አዙሪት መንጻት ዓይነት...
ሣይንስ በደረሰበት ሰዋዊ አረዳድ መሰረት በማናቸውም ቦታ ሕይወት ይፈጠር ዘንድ እነዚህ አራቱ የስጋ ባህሪያት የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ ሆኖም የተሰራንባቸው አራቱ አካለ ባህሪያት መግነጢሳዊ ኃይለ መልኮች (form of energies) እንጂ አንዲያው በሌጣው የሚፈከሩ ቁሳዊ ኢንቲቲስ› አይደሉም፡፡ እነዚህን አራት ስነባህሪያት በቅጡ በማጥናትና በማሰልጠን በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ያንቀላፋውን ጉልበት ማንቃት እና የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ መለኮታዊ ማንነቱ መመለስ ይቻላል፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy


የፓርክ ፖለቲካ

በረከት በላይነህ በደጃፍ ቲቪ ከዳዊት ጋር ድንቅ ውይይት አድርጓል።

17 % የኢትዮጲያ ጠቃሚ መሬት በፓርክ ምክንያት ታጥሯል ።ባቢሌ እና ጭላሎ በመሰሉ ፓርኮች ለ13 ቀይ ቀበሮ እና ለአስራ ሁለት ዝሆን ብዙ ሚሊዮን ህዝብ መመገብ የሚችል ብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ታጥሮ ተቀምጧል ይላል። አድምጡትና ሀሳብ ስጡበት

@Zephilosophy


አለ ክፍት ቦታ
ገጣሚ- ኤፍሬም ስዩም
@zephilosophy


ግርባብ
ፍቃዱ አየለኝ
ተራኪ - ኤፍሬም ስዩም
@zephilosophy


ራስን ማታለል (Bad Faith)

በሕይወትህ ለምን ያህል ጊዜ ለውድቀትህ ሌሎች ሰዎችን ወይም ሁነቶችን ወቅሰህ ታውቃለህ? እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ እሆን ነበር' ብለህስ ታውቃለህ? አለቃህ፣ መምህራኖችህ፣ ወላጆችህ የሆነ ነገር እንድታደርግ አስገድደውህ ያውቃሉ?

የሃያኛው ክ/ዘመን ፈላስፋ የሆነው ዣን ፖል ሳርት እነዚህን ሃሳቦች በአንድ ሰብስቦ “bad faith' ብሎ ይጠራቸዋል። ይህም ራስን ማታለልን ያመላክታል። ብዙውን ጊዜ በሕይወት ላይ አማራጭ እንደሌለን ለራሳችን እናሳምነዋለን፡፡ ይህን ያደርግነው እንዲህ ስለሆነ ነው የሚል ምክንያትም ከድርጊቶቻችን ጀርባ እናስቀምጣለን። አሁን ላለንበት ደረጃ ያበቁንን አስገዳጅ ምክንያቶች እና ሰበቦች እንደረድራለን፡፡ ራስን ማታለል በዙሪያችን እስር ቤት የመገንባት ያህል ነው።

ማህበረሰቡ ባስቀመጠልን አስገዳጅ ህጎች አልያም ልማዶች ራሳችንን ወስነን በነጻነት ከመምረጥ እንገደባለን፡፡ ለምሳሌ ሜሴጅ እንደላከልሽ ወዲያውኑ አትመልሽለት” አይነት ተራ ሕጎች ጀምሮ እስከ በዳኛ የተደነገጉ ሕጎች ድረስ - የመምረጥ ነጻነታችን ይገደባል።

እናም ራስን ማታለል (bad faith) የሚጀምረው ለውድቀታችን እነዚህን ህጎች ተጠያቂ ስናደርግና በእነርሱ ውስጥ ስንሸሸግ ነው::

እናም ከማህበረሰቡ ተውስን የምንወስዳቸው ብዙ ጭንብሎች አሉን፡፡ በብዙ የሕይወት ክፍሎቻችን ላይ እንዲህ መሆን አለብህ ስለተባልን ልክ እንደ ተዋናይ ሆነን እንተውናለን፡፡
ነገር ግን ይለናል ሳርት፤ ህግ፣ ደንብ፣ ባህል እና ወዘተ... ከመምረጥ አያግዱንም፡፡ ምርጫዎችን የመምረጥ እና የመወሰን ፈቃዱም በእኛ እጅ ላይ ነው ያለው፡፡

በእያንዳንዷ ቅጽበት፣ በእያንዳንዱ ቀን ምርጫዎች አሉን። በእያንዳንዱ ሰከንድም የወደድነውን የመምረጥ ነጻነት አለን። ይህንን ነፃነት ምንም አይነት ነገር ከእኛ ሊቀማን አይችልም፡፡ ነጻ ለመሆንም የተገባን ነን።

በዚሁ ልክም ለእያንዳንዱ ምርጫዎቻችን ውጤት የምንጠየቀው እኛ ብቻ ነን። ቀድሞውኑ በሚገባ አመዛዝነን ካልወሰንን እና መንገዳችን ወደ መጥፎ መዳረሻ ካደረሰን፣ ከእኛ ውጪ ልንከሰው የሚገባ አካል አይኖርም፡፡ ጥፋታችንንም ከማመን ውጪ ማንም ላይ ማላከክ የለብንም፡፡

ነጻ ነህ ... ነጻነትህን ተጠቅመህ መንገድህን ምረጥ...

ምንጭ-ፍልስፍና ከዘርዓ ያዕቆብ እስከ ሶቅራጠስ
ዝግጅት-ፍሉይ አለም

@Zephilosophy
@Zephilosophy


ጭፍን እምነትን አውልቃችሁ ጣሉ

ምንጭ ፦ የፍልስፍና ሀሁ
ፀሀፊ ፦ በላይ ደስታ

መሪር ሀሳቦችን ለማንሳትና ለመወያየት ካልደፈራችሁ? ሗላ ቀር የሆነውና ከቤተሰቦቻችን የወረስናቸው ልማዶችና አስተሳሰቦች እርስ በእርስ አባልተው ይጨርሱናል፡፡ ስለእውነት ነው የምላችሁ፣ እንደሰው ተፈጥረን እንደድመት የምናልፍ ከንቱዎች እንሆናለን። በየጎጡ ጎራ እየሰራን እንለያያለን:: እምነታችን ሁሉንም የዓለም ህዝብ ካልቀየረ ብለን አክራሪነት ውስጥ ተቻኩለን እንወተፋለን። በንቁ ሀሳባችን ካልተመራን፣ ያው መሪያችን ልማድ ሆኖ መቅረቱ ግልጽ ነው፡፡

በሀሳብ፣ ልማድና እምነት መካከል ሰፊ ርቀት አለ፡፡ በሀሳቡ የሚያምን ሰው ይልቃል። በእምነቱ የሚያምን ግን አዲስ ሀሳብ አይፈጥርም፡፡ ቀድሞ የተፈጠረውን ስርዓት ተቀብሎ ወደ ልጁ ሰፈር ያደርሳል። እንደዱላ ቅብብል ማለት ነው። የዱላ ቅብብል ተወዳዳሪ ስለዱላው ምንም የሚያስበው የለም፡፡ ዱላው ብረት ይሆን እንጨት አያስብም። የሱ ስራ፣ ከኋለኛው አጋሩ የተቀበለውን ዱላ ይዞ ወደ ፊት መሸምጠጥ ብቻ ነው። ከዚያ ከፊቱ ለሚጠብቀው ሯጭ እስኪያቀብል ሳያባራ ይሮጣል፡፡

በእምነትና በባህላዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችም እንዲሁ ናቸው። ከአባቶች የወረሱትን እምነትና ትዉፊት የሙጥኝ ብለው ወደፊት ይሮጣሉ። ለቀጣዩ ትዉልድ እስኪያስረክቡና ህይወታቸው እስኪያልፍ የሚያስቡት አዲስ መንገድ አይኖርም፡፡ አእምሯቸው በጥልቀት እንዲያስብ ፈቃድ አይሰጡትም፡፡ ለዚህ ነው፣ ብዙ እምነት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ስልጣኔን የሚሸሹት።

እምነትን ብቻ የሁሉ ነገር ምንጭና መንገድ አድርጎ የሚቆጥር ህዝብ ያየለበት ማህበረሰብ ወይም ሀገር፣ ኋላቀርነቱ እዚያው ኋላ እንደቀረ የሚኖር ይሆናል። ትልቁ ፈተና ደግሞ፣ እምነት ውስጥ የተኛ ህዝብ ኋላ ቀርነቱን እንደጸጋ ማየቱ ነው፡፡ የትኛውም የኑሮ ገጠመኝ ማለትም ድህነት፣ አለመማር፣ አለማወቅ፣ የበታች መሆን፣ ስደት፣ በሽታ፣ ጦርነትና መሰል እልፍ ወረርሽኞች እግር ተወርች አስረውት ጭምር አያዝንም፡፡ እልህ ውስጥ አይገባም፡፡ ለምን እንዲህ ተፈተንኩ ማለትን አይፈልግም፡፡

"የፈጣሪ ፈቃድ ነው ብለን ዝም አልን” በሚል የተለመደ ዋሻ ውስጥ ይደበቃል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ፣ ዛሬም ወደ ራሳችን ማየት ነው፡፡ እየወደቅንም ፈጣሪ የምንለውን ሀይል አመስጋኞች ነን። ብንራብ፣ ብንጠማ፣ ፈተናዎች ቢደራረቡብን፤ ጦርነት ውስጥ ብንናጥ ሁሌ እያመሰገንን እናልፋለን፡፡ ለምን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ገባን? እንዴትስ መውጣት እንችላለን? ብለን አንጠይቅም። ምክንያቱም "ሁሉም ነገር የፈጣሪ ፈቃድ ነው” በሚለው ራሳችንን እናታልላለንና።

መፍትሔ የምንጠብቀው ከጸሎትና ከፈጣሪ ነው። እጆቻችንን ወደ መሬት አዙረን መዶሻና አካፋ አንይዝም፡፡ ምንም ሳንይዝ አየሩ ላይ ወደ ሰማይ አንጋጠን እንለምናለን። በዛ ጥፋታችን ለፈረሰ ቤት ጥገና የምንጠይቀው ፈጣሪን ነው:: ይህ መንገድ ለሁሉም ነገር መፍትሄ አይሆንም፡፡

ፍጹም አማኝ ሆኖ የተሰባሰበ ህዝብ ስልጣኔ የማይሰራው ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው። የተሰባሰበው ሰማያዊ መንግስትን እያሰበ እንጂ፣ በእጁ የጨበጠውን የምድር ህይወት ከግምት አያስገባም፡፡ እየኖረ በመሆኑ ግን፣ የግድ መንግስት ይፈጥራል። የሚፈጥረው የመንግስት አይነት ግን ምድር ላይ ያለውን እውነት ያማከለ አይሆንም፡፡ የተዘበራረቁ መልኮች ይኖሩታል፡፡

የራሱን የህይወት መንገድ እንዲፈጥር ነጻነትን ያልተማረ ህዝብ፣ ጥያቄ አይጠይቅም፤ የተለየ ሀሳብም አያስብም፡፡ ሀሳብ የሚያድገው ደግሞ በፍልስፍና ነው ! በፍልስፍና አስተሳሰብ ያልተገራ ህዝብ በነጻነት ውስጥ ሆኖ የእውቀት ልዩነት የሚፈጥር የሀገር ቅርጽ አይወልድም፡፡ በጥንት ልማድና አሁን ባለው የሀገር ቅርጽ መሃል የተለየ ማንነት አይኖርም።

በልማድና በእምነት ውስጥ ብቻ የሚኖር ህዝብ አንደኛው ችግር ይኼው ነው፡፡ ከዘመን መለወጥ ጋር የሚያድግ ርዕዮት አይፈጥርም፡፡ የእርሱ ጉዳይ ዶግማዎችን እንዳሉ ማስቀጠል ነው፡፡ የባህል ዱላ ቅብብል ላይ የተገደበ ስርዓት ነው የሚፈጥረው፡፡ ባህል ግን ብቻውን ስልጣኔ አይሆንም ፤ ስልጣኔንም አያመጣም፡፡ ባህል የቡድን ባህሪ እንጅ የግለሰብ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ የሳይንስ ወይም የፍልስፍና ተግባር ደግሞ ዶግማዎችን ብቻ ማስቀጠል አይደለም።

ኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ ሥነቃላዊና የፅሁፍ ፍልስፍናዎች ባለቤት ናት። ከአስራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት፣ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ መልኩ በርከት ያሉ የፍልስፍና ስራዎችን በመስራት በቀዳሚነት የምትጠቀሰው በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ከተጻፉት የፍልስፍና ስራዎቿ መካከል ከፊሎቹን በትውልድ ካናዳዊ፣ በምርጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነው ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ እድርጓል። ሌሎች በርካታ በግዕዝና በአረብኛ ቋንቋዎች የተፃፋ የጽሁፍ ስራዎች በጥንታዊ ቤተእምነቶችና ቤተመዛግብት ውስጥ ተቀምጦ አንስቶ የሚመረምራቸውን የሀገራቸውን ጠቢብ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ፍልስፍና በጥቅሉ የተጻፉትንና በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፋትን የማህበረሰብ ወጎች፣ ልማዶች፣ ጥበቦች፣ የእውቀት ዘርፎችንና አስተሳሰቦችን፤ በግለሰብ ፈላስፋዎች፣ በአንድ ዘመን ተሰርተው በጽሁፍ የተላለፉትን ስራዎች የሚመለከት ምጡቅ የጥበብ ዘርፍ ነው። በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ማኅበረሰባዊ ፍልስፍናዎች፤ በተረትና ምሳሌ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በዘይቤዎች፣ በቅኔዎችና በወጎች ሊገለጡ ይችላሉ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ገና ያልተጠኑ የበርካታ ጥንታዊ ስነ ጽሁፎች ባለቤት ናት፤ ማጥናትና መመርመር አቅቶን ሌሎች አጥንተው የቅጂ መብቱን ከመውሰዳቸውና የታሪክ ክፍትት ተፈጥሮ በመጪው ትውልድ ተወቃሾች ከመሆናችን ሰፊት፣ ከትምህርት ቤት ጀምሮ፣ በወጣቶች አዕምሮ ውስጥ የምርምር ሀሳቦችን በማንሳትና የዘርፉ ምሁራንም ተገቢውን ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ በየደረጃው ያሉ የትምህርት ተቋማትም፣ የፍልስፍና ጥበብን በትምህርትና በምርምር ስራቸው ውስጥ በማስገባት፣ ወጣቶች ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥተው፣ በተለያዩ የፈጠራ አስተሳሰቦች ውስጥ እንዲመሰጡ ማበረታት ወቅቱ የሚጠይቀው አቢይ ስራ ነው፡፡

እየኖርን ባለነውም ሆነ ወደፊት በምንኖረው ዘመን፣ ለአንድ ሃገር አስፈላጊና ወሳኝ ነገሮች ናቸው ተብለው ከሚታመንባቸው ጉዳዮች መካከል፤ ለዘመኑ የሚመጥን የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤት ሊያመነጭ የሚችል ተመራማሪ ትውልድ ማፍራት መቻል ነው፡፡ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶችንና የተራቀቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሊያመነጩ የሚችሉ ጠይቂ አዕምሮዎች እንዲፈጠሩ ደግሞ፣ በነባሩ ባህላዊ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ዜጎች፣ አዲሱ ትውልድ፣ የምርምር ሀሳቡን በሚያምንበት መንገድ ያለገደብ፣ እንዲያራምድና እንዲያዳብር መፍቀድ መቻል አለባቸው።

@Zephilosophy
@Zephilosophy


#ጊዜ_አባካኞች

“በታሪክ ያሉ የምጡቅ አእምሮ ባለቤቶች ሁሉ በዚህ ነጠላ ጭብጥ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ፣ የሰው ልጆች አእምሮ ድብቅነት ውስጥ ግራ መጋባታቸውን በጭራሽ ሊገልጹ አይችሉም፡፡ አንድም ሰው ከራሱ ግዛት አንድ ኢንች አይተውም፤ ከጎረቤት ጋር ያለ ትንሽ ግጭት በከባድ የሚያስከፍል ሆኗል፤ ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ሌሎች ጣልቃ እንዲገቡ በቀላሉ እንፈቅዳለን፤ የከፋው ነገር ደግሞ በአብዛኛው ሊያጠፉት ለሚችሉት ሰዎች መንገድ የምናመቻች መሆናችን ነው፡፡ ማንም ሰው ለአላፊ አግዳሚው ገንዘቡን አይሰጥም፤ ግን እያንዳንዳችን ለምን ያህል ሰዎች ሕይወታችንን ሰጥተናል! ለንብረትና ለገንዘብ እጃችን አይፈታም፤ ሁላችንም እጅግ ስስታሞች መሆን ለሚገባን ለሚባክን ጊዜ ግን የምናስበው እጅግ ትንሽ ነው፡፡”
                   #ሴኔካ

በአሁኑ ጊዜ ማለቂያ የሌላቸው መበጥበጫዎች አሉ፤ የስልክ ጥሪዎች፣ ኢ-ሜይሎች፣ ጠያቂዎች፣ የማይጠበቁ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በባርነት ውስጥ የተወለደውና ኋላ ላይ ራሱን አስተምሮ የግሉን ኮሌጅ እስከ መክፈት የደረሰው ኮሌ ቡከር ቲ. ዋሽንግተን፣

“ያለ ምንም አላማ የሰውን ጊዜ ሊጠቀሙ የተዘጋጁ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡” ብሎ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ፈላስፎች፣ የእነሱ ነባሪ ሁኔታ ውስጣዊ እውቀት መሆን እንደሚገባው ያውቃሉ፡፡ ግላዊ ቦታዎቻቸውንና ሀሳቦቻቸውን ከዓለም ረብሻ  በትጋት የሚጠብቁት ለዚያ ነው፡፡ የጥቂት ደቂቃዎች ምልከታ ከየትኛውም ስብሰባ ወይም ሪፖርት የበለጠ ዋጋ እንዳለው ያውቃሉ፡፡ በተጨማሪም በሕይወት የተሰጠን ጊዜ ትንሽ እንደ ሆነና ምን ያህል ፈጥኖ ሊያልቅ እንደሚችልም ይረዳሉ፡፡

ሴኔካ አካላዊ ንብረቶቻችንን መጠበቅ ላይ ጥሩ የሆንነውን ያህል፣ አእምሯዊ ድንበሮቻችንን ማስመር ላይ ግን ግድ የለሽ መሆናችንን ያስታውሰናል፡፡ ማንምም እንዳሻው ድንበራችንን አልፎ ሲገባ አንቃወመውም። ንብረት ተመልሶ ሊገኝ ይችላል፤ እንዲያውም ገና ብዙ የምድር ሃብቶች በሰው አልተነኩም።

#ጊዜ_ግን? ጊዜ ፈጽሞ ሊተካ የማይችል ሀብታችን ነው፤ ተጨማሪ መግዛት አንችልም፡፡ ማድረግ የምንችለው በተቻለ መጠን ጥቂት ብቻ ለማባከን ጥረት ማድረግ ነው፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy


ሕይወት የምትጀምረው መቼ ነው?

ሁለት ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ይከራከሩ ነበር፡፡ አንዱ፣ “ሕይወት የምትጀምረው ልክ አንድ ጽንስ በተጸነሰበት ቅጽበት ነው” በማለት ያንን እምነቱን በግለት ያስተጋባል፡፡

ሌላኛው ደግሞ፣ “አይደለም! ሕይወት የምትጀምረው የተጸነሰው ልጅ የመጀመሪያውን ትንፋሽ ወደመተንፈስ ደረጃy ሲደርስ ነው” በማለት የተጋጋለ ምላሹን ይናገራል፡፡

ይህንን ሃሳብ ሳይለቁ ለሰዓታት ሲከራከሩ የተመለከተ አንድ ሰው እያዋዛ አንድን ትምህርት ትቶላቸው አለፈ፣ “ሁለታችሁም ተሳስታችኋል፤ ሕይወት የምትጀምረው ሰው የተፈጠረለትን ዓላማውን ሲያውቅና ያንን መከተል ሲጀምር ነው”!!!

ዓላማችንን እንወቅ! በግለት እንከታተለው! እንኑረው!

@zephilosophy




ስለመፅሐፍ የተነገሩ አባባሎች!


ወዳጆች ዛሬ የአለም የንባብ ቀን እንደመሆኑ የንባብ ባህላችን እንዲዳብር ሊያነሳሱን የሚችሉ ስለመፃሕፍት የተነገሩ የተለያዩ ሠዎችን አባባል ዛሬ ልንዘክር ብዕራችንን ከወረቀቱ አገናኝተናል፡፡

መፅሐፍ የሚሠጡት ጥቅም የታወቀ ቢሆንም በማንበብ ብቻ ግን አዋቂ መሆን አይቻልም ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም መፃሕፍትን ከማንበብ ባሻገር በንባብ ያገኘናቸውን ሃሳቦች ከሃሳባችን ጋር በማስተያየትና በማሻሻል፣ በማሠላሠልና በማስተዋል አዲስ ሃሳብ ካልፈጠርንበት መፅሐፍ ማንበብ ሳይሆን መፅሐፍ መቁጠር ነው የሚሆነው፡፡ ባነበብነው ሃሳብ ተገዝተንና አዲስ የባህሪ ለውጥ ወይም አዲስ ነገር ካልፈጠርንበት ማንበባችን ዕውቀት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ዕውቀት ስንል በተጨባጭ በተግባር የሚገለፅ ነውና፡፡
ለማንኛውም አባባሎቹን እነሆ እላለሁ..! ሃሳብና አስተያየታችሁ የተጠበቀ ነው፡፡ መልካም ንባብ!

‹‹መፅሐፍ አንድ ቁምነገር አለው፡፡ ይሄም እግርህን ከቤትህ ሳታነሳ ዓለምን እንድትዞር ያደርግሃል›› (ጁምባ ራሂሪ)

‹‹አንባቢ ከመሞቱ በፊት አንድ ሺ ኑሮ ይኖራል፡፡›› (ጆርጅ ማርቲን)

‹‹መፅሐፍት ተንቀሳቃሽ አስማቶች ናቸው›› (ስቴፈን ኪንግ)

‹‹እንደ መፅሐፍ ያለ ታማኝ ጓደኛ የለም፡፡›› (ኸርነስት ኸርሚንግወይ)

‹‹ አንድ ነገር አንርሳ! አንድ መፅሐፍ፣ አንድ እስኪብርቶ፣ አንድ ሕፃን፣ አንድ መምህር ዓለምን መለወጥ ይችላሉ፡፡›› (ማላላ ዮሶፍዜ)

‹‹ዓለም መፅሐፍ ናት፡፡ ዓለምን ተጉዘው ያላዩ መፅሐፍ ይግለጡ፡፡›› (ቅዱስ አውግስጦስ)

‹‹መፅሐፍ በየዕለቱ የሚያጋጥመንን የህይወት ጉድፍ የሚያስወግድልን የነፍሳችን ማጠቢያ ነው፡፡›› (ያልታወቀ ሠው)

‹‹ማንበብ ለአዕምሮ ሲሆን አዕምሮም አካላችን ምን ማድረግ እንዳለበት ያቀናጃል›› (ያልታወቀ ሠው)

‹‹መፅሐፍ ከባድ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ዓለሙ ሁሉ በእርሱ ታጭቋልና፡፡›› (ኮሜሊያ ፈንክ)

‹‹ዛሬ አንባቢ የሆነ ነገ መሪ ይሆናል፡፡›› (ማርጋሬት ፉለር)

‹‹ዛሬ ልታነበው የምትችለውን መፅሐፍ ለነገ አታቆየው፡፡›› (ያልታወቀ ሠው)

‹‹ካነበብኩ መላው ዓለም ለእኔ ክፍት ነው፡፡›› (ሜሪ ማክሎድ ቤቱን)

‹‹አንዳንድ መፅሐፍት ነፃ ይተዉናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ነፃ አድርገው ይሠሩናል፡፡›› (ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን)

‹‹መፅሐፍ ወደፊት ልንሆን የምንፈልገውን የያዘ ህልማችን ነው፡፡›› (ኔል ጌማን)

‹‹ቤተ-መፃሕፍቶች ልክ እንደጥሩ ትዝታ መዓዛቸው ያውደኛል፡፡›› (ጃኩሊን ውድሰን)

‹‹መፅሀፍ አስተሳሰባችንን የሚያቀጣጥል መሣሪያ ነው፡፡›› (አላን ቤኔት)

‹‹ሌላ ሠው ያነበበውን ብቻ እያነበብክ ከሆነ ሌላ ሠው የሚያስበውን ብቻ ነው እያሠብክ ያለኸው፡፡›› (ሐሩኪ ሙራካሚ)

‹‹ቤት ያለመፅሐፍት ማለት አካል ያለነፍስ ማለት ነው፡፡›› (ሲስሮ)

‹‹ተራ ሠዎች ትላልቅ ቲቪ አላቸው፡፡ ብልህ ሠዎች ግን ቤተመፃሕፍት አላቸው፡፡›› (ያልታወቀ ሠው)

"መፅሀፍ ማለት በኪሳችን ይዘነው የምንዞረው በመልካም ፍሬዎች የተሞላ እርሻ ነው።” ቻይናውያን

“መፅሀፍ ስናነብ ወደ ውስጣችን በጣም ጠልቀን በመግባት ስለራሳችን የበለጠ ብዙ ነገሮችን ማወቅ እንጀምራለን።”
ዊልያም ሀዝሊት


@Zephilosophy
@Zephilosophy

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.