እውነት ለሁሉ ewnetlehulu.net dan repost
ኢትዮጵያን የአረብ ሊግ አባል የማድረግ እንቅስቃሴ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዕድገት ፋይዳ የሌለው በአንጻሩ ግን ጎጂ የሆነ እንቅስቃሴ ነው። ሊጉ ሃይማኖታዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ዓላማ የሌለው ከንቱ ስብስብ ነው። የሊጉ አባል ሀገራት ምን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አገኙ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ምንም የሚል ነው። በፖለቲካውም ረገድ አባል ሀገራቱን ከመበታተን አልታደገም። ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ሶርያ፣ የመን፣ ሊብያ እና ኢራቅ አባላት በመሆናቸው ምን አተረፉ? በሊጉ ስር የተጠለሉት የእርዳታ ድርጅቶች በብዙ ሀገራት ይንቀሳቀሳሉ። መስጊዶችንና መድረሳዎችን ከማስገንባት የዘለለ ለሰው ልጆች የሚጠቅም ምን የረባ የልማት ሥራ ሠርተው ያውቃሉ? አባላቱን ለመቀላቀል በመንግሥት እየተሰጠ ያለው ሰበብ የግብፅን ተፅዕኖ ለመቋቋም ያስችላል የሚል ነው። ነገር ግን አዋጭነቱ ምን ያህል ነው? ጉዳቶቹስ ታስበውባቸዋል ወይ? ብሎ መጠየቅ አስተዋይነት ነው። ግብፅ ከምዕራባውያን የምትቀበላቸውን አጀንዳዎች በአረብ ሀገራት ላይ የምትጭነው በዚህ ሊግ አማካይነት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሌሎቹ ሀገራት የሊጉ አባላት መሆናቸው የግብፅ ተገዢ ካደረጋቸው አባል መሆን ኢትዮጵያን ሰተት አድርጎ የግብፅ ብብት ስር የሚከት እርምጃ ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለ? የግብፅን ጫና ለመቋቋም አዋጭ የሆነው መንገድ ሌሎች ሀገራትን ጠቅልሎ የግብፅ ተገዢ ያደረገ ማሕበር ውስጥ መግባት ሳይሆን የውስጥ አንድነት ማስጠበቅና በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ረገድ የሀገራችንን ፍላጎት ከሚጋሩ ሀገራት ጋር የጋራ ሕብረት መፍጠር ነው። ግብፅ ሁል ጊዜ እኛን አጀንዳ አድርጋ በሊጉ ስብሰባዎች ላይ ማቅረቧ ሊጉን ለመቀላቀል በቂ ሰበብ አይሆንም። የግብፅን ክስና ሀሜት መስማት ካስፈለገ የግድ አባል መሆን አይጠበቅም። ሕንድን የመሳሰሉት ሀገራት በታዛቢነት እንደሚገኙት ሁሉ ታዛቢ ሆኖ መቅረብ ይቻላል። አረቦችና የአረብ ባሕል እንዳላቸው የሚያስቡ ሀገራት የፈጠሩት ማሕበር አባል መሆን አረባዊ ላልሆነችና አብዛኛው ሕዝብ ክርስቲያን ለሆነባት ሀገር ጠቃሚ አይደለም። ይሁን ከተባለም መዘዙ ከፍተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ውሳኔ እንጂ የጥቂት ፖለቲከኞችና የጥቂት ሙስሊም መሪዎች ውሳኔ ሊሆን አይገባውም።