እዚሁ ፌስቡክ ሰፈር ስለ ወንድማችን ኡስታዝ ካሚል ጦሃ የተነገረውን መልዕክት አንብቤ አግራሞት ጭሮብኛል። በርግጥ ጉዳዩ ለብዙ ዳዕዋ ላይ ላሉ ኡስታዞችና መሻይኾች እንግዳ አይደለም። ብዙዎች ከመስጅድ መስጅድ፣ ከመድረሳ መድረሳ እየተዟዟሩ ዳዕዋ ሲያደርጉ፣ ኪታብ ሲያስቀሩ፣ በየ ክፍለ ሃገሩ እየዞሩ ህዝቡን ሲያስተምሩ፤ ከጀርባቸው ያለውን ነገር የሚያጠና ሰው ውስን ነው።
እነርሱም እንደኛ ቤተሰብ አላቸው። ሳይበሉና ሳይጠጡ የሚያድሩ መንፈሶች አይደሉም። ጊዚያቸውን በዳዕዋ እስካሳለፉ ድረስ፤ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚደግፍላቸውና የሚያስፈልጋቸውን ጎደሎ የሚሞላላቸው አካል ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ ከየትኛውም ጥገኝነት ነፃ የሆነ፤ የራሳችን የሚሉት ነገር ቢኖራቸው፤ ያለ አንዳች ስጋት ዳዕዋውን ለማስሄድ ብርታት ይሆናቸዋል።
በአንድ ወቅት ከአንድ አላህ የፈቀደውን ያክል አቅም ከሰጠው ወንድም ጋር አጭር ወሬ ስናወራ፤ የተወሰኑ አቅም ያለን ሰዎች ተረባርበን አንድ ባለ 10 ወይም 12 ፎቅ የሆነ አፓርታማ ብንገነባና፤ ሁሉን ነገሩን አሟልተን ለእያንዳንዱ ዳዒ ባለ 3 መኝታ ቤት ብንሰጠው፤ በሰላም ከነ ቤተሰቡ ሳይሳቀቅ ይኖራል የሚል ሃሳብ አንስቶ እንደሚያውቅና ዳር ሳይደርስ እንደቀረ ነግሮኝ ነበር። በዳዕዋ ላይ እስከቀጠለ ድረስ የቤቱ ባለቤትም ይሆናል። አስቡት! 100 ባለሃብቶችን አነጋግረን ከእያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን ብር ብንቀበል፤ የብዙ ዳዒዎችን ራስ ምታት የሆነውን የቤት ጉዳይ መዝጋት በተቻለ ነበር።
የሚያሳዝነው የተወሰኑ ሰዎች በኡማው ትከሻ ባገኙት ዝና ሰበብ በብዙ መንገድ ገንዘብ እንዲያካብቱ በር ከፍቶላቸው ሳለ እነርሱ በዱንያ ሲጠመዱ የዲኑን ጉዳይ ደፋ ቀና እያሉ እየታገሉ ያሉ ወንድሞችን ዞረው አለማየታቸው፣ የመኪና ብራንድ ሲቀያይሩና የቤት አይነት ሲያሻሽሉ፣ የቢዝነስ አይነት ሲያስፋፉ… በዳዕዋ ላይ ላሉት ወንድሞች 2 ክፍል ቤት መግዛት ቢያቅታቸው ኪራይዋን መክፈል አለመቻላቸው ነውር ነው።
በዳዕዋው መስክ የሚታወቁ ሰዎች ቢቸግራቸው ወይም ቢያማቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ እንደ ማንኛውም ሰው ፐብሊካሊ ከማሰባሰብ ይልቅ ውስጥ ለውስጥ በውስን ሰዎች ፋይሉን መዝጋት አለመቻሉ በራሱ፤ በዳዕዋ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ተስፋን ያጨልማል። የነርሱም ሆነ የቤተሰባቸው ሞራል ይነካል። እነርሱ ዲኑ ስለገባቸው እንጂ እንደኛ ሁኔታ ግን ዳዕዋውን ጥለው ኑሮን ለማሸነፍ መርካቶ መግባታቸው አይቀርም ነበር። ቤተሰብም ጫና ሊያደርግባቸው ይችላል። ሚስትና ልጆች እኛ እየተሰቃየን ወደየት? ማለት ሊመጣ ይችላል።
አሁንም ቢሆን መሰል ችግሮች በበርካታ ዱዓቶችና መሻይኾች ቤት ታፍኖ ይኖራልና፤ ይህ ጉዳይ ከጊዚያዊ እሳት ማጥፊያ ይልቅ ቋሚ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። መጅሊሱ ራሱ በዚህ ዘርፍ ባለሃብቶችንና የውጭ ረድዎችን አፈላልጎና አስተባብሮ ብዙ መሥራት ይችል ነበር። ከአላህ ውጭ ማንም የውስጣችሁን የማያውቅላችሁ ዱዓቶች ሁሉ፤ አላህ ምንዳችሁን ይክፈላችሁ፣ በትክክለኛ መንገዱ ያፅናችሁ፣ ለብዙዎች የጅህልና ጨለማ መገፈፍ ሰበብ እንደሆናችሁት ሁሉ፤ አላህ የናንተንም የድህነት ጨለማ በእዝነቱ ይገፈፍላችሁ።
||
t.me/MuradTadessse