Posts filter


Silence
[በሚስጥረ አደራው]

የእግዛብሄር ዝምታ ሃቅ ያመላክታል
ሌላው ሌላው ጩኸት መንገድን ያስታል
ለጸሎትህ ምላሽ ለእንባህ ማበሻ
ከቃላት መልስ ይልቅ፤የእግዜርን ዝምታ በልቦናህ እሻ!

"God Speaks in the silence of the heart, listening is the beginning of prayer" _ Mother Teresa

Trust the silence, trust it even if you are desperately looking for an answer. We have mistaken God's silence as a rejection for long. Now is the time to learn the language of God, which is silence.

@enlighten_ethiopia


ፍኖተ አእምሮ-የእውቀት ጎዳና-@BOOKALEM.pdf
8.6Mb
ፍኖተ -አእምሮ
የእውቀት ጎዳና


Ego Is the Enemy by Ryan Holiday.pdf
2.0Mb
📖 TITLE: "Ego is the Enemy"

📖 AUTHOR: Ryan Holiday

📖 GENREs: Philosophy, Psychology, Self Help > Personal Dev't, Business, Leadrship, History, Productivity, Relationships & Lifestyle


Zero_to_One_Notes_on_Startups,_or_How_to_Build_the_Future_by_Peter.pdf
3.0Mb
TITLE: "ZERO TO ONE"

🔗 AUTHOR: Peter Thiel

🔗 GENRE: Business, Entrepreneurship, Management, Finance, Science, Technology, Leadership, Economics...








እንኳን ለአለም የመፅሀፍ ቀን አደረሳችሁ።
ዛሬ ቀኑን ምክንያት በማድረግ 7 ድንቅ የስነ ልቦና መፅሀፍቶችን እንጋብዛችዋለን።


ለመላው የክርስትና እምነት ተከታይ የቻናላችን ቤተሰቦች እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

መልካም በዓል ይሁንላችሁ።


Forward from: ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
‹‹ትንንሽ ደስታዎች››
(በገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹የሚያፅናኑ›› ላይ ተመስርቶ የተጻፈ)
-------



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ- ለአፍታም ቢሆን 'ሚከልሉ

በፈተና 'ሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ፣
ከኑሮ ውክቢያ- ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር 'ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች





የፍቅር ውጥን
የሚያጓጓ፣  ልብ 'ሚያግል

ቀጭን ደሞዝ…
ለአምስት ቀናት- እንደንጉስ 'ሚያንቀባርር

ሚጢጢ ቤት
እንደልብህ 'ምትሆንባት
ኡፎይ ብለህ 'ምታርፍባት


አዲስ ልብስ
ፕ-ስ-ስ-ስ!


አዲስ ጫማ
ላረማመድ የሚስማማ…


ቆንጆ ጭልፋ፣ ማንቆርቆሪያ
ብርጭቆ፣ ድስት፣ አዲስ ቂጣ መጋገሪያ


የተቆላ ቡና፣ ፈልቶ ሲወርድ፣ ሲጨስ እጣን
ትኩስ ቄጠማ ተጎዝጉዞ ያለው ጠረን



ሻይ በስኳር ከአምባሻ ጋር
ምሳ ሽሮ- እራት ምስር


ኮልታፋ ህጻን ነፍስ የማያውቅ
ያለ ሰበብ ስቆ 'ሚያስቅ


ሳያስቡት በድንገት
የሚደውል ወዳጅ ዘመድ
እንዴት ነህ ብቻ ለማለት…



ውብ የራስጌ መብራት

መጽሐፍት!  መጽሐፍት! መጽሐፍት!


ዘፈን! ዘፈን! ዘፈን!
የጂጂ፣ የቴዎድሮስ፣ የአስቴር፣ የመሐሙድ፣
የፍቅርአዲስ እና የጥላሁንዘፈን!


መታቀፍ መታቀፍ…!
በሚያፈቅሩት እቅፍ እንደሞቁ እንቅልፍ

እንቅልፍ! እንቅልፍ! እንቅልፍ!



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ ለአፍታም ቢሆን  'ሚከልሉ

በፈተና የሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ
ከኑሮ ውክቢያ ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች

✍️ሕይወት እምሻው

@Zephilosophy


በመላው አለም የምትኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ሙስሊም ወገኖቻችን እንኳን ለ1446ኛው የዒድ  አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

ዒድ ሙባረክ !!!‌‌


ጎሰሳችን ከሽፎ እንጂ

ጥዑም ጊዜ ላይ ነበርን፡፡ ወይን እየተጎነጨን፣ እየተሳሳምን፣ ድንገት ሳላቅድ፣ ሳልቀምር፣ ሳላስብበት ከአንደበቴ የውስጤ እውነት አመለጠኝ።

ትክ ብዬ ሳያት ፈገግ ብላ “እችን የመሰለች ልጅ ጠበስክ አ?” አለችኝ ወደ ራሷ እያመለከተች፤ በትንሹ ፈገግ አልኩ፡፡ ፈገግታዬን እንደ መስማማት ቆጥራ በሚያምር ፈገግታዋ እያየችኝ “እናትህማ መርቀውሃል” ስትለኝ ይሄኔ ነበር የልቤ እውነት ያመለጠኝ፡፡

ታውቂያለሽ ግን አንቺ ሕልሜ እንዳልሆንሽ፤ የመጣሽበት መንገድ፣ ዕቅድሽ፣ መርሕሽ ከእኔ ጋ መች ይሄዳል? አልኳት።

ሽማግሌ ከላክሁኝ በኋላ፣ በጋራ ስለምንወልዳቸው ልጆቻችን ስናወራ ከርመን እንዴት እንዲህ ይባላል? ሁሉ እውነት እንዴት ይወራል? የልብ እውነት ሁሉ ይዘረዘራል?! ትበሳጫለች ብዬ ነበር ግን ደግሞ የጠበኩትን የፊት መለዋወጥ አላየሁም። ረጋ እንዳለች፣ ፊቷ ሳይለዋወጥ ትክ ብላ አየችኝ፤ ቅፍፍፍ የሚል ስሜት ዋጠኝ፤ ምን አለ አስማተኛ በሆንኩ እና እንዳልሰማች ማድረግ አልያም እንዳልተናገርኩ መሆን ብችል።

ቃላቱን እርግጥ አድርጋ

“ትክክል!! ጊዜው አሳዝኖን ነው አብረን የሆነው፤ አብረን ሆነን በስሱ ሌላ የፍለጋ ሙከራ ስላልተሳካልን ነው የምንጋባው። አንዲት ቀን Messenger'ህን ከፍቼ አይቻለሁ፡፡ የምታወራቸውን እንስቶች ቀልብ ለመግዛት የምትሄድባቸውን መንገዶች፣ መሻፈዶች፣ ላጤ ነኝ ጨዋታዎች፣ ብልግናዎች ተመልክቻለሁ፤ ሁሉም ከእኔ ጋ አንድ ዓይነት ነበሩ። የማደርገውን ነበር የምታደርገው፤ ከፍቶኝ ነበር እንዳላኮርፍ፣ እንዳልጨቀጭቅህ፣ እንዳልጣላህ ካንተ አለመሻሌ አሸማቀቀኝ። የብዙ ሰዎች ትዳር እንዲህ እንደሆነ አይቻለሁ፤ ከገቡ በኋላ በልጆቻቸው ይጽናናሉ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሚስትና እና ባላቸውን እየከሰሱ ኑሮን ይገፉታል።

ለዛ ነው እንከን የለሽ ትዳር የሚያስሱት ቆመው የሚቀሩት!
በቆዩ ቁጥር መለኪያቸውን እየቀየሩ ካጣጣሉት፣ ከተጠየፉት የኑሮ ቀንበር ላይ ራሳቸውን ያገኙታል። ለዛ ነው እንደሚታረድ በግ ሁሉን እያወቅኩ ሽማግሌ ስትልክ፣ ቀለበት ስታጠልቅልኝ፣ የልቤን እውነት አፍኜ የምከተልህ፡፡”

ሲዘበራረቅብኝ ይታወቅኛል። ግራ ገባኝ፤ የሕይወት አጋርን በዚህ ደረጃ አለማወቅ ምን ይባላል? እችን ልጅ ነገሮች በዚህ ደረጃ ይገባታል ብዬ አላሰብኩም። ሴት ልጅ ትታለልልሃለች እንጂ አታታልላትም፤ እኔ እንዲህ እንደሚሰማኝ እንጂ እሷ እንደዚህ እንደሚሰማት አላውቅም ነበር።

ለምን ታድያ አብረን እንሆናለን ሁለታችንም እንዲህ ከተሰማን?

“እኔንጃ”
ምን አልባት ጊዜያችን፤
ምን አልባት ዕድሜያችን አሳዝኖን?
ምን አልባትም በዙሪያችን ያለ ውትወታ?
ምን አልባት ዘራችንን ለመተካት ካለን ፍላጎት?
ምን አልባት መላመዳችን እንዳንለያይ አግቶን ይሆን?

ምን አልባት አንዳችን ለአንዳችን ካለን ውስጣዊ ስሜት ይሆን?

ምን አልባት በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የበለጠ ስለምንዋደድ??

ምን አልባት በስሱ ሌላ ለማግኘት ያሰስነው ኀሰሳ ስላልተሳካ??”

ሰው የልቡን ሁሉ አለማውጣቱ ይሆን ቁርኝታችንን ያላሳደፈው? ባለጋራችንን አለማወቅ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? አንዳንድ ዕውቀት ምቾት አይሰጥም፡፡ ዕውቀት ትካዜን ታበዛለች እንዲል መጽሐፉ፤ አንዳንድ ውይይቶች ሽንቁር ያበጃሉ፡፡ የጀመርኩትን ወይኔን በአንድ ትንፋሽ ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሎጂክ ተዘባዝቦ ግንኙነት፣ ትዳር መመሥረት ይቻል ይሆን? እንዳለችው ፍርሀት ነው? እጦት ነው? መላመድ ነው? ምንድን ይሆን በትክክል ያጋመደን?
ምን አስቸኮለን? ምን አሸበረን? ይሄን እውነታ ከተዘራዘሩ በኋላ እንዴት ጎጆ ይቀለሳል? ልጅ ሳይመጣ፣ ንብረት ሳናፈራ፣ ኑሮ ሳይንጠን የግንኙነታችንን መዓዘን መገምገም እንዳለብን ነው የገባኝ። አሁን የምጎዳት ነገ ከምሰብራት አይበልጥም፤ ዛሬ የሚሰማኝ ሕመም ነገ ከሚጋረጥብኝ መከራ አይበልጥም፡፡

ማሬዋ ሰው ውድ ፍጠር ነው። ችኮላችን፣ ብልጣብልጥነታችን፣ በራሳችን ማስተዋል ላይ መንጠልጠላችን የእኛ የራሳችን የሆኑት ሰዎች ጋ አንድንሸዋወድ ያደርገናል። ጊዜ እንውሰድ፣ ተነጣጥለን ዙሪያችንን፣ መንገዳችንን እንመርምር፤ ብልግናችንን ይቅር እንበለው። የቆምንባቸውን ስፍራዎች እንቃኛቸው፣ ከፈጸምናቸው ጥፋቶች ጋ እንፋጠጥ፣ እናርማቸው፣ እናበጃጃቸው፡፡ ብቸኝነት አባብቶን፣ አቻ ግፊት ወትውቶን፣ መላመድ አሳስሮን፣ የቤተሰብ ግፊት ገፈታትሮን ኑሮ አይመሠረትም። የሁሉም ጓዳ እንዲህ ነው ተብሎ አዲስ ጎጆ አይበጅም፤ ሁሉም ሄዷል ተብሎ እንኳን በስሕተት መንገድ በትክክለኛ መንገድ መሄድ ተገቢ አይደለም።

ከመጣንበት መንገድ የምንሄድበት ሩቅ ነው። ራሳችንን ከእርስ በእርሳችን ነጣጥለን እናጢነው። የአሰተውሎት መንገድ ደግሞ አሜን ካልነው ባሻገር ያለውን እውነታ መጋፈጥን ይጨምራል።

ያኔ የውስጣችን እውነት ፍንትው ብሎ ይታየናል፤ ለውሳኔም ይረዳናል። ስሕተታችንን ለማረም የመጀመሪያው እርምጃ ነው።
ከዚህ ሁሉ መንገድ ከፍርሀት ጋ መጋፈጥ
በኋላ መመለስ እንዳስፈራት ታስታውቃለች፡፡ እኔም የወጠንኩትን፣ የለመድኩትን፣ የወሰንኩትን ዳግም ለመመርመር እና ለመከለስ ሳስብ ደስስ የማይል የሚቀረዝዝ ስሜት ሲወረኝ እየተሰማኝ ነው።

መፅሀፍ- አዎ እሱጋ ያመኛል
ደራሲ - አድሀኖም ምትኩ
#share


የጆሀሪ መስኮቶች: የማንነታችን አራቱ ክፍሎች
=====================
የጆሀሪ መስኮቶች ከሰው ጋር እንዲሁም ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት በተሻለ ለመረደት የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡ ጆሀሪ ስያሜውን ያገኘው ንድፉን በጋራ ከፈጠሩት የስነ ልቦና ባለሞያዎቹ ጆሴፍ ለፍት እና ሀሪንግተን ኢንግሀምን ስም በማቀናጀት ነው፡፡ ማንነታችን በአራት ሊከፈል ይችላል፦ ግልፅ፣ ድብቅ፣ የተሰወረ እና ጨለማ፡፡

ግልፁ ማንነት፦
-----------
ይሄኛው ስለራሳችን እኛም ሌላውም ሰው የሚያውቀው ሲሆን ድርጊቶችን፣ እውቀትን፣ ክህሎትን ያጠቃልላል፡፡ ስለዚህኛው ማንነታችን ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ችግር የለብንም በተጨማሪም ሰዎች ስለዚህ የማንነታችን ክፍል በሚሰጡት አስተያየት በብዛት እንስማማለን፡፡

ድብቁ ማንነት፦
------------
ይህ ማንነት ራሳችን የምናውቀው ሲሆን ከሌሎች የተደበቀ ነው፡፡ በዚህ መስኮት ውስጥ ያሉ ማንነቶቻችንን ስለምናፍርባቸው ወይም የግል ህይወታችን ስለሆኑ  ተጋላጭ እንዳንሆን ከሌሎች እንደብቃቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ በትህትና ምክኒያት ሰዎች እንዲያውቁ የማንፈልጋቸው ችሎታዎቻችን እውቀታችንንም ያካትታል፡፡

የተሰወረ ማንነት፦
-------------
ይሄኛው ሌሎች ሰዎች የሚያዩት ከኛ ግን የተሰወረው ማንነት ነው፡፡ ምክኒያታዊ እንደሆንን እናስብ ይሆናል ሰዎች ግን ግትር እንደሆንን ነው የሚያውቁት፡፡ ወይም ራሳችንን 'ምንም እንደማያውቅ 'ልናስብ እንችላለን ሰዎች ግን በጣም ብልህና አስተዋይ እንደሆንን ሊረዱ ይችላሉ፡፡  በዚህ መስኮት ውስጥ ነው ሰዎች ቃላችን እና ድርጊታችን እንደሚለያይ የሚያስተውሉት፡፡

ጨለማ (የማይታወቀው) ማንነት፦
------------------------
ይህ ማንነት በራሳችንም ሆነ በሌሎች የማይታወቅ ክፍል ነው፡፡ ጥሩም ጥሩ ያልሆኑ ሀሳቦች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡

በአጠቃላይ የ ጆሀሪ መስኮቶቸ ራሳችንን ለመረዳት ከዚያም ለማገጎልበት እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያግዝ ንድፍ ነው፡፡

ዶ/ር ዮናስ ላቀው

መልካም ጊዜ!


Forward from: ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
ከከፍታ ምሳሌነት ወደ የኋላቀርነት ማሳያነት ለምን ተሸጋገርን?

ታሪክን ከእኛ ጋር አያይዤ ሳስብ ያለፉ ኹነቶቹን ምርኩዝ አድርገን ኢትዮጵያኖች "ትልቅ የነበረን ሕዝቦች ነን" የሚል ጥቅስ በየልባችን ሰንቀን፣ ጀርባችን ላይ በሚሰማን ሙቀት አማካኝነት ያለንበትን ኹኔታ እየለካን “ደህና ነን " እያልን የምንኖር መሆናችን አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለዛሬ ጉድለታችን፣ ለአሁን ክፍተቶቻችን፣ ለስንፍናችን ሰበብ ፍለጋ ከአጽም ጋር ትግል ላይ መክረማችንም ይደንቀኛል፡፡

ቀዳሚ እንጂ ተከታይ ተሸናፊ ሳይሆን አሸናፊ እንደነበረን የቀደምት ስልጣኔዎቻችንን ምስክር ናቸው፡፡ ታዲያ ከቀዳሚነት ወደ ተከታይነት ፤ከክብር ወደ ውርደት፤ ከከፍታ ምሳሌነት ወደ የኋላቀርነት ማሳያ መቼ?፣ ለምን? እና እንዴት? ተሻጋገርን የሚለውን ለማወቅ  ታሪካችንን መመርመር ያስፈልጋል። ሌላው ቢቀር ታሪክን በመፈተሸ ለውጥ በማስተናገድ ሂደት ላይ የሚፈጠሩ መሰናክሎችን መቀነስ ይችላል፡፡

ዛሬ ሙሉ ሰውነታችን በድህንነት፣ በአስተሳሰብ ልልነት፣ የሚበጀንን ስልጣኔ በማጣት ቆሻሻ ታወሯል። ይህን ቆሻሻ የአመክንዮ እንዶድ በመቀንጠስ፣ ከሳይንስና ከጥበብ ወንዝ መመራመርንና መጠየቅን በመጭለፍ እንደመጽዳት ፋንታ በተቃራኒው እኛ እያደረግን ያለነው በአንድ እጃችን የድህንነት እከካችንን እያከክን፣ በሌላኛው ደግሞ ላለንበት ኹኔታ ምክንያት ናቸው ወደ ምንላቸው እየጠቆምን ጊዜያችንን በመንቀፍ እና በመተቻቸት መፍጀት ነው።

አሁን ላይ ላለንበት ኹኔታ ሰበብ ፍለጋ ከቅርጫታችን ውጪ በሚገኙ አካላት ላይ ጣት የመቀሰር አባዜ ማብቃት አለበት፡፡ ማውገዝ አለብንም ከተባለና ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ገዢዎችን፣ ለሆዳቸው ያደሩትን የማኅበረሰብ ወኪሎቻችን እና የሃይማኖት መሪዎችን ነው (ኹሉም ባይሆኑም ውሉ)፡፡ በየትውልዱ ብቅ ለማለት ድፍረት ያገኙትን እና ሊያነቁን የሞከሩቱን ሲያሳድዱ፣ ሲያስሩ እና ሲገድሉ እንደነበር ስለ ታሪካችን የሚናገሩትን መጽሐፍት ይነግሩናል። ኾኖም እነሱንም ቢሆኑ የሰሩት ስህተት ዳግም እንዳይከሰት ለመማሪያነት ካልተገለገልንበት በስተቀር ስማቸውን እየጠራን መቆዘሙና የጥፋተኝነት ካባ እያከናነቡ መሰንበቱ ምኑም አይጠቀመንም! መወጋገዝን ካመጣን አይቀር ራሳችንንም እናውግዝ፤ የማይጠቅሙ ባህሎችን መርምሮ ጥቅም ጉዳቱን ሊነግረን ላይ ታች የሚል አንቂዎቻችንን ያልሆነ ስም ሰጥተናልና፤ ልፋታቸውን መና ማድረግን የጀግንነት መስፍርት አድርገን አስቀመጠናልና!

ኢትዮጵያውያን አሁን ላለንበት ማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች ምን ይሆኑ ብዬ ብጠየቅ "ባይመችን እንኳን ተቀመጡ ባሉን ቦታ ላይ ቦታ ከመቀየር ይልቅ መቀመጫችንን እያታከክን ለመኖር በመመርጣችን ነው" ብዬ አስቀድሜ እመልሳለሁ፡፡ ዛሬም ድረስ የተቀመጥንበት ቦታ እንደቆረቆረን ብንገኝም ማን እንዳስቀመጠን እና ለምን እንደተቀመጥን አልጠየቅንም፡፡ ባይሆን መቀመጫችንን ከቦታው ጋር ለማለማመድ ጊዜና ጉልበታችንን እናባክናለን። ግና አሁንም ቢኾን አረፈደምና እንጠይቅ። ካልሆነ ግን ከድጡ ወደ ማጡ መንሸራተታችን አይቀርልንም(መንሸራተቱንማ ከጀመረን ቆይተናል፡፡)

ሌላኛው ምክንያት ብዬ የማስቀምጠው 'የሀገራችን ልክ ያልሆነና ወደ ኋላ ጎታች የሆነ ማኅበረሰባዊና ፓለቲካዊ ሥርዓት ጠልቆና ጠንክሮ በሀገራችን በመገንባቱ ነው' የሚል ነው፡፡ ይህ ሥርዓት  የሕዝብን ጊዜያዊ ስሜት በመኰርኰር የተካኑ ብልጣ-ብልጥ አላዋቂ ብሔርተኞችንና ጥቅመኞችን ንጉስ አድርጎ የሚያሾም ፤ በየዘመኑ ያሉብንን ችግሮች በመለየት ያሳዩንን፣ወደ ኋሊት እየተጓዝን መሆኑን በማስመልከት ሊያነቁን የሞከሩትን  አገርና ሕዝብ ወዳዶችን ደግሞ የበዪ ተመልካች የሚያደረግ ነው።

ትልቁ ችግራችን በርካታ ነገሮችን ሳንመረምር፣ ሳንፈትሽ እና ሳንጠይቅ እንደተነገረን የምንቀበል መሆናችን ነው።ብዙዎቻችን ስለ አንድ ነገር የሚኖረን ድምዳሜ አሊያም “እውነታው' ተብሎ የሚነገረንን ሐሳብ ለመፈተሽና ለመፈተን ጥረቱና ድፍረቱ የለንም።፡ በቸልተኝነት አውሎ ንፋስ የተወሰድን፣ ከፍርሃት ጥላ ገለል ማለት የተሳነን ሆነናል። አጎንብስ ስንባል እሺ፣ ተቀመጥ የሚል ቃል ስንሰማ ዝፍዝፍ፣ ሩጥ የሚል ድምጽ ስንሰማ ፈርጣጭ ሆነናል።

መፅሀፍ - ጥያቄዎቹ
ደራሲ- ፍሬው ማሩፍ

@zephilosophy
@zephilosophy


Forward from: Dildiy - (ድልድይ)
ጥበቃ... [Expectation]

___

["Blessed is he who expects nothing, for he shall never be disappointed." — Alexander Pope]

___

መጠበቅን መሰላል እንደመውጣት ነው የማስበው፤ በጣም ትጠብቃለህ ማለት በመሰላሉ ከፍተኛ እርካብ ላይ አለህ ማለት ሲሆን ጥበቃህ ዝቅተኛ ወይም መካከለኛ ነው ማለት ደግሞ የመሰላሉን ተመሳሳይ ቦታ ይዘሃል ማለት ነው...


እንግዲህ መሰላል የወጣ ሰው ዕጣፈንታ ሁለት ነው... ወይ እንዳወጣጡ ይወርዳል፣ አልያም ከደረሰበት ነጥብ እርካብ ከድቶት ይወድቃል... 


[የመጠበቅ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው መሰላሉ ላይ በሰቀለህ እውነታ ነው... ብዙውን ጊዜ ግን ጥበቃ ከእጅ ካለው የታወቀ ሁኔታ ይልቅ ባልተጨበጠ ተስፋ ላይ የሚመሰረት ይሆንና መውደቅን ውጤቱ ያደርጋል...]


በመስተጋብራችንም ሆነ በግል ልምምዳችን ውስጥ እጅግ አደገኛው ስሜት መጠበቅ ሲሆን አስከፊ ውጤቱ ደግሞ የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር የሚፈጠረው ስብራት ነው... 


ይህ ጥበቃ የታክሲ ሰልፍ ወይም የቦኖ ወረፋ አይደለም... ጊዜ ሲደርስ የምትደርስበት ወይም የመሆን ዋስትና የጨበጠ አይደለም... የስሜት ዕዳ ነው... የቅጽበት ክስተት... ቀጥሎ ምን እንደሚሆን የማይታወቅባት ዓለም ዕዳ...


እኛ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሕይወት ጋር በጸጥታ የምንገባው ውል አለን... ኮሽታ ሳናሰማ በተስፋ፣ በህልም፣ በምኞት በመፃኢ ላይ የተመሰረተ ስምምነት እንፈጽማለን... በአዕምሮአችን ውስጥ ጥንቅቅ ብለው የተሰደሩ በርካታ ውብ ስዕሎች አሉን... ጠንክረን ስለሰራን፣ አጥብቀን ስላፈቀርን፣ ተግተን ስለጠበቅን ሕይወትም በዚያው መሰረት ምላሽ እንደምትሰጠን እናስባለን - እናምናለንም... ግና ምኞትና እውነታ ሁሌ አይሰምሩም... ያንጊዜ ደግሞ የመንፈስ ስብራት ይገጥመናል...


ስብራት ያልሰመረ ጥበቃ ውጤት ነው... ብዙ የለፉለት ግንኙነት ምላሽ ሲያጣ፣ ለረጅም ጊዜ የጠበቁት ዕድል ቅዠት ሲሆን፣ እንደ ጣልንባቸው ተስፋና እንደ ሰጠናቸው ቦታ ሰዎች ሳይከውኑ ሲቀሩ ህመም ይገጥመናል... ህመሙ ግን ስለ እጦታችን ብቻ አይደለም... ከእጃችን በሌለ ነገር ላይ የገነባነው ተስፋ ከፊታችን ብን የማለቱ ሃቅ ብሎም ለርሱ ብለን ያጠፋነው ጊዜ የሚፈጥረው ቁጭትም እንጂ...


“Disappointment is a sort of bankruptcy—the bankruptcy of a soul that expends too much in hope and expectation.” — Eric Hoffer


[ነገሩን በምሳሌ እናፍታታው...]


ያፈቀርካት ልጅ ከልብህ የቀለስክላትን ጎጆ አክላ እንድትከሰትልህ ትጠብቃለህ - በእርሷ ልብ ውስጥ ዳስ የተጣለለት ተፈቃሪ ሊኖር መቻሉን ግን ትዘነጋለህ...


[እናም - 'አይሆንም' አለችኝ በሚል ሰበብ ልብህ እንክት ትላለች...]


___

ሃሳብህን ሰው ሁሉ እንዲረዳልህ ትጠብቃለህ - ግና ሁሉም ሰው በየራሱ ንሸጣ፣ በየራሱ መንገድ እንጂ ባንተ መንገድ ብቻ ነገርህን ሊገነዘብ እንደማይችል ትዘነጋለህ...


[በዚህ ምክንያት ድብርት ትከናነባለህ...]


___

ሰዎች ሁሌም በበጎ ቃልና በፈካ ፊት እንዲቀበሉህ ትጠብቃለህ - ሆኖም በብዙ ዓይነት የስሜት መዋዠቅ ውስጥ እንደሚያልፉ፣ ያም ቀናነታቸውን እንደሚያደበዝዘው ትዘነጋለህ...


[በዚህ ምክንያት ቀንህን አስረክበህ ትውላለህ... አንዳንዴም ቂም ቋጥረህ ግንኙነትህን ታበላሻለህ...]


___

ሎተሪ እንዲደርስህ ትጠብቃለህ - ሆኖም ከብዙ ሚሊዮኖች ጋር የሚደረግ ውድድር መሆኑን ትዘነጋለህ...


[በዚህ ሰበብ ዩኒቨርሱን በአድሎ ፈፃሚነት ትከሳለህ...]


___

በድካምህ ልክ ሹመት፣ በጥረትህ ልክ ሽልማት ትጠብቃለህ - የሰዎች ሚዛን ያለው ራሳቸው ጋ መሆኑን ግን ትዘነጋለህ...


[እናም ይህን ሰበብ አርገህ የስራ ሞራልህን ትገድላለህ...]


___

ብዙ ድካምና ሃብት ያፈሰስክበት ቢዝነስ ፈጥኖ ውጤታማ እንዲሆን ትጠብቃለህ - የጊዜና የሁኔታዎችን ምቹነት የማጤን አስፈላጊነት ግን ትዘነጋለህ...


[በዚህ ምክንያት የሚያድግ ወረትህን ትቀብራለህ፣ ሌላ የመጀመር ድፍረትህንም ትሰዋለህ...]


___

በችግራቸው ጊዜ አለሁ ያልካቸው ሁሉ ኑሮ ሲፈትንህና ምርግ ሆኖ ሲጫንህ እንዲደርሱልህ ትጠብቃለህ - ከጓዳቸው ያደፈጠ፣ ከገመናቸው የተሻጠ ምስቅልቅል ሊኖር እንደሚችል ግን ትዘነጋለህ...


[አዎን - በዚህ ተቀይመህ ሰው ትርቃለህ... የልብህንም ሰዎች ታጣለህ...]


___

ወዳጆችህ በሃዘንህ ጊዜ ጎንህ ተገኝተው እንባህን እንዲጠርጉ፣ በክፉ ጊዜህ ገመናህን እንዲሸሽጉ፣ በደስታህ ጊዜ ድግስህን እንዲያደምቁ ትጠብቃለህ - ከእነርሱ ታዛ ሰው የማይደርስበት ለቅሶና ምሬት፣ በሳቅ የሚከልሉት ችግርና ብሶት ሊኖር እንደሚችል ግን ትዘነጋለህ...


[እናም በዚህ ሰበብ ሰው የምታይበት ዓይን፣ የምታቀርብበት ወሰን፣ የምታርቅበትም ሚዛን ይዥጎረጎራል...]

___

"We are all prisoners of our expectations." — Georges Bernanos

___

[ታዲያስ?...]


እንግዲህ ጥበቃ የአዕምሮ ቅኝት ነውና ይቆጣጠሩታል እንጂ አያስቀሩትም... ይመጥኑታል እንጂ አልቦ አያደርሱትም... 


ማግስቱን ለድብርት፣ ከርሞ ለስብራት ምክንያት እንዳይሆን ግን ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል...

___

[ሦስት መላዎች ይታዩኛል...]

___


፩) Flexibility - 'ይህን ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ' ከማለት ይልቅ 'ይህ ባይሆን ያንን አሳካለሁ' ብሎ ማሰብ... ችክ አለማለት... አማራጮችን ማየት... አንዳንድ ጊዜ ያጣነው በመሰለን አንድ ነገር ፈንታ ያልጠበቅነው እልፍ ስጦታ ሊደርሰን ይችላል... የጠበቅነው የሚጎዳን፣ የሚሰጠን የሚያስደስት ሊሆንም ይችላል...


፪) እንዲሆን የሚፈልጉት ነገር ላይ what if መቀላቀል... ባይሆንስ ብሎ ማሰብ... ቢቻል የጉዳዩን ተጨባጭነት ማጤን፣ አልያም ጥበቃን ማመጣጠን...


[በመሰላሉ ግርጌ ላይ መቆየት... ነገሩን የሚያመጣው ወይም የሚያስቀረው ጥበቃው ሳይሆን የጉዳዩ ተጋጋዥ ሁኔታዎች ሕብር ነው... ሊመጣ ያለን - ባለመጠበቅ አታጣም፣ የማይመጣንም በመጠባበቅ አትወልድም...]


፫) መቀበል... የሆነውን እንደመሆኑ ማስተናገድ... ስለ ጉዳዩ ከመብሰልሰል ይልቅ ክስተቱን እንደሁኔታው ተቀብሎ ወደፊት መጓዝ... ባለፈው ጎርበጥባጣ የባከነ ጉልበትህን ሳይሆን ቀሪው  አቅምህ የሚያስወጣህን አቀበት ማስተዋል... Let it go!

___

"We must accept finite disappointment, but never lose infinite hope." — Martin Luther King Jr.
___

መልካም አሁን!!

___

@bridgethoughts


ዐፄ ምኒልክ ከዐድዋ ድል በኋላ ለአውሮጳና ለሞስኮ መንግሥታት በላኩት ደብዳቤያቸው፤ የኢትዮጵያውያንን ታላቅ የሆነ የመንፈስ ልእልና የተላበሱ፣ ሰብአዊነትን፣ ርኅራኄንና ይቅር ባይነትን ገንዘብ ያደረጉ እና የላቀ የሞራል ከፍታ/High Moral Standards ያላቸው የታላቅ ሕዝብ መሪ እንደሆኑ አስመስክረዋል። ለአብነትም ዐጤ ምኒልክ ከዐድዋ ድል በኋላ መጋቢት 23 ቀን 1988 ዓ.ም. ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው፤

"… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ እርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግ ተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ሰዎች ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡"
ብለዋል


ቀስ በቀስ የምታጡት ነገር!

አላግባብ የአስተዳደራችሁትን (manage ያላደረጋችሁትን ወይም mismanage ያደረጋችሁትን) ነገር ቀስ በቀስ ታጡታላችሁ፡፡

በእጃችሁ ያለው የገንዘብ መጠን በዛም አነሰም፣ በትክክል manage ካደረጋችሁት ትጠብቁታላች፣ ታባዙትማላችሁ፡፡ አለዚያ ግን ቀስ በቀስ ከእጃችሁ ይወጣል፡፡

የእኔ ናቸው የምትሏቸው ቤተሰቦች፣ ቀድሞውኑ (by default) የእናንተ ስለሆኑ ብቻ የትም አይሄዱም ብላችሁ ችላ ካላችኋቸውና ግንኙነታችሁን በትክክል manage ካላደረጋችሁት ትዳርም ሆነ የቅርብ ቤተሰብ ሁኔታ ቀስ በቀስ ከእጃችሁ መውጣት መጀመሩ አይቀርም፡፡

በነጻ የተሰጣችሁ ጤንነት የተሰኘውን የፈጣሪ ስጦታ፣ ስሜትን በሚገባ በመያዝ፣ በጥሩ አመጋገብ፣ በስፖርትና በበቂ እረፍት በትክክል manage ካላደረጋችሁት፣ በኋላ ካጣችሁት በኋላ ነው የምትባንኑት፡፡ አብዛኛው ጊዜ ደግሞ ስትባንኑ ሁኔታውን ለመቀልበስ ጊዜው አንዳለፈበት ትገነዘባላችሁ፡፡

የምትመሩትና የምታስተዳድሩት የሰው ኃይልም ሆነ ሕዝብ በትክክል ካላስተዳደራችሁት (mismanage ካደረጋችሁት) አብሮነቱንና አጋርነቱን ቀስ በቀስ እያጣችሁት መሄዳችሁ አይቀርም፡፡

የጀመራችሁት ንግድ (business) ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ በትክክል manage ካደረጋችሁት ታሳድጉታላች፡፡ ካላደረካችት ደግሞ ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ ይሄዳል፡፡

እያለ መርሁ ከብዙ ዘርፎች አንጻር እውነታነቱ ያው ነው፡፡

አንድን ነገር በትክክል manage ማድረግ ማለት፣ ትክክለኛውን መርህ መከተል፣ በእቅድ መኖር፣ ስህተት ሲኖር ቶሎ ማረም እና የመሳሰሉትን አስፈላጊ ሂደቶች ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው፡፡

ዶ/ር እዮብ ማሞ


የጅምላ ኢጎ
✍️ኤካህርት ቶሌ

ኢጎ በግላዊ ማንነቱ አለመርካቱን ለማመልከት ከሚያደርጋቸው ሙከራዎች አንዱ ከቡድን ጋር አንድ በመሆን የማንነት ስሜቱን ማስፋፋት እና ማጠናከር ነው። እነዚህ ቡድኖች ሃገር፣ብሄር፣ የፓለቲካ ፓርቲ፣ ማህበራት፣ ተቋማት፣ ሴክተሮት፣ ክለብ፣ አደገኛ ቦዘኔዎች ፣ የእግር ኳስ ቡድኖች እና ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ የሆነ ሠው እኔነቱን ትቶ ለጅምላው መልካም ነገር ሲል ምንም ዓይነት የግል ጥቅም፣ ችሮታ ወይም ክብር ሳይፈልግ፣ ህይወቱን እስከመሰዋት ድረስ ሲሰራ ግላዊ ኢጎው የከሰመ ሊመስል ይችላል። የቡድኑ  ያህል ዋጋ ቢከፍሉም፣ደስተኝነት ሙሉነት ይሰማቸዋል። ከኢጎ ባሻገር የሄዱ መስለው ይታያሉ። ነገር ግን  ከኢጎ ነፃ ወጥተው ሳይሆን  ኢጎ ከግላዊ ወደ ጅምላዊ ተሸጋግሮ ነው።

የጅምላ ኢጎ ልክ እንደ ግል ኢጎ ግጭትንና ጠላትን የመፈለግ፣  በተሳሳቱ ሌሎች ላይ ትክክል መሆንን መፈለግ እና የመሳሰሉት ተመሳሳይ ባህሪያት አሉት። ፈጠነም ዘገየም፣ ቡድኑ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ምክንያቱም ግጭትንና የራሱን ክልል ለመወሰን ብሎም ማንነቱን ለማግኘት ተቃውሞን ሳያውቅ ይፈልግ ነበር።አባሎቹም ማንኛውም ከኢጎ ተነሳሽነት የሚፈጠረውን ተግባር ጋር ተከትሎ የሚመጣውን ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ። በዚህም ጊዜ የነበሩበት ቡድን ጠንካራ የጥፋት ተልዕኮ እንደነበረው ሊነቁና ሊገነዘቡ ይችላሉ።

የነበርክበት እና እራስህንም ያዛመድክበት ብሎም ስትሰራለት የነበረው ቡድን፣ በርግጥ የጥፋት መሆኑን በድንገት ስትረዳ በመጀመሪያ የሚያም ይሆናል፡በዚያ ጊዜ አንዳንዶች የበለጠ ክፉና መራር ይሆናሉ። ይህም ማለት የቀድሞው ሃሳብ፣ውዥንብር እና የወደቀ መሆኑን ሲረዱ ወዲያውኑ የሌላ አይነት ዕምነት ስርዓት ይቀበላሉ ማለት ነው። የኢጎአቸውን ሞት ከመቀበል ይልቅ፣ ከዚያ በማምለጥ በሌላ አዲስ ኢጎ ዳግም ይወለዳሉ።

የጅምላ ኢጎ ጅምላውን ከፈጠሩት ግለሰቦች ኢጎ በላይ ማስተዋል የለሽ ነው። ለምሳሌ ሰልፈኞች (ጊዜያዊ የጅምላ ኢጎ ስብስቦች) ግለሰቦቹ ከሰልፈኞቹ ውጪ ቢሆኑ ኖሮ የማይፈፅሙትን አይነት ከፍተኛ ጥፋት የመፈፀም አቅም አላቸው። በግለሰብ ደረጃ ቢሆን ኖሮ ዕብደት ተደርጎ የሚወሰድን ተግባር፣ አገሮች ግን በተደጋጋሚ ሲፈፅሙት ይታያል።

የሰዎች፣ የብሄሮችና የሐይማኖት ተቋማት የጅምላ ኢጎ ፣ “እኛ ቅዱሶች፣ ሌሎች እርኩሶች” የሚል ጠንካራ የፓሪኖያ ችግር አለበት። የስፔናውያን ስቃይ፣ አፈንጋጮችንና “ጠንቋዮች”ን ማንገላታት እንዲሁም ማቃጠልና፣ እስከ ኣንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ድረስ የደረሰው የሐገራት ግንኙነት፣ አጠቃላይ የኮሚዩኒዝም ታሪክ፣የመስቀል ጦርነት ፣ጀሀድ፣ ቀዝቃዛው ጦርነት፣ በ1990ዎቹ በአሜሪካ የነበረው ማካርቲዝም፣ እስካሁን የዘለቀው የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት፣ ሁሉም በሰው ልጆች ውስጥ በእጅጉ አሰቃቂ እና በፅንፈኛ ጅምላዊ የኢጎ በሽታ የተሞሉ የታሪክ ክፍሎች ናቸው።

ግለሰቦች፣ ቡድኖች አገሮች እስተዋይ ባልሆኑ ቁጥር፣ይሄ ኢጎአዊ በሽታ ወደ አካላዊ ጥቃት  መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። አካላዊ ጥቃት ኋላቀርነት ይሁን እንጂ
አሁንም ድረስ የተንሰራፋ ተግባር ነው። ምክንያቱም ኢጎ የእራሱን አሸናፊነት መጠበቅ፣ እራሱን ትክክል ሌሎች ስህተት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሲል ይጠቀምበታል። ማስተዋል የለሽ በሆኑ ሠዎች መካከል ትንንሽ ክርክሮች ወደ  አካላዊ ጥቃት በቀላሉ ያመራሉ። ክርክር ምንድን ነው? ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሠዎች የየራሳቸውን ምልከታ ይገልፃሉ፤ እነዛም ምልከታዎች ይለያያሉ። እያንዳንዱ ሠው ምልከታው ከፈጠረለት ሃሳብ ጋር አንድ ከመሆኑ የተነሳ፣ ሃሳቦቹ ጠንክረው የማንነትና የሃሳብ ስሜት ላይ የዋሉ አዕምሮአዊ እቋም ይሆናሉ። በሌላ አባባል ማንነትና ሃሳብ ይቀላቀላሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ  ለአመለካከቴ ስከራከር ወይም ስቆም ፣ ልክ እራሴን እንደምከላከል ይሰማኛል፤ እተውናለሁም። ሳላስተውለው ልክ ለህልወናዬ እንደምዋጋ እሆናለሁ፤
ስሜቶቼም የዚህን ማስተዋል የለሽ እምነት ያንፀባርቃሉ። እበሳጫለሁ፣ እናደዳለሁ፣እከላከላለሁ ወይም ኃይለኛ እሆናለሁ። እንዳልጠፋ በሚል ስጋት፣ ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል
ማሸነፍ አለብኝ።ውዥንብሩ ያ ነው። ኢጎ እራሱ የማትመለከተው አዕምሮ በመሆኑ ምክንያት አዕምሮም ሆነ ሀሳባዊ አቋሙ ከማንነትህ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አያውቅም።

@zephilosophy


Forward from: ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy
አሁንን የመኖር ሀይል

በመጀመሪያ አሁን የጊዜ አካል አይደለም። ጊዜ እንዲኖር ያለፈው ወይም የወደፊቱ መኖር አለበት። አሁን የጊዜ አካል ሳይሆን ዘላለማዊ (eternal) ነው። ልብ ብላቹ ካሰባችሁት ጊዜ ያለው አእምሮአችን ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም ምናስባቸው ሀሳቦች በጊዜ ውስጥ ማለትም በባለፈው እና በወደፊቱ ጊዜ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። እስኪ ምታስቧቸው ሀሳቦች ላይ ለተወሰነ ደቂቃ ለማተኮር ሞክሩ፤ ከዚያ አእምሮአችሁ በባለፈው(past) እና በወደፊቱ(future) ላይ ተጠምዶ ታገኙታላቹ።

ስለ አሁን(present) ማሰብ አትችሉም። አሁን ላይ ማሰብ ሳይሆን መኖር (አእምሮ አልባ መሆን) ነው ምትችሉት። እስኪ ስለአሁን ለማሰብ ሞክሩ ምን ሀሳብ ወደ አእምሮአችሁ መጣ? በርግጠኝነት ምንም ማሰብ አልቻላችሁም፤ ስለዚህ ሀሳብ የሚያርፍበት ጊዜ ይፈልጋል ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ምንም የማያስብ ስራፈት ትሆናላችሁ ማለት አይደለም። አሁን ላይ መኖር ስትጀምሩ ከአእምሮአችሁ በላይ መሆን ትጀምራላችሁ። ስለዚህ አእምሮአችሁን ምን ማሰብ እንዳለበት የምትወስኑት እናንተ መሆን ትጀምራላችሁ ማለት ነዉ። ነገር ግን አእምሮ ካለናንተ ፍቃድ በራሱ ማሰብ ያቆማል። አእምሮአችሁ እናንተ ሳትፈልጉ በሀሳብ የሚጠመድ ከሆነ ግን አሁን ላይ እየኖራችሁ አይደለም ማለት ነው።

አሁን ላይ ለመኖር ተደጋጋሚ የተመስጦ (meditation)  ልምምድ ያስፈልጋችኃል፤ ምክንያቱም ከአእምሮአችሁ ካልተላቀቃችሁ አሁንን መኖር አትችሉም። ተመስጦ (meditation) ማለት ደግሞ ምንም ሳይሆን እራሳችንን ከአእምሮ ቁጥጥር የምናላቅቅበት መንገድ ማለት ነው። ከአእምሮአችሁ ስትላቀቁ ህይወትን ከዳር ቆማችሁ እንደ ተመልካች መታዘብ ትችላላችሁ።

ህይወትን በሙላት መኖር ከፈለጋችሁ ከኢጎ (ከአእምሮ ቁጥጥር) መላቀቅ ይኖርባችኃል። ኢጎ ከሌሎች የተሻላችሁ እንደሆናችሁ እንዲሰማችሁ እና ሌሎችን እንድትጨቁኑ ይነግራችኃል። አለማችን ላይ የምናየው ጦርነት፣ ክፉት፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ፅንፍ የወጣ ሀይማኖትን ተገን ያደረገ የሰዎች ጭፍጨፋ በሙሉ የኢጎ ውጤቶች ናቸው። ሁላችንም ውስጥ አይነቱ ይለያይ እንጂ የሆነ አይነት ኢጎ አለ። ኢጎ አሁንን እንዳንኖር የሚገዳደረን ቀንደኛ ጠላታችን ነው።

ሁላችንም ኢጎን አሽቀንጥረን መጣል ይኖርብናል። አለበለዚያ ሰዎች በሰላም የሚኖሩባት የተዋበች ምድር ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ከኢጎ መላቀቅ እንደምናስበው ቀላል አይደለም። ከህፃንነታችን ጀምሮ የሆነ የኢጎ ማንነት ስንገነባ ኖረናል። ኢጎአችን ትክክለኛ ማንነታችን እስኪመስለን ድረስ ከስብዕናችን ጋር ተጣብቋል። አንዳዶቻችን የብሔር ማንነትን፣ ሀይማኖትን፣ ግለሰባዊ አስተሳሰብን፣ የበላይነት ስሜትን፣ የቆዳ ቀለምን እና የመሳሰሉትን እንደ ተፈጥሮአዊ ማንነት በመቁጠር ከሌሎች ጋር እስከ መጋጨት እና መተላለቅ የሚያደርሱን የኢጎ ገፅታዎች አሉን። እነዚህ ኢጎዎች ከፍ ሲሉ በሀገራት ደረጃ አሁን የምናየውን ጎራ ለይቶ መጠፋፋት ያስከትላል።

አእምሮአችን ህይወትን ውስብስብ አድርጎብናል። ህይወት ግን በጣም ቀላል ናት። አእምሮአችን ማፍቀር አይችልም፤ አእምሮአችን የሚችለው ማስላት ነው። ህይወት አሁን ናት። ከአሁን ወጪ ማድረግ ምትችሉት ነገር አለ? መኖርስ? ያለፈው እና የወደፊቱ ጊዜ ቅዠት ብቻ ናቸው። ያለፈ የምንለው ጊዜ ስንኖርበት አሁን ነበር፤ የወደፊቱም አሁንን ሆኖ ነው ሚመጣዉ። አሁን ላይ መኖር ስትችሉ ከሁለንተና ጋር ትዋሀዳላችሁ።

ብዙ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለምሳሌ፦ ተራራ መውጣት፣ ከፍተኛ ህመም፣ ከባድ የህይወት ፈተና ሲያጋጥማቸው አሁን ላይ የመገኘትን አጋጣሚ አግኝተዋል። ነገር ግን አሁን ላይ ለመገኘት የግድ እንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች መጠበቅ የለባችሁም። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ አሁን ላይ መገኘት ትችላላችሁ።

@zephilosophy
@zephilosophy


Forward from: Tesfaab Teshome
"ክፉ ቀኖች ያልፋሉ ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል"
(ተስፋኣብ ተሾመ)
* * *

ሀ፥ በህወሓት እና በኦነግ መካከል ያለው የፖለቲካ ሽኩቻ የመስዋዕት በግ ፈለገ። ሁለቱ እንዲሸናነፉ ያለ ሀጢያቱ የሚታረድ ሚስክን ተፈለጎ ተገኘ። ያ ምስክን በሀረርጌ ገጠራማ አከባቢ የተከበረ አባት ነው።ሰውዬው እንደዋዛ "ኦነግ ገደ*ለው" ተብሎ ተገ*ድሎ ተጣለ። የሰውዬው ሞት ቤተሰባዊ ምስቅልቅል ወለደ።

ጥላዬ ታደሰ የተባለ ሰቃይ ተማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበር። የአባቱን ሞት የሰማ ቀን ሰማይ ተደፋበት። ተስፋው ጨለመ፥ የመኖር ፍላጎቱ ትቶት ተሰደደ።
ጥላዬ ታደሰ ከአባቱ ሞት በኋላ ሌላ ሰው ሆነ። ሙሉ ለሙሉ ሱስ ውስጥ ተዘፈቀ። ጫት ፥ ሲጃራ እና አረቄ መደበቂያው ሆኑ። ሀዘኑን በአረቄ ሸሸገው።

ጥላዬ ሱሰኛ ሆነ ሲባል ዝም ብሎ ሱሰኛ አይደለም የሆነው። አንድ እሁድ እለት እስኪሰክር ጠጥቶ ተኛ። ከስካር ወለድ እንቅልፉ የነቃው ሰኞ ሳይሆን ማክሰኞ ነው። ከእሁድ እስከ ማክሰኞ በእንቅልፍ አሳለፈ። ሰኞ እለት ሳይኖርባት አለፈች። ጥላዬ ታደሰ ሲሰክር እዚህ ድረስ ነው።

የአባት ሞት ፥ ተስፋ መቁረጥ ፥ ሱሰኝነት ፥ ብተኝነት እየተፈራረቁ የደቁሱት ዶክተር ጥላዬ "ጥላዬ ቀደምኩት" የሚል ህይወቱን የሚናገር ግሩም መፅሐፍ አለው። "ይህ ሰው ማነው?" የሚል ጠያቂ ካለ ዶክተር ጥላዬ ዛሬ የተከበረ የናሳ ሳይንቲስት ነው። አዎን የናሳ ሳይቲስት!

ህይወቱ ከሱስ እስከ ናሳ በአስገራሚ ክስተቶች የተሞላ ነው። የዶክተር ጥላዬ ህይወት የሚነግረን ግሩም መልእክት አለ! ያም መልእክት "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል" የሚል ነው።

ለ፥ ፓስተር ታምራት ሀይሌ "አባት" ብለን ብንጠራቸው ከማያሳፍሩን ጥቂት የሃይማኖት ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በወንጌላውያን አማኞች ዘንድ እጅግ የከበረ ስም ካላቸው ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዱ ፓስተር ታምራት ሀይሌ ነው።

የፓስተር ታምራት የትላንት ህይወቱ በብዙ ፈተና እና ውጣ ውረድ የታጨቀ ነበር።
አባቱ ታዋቂ ባለ ውቃቢ ነበር። ያ ብቻ ሳይሆን የአባቱ ውቃቢ እንዲያርፍበት ታምራት ተመረጠ። ከዚህ በኋላ ህይወቱ የሰቀቀን ሆነ። ገና በልጅነቱ ከእኩዮቹ ጋር በነፃነት መንቀሳቀስ የማይችል ሆነ። መናፍስት እየተገለፁለት ያሰቃዩት ነበር።

ቤተሰቦቹ ለሊት ለሊት ወንዝ ዳር እየወሰዱት የአምልኮ ስርኣት ፈፅመውበታል። ሰውነቱን እስኪቆስል በአሸዋ ከፈተጉት በኋላ በውሃ ይነከራል። የልጅ ሰውነቱ ላይ የተፈጠረው ቁስል ውሃ ሲያገኘው ስቃይ ቢፈጥርበትም ለውቃቢው ሲባል ደጋግሞ አድርጎታል።

ታምራት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በሰው ቤት ተቆጥሮ ሲሰራ ከሰው በታች ሆኖ ተዋርዷል፥ ስድብ እና ዱላን እንደዋዛ ተቀብሏል። ራሱን ስለማጥፋት አስቦም ያውቃል።

ዛሬ ላይ ፓስተር ታምራት የተከበረ ሰው ነው። "የታምራት አምላክ ተአምረኛ" የሚል የህይወት ታሪኩን የሚያወሳ መፅሐፍ አለው።
የታምራት ህይወት ምን ይነግረናል? "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!"

ሐ፥ ኢትዮጵያ ከምትኮራባቸው ጥቂት የላቁ አእምሮዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው በቀላሉ የማይደገሙ ሊቅ ናቸው። ብቻቸውን ብዙ ሰው!

ጌታቸው ገና ጨቅላ ሳለ የፋሽስት ወረራ ቤተሰባዊ ምስቅልቅልን ወለደ። ከዛ በኋላ ብዙ አስቸጋሪ ወቅቶችን አሳልፏል።

አባቱ ለትምህርት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ልጃቸው እንዲማር ዘመድ ዘንድ ሰደዱት። ውጤቱ ግን የተገላቢጦሾ ሆነ። ህፃኑ ጌታቸው መማር አልቻለም። እረኝነት እጣ ፈንታው ሆነ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የመማር መብቱን የተነፈገው ህፃን ሰብአዊ ክብሩንም ተቀማ። ሰውነቱ በእከክ ሲወረር አዛኝ አጣ። ሰውነቱ እስኪቆስል ድረስ ማከክ ግዴታው ሆነ።

ወደ አባቱ ሲመለስ የተከበረ ኑሮ አልጠበቀውም። ከአባቱ ጋር በመቃብር ቤት እየኖረ መማር እጣ ፋንታው ሆነ።

ጌታቸው ሀይሌ የእናቱን ፍቅር ሳይጠግብ ገና ጨቅላ ሳለ እናቱ ተለይታው ሄደለች። የእናት ናፍቆቱን የሚወጣበት በቂ እድል አልነበረውም።
አባቱ የጤና እክል ገጥሞት ከአልጋ መዋል ግዴታው ሲሆን ብቻውን ለአባቱ ቂጣ እየጋገረ ይኖር ነበር። እንደ እኩዮቹ መጫወት ሳያምረው አባቱን እያስታመመ እና ለአባቱ ምግብ እያበሰለ ልጅነቱን አሳልፏል።

ትዳር ከመሰረተ በኋላ ሐገር ለማገልገል በሚጥርበት ዘመን የደርግ ሰዎች ሊይዙት ቤቱ ድረስ ከመጡ በኋላ ተታኩሰው ጉዳት አድርሰውበታል። ፕሮፌሱሩ ለረጅም ዘመን በዊልቸር እንዲቀመጥ ያስገደደውን መዘዝ ያመጣው ያ ጉዳት ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ ባለ ግርማ ሊቅ ሆነዋል። የስኬት ጫፍ ላይ ተገኝተዋል። ህይወታቸውን "አንዳፍታ ላውጋችሁ" በሚል መፅሐፍ ከትበውታል።

ህይወታቸው ምን ይነግረናል? ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!

ሁላችንም በአንዳች አይነት መከራ እያለፍን ይሆናል። እጅ የማይሰጥ ፅኑ መሆን እንዳለብን የብዙዎች ህይወት ይነግረናል!

በእርግጥ ክፉ ቀኖች ያልፋሉ!

Nb፥ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለው "ክፉ ቀኖች ያልፋሉ ፥ ፅኑ ሰዎች ያልፉታል" የሚል የትርጉም መፅሐፍ አንብቤ ነበር። የመፅሐፉ ደራሲ ሮበርት ሹርለ ይመስለኛል።

@Tfanos
@Tfanos

20 last posts shown.