❤ፍቅር ማለት
....የቀጠለ
ትናንት ከመቅደሱ በራፍ ቆሜ መንገደኞቹን ስለ ፍቅር ተዓምራቶችና ጥቅሞች ያውቁ እንደሆነ በጥያቄ ሳደርቃቸው ዋልኩ፡፡
አንድ የደከመና የገረጣ ፊት ያላቸው በዕድሜ የገፉ አዛውንት በአጠገቤ እያለፉ እንዲህ አሉኝ፡-
«ፍቅር ከመጀመሪያው ሰው የተሽለምነው ተፈጥሯዊ ድክመት ነው፡፡»
ይሁን እንጂ አንድ ጎበዝ ወጣት በንዴት መልስ ሰጠ፡- .. «ፍቅር ዛሬን ከትናንት እና ከነገ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው።»
አንዲት ሃዘን የተላበሰ ፊት ያላት ሴት አቃስታ እንዲህ አለች «ፍቅር በገሃነም የሚድሁ ጥቋቁር እፉኝቶች የሚወጉን ገዳይ መርዝ ነው መርዙ እንደ ጤዛ ትኩስ ስለሚመስል የተራበች ነፍስ ተስገብግባ ትጠጣዋለች ከመጀመሪያው ስካር በኋላ ግን ጠጪው ይታመምና ቀስ በቀስ ይሞታል፡፡»
ከዚያም አንዲት ውብ ጉንጮቿ እንደ ፀሃይ የሚያበሩ ልጃገረድ ፈገግ ብላ እንዲህ አለች፡
«ፍቅር በንጋት ሙሽሮች የሚቀርብ ጠንካራ ነፍሶችን የሚያጠነክርና ወደ ከዋክብት እንዲመጥቁ የሚያስችላቸው ወይን ነው፡፡»
ከእሷ በኋላ አንድ ጥቁር ካባ የደረበ ፂማም ሰው አይኖቹን አፍጥጦ ተናገረ፡
«ፍቅር ወጣትነት የሚጀምርበትና የሚያበቃበት የታወረ ድንቁርና ነው፡፡»
ሌላኛው ፈገግ ብሎ ቀጠለ፡«ፍቅር ሰው የአምላካቱን ያህል እንዲያይ የሚያስችል ሰማያዊ ዕውቀት ነው፡፡»
አንድ አይነ - ስውር መንገዱን በበትር እየፈለገ እንዲህ አለ፡
«ፍቅር ነፍስ የህያውነትን ሚስጥር እንዳታሳይ የሚከልላት፣ በዚህም ልብ ከኮረብቶች መሃል የሚንቀጠቀጡትን ጣዕረ - ሞቶች ፍላጎት ብቻ እንዲያይ እና የድምፅ አልባዎቹን ሸለቆዎች የመስተጋባት ጩኸት ብቻ እንዲሰማ የሚያደርግ የጉም መጋረጃ ነው፡፡»
አንድ ወጣት ክራሩን እየመታ እንዲህ ሲል ዘመረ-
«ፍቅር ከሚነደው የነፍስ ጉድጓድ በመመንጨት ምድሪቱን በብርሃን የሚሞላ አስማታዊ ጨረር ነው፡፡ ፍቅር ህይወትን በንቃትና ባለመንቃት መሃል እንዳለ ቆንጆ ህልም እንድናየው የሚያስችለን ነው፡፡»
አንድ ሽማግሌ ሰው እግሮቻቸውን እንደ ቡትቶ ጨርቅ እየጉተቱ
በሚንቀጠቀጥ ድምፅ እንዲህ አሉ፡
«ፍቅር በፀጥታማ መቃብር ያረፈ እስክሬን፣ በዘላለማዊነት ውስጥ
የሰጠመች ነፍስ ነው፡፡»
ከዚያም አንድ የአምስት ዓመት ህፃን እንዲህ አለ፡
«ፍቅር እናትና አባቴ ናቸው:: ከእናትና ከአባቴ በቀር ደግሞ ፍቅርን የሚያውቀው የለም።»
እናም ያለፉት በሙሉ ፍቅር የተስፋቸውና የተስፋ መቁረጫቸው ነፀብራቅ እንደሆነ በመግለፅ ሚስጥርነቱን የበለጠ አጎሉት።
ከዚያም በመቅደሱ ውስጥ አንድ ድምፅ ሰማሁ፡
« ህይወት እኩል ሁለት ቦታ ትከፈላለች፣ አንዱ በረዶ እና ሌላኛው እሳት፤ የሚፋጀው ግማሽ ፍቅር ነው፡፡»
በመጨረሻ ወደ መቅደሱ ገባሁና ተንበርክኬ ደስ እያለኝ ፀለይኩ፡- «ጌታዬ ሆይ፣ የነበልባሉ ራት አድርገኝ ... ጌታዬ ሆይ፣ የተከበረው እሳት ምግብ አድርገኝ ... አሜን፡፡»
ምንጭ- የጥበብ መንገድ
ደራሲ - ካህሊል ጂብራን
@Zephilosophy@Zephilosophy