ኢትዮጵያዊነት በጣም ልዩ የሆነ ምስጢር ነው። እኛ ከምናውቀውና ከምናስበው በላይ ፍጹም የተለየ የረቀቀ ምስጢር አለው። ይህንንም ከምናውቅበት መንገዶች አንዱን እንመልከት።
ይህም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የሴም፣ የካምና የያፌት የዘር ሀረግ ውህድ ነን። ይህ እጅግ የተለየ ድንቅ ነገር ነው። ደግሞም እውነት መሆኑን ለማየት አስቀድመን ሳይንሳዊ ወይም ታሪካዊ ማስረጃን እንመልከት።
በመጀመሪያ እኛ ኢትዮጵያውያን የጥቁሮች የካም ዘር እንዳለብን ግልጽ ነው። ከዚህም ውስጥ የኩሽ የዘር ሀረግ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ብዙዎች እንደምናስበው አንዱ ብሄር ሴም አንዱ ኩሽ የሚለው ፍጹም ስህተት ነው። ለምሳሌ ሴማዊ ብለን ከምናስባቸው "ብሔሮች" ውስጥ እንመልከት። አማርኛ ተናጋሪ ህዝቦችን ብንመለከት ታሪክ አጥኚዎች ጭምር እንዳሳዩት የአማራ ነገድ የሚመጣው በከፊል ከሴማውያን ህዝቦች፣ በከፊል ደግሞ ከአገዎች ነው። ይህንንም ተድላ መላኩ ስለ አማራ መገኛና አመጣጥ በጻፈው መጽሐፉ ጠቅሶታል። ቋንቋውም በዚሁ መልኩ የኩሻውያን ቋንቋ ከግዕዝ ጋር እየተቀላቀለ ሲመጣ የተፈጠረ መሆኑ ይታወቃል። ለዚህ ነው ከግዕዝ ውጪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጥ ያሉ ሴማዊ ቋንቋዎች ከሌላው ሴማዊ ቋንቋዎች የተለዩ የሆኑት። በቮካቡለሪም ደረጃ ወጣ ያሉት። ተመሳሳይ ነጥብ ስለ ጉራጊኛም ሆነ ስለ ትግርኛ ማንሳት እንችላለን።
በሌላው መልኩ ደግሞ እንደ አፋር እና ሶማሊ ያሉትን ደግሞ ስንመለከት ኩሻዊ ተብለው ቢፈረጁም ቋንቋቸው እጅግ ከባድ የአረብኛ ተጽዕኖ ያለበት መሆኑ የሚያስገርም ነው። ያ ተጽዕኖ ደግሞ እንዴት መጣ ካልን ከአረቦች ጋር የመነካካት አጋጣሚ እንደነበራቸው ያስታውቃል። ይህም የአዳል ሱልጣኔት መንግስት ስር በነበሩበት ወቅት ይሆናል። ከዚህም በላይ አረቦች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በንግድ እና ወደ አከባቢው ህዝብ በመጋባትና በመቀላቀል ስለሆነ አፋሮቹና ሱማሌዎቹ ከሴማውያኑ አረቦች ጋር የዘር መቀላቀል ነበራቸው ማለት ነው። ስለዚህ አፋሮች እና ሱማሌዎች ንፁህ ኩሻውያን ናቸው ብንል ትክክል ይሆናል?
በተመሳሳይ መልኩ፣ ዛሬ በሀረር፣ በአርሲ እና በባሌ ያሉ ሙስሊም ኦሮሞዎች፣ በአረቦቹ የስብከት ቴክኒክ ምክንያት ወደ እስልምና የመጡ ናቸው። አረብቹ ከሀገሬው ሰው እያገቡ፣ ቤተሰብ እየመሠረቱና ያንን ቤተሰብም ወደ እስልምና እያመጡ፣ እምነቱን ስላስፋፉ፣ እነዚያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችም የዚህ ተጽዕኖ ውጤት ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ንፁህ ኩሽ ናቸው ማለት እንችላለን? የምንችል አይመስልም።
ይህ አንዱ ማሳያ ነው፣ የሴም እና የካም ውህድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖሩ። ሌላው ማሳያ ብንመለከት ደግሞ የእስራኤላውያን በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘት ነው።
የዚህ መነሻው በንጉስ ሰሎሞን ዘመን ሰሎሞን ከኢትዮጵያዊቷ ማክዳ የወለደው ልጁ ምኒልክ ቀዳማዊ አባቱን ሊጎበኝ ወደ እስራኤል በሄደበት ወቅት ነው። በዚያም አባቱ ከአስራ ሁለቱም የእስራኤል ነገድ አድርጎ በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያንን አብሮ ወደ ኢትዮጵያ ልኳል። በዚህም እነዚያ እስራኤላውያን በከፍተኛ ሁኔታ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተቀላቅለዋል። ይህ ታዲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ የምታምነው ያልተረጋገጠ ነገር ሊመስል ይችላል። እውነታው ግን ነገሩ ፍጹም የተረጋገጠ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ 3ሺህ ዓመት የሚሆናቸው የኦሪት መሰዊያዎች ተገኝተዋል። ያም እስራኤላውያኑ በቦታው ከመጡበት ጊዜ ጋር ይስተካከላል። በጊዜው የኦሪት ህግን የሚከተሉት እስራኤላውያን ብቻ መሆናቸው ደግሞ በትክክልም እስራኤላውያን በጊዜው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበሩ ማሳያ ነው። እንዲሁም በሚገርም ሁኔታ አንድ የጄኔቲክስ ጥናት በኢትዮጵያ ውስጥ ከ3 ሺህ ዓመት በፊት ከፍተኛ የሆነ ፍልሰት ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ኢትዮጵያ እንደተካሄደ አረጋግጧል። ጥናቱ ይህንን ክስተት "back migration" ነው ያለው፣ ምክንያቱም ሳይንቲስቶች የሰው ልጅ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ሌላው ዓለም "migrate" እንዳደረገ ስለሚያምኑ ነው። የጥናቱን ሊንክ በዚህ ታገኙታላችሁ፦
https://www.bbc.com/news/science-environment-34479905ይህም ብቻ ሳይሆን እስራኤላውያን በቅርቡም ወደ ኢትዮጵያ እንደፈለሱ ይነገራል። ይህም በ70 ዓመተ ምህረት የሮም መንግስት ኢየሩሳሌምን ባፈረሰ ጊዜ እስራኤላውያን በመላው ዓለም ሲበተኑ፣ እንዲሁም በ1453 ቱርኮች የቢዛንቲንን መንግስት በተቆጣጠሩ ጊዜ እዚያም ተሰደው ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ እንደፈለሱ ይነገራል።
እናም እነዚህ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሀገራችን የመጡ እስራኤላውያን በዋናነት በሸዋ፣ ጎንደር እና የተወሰኑ የትግራይ ክፍሎች ውስጥ በሰፊው እንደተቀመጡ ይታወቃል። ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህ እስራኤላውያን በታሪክ አጋጣሚዎች ከሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶች ጋር ተቀላቅለዋል። በአክሱም የአገዎቹ የዛግዌ ነገስታት ከፊል እስራኤላውያኑ የአክሱም ነገስታት ጋር ተቀላቅለዋል። የአክሱም መንግስት ተቀጥያ በሆነው የሰሎሞናዊው ስርወ መንግስት ጊዜም እንደ ከፋ እና ወላይታ ያሉት ህዝቦች በጦርነት ምክንያት ከሸዋዎቹ ከፊል-እስራኤላውያን ጋር እንደተላቀሉ በታሪክ ተገልጿል። ያም ብቻ ሳይሆን እነዚህ እስራኤላውያን በአከባቢው ከነበሩ እንደ ፈጠጋርና ደዋሮ ማለትም የዛሬዎቹ አርሲና ሀረር ውስጥ በብዛት ይኖሩ እንደነበር፣ የአከባቢው ገዢዎችም እንደሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል።
በኋላም የኦሮሞ መስፋፋት ሲካሄድ ኦሮሞዎች የሚቆጣጠሩትን አከባቢ ህዝብ ቋንቋና ባህላቸውን ወደ ኦሮሞ ቢለውጡም ህዝቦቹ ግን ዘራቸው ቀድሞ የነበሩት ናቸው። በዚህም ምክንያት እነዚህ የእስራኤል ዘር ያላቸው ህዝቦች ከኦሮሞዎች ጋርም ተቀላቅለዋል። በዚህም ምክንያት፣ በአርሲ፣ ባሌና ወለጋ ብቻ ሳይሆን በሸዋም ጭርምር ያሉ ኦሮሞዎች ኩሻዊ ቋንቋን ይናገሩ እንጂ በዘራቸው የሴም ዘር ቅልቅል ያለባቸው ናቸው።
ከዚያ እጅግ የሚገርመው ደግሞ በግራኝ ጦርነት የአዳል መንግስት ከክርስቲያኑ መንግስት ጋር በሚዋጋ ጊዜ አዳልን ለመርዳት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አረቦች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። በአከባቢው ካሉ ህዝቦችም ጋር ፍጹም ተቀላቅለው ነበር። በጣምም ከመቀላቀላቸው የተነሳ የኢትዮጵያ ነገስታት ጭምር ዘራቸው ከነዚህ አረቦች የሚመዘዝ አሉ። የጅማው አባጅፋር አንዱ ምሳሌ ነው። እንዲሁም የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት ሌላው ምሳሌ ነው። የሚገርመው የንጉስ ምኒልክ የልጅ ልጅ የሆነው ልጅ እያሱ ሁሉ የዘር ሀረጉ ወደ ኋላ ሲቆጠር፣ በግራኝ ጦርነት ጊዜ ከኢራቅ አከባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ሰው እንደሆነና የዛ ሰውን ታሪክ አረቡ ታሪክ ጸሐፊ ሁሉ እንደዘገበው ይነገራል።
ይህንን ሁሉ ስንመለከት መላው ኢትዮጵያ የሴምና የኩሽ ዘር ፍጹም የተቀላቀለባት መሆኗን እና "ሴም"፣ "ኩሽ" ተብሎ የተመደበው የብሔር/የቋንቋ አመዳደብ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን እንመለከታለን።
ነገር ግን የያፌት ነገድስ? ከየት የመጣ ነው? የሚለውን እንይ።
አንዱ ቀላል ማሳያ የግራኝ ጦርነት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ቱርኮች ናቸው። በትልቅ ቁጥር የመጡት ቱርኮች በወሎ አከባቢ እንደተቀመጡ ይነገራል። የቱርኮችን መገኛ ስናይ ደግሞ ከያፌት ነገድ እንደተገኙ እንመለከታለን።
ይቀጥላል👇👇