የካቲት ፳፭ /25/
በዚች ቀን የከበሩ አውሳንዮስና ፊልሞና ስሟ ሉቅያ የሚባል አንዲት ድንግልም በሰማዕትነት ሞቱ።
እሊህ ቅዱሳንም በአፍራቅያ ሀገር ሳለ በከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ ትምህርት ያመኑ ናቸው ከሀድያንም ዝሑራ በሚባል ኮከብ ስም ለሚጠሩት ለአርታዳሚ ጣዖት በዓልን በአደረጉ ጊዜ አይተው በስሕተታቸው ሊዘብቱ እሊህ ቅዱሳን ተሰብስበው ወደ ጣዖቱ ቤት ገቡ ሰዎችም ለጣዖቱ ሲሠዉና ከፍ ከፍ ሲያደርጉት በአዩአቸው ጊዜ በክብር ባለቤተ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እሳትነት ልባቸው ነደደ ከጣዖቱም ቤት ወጥተው ወደ ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሔደው የክብር ባለቤት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብሩንና ልዕልናውን አብዝተው አመሰገኑ።
ከዚያ ካሉት አንድ ሰው በሰማቸው ጊዜ በጣዖታቸው ላይ እንደ ዘበቱ የተናገሩትን ልብ ብሎ በመኰንኑ ዘንድ ወነጀላቸው መኰንኑም በፈረስ ተቀምጦ ሔደ ከወታደሮቹም ጋር ቤተ ክርስቲያኒቱን ከበባት ከምእመናንም ሰዎች የሸሹ አሉ።
እሊህንም ሦስቱን ቅዱሳን ያዛቸው የብረት ዘንጎችን በእሳት አግለው በቅዱሳኑ ጐኖች ውስጥ አደረጉት ከዚህም በኋላ የከበረ አውሳንዮስን ወደ ጒድጓድ ወረወሩትና ነፍሱን እስከ ሰጠ ድረስ በደንጊይ ወገሩት።
የከበረ ፊልሞናንና የከበረች ሉቅያን ግን ብዙ ጊዜ በጸና ሥቃይ ያሠቃዩአቸው ጀመር ነፍሳቸውንም ይወስድ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሳቸውን ወሰደ።
በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ እነሆ የምስክርነታቸውና የሃይማኖታቸው መታሰቢያ ተጽፎአል ። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን( መዝ 150 - 6 )
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መዝሙሮችን ለማግኘት
ይሄን link በመንካት ይቀላቀሉን 👇👇👇
@ney_ney_emye_maryam
#ሼር
🙏🙏🙏🙏🙏
🕊ለወዳጅ ለዘመዶ ያካፍሉ🕊