በመርካቶው ቃጠሎ ጉዳት ለደረሰባችሁ ወገኖች ሁሉ። ከምንም በፊት ሶብር አድርጉ። አላህ ሰጠ። አላህ ነሳ። ሙስሊም በደስታውም በሀዘኑም ጌታውን ያስባል። ጌታችን እንዲህ ይላል፦
{ وَلَنَبۡلُوَنَّكُم بِشَیۡءࣲ مِّنَ ٱلۡخَوۡفِ وَٱلۡجُوعِ وَنَقۡصࣲ مِّنَ ٱلۡأَمۡوَ ٰلِ وَٱلۡأَنفُسِ وَٱلثَّمَرَ ٰتِۗ وَبَشِّرِ ٱلصَّـٰبِرِینَ (155) ٱلَّذِینَ إِذَاۤ أَصَـٰبَتۡهُم مُّصِیبَةࣱ قَالُوۤا۟ إِنَّا لِلَّهِ وَإِنَّاۤ إِلَیۡهِ رَ ٰجِعُونَ (156) }
"ከፍርሃትና ከረሃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎችም በመቀነስ በእርግጥ እንሞክራችኋለን፡፡ ታጋሾችንም (በገነት) አብስር። እነዚያን መከራ በነካቻቸው ጊዜ፡ 'እኛ ለአላህ ነን፤ እኛም ወደርሱ ተመላሾች ነን' የሚሉትን።" [አልበቀረህ፡ 155-156]
አልሐምዱ ሊላህ በሉ። የሙእሚን ወጉ ይሄ ነው። በመከራውም በደስታውም ጊዜ ጌታውን አይረሳም። የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
عَجَبًا لأَمْرِ المُؤْمِنِ، إنَّ أمْرَهُ كُلَّهُ خَيْرٌ، وليسَ ذاكَ لأَحَدٍ إلَّا لِلْمُؤْمِنِ، إنْ أصابَتْهُ سَرَّاءُ شَكَرَ، فَكانَ خَيْرًا له، وإنْ أصابَتْهُ ضَرَّاءُ، صَبَرَ فَكانَ خَيْرًا له.
"የሙእሚን ነገሩ ይደንቃል። ሁለ ነገሩ መልካም ነው። ይሄ ለሙእሚን እንጂ ለማንም አይደለም። አስደሳች ነገር ቢያገኘው ያመሰግናል። ይሄ ለሱ መልካም ነው። ጉዳት ቢያገኘውም ይታገሳል። ይሄ ለሱ መልካም ነው።" [ሙስሊም፡ 2999]
በማመስገን ታተርፋላችሁ እንጂ አታጡም። በአይነ ህሊናችሁ ቃኘት ቃኘት ብታደርጉ አገር ምድሩ በፈተና ተጥለቅልቆ ታያላችሁ። የባሰ የገጠማቸውን ተመልከቱ። ንብረት ብቻ ሳይሆን ሙሉ ቤተሰብ ያለቀበት ስንት ጉድ አለ። አስቡ። ለመፅናናት ይጠቅማችኋል። ከተስፋ መቁረጥ ይታደጋችኋል። ከባሰ ሁሉ በላይ የባሰ አለ። ከባሰው ያዳናችሁን አመስግኑ። ተስፋ መቁረጥ፣ አጉል ብስጭት ያለፈውን ላይመልስ ከሁለት ያጣ ያደርጋል። ደግሞም እወቁ! አያልፍ የመሰለው ሁሉ ያልፋል። ኢንሻአላህ ነገ ሌላ ቀን ነው።
ከምንም በላይ ግን ዱንያ ነው። ትልቁ ኪሳራ የኣኺራ ኪሳራ ነው። ጌታችን እንዲህ ይላል፦
{ قُلۡ إِنَّ ٱلۡخَـٰسِرِینَ ٱلَّذِینَ خَسِرُوۤا۟ أَنفُسَهُمۡ وَأَهۡلِیهِمۡ یَوۡمَ ٱلۡقِیَـٰمَةِۗ أَلَا ذَ ٰلِكَ هُوَ ٱلۡخُسۡرَانُ ٱلۡمُبِینُ }
" 'ከሳሪዎች ማለት እነዚያ በቂያማ ቀን ነፍሶቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያከሰሩ ናቸው። ንቁ! ይህ እርሱ ግልጽ ከሳራ ነው' በላቸው።" [አዙመር፡ 15]
አላህ ሶብሩን ይስጣችሁ። በተሻለ ይተካችሁ።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor