ኢስላማዊ መገለጫዎችን (ሸዓኢር) መጠበቅ ያሉት ፋይዳዎች
~
በቅድሚያ "ሸዓኢር" ወይም መገለጫዎች ስል እዚህ ላይ ማተኮር የፈለግኩት ሙስሊምነትን በርቀት የሚናገሩ፣ አለፍ ሲልም ለሸሪዐዊ ትእዛዛት ታዛዥነትን በከፊልም ቢሆን የሚጠቁሙ ውጫዊ የዲን ቀንዘሎችን ነው።
ለወንድ ልብስን ማሳጠር፣ ፂምን ማሳደግ፣ ለሴቶች ጂልባብ ወይም ኒቃብ መልበስን #የመሳሰሉ ለማለት ነው። እነዚህንና መሰል ነጥቦችን በራስ ላይ መተግበር የተለያዩ ፋይዳዎች አሉት። ከነዚህም ውስጥ:–
① ዋናው ፋይዳ ነብያዊውን ሱና መፈፀም መሆኑ ነው። ይሄ ትልቅ መታደል እንደሆነ ለማንም አይሰወርም።
② ከግልፅ ወንጀሎች ለመራቅ አጋዥ ነው። ዲናዊ ነፀብራቅ የሚታይባቸው ሰዎች ከሌሎች በተሻለ ወንጀል እየፈፀሙ ባደባባይ መታየት አይፈልጉም። ግልፅ ወንጀሎች ላይ ቀርቶ ከግብረ ገብነት ወጣ ያሉ ነገሮች ላይ የሚታዩት ከሌሎች አንፃር ያንሳሉ። "እኔ ገና ስንት ነገሬን ሳላስተካክል ኒቃብ/ ጂልባብ መልበስ፣ ፂም ማሳደግ፣ ልብስ ማሳጠር ይከብደኛል" የሚሉ አጋጥመዋችሁ አያውቁም? የዚህን አነጋገር ሌላ ገፅ አስተውላችሁታል? ሰዎች ዲናዊ ነፀብራቅን እያንፀባረቁ ወለም ዘለም ሲሉ መታየት አይፈልጉም ማለት ነው። ሎጂካቸው ነፀብራቆቹን ላለመፈፀም ጤነኛ ምክንያት ባይሆንም ኢስላማዊ ነፀብራቆችን እያሳዩ ጥፋት ላይ መታየት እንደሚከብዳቸው ጠቋሚ ነው። የእውነትም ወንጀልን ቢያስቡ እንኳን በላያቸው ላይ የሚታዩ ዲናዊ ነፀብራቆች አስረው የሚይዟቸው ብዙ ናቸው። እራሳቸውን ማሸነፍ አቅቷቸው ጥፋት ላይ ቢወድቁ እንኳን "ኒቃብ ለብሰሽ እንዲህ ትሆኛለሽ? ፂምህን አሳድገህ ይህን ትሰራለህ?" የሚል ብርቱ ተግሳፅ ከዓሊም ቀርቶ ከጃሂል ይመጣባቸዋል። ይህም ከሌሎች የተሻለ የመመከር እድል አላቸው ማለት ነው። ይሄ ታዲያ ትልቅ ጥቅም አይደለምን?
* ሸዓኢር የሚታይባቸው አጥፊዎች የሉም እያልኩ አይደለም። በንፅፅር ነው ያወራሁት።
③ ዲናዊ መገለጫዎችን ማንፀባረቅ ለእውቀት ፍለጋ ያነሳሳል። ህዝባችን ዲናዊ ነፀብራቅ የሚታይበትን አካል በብዙ ዲናዊ ነገር ወደፊት ያስቀድማል። ከሌሎች የተሻለ አድርጎ ይገምታል። ኢስላማዊ ውይይት ቢነሳ የተሻለ ሀሳብ ሊያመነጭ እንደሚችል ይጠብቃል። ጀማዐ ያለፋቸው ሰዎች መስጂድ ውስጥ ቢገቡ ልብሱ ያጠረውን፣ ፂሙ ያደገውን ለኢማምነት ያስቀድማሉ። በዚህን ጊዜ ሰዎች እንደሚያስቡት በቂ ግንዛቤ የሌለው ከሆነ ይሸማቀቃል። በራሱ ያፍራል። ከሌሎች በተሻለ ለዒልም ይነሳሳል። በሌሎችም ዘርፎች እንዲሁ ነው። ታዲያ ይሄ የራሱ ጥቅም አልኖረውምን?
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 13/2010)
የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor