በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በፀደቁ ሁለት አዳዲስ አዋጆች ዙርያ ቅሬታ ያቀረቡ ፖለቲከኛ ዛሬ ጠዋት ታሰሩ
ከሰሞኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በነበረ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቀርቦ የፀደቀውን የየእርከኑ የምክር ቤት ተወካዮች ብዛት ለመወሰን የወጣ አዋጅ እንዲሁም የክልሉ ህገ መንግስትን እንደገና ለማሻሻል የወጣውን አዋጅ ተቃውመው ቅሬታ ያስገቡት ፖለቲከኛ ዛሬ ጠዋት ለእስር ተዳርገዋል።
መሠረት ሚድያ እንዳረጋገጠው የቦሮ ዲሞክራያዊ ፓርቲ የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ እና የክልሉ የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑን አቶ ዮሐንስ ተሰማ በፀጥታ ሀይሎች ተወስደዋል።
የቦሮ ዲሞክራያዊ ፓርቲ በውሳኔዎቹ ላይ ቅሬታ የነበረው ሲሆን ሶስቱ የምክር ቤቱ አባላት በወቅቱ ተቃውሞ አቅርበው ውሳኔውንም 'የህገ መንግስት አተረጓጎም ላይ የቀረበ ቅሬታ' በሚል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተጨማሪ ጥያቄዎች ጋር አቅርበው ነበር።
"በዚህ ሁኔታ ያቀረቡትን ጥያቄ የተለያዩ አንድምታ እየሰጡ ይባስ ብለው ዛሬ አቶ ዮሀንስን አስረውታል" ብለው የክልሉ የመረጃ ምንጫችን ለሚድያችን ተናግረዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ከየካቲት 10 እስከ 11 2017 ዓ/ም በአሶሳ ከተማ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ በስራ ላይ የሚገኘውን የክልሉን የምክር ቤት የመቀመጫ ቁጥር ከ99 ወደ 165 አሻሽሏል፡፡
የቦሮ ዲሞክራያዊ ፓርቲ ግን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሳይደረግ 165ቱ የመቀመጫ ብዛት አሁን በስራ ላይ ለሚገኙ የምርጫ ክልሎች የተከፋፈለበት መንገድ የህዝብ ብዛትን ያማከለ አለመሆኑን እና ነባር የምርጫ ክልሎች የፈረሱበትና አዳዲስ ምርጫ ክልሎች የተቋቋሙበት ሂደት ህገ መንግስቱን የጣሰ በመሆኑን እንዲሁም በቂ ውይይትና ክርክር ያልተደረገበት መሆኑን በመግለፅ ቅሬታውን ገልፆ ነበር።
ምንጭ መሠረት ሚዲያ
@Addis_Reporter @Addis_Reporter