ለምንወዳቸዉ ልጆቻችን ምን አይነት ወላጆች ነን?
ይኽንን ጹሑፍ አንብበዉ ምን አይነት ወላጅ እንደሆናችሁ ታዉቁ ዘንድ በፍቅር ጋበዝኳችሁ።
አንዲት አስተማሪ ተማሪዎቿ የሰሩትን የቤት ስራዎች እየፈተሸች ባል ደግሞ የሚወደውን ጌም በስማርት ፎኑ ይጫወታል። ሚስቲቱ የመጨረሻውን የቤት ስራ ስታነብ ቆይታ በዝግታ ማልቀስ ትጀምራለች። ባል ወዲያው ደንግጦ ምን ሆና እንደሆነ ይጠይቃል?
ሚስቲቱም ትናንት ለተማሪዎቿ 'ምኞቴ' በሚለው ርእስ ላይ የሆነ ነገር እንዲጽፉ የቤትስራ እንደሰጠቻቸውና የመጨረሻውን ጽሁፍ ስታነብ እንዳስለቀሳት ለባሏ ትነግረዋለች።
ባልም ምን እንደሆነ ለማወቅ በመጓጓት ሚስቱ እንድታነብለት ሲጠይቅ እሷም እንዲህ አነበበችለት፦
"እኔ መሆን የምፈልገው 'ስማርት ፎን' ነው !"
. . . ቤተሰቦቼ ስማርት ፎናቸውን ይወዳሉ ለስማርት ስልካቸው በጣም ይጨነቃሉ አንዳንዴ እኔን መንከባከብ እንኳ ይረሳሉ።
አባቴ ከስራ ደክሞት ሲመጣ ለስልኩ የሚሆን ጊዜ ነው እንጂ ለእኔ የሚሆን ጊዜ አይኖረውም። ቤተሰቦቼ አስፈላጊ ነገር እየሰሩ ስልካቸው ሲጠራ በአንደኛው ጥሪ ቶሎ ምላሺ ይሰጣሉ። እኔ ግን እያለቀስኩ እንኳ ብዙም ትኩረት አይሰጡኝም። ቤተሰቦቼ እኔ ጋር ሳይሆን ስማርት ፎናቼው ጋር ነው የሚጫወቱት።በስማርት ስልካቼው ከሰው ጋር በስልክ እያወሩ እኔ ጠቃሚ ነገርም ባወራቼው አይሰሙኝም። ስለዚህ የእኔ ምኞት 'ስማርት ፎን' ነው።
ባል ይህን ሲሰማ ስሜታዊ ሆኖ ማነው ግን ይኸን የጻፈው በማለት ሚስቱን ይጠይቃታል።
ሚስትም 'የእኛ ልጂ' በማለት መለሰችለት።