ሕዳር 11 /፲፩/
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ዐሥራ አንድ በዚች ዕለት አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናቷ የሆነች የተመሰገነች የቅድስት ሐና የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው።
ይችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኔታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ያገለገለቻት ናት።
ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧትና እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት እሊህም ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
ይህችም ጻድቅት ሐና መካን በመሆንዋ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር በጸሎት ትማልድ ነበር እግዚአብሔርም በእርሷ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ይቺን የተባረከችና የከበረች ልጅን ሰጣት እርሷም አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት።
ስለዚህም ይህን ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት የበዓሏን መታሰቢያ በደስታ ልናከብር ይገባናል። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከእኛ ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
@mekra_abaw