🔴 ምክረ አበው MEKRA ABAW™


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


#አባቶችን_ጠይቅ_ይነግሩሃል
● ጠቢብ ከሰነፍ ጋር ቢጣላ፥ ሰነፍ ወይም ይቈጣል ወይም ይስቃል፥
ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ ደግሞም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ።
ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል።
○ መጽሐፈ ምሳሌ ምዕ. 29 ○
ሀሳብ ካላችሁ @habmisget

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter




እንኳን አደረሳችሁ




ለሕይወት እንጠይቅ

"የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?"ይህን ጥያቄ ጌታን የጠየቀው አንድ ሃብታም ወጣት ነው። ይህ ወጣት የጥያቄውን መልስ ባይተገብረውም የጠየቀው ጥያቄ ግን በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው። እኛ የሰው ልጆች የተፈጠርነው ለሕይወት ነው ለሕይወት ተፈጥረን ሳለ ግን በዙሪአችን ባሉ distraction  ተስበን ዋና ዓላማችንን ችላ እያልን ነው። ክርስቶስ የሞተው በእርሱ ለዘለዓለም እንድንኖር ነው ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ክርስቲያን የኾነውም ከክርስቶስ ጋር ለዘለዓለም ለመኖር ነው። አብዛኞቻን ግን ክርስቲያን የኾነው በክርስቶስ ለመኖር ሳይኾን ነፍስ ካወቅን ጀምሮ እራሳችንን በክርስትና ውስጥ ስላገኘነው ነው። ስለዚህም የምንጠይቃቸው ጥያቄዎችም ለሕይወት የሚኾኑ አይደሉም። "በሚካኤል ቀን ልብስ ይታጠባል?" ፣ "አሳማ ይበላል?" ፣ " በሰንበት ቡና ይወቀጣል?"፣ " የሙስሊም ሥጋ የበላ ሰው ቄደር ይጠመቃል?" እያልን ለድኅነት እንኳን ረብ የሌላቸው ጥያቄዎች ላይ ጊዜ እናጠፋለን።

እንዲሁም ልክ ለመንጻት ሥርዓት ብቻ እንደሚጨነቁ ፈሪሳውያን ሰውን በየእያንዳንዱ ነገሮች እያሳቀቅን ከክርስቶስ እናርቃለን እንደው በጌታ "በበዓል ቀን ወፍጮ ፈጨህ ፣ ሥራ ሠራህ"፣ "የአርሴማን ጸበል ተጠምቃ ቡና ጠጣች" ፣ " በማርያም ቀን ልብስ አጠብክ" ፣ " በወር አበባ ላይ ኾና ጸበል ጠጣች" እያሉ ክርስቲያኑን ማሳቀቅ ተገቢ ነው? ይህ በክርስትና ውስጥ የተደበቀ ፈሪሳዊነት ነው! ክርስቶስ አሁን ቢመጣ ኖሮ "ሰንበት ለሰው ተሠራች እንጂ ሰው ለሰንበት አልተሠራም" ብሎ ፈሪሳውያንን እንደ ወቀሰ አንደኛ ተወቃሾች እኛ ነበርን።

ክርስቲያን የኾነው በክርስቶስ የዘለዓለምን ሕይወት እናገኝ ዘንድ ነው ስለዚህ የኹል ጊዜ ጥያቄያችን "ወደ ክርስቶስ እንዴት ልቅረብ?" ፣ "የዘለዓለም ሕይወትን እንዴት ላግኝ?" ይኹን ለሕይወት እንጠይቅ፤ ፈሪሳዊነት ከመካከላችን ይውጣ!


በኖራ የተለሠነ ግድግዳ

ቅዱስ ጳውሎስ በሊቃነ ካህናት ሸንጎ ፊት ቆሟል ሕዝቡ ሕግን ይሽራል ቤተ መቅደሱን ይቃልላል በማለት አመጽ በማስነሳታቸው ለፍርድ Sanhedrin ታላቁ ጉባኤ ፊት ቆሞ እራሱን ይከላከላል። ጳውሎስ መብቱን የሚያቅ ሰው ነው መች ይሰማል ሺህ አለቃው ያለ ፍርድ ሊያስገርፈው ሲል "የሮሜን ዜጋ ያለ ፍርድ ትቀጣለህን" በማለት ከመገረፍ ቢያመልጥም አሁን ግን ሊቃነ ካህናቱ ፊት ፍርዱን እየጠበቀ ነው። ይሄን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ሀናንያ ጳውሎስን እንዲመቱት አዘዘ:
"በዚያን ጊዜ ጳውሎስ፦ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን?” አለው።" (ሐዋ 23:3) በማለት ይመልሳል። በዛ የተሰበሰበው ሕዝብ ሊቀ ካህናቱን ተሳደበ ብለው ጮኹ ጳውሎስ ግን እውነቱን ነው ተየናገረው በኖራ የተለሰነ ግድግዳ በውጪ ለሚያዩት ነጭ ነው ከልስኑ ስር ግን ስንት ቆሻሻን ደብቋል እንዲሁ ፈሪሳውያን በሰው ፊት ጻድቅ ጻድቅ ይጫወታሉ ውስጣቸው ግን በኃጢአት የተጨማለቀ ነው ፤ እነዚህን ክርስቶስ "ቀራጮች እና ዘማዎች መንግስተ ሰማያት በመግባት ይቀድሟችኋል" ሲል ይናገራቸዋል።

እኛስ በኖራ የተለሰንን ግድግዳዎች አይደለንም? ከነጩ ነጠላ ውስጥ ስንት ክፋትን ይዘን ነው ወደ ክርስቶስ የምንገባው ሰውን በነጭ ነጠላችን እንሸውዳለን ክርስቶስ ግን በዚህ አይሸወድም ልብና ኩላሊትን ይመረምራልና።

ፈሪሳውያን ተቆጡ እንዴት ሊቀ ካህናታችንን ትሰድባለህ አሉ። ጳውሎስ ግን "ሊቀ ካህናት መኾኑን አላወቅሁም" ሲል በስላቅ ቃል መለሰ በዝያን ጊዜ ሀናንያ ለሮማውያን ጉቦ ከፍሎ በግድ ቦታውን የያዘ ነውና ሕዝቡ የመረጠው ሊቀ ካህናት ግን ዮናታን ነበር። (ጳውሎስ ይቀልደው የለ እንዴ 😋) ። ይህ ብቻስ አይደለም ጳውሎስ የሚያውቀው ሊቀ ካህናት አንድ ብቻ ነው እርሱም ወደ ሰማያዊቷ መቅደስ በደሙ የገባው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፤ በደሙ ቀይ ቢኾንም በባሕርይው ጸአዳ ነጭ ነው!


"ለዱር አውሬዎች ምግብ እኾን ዘንድ ፍቀዱልኝ በእነርሱ ወደ እግዚአብሔር እደርሳለሁና። እኔ የእግዚአብሔር ስንዴ ነኝ በዱር አውሬዎች ተፈጭቼ  የክርስቶስ ንጹሕ ኅብስት ኾኜ እገኝ ዘንድ ተዉኝ...

ስጽፍላችሁ በሕይወት ብኖርም ልሞት ግን እናፍቃለሁ ፍቅሬ ተሰቅሏልና መመገብም የሚፈልግ እሳት በውስጤ የለም። ነገር ግን ፡- ወደ አብ ና የሚለኝ ሕያውና የሚናገር ውኃ በውስጤ አለ። በሚጠፋ መብል ወይም በዚህ ሕይወት ተድላ ደስ አይለኝም። የእግዚአብሔርን እንጀራ ሰማያዊውን ኅብስት የሕይወትን እንጀራ እመኛለሁ እርሱም በኋላ ከዳዊትና ከአብርሃም ዘር የኾነ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ነው ። የእግዚአብሔርንም መጠጥ እሻለሁ እርሱም ደሙ የማይጠፋ ፍቅርና የዘላለም ሕይወት ነው።"

(ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለሰማዕትነት ወደ ሮም ኮሎሲየም እየተወሰደ እያለ የሮም ምእመናን ከሰማዕትነቱ ወደ ኋላ እንዳይሉት የላከባቸው መልእክት)

የክርስቶስ ፍቅር
ለሰማዕትነት መሮጥ
ቁርባናዊ ሕይወትና አገላለጽ
ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ
ክርስቶስ ኢየሱስ ❤️

https://www.newadvent.org/fathers/0107.htm


ለቅዳሴ ያለንን ቦታ እንፈትሽ

እስቲ ቅዳሴ የምንቀርበትን ምክንያቶች እንፈትሻቸው ክርስቶስ በአካል ከሚገኝበት ቦታ ምን በልጦብን ነው የምንቀረው? ኳስ መጫወት ፣ ስፖርት መሥራት ፣ እንቅልፍ? እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ጥሩ ቢኾኑም የጌታን ቦታ እየወሰዱ ከኾነ ግን ዝሙት ናቸው። ቅዱስ አውግስጢኖስ "አንድን ነገር የሙሽራውን የክርስቶስን ቦታ እስኪወስድ ድረስ የምንወድ ከኾነ በሙሽራችን ላይ የሚፈጸም ዝሙት ነው" ይለናል። ለአንድ ክርስቲያን በጌታ ቀን በዕለተ እሑድ ቅዳሴ ቀርቶ ሌላ ቦታ መዋል የሙሽራውን ድግስ አልፈልግም በማለት በሙሽራው ላይ የሚፈጸም አመጽ ነው! አሁን በምድራዊው የክርስቶስ ሠርግ ላይ ካልተገኘን እንዴት በሰማያዊው ሠርግ ላይ የመሳተፍ እድል አለን ብለን እናስባለን? ለቅዳሴ ፣ ለክርስቶስ ያለንን ቦታ እንፈትሽ።

መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ጥሩ ነን ብለን እራሳችንን የምናስብ ሰዎችም ቢኾን ለቅዳሴው ያለንን ቦታ መልሰን እንፈትሽ፤ ስንት ጊዜ ነው ማኅሌት ተሳተፍን ብለን ቅዳሴው እየተጀመረ ረግጠን የወጣነው? ስንት ጊዜ ነው በጌታ ቀን ቅዳሴውን ትተን መንፈሳዊ ጉዞ ብለን የሔድነው? በቤተክርስቲያን ውስጥ የትኛውም አገልግሎት ሊቀር ይችላል ቅዳሴ ግን በፍጹም አይቀርም ቅዳሴ ለቤተክርስቲያን ሕይወቷ ነውና!

የታረደው በግ ደም እንዳይፋረደን በበጉ ሠርግ ላይ እንገኝ የሕይወትንም መድኃኒት እንቀበል!


"ሰው የዘራውን ያጭዳል"

በጭካኔውና በፍትህ አልባነቱ ሞቱን የሚመኙለት የአንድ አገር ንጉሥ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ንጉሥ ያልተጠበቀ አዋጅ አስነገረ፡፡ አዋጁም “ከዚህ በኋላ የከዚህ በፊቱን አስቀያሚ ግብሬን ትቼ አዲስና ንጹህ ሰዉ ለመሆን ወስኛለሁ!” የሚል ነበር፡፡ በነቂስ ወጥቶ ንጉሡ ያስተላለፈውን አዋጅ የሰማው ሕዝብ እጅጉን ተደንቋል፡፡ እርስ በርሱም እንዴትስ እንዲህ ሆነ? ምን ቢያይ ነው በማለት አዋጁን እርስ በርሱ ያዳንቀው ጀመር፡፡ አሁንም ንጉሡ ድምጹን ከፍ አድርጎ “ከዚህ በኋላ ጨካኙ ንጉሥ፤ ፍትህ አልባው ንጉሥ የለም” ሲል በአደባባይ ቃል ገባ፡፡ ቃሉንም ጠብቆ እንደ ቃሉ ሆነ፡፡ ደጉ ንጉሥ በሚልም መታወቅ ጀመረ፡፡

ከወራት በኋላ ይሄንን ያልጠበቀውን ፍጹም ለውጥ የተመለከተ አንድ ባለሟል እንዲህ ዓንይነት ለውጥ በልቡ ምን እንዳሳደረበት የማውቅ ፍላጎቱ ጨምሮ ንጉሡን የለወጡን ምክንያት ጠየቀው፡፡ ንጉሡም እንዲህ መለሰ “በጥብቅ ደኑ ውስጥ ሳልፍ ዓይኔ በአንድ ተሳዳጅ ቀበሮ ላይ አረፈ፡፡ ቀበሮው ወደ ጉድጓዱ ገብቶ ለማምለጥ ሲሞክር አዳኙ ውሻ እግሩን ነክሶ ጉዳት ስላደረሰበት ቀበሮው በቀሪ ዘመኑ አንካሳ ሆኖ ቀረ፡፡ በዚህ ልቤ ተነክቶ ወደ መንደሩ በተመለስኩ ጊዜም አንድ ሰው ትልቅ ደንጋይ አንስቶ ውሻውን ሲያሳድድው፤ በወረወረው ደንጋይም ውሻውን እግር ሲሰብረው ተመለከትኩ፤ የሚገርመው ነገር ግን ሰውየው ድንጋዩን ወርውሮ ብዙም ሳይራመድ ከየት እደመጣ ባላየው ፈረስ በእርግጫ ጉበቱን በመመታቱ አካል ጉዳተኛ ሆነ፡፡ ፈረሱም ተራግጦ ወደ መስኩ ሲሸመጥጥ ገደል ውስጥ በመግባቱ እግሩን ተሰብሮ እንዳልሆነ ሆነ፡፡ የእነዚህን ክስተቶች ሁናቴ ባስተዋልኩ ጊዜ አእምሮየ መልሶ መላልሶ ‘መጥፎነት የባሰ መጥፎነትን ይወልዳል’ ሲል አቃጨለብኝ፡፡ እናም በዚህ እኩይ ምግባሬ የምቀጥል ከሆነ በባሰ መጥፎነት መወሰዴ ስለገባኝ እራሴን ለመለወጥ ውሳኔ ላይ ደረስኩ” በማለት በዝርዝር አስረዳው፡፡

ባለሟሉ የንጉሡን ሀሳብ ይሰማው የነበረው በሌላ እኩይ ሀሳብ ተውጦ ነበር፡፡ የንጉሡን ንግግር ከሰማ በኃላ ንጉሡን ጥዬ በንግስናው መንበር የምቀመጥበት ሰዓት ደርሷል፤ እንዴትስ አድርጌ ይህን ጅላጅል ንጉሥ ከመንበሩ ላይ ልጣለው እየለ ሴራውን እያውጠነጠነ ሲራመድ ደረጃውን ስቶ ክፉኛ ይወድቅና አንገቱን ተሰብሮ በዚያው ይህችን ዓለም ተሰናበታት፡፡

ሰው የዘራውን ያጭዳል ነው ነገሩ፡፡ ኩርንችት የኩርንችት ፍሬ ነው የሚያፋራው እንጅ ወይንን አያፈራም፡፡ እኩይነትም የትሩፋት ሥራን አይሰራም፡፡ "የሚገባበት ማን እንደሆነ አይታወቅምና አርቀህ አትቆፍረው" ይላል አገርኛ ብሂሉ እንዲህ አይነቱን ለማዘከር ነው፡፡ መሳሳት ለሥጋ ለባሽ የሚስማማው በመሆኑ ክፋት ቢያድርበትም ዋናው ማሰሪያ ውሉ ከክፋቱ ተመልሶ ከስህተት መማር መቻሉ ላይ ነው፡፡ ቅንነትን ገንዘቡ ያደረገ ምንኛ ታደለ!?

(ከማኅበራዊ ሚዲያ መንደር የተገኘ)


✞✝✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✝✞

❖የካቲት ፲፰ (18) ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ "*+

=>ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያደገ:
የአረጋዊው ቅ/ዮሴፍ የመጨረሻ ልጅ : በንጽሕናውና
ድንግልናው የተመሠከረለት : ከጸሎትና ገድል ብዛት እግሩ
ያበጠ : የመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ኤዺስ ቆዾስ ሲሆን
ቁጥሩም ከ72ቱ አርድዕት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው
ቢሉ:-

=>ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በአባቶቻችን ሐዋርያት መካከል
ትልቅ ሞገስ የነበረውና የጌታችን ወንድም ተብሎ የተጠራ
ነው:: ቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ አባቱ አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ
(የእመቤታችን ጠባቂ) ሲሆን በልጅነቱ ጥላው የሞተችው
እናቱ ደግሞ ማርያም ትባላለች:: በቤት ውስጥም
ስምዖን: ዮሳና ይሁዳ የተባሉ ወንድሞችና ሰሎሜ
የምትባል እህትም ነበረችው::

+እናቱ ማርያም ከሞተች በሁዋላ ዕጉዋለ ማውታ (ደሃ
አደግ) ሆኖ ነበር:: ነገር ግን በፈቃደ እግዚአብሔር አረጋዊ
ዮሴፍ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከቤተ
መቅደስ ሊጠብቃት (ሊያገለግላት) ተቀብሎ ሲመጣ ያ
ቤተሰብ ተቀየረ:: የበረከት: የምሕረትና የሰላም እመቤት
የአምላክ እናቱ ገብታለችና ያ የሐዘን ቤት ደስታ ሞላው::

+እመ ብርሃን ግን ገና ወደ ዮሴፍ ልጆች ስትደርስ
አለቀሰች:: የአክስቷ ልጆች የሚንከባከባቸው አጥተው
ቆሽሸው ነበር:: በተለይ ደግሞ ትንሹ ቅዱስ ያዕቆብ
ያሳዝን ነበር:: እመ ብርሃን ማረፍ አልፈለገችም::
ወዲያው ማድጋ አንስታ ወደ ምንጭ ወርዳ ውሃ አምጥታ
የሕጻኑን ገላ አጠበችው:: (በአምላክ እናት የታጠበ
ሰውነት ምስጋና በጸጋ ይገባዋል!)

+እመቤታችን ጌታ ከመወለዱ በፊት ለ9 ወራት: ከተወለደ
በሁዋላ ደግሞ ለ2 ዓመታት ሕጻኑን ያዕቆብን
ተንከባከበችው::

ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ግን ድንግል ማርያም አምላክ
ልጇን ይዛ ተሰዳለችና ተለያዩ:: ከስደት መልስ ግን ለ25
ዓመታት ቅዱስ ያዕቆብ ከጌታችን ጋር ሲያድግ ወላጅ እናቱ
ትዝ ብላው አታውቅም:: አማናዊቷ እናት ከጐኑ ነበረችና::

+ሊቃውንት እንደ ነገሩን እመቤታችን ለቅዱስ ያዕቆብ
ያልሰጠችው ነገር ቢኖር ሐሊበ ድንግልናዌ (የድንግልና
ወተትን) ብቻ ነው::

ስለዚህም:-
"እመ ያዕቆብ በጸጋ ማርያም ንግሥተ ኩሉ" ይላል
መጽሐፍ:: (መልክዐ ስዕል)

+ቅዱስ ያዕቆብ "የጌታ ወንድም" ተብሎ በተደጋጋሚ
በሐዲስ ኪዳን ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ:-
1.ለ30 ዓመታት ሳይነጣጠሉ አብረው በማደጋቸው፡፡
2.የጌታችን የሥጋ አያቱ (የቅድስት ሐና) የእህት ልጅ
በመሆኑ፡፡
3.በዮሴፍ በኩልም የአንድ ቅድመ አያት ልጆች
በመሆናቸው፡፡
4.ጌታችን ከትህትናው የተነሳ ደቀ መዛሙርቱን
"ወንድሞች" ይላቸው ስለ ነበር ነው:: (ሥጋቸውን ተዋሕዶ
ተገኝቷልና)

+ራሱ ቅዱስ ያዕቆብ ግን "የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ
ባሪያ ነኝ" ብሎ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት
ገልጧል:: (ያዕ. 1:1) ቅዱስ ያዕቆብ ጌታችን ሲያስተምር
ተከተለው::

¤ከ72ቱ አርድእት ተቆጠረ
¤3 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን ተማረ
¤ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንግል ማርያምና ከቅዱስ ዮሐንስ
ጋር ሆኖ "የጌታን ትንሳኤ ሳላይ እሕል አልቀምስም" ብሎ
ማክፈልን አስተማረ
¤መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ወንጌልን አስተማረ
¤የኢየሩሳሌም የመጀመሪያው ሊቀ ዻዻስ ሆኖ አገለገለ
¤በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት የሐዋርያት
ሲኖዶሶችን በሊቀ መንበርነት መራ
¤ሙታንን አስንስቶ: ድውያንን ፈውሶ: የመካኖችን ማሕጸን
ከፍቶ: አጋንንትንም አስወጥቶ ብዙ ተእምራትን ሠራ::
እጅግ ብዙ አይሁዳውያንን ወደ አሚነ ክርስቶስ መልሶ
መልካሙን ገድል ተጋደለ::

+በመጨረሻ ዘመኑ ያላመኑ የአይሁድ አለቆች ወደ ቤቱ
ተሰብስበው "የናዝሬቱ ኢየሱስ ማነው? የማንስ ልጅ
ነው?" ሲሉ ጠየቁት:: እነርሱ ሰይጣን በሰለጠነበት
ልቡናቸው "የዮሴፍ ልጅ ነው: የእኔም ወንድሜ ነው"
እንዲላቸው ጠብቀው ነበር:: (ሎቱ ስብሐት ወአኮቴት!)

+በልቡናቸው ያሰቡትን ተንኮል የተረዳው ሐዋርያ ወደ ቤቱ
ጣራ ወጥቶ መናገር ጀመረ:: "ለስም አጠራሩ ጌትነት
ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ:
ወልደ አብ ወልደ ማርያም: ሥግው ቃል: እግዚአብሔር
ነው:: እኔም ፍጡሩና ባሪያው እንጂ እንደምታስቡት
ወንድሙ አይደለሁም" አላቸው::

+ንዴታቸውን መቆጣጠር ያልቻሉት አይሁድ ከላይ
ወጥተው ወደ መሬት ወረወሩት:: በገድል የተቀጠቀጠ
አካሉንም እየተፈራረቁ ደበደቡት:: አንዱ ግን ከእንጨት
የተሠራ ትልቅ ገንዳ አምጥቶ የቅዱሱን ራስ ደጋግሞ
መታው:: ጭንቅላቱም እንዳልነበር ሆነ:: ሰማዕቱ ሐዋርያ
ቅዱስ ያዕቆብ ወደ ወደደው ክርስቶስ በዚህች ቀን ሔደ::

+ቅዱሱ ሐዋርያ ያዕቆብ ቤቱን እንደ ቤተ መቅደስ አበው
ሐዋርያት ይጠቀሙባት ነበር:: በመላ ዘመኑ የሚያገድፍ
ነገር (ጥሉላት) ቀምሶ: ጸጉሩን ተላጭቶ: ገላውን ታጥቦና
ልብሱን ቀይሮ አያውቅም::

"ወዝንቱ ጻድቅ እኅወ እግዚእነ::
ኢያብአ ውስተ አፉሁ ሥጋ ወወይነ::
ወኢገብረ ሎቱ ክልኤተ ክዳነ::" እንዲል::

+ከጾም: ከጸሎትና ከመቆሙ ብዛትም እግሩ አብጦ
አላራምድህ ብሎት ነበር:: ስለዚህም አበው "ጻድቁ
(ገዳማዊው) ሐዋርያ" ይሉታል:: ቅዱሱ ሐዋርያ
"የያዕቆብ መልዕክት" የሚለውን ባለ 5 ምዕራፍ
መልዕክት ጽፏል::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሙ ይባል ዘንድ
ካደለው ሐዋርያ በረከትን ያድለን:: በምልጃውም
ምሕረትን ይላክልን::

=>የካቲት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (የቅዱስ ዮሴፍ ልጅ : ከ72ቱ
አርድእት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ መላልዮስ ጻድቅ ሊቀ ዻዻሳት (በአንጾኪያ
ሊቀ ዽዽስና ተሹሞ በአርዮሳውያን ብዙ ግፍ የደረሰበትና
በስደት ያረፈ አባት ነው)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ

=>+"+ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ
ያዕቆብ: ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች:: ሰላም ለእናንተ
ይሁን:: ወንድሞቼ ሆይ! የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን
እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ
እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት:: ትዕግስትም ምንም
የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ
ሥራውን ይፈጽም:: +"+ (ያዕ. 1:1)

>


✞✝✞ እንኩዋን ለታላቁ "የጌታ ጾም (ጾመ እግዚእ)" በሰላም አደረሳችሁ ✞✝✞

+*" ጾመ እግዚእ "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን
እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት:: "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው:: የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ አዝማደ መባልዕት (የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች) መከልከልን ይመለከታል::

+"7ቱ" አጽዋማት:-
1.ዓቢይ ጾም
2.ጾመ ፍልሠታ
3.ጾመ ሐዋርያት
4.ጾመ ነቢያት
5.ጾመ ድኅነት
6.ጾመ ነነዌ እና
7.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::

+በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት
ድረስ መጾም ይገባል:: ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት
አለው:: ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ
አስፈላጊነቱ ነው:: "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
መጠየቁ ይቀላል::

+ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ
እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን
መቃወም ነውና:: እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ
አለች:: የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል
እንከራከራለን::

+ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች
በጣም ይገርሙኛል:: ኃጢአትን ለመሥራት : ጾምንም
ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም:: እኛ ግን
¤ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. 4:2)

¤አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. 9:19, ነገ. 19:8, ሐዋ.
13:3, ቆሮ. 4:11) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን
እንጾማለን::

+የጾሙ የመጀመሪያው ሳምንት (ዘወረደ) የሚጾመው
እስከ 12 ሰዓት ሲሆን ከቅድስት (ከ2ኛው ሳምንት) እስከ
ተጽኢኖ (የኒቆዲሞስ ዓርብ) ድረስ ደግሞ እስከ 11
ሰዓት ይጾማል::
በሰሙነ ሕማማት ግን የምንጾመው "እስከ ይሠርቅ
ኮከብ" (እስከ ምሽት 1 ሰዓት) ድረስ ይሆናል::

+ነገር ግን ሁሉም እንደ መጠኑ ነውና ከመምሕረ ንስሃ
ጋር ሊጨዋወቱት ይገባል:: በዓቢይ ጾም ለቻለ ቂጣ
በጨው እየበላ: ውሃ እየተጐነጨ ሊጾም ይገባል::
በእነዚህ 55 ቀናትም ከዕለተ ሆሳዕና በቀር ከበሮ
አይጐሰምም:: ጸናጽል አይጸነጸልም:: ተድላ ደስታም
አይደረግም::

+አብዝቶ መብላት : ሳቅ ማብዛትና ጌጥን ማብዛትም
እንዲሁ አይገባም:: ለቻለ ደግሞ በሌሊት ሰዓታቱን፡
በግህ ኪዳንና ስብሐተ ነግሁን : በመዓልት ቅዳሴውን :
በሰርክ (ምሽት) ደግሞ ምሕላውን ሊሳተፍ ይገባል::

+በእነዚህ 55 ቀናት ፈቃደ ሥጋ ሊደክም : ፈቃደ ነፍስ
ልትሰለጥን ግድ ነውና:: ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወቅቱ
ምጽዋትና ጸሎት የሚደረግበት ነው:: በዚያውም ላይ
ነገሮችን እያመቻቹ በእነዚህ ዕለታት ቅዱስ ቃሉን
መስማት (ማንበብ) ይገባል:: በትዳር ውስጥ ላሉም
መኝታን መለየት ግድ ነው::

=>ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው ይህ ጾም=
1.ዐቢይ (ታላቁ) ጾም
2.የጌታ ጾም
3.ጾመ ሑዳድ
4.የድል ጾም
5.የካሳ ጾም
6.አርባ ጾም
7.የፍቅር ጾም . . .
በሚሉ መጠሪያዎችም ይታወቃል::

=>የጾሙ መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ=
1.ጾመ ሕርቃል
2.ጾመ በረከት ዘሐዋርያት
3.ሰሙነ ዘወረደም ይባላል::

=>ጾሙን የሰላም : የፍቅር : የምሕረት : የፀጋ :
የበረከት ያድርግልን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን፡፡

=>+"+ አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ
በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን
እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም
እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ:: +"+ (ትን. ኢዩኤል 2:12)

✞✝✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✝✞
@mekra_abaw

2k 0 28 2 17

ስለዚህ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር፡- ‹‹ ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እምአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም ፤ ለሕዝብሽ ፣ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ ፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ዅሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትኾኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ሥልጣን አግኝተሻል ›› በማለት አመስግኗታል /አንቀጸ ብርሃን/፡፡

አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡- ‹‹ ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ ፤ የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት፣ መርገም ( ኀጢአት ) ባጠፋን ነበር ›› ብለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡– ‹‹ ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ፡፡ መዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፡፡ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ፡፡ ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ፤ ›› ሲሉ ይማጸኗታል /ቅዳሴ ማርያም ቍ.፻፷፭-፻፸፩/፡፡

ስለዚህም ዘወትር በሥርዓተ ቅደሴአችን፡- ‹‹ ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ዅል ጊዜ ድንግል የምትኾኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊልን፡፡

በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡ በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡

የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን ዘንድ በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፡፡ በእውነት ንግሥት የምትኾኚ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡

ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ፤ ›› በማለት እመቤታችንን እንማጸናታለን፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፤ ›› በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት፣ ጻድቃን ፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባ ፣ እንደሚገባ ተናግሯል /መዝ.፹፰፥፫/፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው? ›› በማለት እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚጠራ ፣ እንደሚያከብር ፣ እንደሚቀድስና ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል /ሮሜ.፰፥፴፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው፤ ›› /መዝ.፹፮፥፫/ በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ዅሉ ልዩ ነው፡፡ ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡-

👉 ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመኾኗ፤
👉 አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለዱ፤
👉 ከመለለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመኾኗ፤
👉 በሁለቱም ወገን (በአሳብም በገቢርም) ድንግል በመኾኗ፤
👉 አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይኾን የእናትነት በመኾኑ፤
👉 ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ ስለመረጣት ነው፡፡

ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን፣ እንደበላዔ ሰብእ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ለመኾን ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን፡፡

✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
@mekra_abaw


የካቲት 16
ኪዳነ ምህረት


‹ ኪዳን › የሚለው ቃል ‹‹ ተካየደ – ተዋዋለ ፤ ቃል ኪዳን ተጋባ ፤ ተማማለ ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ፣ ትርጕሙም ኪዳን፣ ውል ፣ መሐላ ፣ ቃል ኪዳን ፣ የውል ቃል ማለት ነው /ዘዳ.፳፱፥፩፤ ኤር.፴፩፥፴፩-፴፫፤ መዝ.፹ ፰፥፫/፡፡ በሌላ በኩል ኪዳን የጸሎት ስም ሲኾን፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት ኪዳን ይባላል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን (ውል ፣ ስምምነት) የተቀበለችበት ዕለት (የክብረ በዓል ስም) ደግሞ ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡

በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ኾና ‹‹ ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማኅፀንየ ዘጾረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ ፤ ከአንተ ጋር ከአገር ወደ አገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ ›› እያለች ስትጸልይ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ ወደእርሷ መጥቶ ‹‹ ሰላም ለኪ ማርያም እምየ ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው? ›› አላት፡፡

እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን ፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ፤ ለእመቤታችንና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሰየሙትን ዅሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡

ጌታችንም ‹‹ ይህን ዅሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው፤ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ›› ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው ‹‹ … ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት፡፡ አንተ ‹ መታሰቢያሽን ያደረገ ፣ ስምሽንም የጠራ ፣ የዘለዓለም ድኅነትን ይድናል› ብለሃታልና …፤›› በማለት የሚማጸነው፡፡

በተአምረ ማርያም መጽሐፍ እንደተመዘገበው በዚህ ዕለት የሚታሰቡ ሁለት ተአምራት አሉ፤ ከእነዚህም አንደኛው የስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት ከቤቱ ገብቶ ‹‹ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ ሌላ ምግብ አልበላም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆየና ‹‹አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው ›› በማለት፣ ‹‹ የእግዚአብሔርን እንግዳ›› ላለማሳዘን ሲል ልጁን አርዶ አቀረበለት፡፡

እንግዳ መሰሉ ሰይጣንም ሥጋውን ቅመስልኝ ብሎ ግድ አለው፡፡ ስምዖንም (በላዔ ሰብእ) አርዶ ያዘጋጀውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ሰይጣን ስላደረበት (ስለተዋሐደው) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና መንገደኛውን ዅሉ ይበላ ጀመር፡፡ በአጠቃላይ ፸፰ ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ በቍስል የተመታ ሰው አገኘና ሊበላው ሲል ‹‹ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ በሥላሴ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ለመነው፤ እርሱም ዝም አለው፡፡

በመጨረሻም ‹‹ በድንግል ማርያም ስም ›› አለው፡፡ ስምዖን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜም ወደ ልቡናው ተመልሶ ‹‹እስኪ ቃሉን ድገመው ›› አለው ፤ በሽተኛውም መልሶ ‹‹ ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ ‹‹ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ ›› ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው ፤ ውኃው ጕሮሮውን እንኳን ሳያርስለት ‹‹ ጨረስህብኝ ›› ብሎ ነጥቆት ሔደ፡፡

በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አግኝቶ ሊበላ ሲል ገበሬው ‹‹በላዔ ሰብ የምትባል አንተ ነህ? ›› ባለው ጊዜ ‹‹ ለካስ አመሌን ሰው ዅሉ አውቆብኛል ›› ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን ‹‹ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ? ›› አለችው፡፡

ጌታችንም ‹‹ ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ፣ ፈጣሪውን የካደ ሰው ይማራልን? ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?›› ብላ ስምዖንን (በላዔ ሰብእን) አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

ሁለተኛው ተአምር ደግሞ ከብሮ ከኖረ በኋላ ለድህነት በተጋለጠ አንድ ምእመን ላይ የተደረገ ነው ፤ ከክርስቲያን ወገን የኾነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹ ከብሬ በኖርኹበት አገር ተዋርጄ አልኖርም ›› ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ከአገሩ ወጥቶ ሲሔድ ሰይጣን ያዘነ ሰው መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ‹‹ ሥላሴን ፣ ጻድቃንን ፣ ሰማዕታትንን ፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን ወርቅ እሰጥሃለሁ ›› አለው፡፡ ዅሉንም ካደለትና ወርቁን ተቀብሎ ዞር ሲል ‹‹ ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያም ‹ የአምላክ እናት አይደለችም› ብለህ ካድልኝ ›› አለው፡፡

ሰወየውም ‹‹ እርሷንስ አልክድም ›› ስላው በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት የሟቹን ነፍስ ሊወስዱ ሲሉ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ፡፡ እመቤታችንም ጌታችንን ‹‹ ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከልብኑ ይትመሐር እምየ፤ እናቴ፣ ውሻ ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም፡- ‹‹‹ ስምሽን የጠራውን፣ መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ › ያልኸው ቃል ይታበላልን? ›› አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ምሬልሻለሁ›› አላት፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ ›› ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከላይ በተአምራቱ እንደተመለከትነው አንዱ ለእመቤታችን የሰጠው የአማላጅነት ኪዳን ነው፡፡ ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን ፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማድረግ ፣ ማስማር ( ይቅርታ ማሰጠት ) ማለት ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ዅሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን ‹‹ ሰአሊ ለነ ቅድስት ፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን ›› እያሉ ለሚለምኗት ዅሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የምንከተል ምእመናን ዅሉ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ እንደመኾኗ ከዅሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ኾነ በሰው ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት ወይም ቅርብ መኾን ደግሞ አንድን ጉዳይ በቀላሉ ለማስፈጸም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ፡-

👉 መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመኾኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ኾኗል /ሉቃ. ፩፥፲፱-፳፮/፡፡
👉 አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመኾኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች /መጽሐፈ አስቴር ፫፥፲/፡፡
👉 ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመኾኑ ‹‹ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ?›› በማለት ለእስራኤላውያን ምሕረትን አሰጥቷል /ዘፀ.፴፪፥፲፬/፡፡


††† እንኳን ለታላቁ ሊቅና የተዋሕዶ ጠበቃ ቅዱስ ሳዊሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ †††

††† ቅዱስ ሳዊሮስ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው። ወቅቱ መለካውያን (ሁለት ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው። ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል።

ቅዱሱ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ብዙ ሆኖላታል። የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል። ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ።

ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ።" አለችው። እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም።" ሲል መለሰላት። አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት።

እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ። መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው። ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጓዘ። እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ።

በምድረ ግብጽም የጵጵስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ፤ አጸና። በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ።

አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት። ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የካቲት ፲፬ ቀን ዐርፏል።

††† አምላከ ቅዱሳን ሊቃውንት የድንግል እመቤታችንን ጣዕሟን ፍቅሯን ያሳድርብን። የአበውን ሃብትና በረከትም አይንሳን።

††† የካቲት ፲፬ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
፪.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት
፫.አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳሳት
፬.ቅዱስ ዳርዮስ
፭.ቅድስት ሊድና

††† ወርኀዊ በዓላት
፩.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
፪.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
፫.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
፬.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
፭.አባ ስምዖን ገዳማዊ
፮.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
፯.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

††† "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።" †††
(ይሁዳ ፩፥፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††




💢የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት💢

ክፍል ፴፮ [36]

📗የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት

፩.መልእክት ኀበ ሰብአ ሮሜ

ሮም የኢጣልያ ዋና ከተማ ስትሆን በቀድሞ ዘመን ግን በቅኝ ግዛት ለተያዙ አገሮች ሁሉ ርዕሰ ከተማ ነበረች።

የንጉሠ ነገሥት ከተማ ስለሆነች የልዩ ልዩ ሰዎች መናገሻ አድርገው በተለይም አይሁዶች ምኩራብ ሰርተው ሃይማኖታቸውን አጽንተው ብዙ አሕዛብ እየመለሱ ይኖሩ ነበር።

❖ የክርስትና ሃይማኖትም ፈጥኖ ወደ ሮም የገባው ቅዱስ ጳውሎስ ከሮም ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ካላቸው ሀገሮች እንደ ኤፌሶን፣ቆሮንቶስ፣ተሰሎንቄ፣አቴና ባሉት ከተማዎች ትምህርቱና ተአምራቱ ተረድቶ ነበር።ከእነዚህ ሀገሮችም ሰዎች ሮም ሲሄዱ ትምህርቱንና ክርስትናውን ለሌላው ያስረዱ ስለነበር ነው።

►በጰንጠቆስጤ (መንፈስ ቅዱስ በወረደበት) ዕለት በግል ፍላጎታቸው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ከነበሩት ሮማውያን አይሁድ ውስጥ የቅዱስ ጴጥሮስን ሰብከት ሰምተው አምነው ተጠምቀው ሄደው ሮም ውስጥ ክርስትናን ያስፋፉ ሰዎች ነበሩ።

►ቅዱስ ጴጥሮስ ሮም ገብቶ ሲሰብክ ስለነበር ቅዱስ ጳውሎስ በ52 ዓ.ም ከአቴና ወጥቶ ወደ ቆሮንቶስ በሄደ ጊዜ በቀላውዴዎስ ቄሣር አዋጅ ከሮም ተሰደው የመጡ አቂላንና ሚስቱን ጵርስቅላን አገኘ።ከእነርሱም ጋር አንድ ዓመት ከስድስት ወር በዚሁ በቆሮንቶስ ቆየ። አቂላና ጵርስቅላ በሮሜ ስለሚገኙ ክርስቲያኖች ለቅዱስ ጳውሎስ ነገሩት። ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቷን ሲጽፍ ከሮሜ ክርስቲያኖች መካከል የሚያውቋቸው ስላልነበሩ አቂላንና ጵርስቅላ ከከተማዋ ክርስቲያኖች ታዋቂ የሆኑትን የአንዳንዶቹን ስም ሰጥተውት መልእክቲቱን አዘጋጅቶ የክንክራኦስ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቢት በነበረችው በፌቨን እጅ በ54 ዓ.ም አካባቢ ላከላቸው፡፡(ሮሜ 16፥1) የሮሜ መልእክት 16 ምዕራፎች አሉት።

🍀የሮሜን መልእክት የጻፈበት ምክንያት

፩. ሮም ውስጥ የሚኖሩት ክርስትናን የተቀበሉት ሰዎች ወንጌል የምታስተምረውን ፍቅርና ሰላሞ ትተው በሥርዓትና በባሕል አይሁድና አሕዛብ ባለመስማማት በጭቅጭቅ ይኖሩ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲሰማ ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅና በክርስትና እምነት ትምህርት እንዲኖሩ ለማድረግ መከፋፈል እንዳይኖር ይህችን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡ሮሜ1፥5-7

፪.አንዳንድ የክርስትና እምነት ጠላቶች የሆኑ ክርስቲያኖች በመንግስት ላይ ያምጻሉ ግብርም አይከፍሉም እያሉ የሀሰት ወሬ እያወሩ ክርስቲያኖችን በሥጋ ለተሾሙ ሁሉ እንዲገዙ (እምነታቸውን እስካልነኩባቸው ድረስ) በነፍስ ግን ለከርስቶስ መገዛት እንደሚገባ ለማስረዳት ጽፎላቸዋል።ሮሜ 13፥5-7

፫.ወደ ሮም እነርሱን ለመጎብኘት ከመሄዱ በፊት እየተማሩ እንዲቆዩና የጉዞውን ሁኔታም ለማመቻቸት ጽፎላቸዋል።
መ/ር ኢሳይያስ ሀብቴ

@mekra_abaw




✞✝✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✝✞

❖ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

+*" ማር ፊቅጦር "*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ:: ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ! ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው::

=>እስኪ ከበዛው መዓዛ-ገድሉ ጥቂት እንካፈል:-
+ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል:: አረማዊና
ጨካኝ ነው:: እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ
ትባላለች:: ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው 20 ዓመት
ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ
3ኛ አድርጐ ሾመው::

+የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን
የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ
ያማረ: በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት:
ይወዱትም ነበር::

+እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም: ነዳያንን ሲያበላ ይውል
ነበር:: ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ እኩሉን
የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆንኮ
እርሱ የንጉሡ 3ኛ: የሠራዊትም አለቃ ነው:: በዘመኑ
የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ:: ዘመነ
ሰማዕታትም ጀመረ:: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ:: ከ47
ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ::
በመጋዝ ተተረተሩ:: ለአራዊት ተሰጡ:: በግፍም
ተጨፈጨፉ:: ቀባሪ አጥተውም ወደቁ::

+በዚሕ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ
ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ::
ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ::

+ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ
ግብፅ አወረዱት:: መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ
መኩዋንንቱ ሁሉ ተዘባበቱበት:: እርሱ ከምድራዊ ንግሥና
ሰማያዊ መንግስትን: በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ
ሲል መናቅን መርጧልና::

+ለቀናት: ለወራትና ለዓመታት መኩዋንንቱ እየተፈራረቁ
አሰቃዩት:: በርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት
አልነበረም:: አካሉን ቆራርጠዋል: ዓይኖቹን አውጥተዋል:
ምላሱንም ቆርጠዋል:: ሚያዝያ 27 ቀን ግን በሰይፍ
አንገቱን ቆርጠውታል:: ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን
በታላቅ ማክበር ታከብረዋለች::

❖እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው:-
"እንደ አቅሙ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ:
ስምህን ያከበረ: የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግስተ
ሰማያት አስገባዋለሁ::"

❖ይህች ቀን ማር ፊቅጦር የተወለደባት ናት፡፡ እናቱን ቅድስት ማርታ (ሶፍያንም) እናስባለን፡፡

❖ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን:: ከቃል ኪዳኑ አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን::

✞✞ ቅዱስ አውሳብዮስ ካልዕ (ጥዑመ ዜና) ✞✞

=> ቅዱስ አውሳብዮስ በወጣትነቱ ከተባረከች ሚስቱ ጋ
በድንግልና የኖረ; በዘመኑ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ ይጸልይ;
4,000
አቡነ ዘበሰማያት በአንድ ቀን ያደርስ የነበረ; ስለ
ሃይማኖትም በቀስት የተወጋ; በእሳት የቃጠለ; አካሉን
ቆራርጠው
የጣሉትና እግዚአብሔር ከሞት ያስነሳው ጻድቅና ሰማዕት
ነው:: ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ከነሥጋው ወደ ሰማይ
ተነጥቆ ለ14
ዓመታት ቆይቷል:: ወደ ምድርም ተመልሶ ለ40 ዓመታት
በሐዋርያነት ከ85,000 በላይ አሕዛብን ወደ ሃይማኖት
መልሷል::
ጌታም በስምህ የተማጸነውን እስከ 7 ትውልድ
እምርልሃለሁ ብሎታል::"

❖አባቶቻችን ደግሞ 'ስም አጠራሩ የከበረ ዜና ሕይወቱ
ያማረ' ሲሉ ይጠሩታል::

❖ ከበረከቱ ያድለን::

✞ የካቲት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አውሳብዮስ ጻድቅ (ጥዑመ ዜና)
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት (ልደቱ)
3.ቅዱስ ሰርግዮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ መፁን ቀሲስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (የቅ/ፋሲለደስ ልጅ)
6.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት
7.አባ ክፍላ
8.አባ ኅብስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት
3."99ኙ" ነገደ መላዕክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ : እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ :
ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ
አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል
የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ
ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ
መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)

✞✝✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✝✞




††† እንኳን ለኢትዮዽያውያን ሰማዕታት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ኢትዮዽያውያን ሰማዕታት †††

††† በ1929 ዓ/ም: የካቲት 12 ቀን ከ30,000 በላይ ኢትዮዽያውያን አባቶች: እናቶች: ወጣቶችና ሕፃናት በሮማዊው የፋሽስት ጦር ደማቸው ፈሷል:: እነዚሕ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ጐርፍ አዲስ አበባ ላይ የፈሰሰው ስለ ሃገር ፍቅር ብቻ አልነበረም:: ስለ ቀናች ሃይማኖት ተዋሕዶ ጭምር ነው እንጂ::

††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ግፃዌ ላይ ስማቸውን ጽፋ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር እንዲህ ታስባቸዋለች::

"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ::
ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::"
(መዝ. 78:1)

††† ሰማዕታቱን እናስባቸው!

††† ሶምሶን ረዓይታዊ †††

††† እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ: በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ርሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ:: እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ:: ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,200 ዓመታት በሁዋላ መሆኑ ነው::

በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር:: የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን: አማሌቅ: ኢሎፍሊ ስንኩዋ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው::

በጊዜውም የእሥራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) 40 ዓመት በባርነት ገዟቸው:: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) : በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው::

እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት : በአምላኩ ኃይል ታደገ:: ከኃይሉ ብዛት የተነሳም:-
¤አንበሳን እንደ ጠቦት ይገድል (መሣ. 14:5)
¤300 ቀበሮዎችን አባሮ ይይዝ (መሣ. 15:3)
¤በብርቱ ገመዶች ሲያስሩት እንደ ፈትል ይበጣጥሰው (መሣ. 15:14)
¤በአህያ መንጋጋ ሽህ ሰው ይገድል (መሣ. 15:15)
¤ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር:: (መሣ. 16:3)

ውሃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል:: (መሣ. 15:18) በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል:: ጠላቶቹም ዐይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል::

በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ : አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል:: (መሣ. 13--16)
ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው::

††† በዘመኑ ሁሉ ቅዱስ ሚካኤል ረድቶታልና በዚህች ቀን መታሠቢያው ይደረግለታል::

††† የካቲት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."30,000" ሰማዕታተ ኢትዮዽያ (ሮማዊው ፋሽስት የገደላቸው)
2.ቅዱስ ሶምሶን ረዓይታዊ (የእስራኤል መስፍን)
3.ቅዱስ አባ ገላስዮስ ገዳማዊ
4.ቅድስት ዶርቃስ

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ድሜጥሮስ
4.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
6.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
7.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
8.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ

††† አምላከ አበው ቅዱሳን መዓዛ ቅድስናቸውን ያሳድርብን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† "ሶምሶንም:- 'ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል : እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አስበኝ? አምላክ ሆይ! . . . እባክህ አበርታኝ?' ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ:: . . . ሶምሶንም:- 'ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት' አለ:: ተጐንብሶም ምሰሶዎችን በሙሉ ኃይሉ ገፋ:: . . . በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ::"
(መሣ. 16:28)

††† "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ . . ." †††
(ዕብ. 11:32)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††



20 last posts shown.