ብርታት ባልሆነ ብርታታችን፥ ኃይል በሌለው አቅማችን ተደግፈን ነገሮችን ብንጀምር እርሱ ግን ለከንቱነታችን አሳልፎ አይሰጠንም። ያለእርሱ ብንጀምረው አኩርፎ አይተወንም፥ በርኅሩኅ ዐይኖቹ እኛ ልጆቹን በስስት እያየ ይጠብቀናል፥ ስንወድቅ መደገፊያና መነሻ ብቻ አይደለም መውደቂያም ይሆንልናል። የወደቅንበት እርሱ አራግፈን ምናስለቅቀው አቧራን ሳይሆን አፍሰን የምንይዘው ፍጹም ብርታትን እነሆ ይለናል። ዓለም ጥላን እርሱ ላይ ስንወድቅ አንቆስልም፥ ይልቁንስ በክፉዋ ዓለም ጓሮ የቆሰልነውን ቁስል አድርቆ፥ ጉዳታችንን አብሶ የወደቅንበት እርሱ እራሱ መነሻችን ይሆንልናል። ተምረናልና አሁን ብቻችንን መንገዱን አንጀምርም፥ መንገድ የሆነ እርሱን እንይዛለን። በእርሱ ላይ መውደቅ መውደቅ እንደሆነ አላስብም፥ በእርሱ ላይ መውደቅማ መነሳት ከፍ ከፍ ማለት ነው! ተስፋ ባናደርግበትም እርሱ ግን ተስፋን አልቆረጠብንም፥ እንድንነሳ በእርሱ ላይ መውደቃችንን በቅርብ ሆኖ ይጠባበቃል። ስንነሳም ኃይልን ያስታጥቀናል፥ መንገዳችንም ፍጹም ይቀናል። በእውነት “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።” (ኢሳይያስ 40፥31) አቤቱ ጌታ ሆይ አንተን አምኖ በአንተ ላይ መውደቅን፥ በተስፋህም በድል መነሳትን ስጠን። አሜን በእውነት🌸🌷🧎♀