በረመዷን ወር ፆም ላይ እያለ ግንኙነት የፈፀመን ሰው የሚመለከቱ ህግጋት
~
1. በረመዷን ወር ፆም ላይ እያለ የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈፀመ ሰው በቁርኣን፣ በሱናና በኢጅማዕ ፆሙ ይበላሻል፡፡
2. በተጨማሪ ለፈፀመው ከባድ ጥፋት ማካካሻ (ከፋ'ራ) የመፈፀም ግዴታ አለበት፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
3. ሴቷ በጥፋቱ ላይ ተገዳ ከገባች ቀዷም፣ ማካካሻም የለባትም፡፡ [ሸርሑል ሙምቲዕ፡ 6/404] በምርጫዋ ከገባች ማካካሻ ይመለከታታል ወይስ አይመለከታትም በሚለው ብርቱ ውዝግብ ውስጥ መግባት ስላስፈራኝ አልፌዋለሁ፡፡
4. በእለቱ ፆመኛ ሳይሆን ቀርቶ ግንኙነት ቢፈፅም ማካካሻ አይመለከተውም፡፡
5. አንድ ሰው ረስቶ በመብላቱ ወይም በመጠጣቱ ምክንያት ፆሙ የተበላሸ መሰለውና ከዚያ በኋላ ግንኙነት ቢፈፅም ማካካሻ የለበትም፡፡ ረስቶ መብላትና መጠጣት ፆም እንደማያፈርስ እያወቀ ከዚያ በኋላ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ማካካሻ አለበት፡፡
6. በፆም ግንኙነት መፈፀም ሐራም መሆኑን የማያውቅ ሰው ጥፋቱን ቢፈፅም በጥፋቱ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ማካካሻም የለበትም፡፡ “ክልክልነቱን አውቃለሁ፡፡ ቅጣቱን ነው የማላውቀው” ቢል ከተጠያቂነት አይተርፍም፡፡ ማካካሻም ይመለከተዋል፡፡ [አልመጅሙዕ፡ 6/381]
7. ፆመኛ መሆኑን ረስቶት የፈፀመ (ምናልባት ካጋጠመ) ቀዷእም ማካካሻም የለበትም፡፡
8. ፈጅር ገና ያልወጣ መስሎት ግንኙነት የፈፀመና ኋላ ላይ ፈጅር ወጥቶ እንደነበር ያረጋገጠ ሰው ቀዷእም ማካካሻም የለበትም፡፡
9. ግንኙነት እየፈፀመ እያለ ፈጅር የወጣበት ሰው ቀጥታ ማቆም አለበት፡፡ ካቆመ ቀዷእም ማካካሻም የለበትም፡፡ ከቀጠለ ግን ማካካሻ ይመለከተዋል፡፡
10. አንድ ሰው ግንኙነት በመፈፀሙ ምክንያት ማካካሻ ግዴታ ከሆነበት በኋላ በእለቱ ህመም ወይም መንገድ ቢያጋጥመው ማካካሻው አይቀርለትም፡፡
11. አውቆ በመብላት ወይም በመጠጣት ፆሙን ካፈረሰ በኋላ ግንኙነት የፈፀመ ሰው አቡ ሐኒፋ፣ ማሊክ፣ አሕመድ፣ ኢብኑ ተይሚያ፣ ኢብኑል ቀይም፣ ኢብኑል ዑሠይሚን፣ ... ማካካሻ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በዚህ አይነት ሰው ላይ ማካካሻ ግዴታ ባይሆን ግንኙነት ለመፈፀም ያለመ ሁሉ ሆን ብሎ አስቀድሞ ፆሙን በመብላትና በመጠጣት የማፍረስ ብልጠት ሊጠቀም ይችላል የሚል ነው፡፡
12. ግንኙነቱን የፈፀመው ከረመዷን ወር ውጭ ከሆነ ፆሙ ትርፍ ፆምም ይሁን የረመዷን ቀዷእም ይሁን ሌላ ግዴታ ፆምም ቢሆን ማካካሻ የለበትም፡፡ ማካካሻ የሚመለከተው ግንኙነቱ በረመዷን ወር ከተፈፀመ ብቻ ነው፡፡
13. በረመዷንም መንገደኛ (ሙሳፊር) ከሆነ ግንኙነት ቢፈፅምም ቀዷእ እንጂ ማካካሻ አይመለከተውም፡፡ ምክንያቱም መንገደኛ ፍላጎቱ ከሆነ የማፍጠር መብት አለውና፡፡
14. በአንድ ቀን ደጋግሞ ግንኙነት የፈፀመ ሰው ያለበት ማካካሻ በኢጅማዕ አንድ ብቻ ነው፡፡ ግንኙነቱ በተለያየ ቀን የተፈፀመ ከሆነ በቀኖቹ ብዛት ልክ ማካካሻ አለበት፡፡
15. እስካሁን ያሳለፍነው ቀጥታ ግንኙነት ከተፈፀመ ነው፡፡ እንጂ ግንኙነቱን በሌላ አካሎቿ ለምሳሌ ጭኗ ላይ ቢያደርገው ቀዷእ እንጂ ማካካሻ የለበትም የሚለው አቋም የብዙሃን ዑለማእ ምርጫ ነው፡፡ ግንኙነቱ የተፈፀመው በፊንጢጣ ከሆነ ድርጊቱ ከባድ ወንጀል ከመሆኑም ባለፈ ማካካሻ አለበት፡፡
16. ግንኙነቱ በረመዷን ቀን እስከሆነ ድረስ የፈፀመው ከተፈቀደለት ሴት ጋርም ይሁን በሐራምም ይሁን የማካካሻው ብይን እንዳለ ነው፡፡ እያወራን ያለነው ስለ ወንጀሉ እንዳልሆነ ይታወስ፡፡
ማካካሻውን በተመለከተ
-
[ሀ] በረመዷን ቀን ግንኙነት በመፈፀም ፆሙን ያፈረሰ ሰው ጥፋቱን ለማካካስ የተቀመጡት ነጥቦች ሶስት ናቸው፡፡ እነሱም
1- ባሪያ ነፃ መውጣት፣
2- ሁለት ወር በተከታታይ መፆም እና
3- ስልሳ ምስኪኖችን ማብላት፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
እነዚህ ትእዛዞች በቅደም ተከተል /በተራ/ እንጂ በምርጫ አይደለም የሚፈፀሙት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባሪያ እንደሌለ ይታወቃል። ስለዚህ 2ኛና 3ኛ ምርጫዎች ይቀራሉ ማለት ነው። 2ኛውን የሚችል ሰው ወደ 3ኛው መዝለል አይችልም፡፡
[ለ] ስለዚህ የሚችል ከሆነ ሁለት ወር በተከታታይ መፆም አለበት ማለት ነው፡፡ የጨረቃውን ወር አንድ ሲል ተከትሎ ከሆነ የሚፆመው ሁለቱም ወራት 29፣ 29 በድምሩ 58 ቀን ሆነው ቢያልቁም ሁለት ወር ሙሉ እንደፆመ ነው የሚቆጠረው፡፡ የጀመረው ከወሩ መጀመሪያ ካልሆነ ግን ስልሳውን ቀን መድፈን አለበት፡፡ ፆሙን ሆን ብሎ በመሀል ያቋረጠ ሰው እንደገና አንድ ብሎ መጀመር ግዴታው ነው፡፡ በመሀል የተቋረጠው በህመምና መሰል ከአቅም በላይ በሆነ ሰበብ ከሆነ ካቆመበት ይቀጥላል፡፡ መጠንቀቅ የሚችሉት አይነት ምክንያት ከሆነ ግን በዚህ ማቋረጥ አይቻልም፡፡ ያለበለዚያ እንደገና አንድ ማለት ግድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በመሀል ላይ ከማካካሻው ውጭ የሆነ ሌላ አይነት ፆም እንኳን ማስገባት አይቻልም፡፡ [አልሙግኒይ፡ 7/367]
[ሐ] ሁለት ወር በተከታታይ መፆም ያልቻለ ሰው የሚኖረው ምርጫ 60 ምስኪኖችን ማብላት ነው፡፡ እዚህ ላይ ማከታተል ግዴታ አይደለም፡፡ ባይሆን አንድን ምስኪን በመደጋገም ሳይሆን የተለያዩ ምስኪኖችን ሊሆን ይገባል የሚያበላው፡፡ የማስረጃው ቀጥተኛ መልእክት ይህን ስለሆነ የሚጠቁመው ራስን ከውዝግብ ማራቁ የተሻለ ነው፡፡ የሚያበላው ቤተሰቡን ከሚመግበው ምግብ መካከለኛ ከሚባለው ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
[መ] ሶስቱንም የማካካሻ አይነቶች መፈፀም ያልቻለ ሰው እስከሚችል ድረስ ይጠብቃል እንጂ ከማካካሻ ነፃ አይሆንም፡፡ [አልኢስቲዝካር፡ 10/105]
ወላሁ አዕለም፡፡
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 06/2010)
https://t.me/IbnuMunewor