እውነተኛ አኗኗር፣ ትርጉምና ዋጋ ያለው ሕይወት ለመኖር የትምህርት ደረጃ፣ ጥሩ ስራ፣ የተንጣለለ ቪላ ቤት፣ መልካም ስምና ዝና፣ ገንዘብ ወሳኝ አይደሉም፡፡ እውነተኛ አኗኗር (Authentic life) ከውስጥህ ጋር በመነጋገር፣ ከራስህ በመከራከር፣ ከልብህ ጋር በመመካከር፣ ከህሊናህ ጋር በመግባባት፤ ከአስተሳሰብህ ጋር በመሟገት፣ ከስሜትህ ጋር በመተናነቅ፤ ፍላጎትህንና ምኞትህን ፊትለፊት በመጋፈጥ፤ ውስጣዊውንና ውጫዊውን ዓለምህን በማዋሃድና አንተነትህን ከልብህ በሚፈልቀው ጥበብ በማደርጀት የምታገኘው ውጤት ነው፡፡
አንዳንድ ሰው ሀብት ኖሮት፣ መልካም ስም ተሸክሞ፣ የዲግሪ መዓት አግበስብሶ፤ የሃይማኖተኝነት ጭምብል አጥልቆ፣ በሕዝብ ስልጣን ላይ ተንፈላስሶ፤ በአካባቢው ተሰሚና የተከበረ ሰው ሆኖ እውነት ያለው ደስታ፤ ስራ ያለው እምነት፤ መልካም እርካታ ያለው ሕይወት ሲመራ አይታይም፡፡ እምነቱን ቢያንጠለጥልም ግብሩን ጥሎታል፤ ክበሩን ቢሸከምም በየጓዳው አነውሮታል፤ ስልጣኑ አላሰለጠነውም፡፡ ስጋው ቢደላውም መንፈሱ ተራቁቷል፤ ከዓለሙ ጋር የተስማማ ሕይወት ቢኖረውም ለውስጡ የሚሆን ህይወት አልያዘም፡፡ አካሉ ሊፋፋ ቢችልም ነፍሱ ኮስሷል፡፡ ውስጡን የዘነጋ ሕይወቱ የተወዛገበ ነውና!
ቅዱስ ቶማስ በወንጌሉ፡-
‹‹በእናንተ ውስጥ ያለውን ሃይል ብትጠሩት ያድናችኋል፡፡ ካልጠራችሁት ግን ያጠፋችኋል፡፡›› (If you call forth that which is in you, it will save you. If you do not call forth what is in you, it will destroy you)›› ይላል፡፡
እውነት ነው! በውስጣችን ያለው የተከማቸ ሃይል ሊያድነንም ሊያጠፋንም ጉልበት አለው፡፡ ውስጣችን ያለውን ሃይል ከዘነጋነው በፀፀት ሕይወት፣ እርካታና ደስታ በሌለው አኗኗር ይቀጣናል፡፡ ከውስጥህ ጋር ካልተስማማህ ከዓለሙ ጋር አትስማማም፡፡ ከራሱ ጋር የተጣላ ከሌላው ጋር ወዳጅ የሚሆነው በማስመሰል እንጂ በእውነት አይደለም፡፡ የውስጡን መክሊት ፈልጎ ያላገኘ፣ ፀጋውን ያልተጠቀመ በሕይወቱ የከሰረ ነው፡፡ ከራሱ ጋር የተፋታ የሌሎች አስተሳሰብ ባሪያ እንጂ የራሱን ሃሳብ ተከታይ አይሆንም።
ብዙ ሰው በተለያየ ሱስ ራሱን ደብቋል፡፡ ከራሱ ጋር ተኮራርፎ ደስታ ርቆታል፡፡ በመፅሐፍ ፍቅር ራሳቸውን የሰወሩ አንባብያን አሉ፡፡ ከሕይወት መከራው፣ ከፈተናው፣ ከማህበራዊው ውጣውረድ ተገልሎ መፅሐፉን ገዳም ያደረገ ቀላል ቁጥር የለውም፡፡ ማንበብ ራስን ለመሆን ካልረዳ ጥቅም የለውም፡፡ ራሱን መፅሐፍ ውስጥ የሸሸገ ከሚያነበው መፅሐፍ እየተጠቀመ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነቱ አንባቢ መፅሐፉን ሲከድን የሚሄድበት ይጠፋል፡፡ ለእሱ መፅሐፍ ማንበብ ሱስ እንጂ ሕይወት መለወጪያ፣ ሃሳብ መግዢያ፣ ራስን ማንበቢያ አይደለም፡፡ ማንበብ ነፃ ካላወጣ ከአጉል ሱስ ተለይቶ አይታይም፡፡ ሌላው በሙዚቃ ገዳም ውስጥ ገድሟል፡፡ ሙዚቃው ሲያልቅ ይቅበዘበዛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሱስ ከስካር፣ ከቁማር፣ ከሴሰኝነት፣ ወዘተ ሱስ የተለየ አይደለም፡፡ ያደፈጠ እንጂ ራሱን ሆኖ በነፃነት አደባባይ የወጣ በጣም ኢምንት ነው፡፡ እውነተኛ አኗኗር ህልም ሆኖበት በቅዠት ዓለም ውስጥ የሚተራመሰው እልፍ ነው፡፡ በጓደኝነት ስም ራሱን የረሳ በርክቷል፡፡ ከወዳጁ ሃሳብ የተለየ ሃሳብ እያለው በወዳጅነት ስም በማያምነውና በማይቀበለው አስተሳሰብ ሎሌ ሆኖ የሚኖር የትየለሌ ነው፡፡ ራሱን ሆኖ ሳይሆን ሌሎችን መስሎ በመኖር የሚሰቃይ ብዙ ሺ ነው፡፡
ቲስ ኤሎይት የተባለ እንግሊዛዊ ገጣሚ “Little Gidding” በተባለ ግጥሙ፡-
‹‹We shall not cease from exploration,
And the end of all our exploring
Will be to arrive where we started,
And know the place for the first time.›› ይላል፡፡
ሃሳቡም፡- ‹‹ራሳችንን ከመፈለግ ማቆም የለብንም፡፡ የፍለጋችን ማብቂያው ከየት እንደምንጀምር የምናውቅበት ነው›› የሚል ነው፡፡ ራሳችንን የመፈለግ መዳረሻ የሕይወት መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም ሲለን ነው፡፡
ወዳጄ ሆይ... አንተም ፍለጋህን ጀምር! የውስጥህን ሃይል ጥራ! ልቦናህን አጥራ! አንተነትህን አውጣ! የአንተን የሕይወት ጥያቄ ከአንተ የተሻለ ማንም የሚመልስልህ የለም፡፡ ሌላው ስለራሱ ልምድ፣ ውጣውረድና ስኬት ሊያወጋህ ይችላል፡፡ የምታነበው መፅሐፍ፣ የምታዳምጠው ሙዚቃ፣ የምታየው ተውኔት ወዘተ ጊዜያዊ ስሜትህን ያረካ ይሆን እንጂ ቋሚ ደስታን አይሰጡህም፡፡ እነዚህ ሁሉ ራስህን ለመፈለግና ውስጥህን የሕይወትህ መሰረት ለማድረግ ካልረዱህ ዋጋ የላቸውም፡፡ የአንተን የነፍስ ረሃብ፣ የመንፈስ ጥማት፣ ውስጣዊ ጉጉትህን፣ ዘላለማዊ ደስታህን፣ ዘመን የማያከስመውን ምኞትህን፣ ገፊ ስሜትህን ምን እንደሆነና እንዴት እንደምትቋቋመውና ራስህን ሆነህ እንዴት መኖር እንደምትችል ማንም ሊያስረዳህ አቅም የለውም፡፡ የራሱን ያልደረሰበት፣ ከራሱ ጋር ያልተግባባ፣ ውስጡን ያላገኘ በሚተራመስበት ዓለም ውስጥ ምን ተምሬአለሁ ቢል፣ ምን ሊቅ ጠቢብ ነኝ ቢል ስላንተ ሊያውቅልህ አይችልም፡፡ አንተነትህን ከዘልማድ አኗኗር አላቀህ፣ ህሊናህን ከትናንት እስራትህ ፈትተህ፣ ማንነትህን ከተጫነብህ የአስተሳሰብ ሸክም አሳርፈህ ትርጉምና ዋጋ ያለው እውነተኛ ሕይወት እንድትኖር የሚያደርግህ አንተና አንተ ብቻ ነህ፡፡ በሕይወትህ ያልመለስካቸውን ጥያቄዎች መልስ ልታገኝ የምትችለው የሌሎችን መልስ በመኮረጅ ሳይሆን የራስህን መልስ በመስራት ነው፡፡ መልሱን የምታገኘው በቁፋሮ ነው፡፡ ቁፋሮው ወደውስጥህ እንጂ ወደውጪ አይደለም! አርባ አራት ነጥብ!
ቸር ራስን ፍለጋ✔️