የነነዌ ሰዎችና እኛ
ከነነዌ ሰዎች በላይ ማን ክፉ ነበር? ከእነርሱ በላይ አላዋቂስ ማን ነበር? ("ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ" ተብለው ተጠርተዋልና፡፡) ነገር ግን እነዚህ አሕዛብ፣ እነዚህ አላዋቂ፣ እነዚህ አንድ ሰውስ እንኳን የጥበብን ነገር አስተምሮአቸው የማያውቁ፣ እነዚህ ከማንም ይኹን ከማን እንደዚህ ዓይነት ትእዛዝን ያልተቀበሉ ሰዎች ነቢዩ፡- “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” ሲል በሰሙት ጊዜ ክፉ ልማዳቸውን ኹሉ በሦስት ቀናት ውስጥ አስወግደዋል (ዮና.3፥4)፡፡
ዘማዊው ንጹህ፣ ደፋሩ ትሑት፣ ስስታሙና ጨቋኙ ራሱን የሚገዛና ደገኛ፣ ሐኬተኛውም ትጉህ ኾነ፡፡ እነዚህ ሰዎች በርግጥ ያሻሻሉት ክፋታቸውን ኹሉ እንጂ አንዱን ወይም ኹለቱን ወይም ሦስቱን ወይም አራቱን አይደለም፡፡ “እንዲህ የሚልስ የት አለ?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስለታለሁ፡- እነርሱን ሲወቅሳቸው የነበረውና፣ “የክፋታቸውም ጩኸት እስከ አርያም ድረስ ወጥቷል” ብሎ የተናገረው ነቢይ መልሶ ደግሞ የዚሁ ፍጹም ተቃራኒ የኾነን ምስክርነት አስቀምጧልና፤ እንዲህ ሲል፡- “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደ ተመለሱ ሥራቸውን አየ” (ዮና.1፡5፣ 3፡10)፡፡ ተመልከት! ከዝሙት ወይም ከአመንዝራነት ወይም ከሌብነት ራቁ አላለም፤ “ከክፉ መንገዳቸው” እንጂ፡፡ እንዴትስ ከዚያ ሊርቁ ቻሉ? ይህን እግዚአብሔር ያውቋል እንጂ ሰው ሊመረምረው አይችልም፡፡
እንግዲህ አሕዛብ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ክፋታቸውን ኹሉ ማስወገድ ከቻሉ፥ ለአያሌ ቀናት የተመከርንና የተዘከርን እኛ ግን አንዲት ክፉ ልማድን [ለምሳሌ መሐላን] ሳናስወግድ ስንቀር ልናፍር አይገባንምን? ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ቀድሞ ክፋታቸው ጣሪያ ደርሶ ነበር፤ “የክፋታቸውም ጩኸት እስከ አርያም ድረስ ወጥቷል” የሚለውን ስትሰማ ከክፋታቸው ብዛት በቀር ሌላ ምንም ልትገነዘብ አትችልምና፡፡ ነገር ግን በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ መልካም ምግባር ፍጽምና መድረስ ተችሏቸዋል፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባለበት ቀናት ወይም የጊዜ ብዛት አያስፈልግምና፡፡ በተቃራኒው ይህ ፍርሐት በሌለበት ደግሞ የጊዜ ብዛት ምንም ጥቅም የለውም፡፡
የዛጉ ብረቶችን በውኃ ብቻ የሚያጥባቸው ሰው ምንም ያህል ጊዜ እነርሱን በማጠብ ቢያሳልፍም እነዚያን ዝገቶች ኹሉ ማስለቀቅ አይቻለውም፡፡ ወደ እሳት ጨምሮ የሚያወጣቸው ሰው ግን አዲስ ከተሠሩ ብረቶችም ጭምር ሳይቀር እጅግ ጽሩያን ያደርጋቸዋል፡፡ በኃጢአት የዛገ ልብም እንዲሁ በትንሽ በትንሹና በግድየለሽነት ኾኖ ዕለት ዕለት ንስሐ ቢገባም ምንም ጥቅም አያገኝም፡፡ ራሱን ወደ እቶን - ይኸውም ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር የሚጥል ከኾነ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኹሉንም ማስወገድ ይቻለዋል፡፡
(በእንተ ምክንያተ ሐውልታት፥ ፳:፳፩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው)