🔹አጥፊዎችን በስም ጠቅሶ ማስጠንቀቅ፣ ከሰለፎች ፈለግ!
(መረጃ ለሚያከብሩ ብቻ!)
~
ዛሬ ዛሬ ስለ ቢድዐ ማውራት፣ የቢድዐ አራማጆች ሰዎችን እንዳያሳስቱ ማስጠንቀቅ እንደ አፍራሽ ተግባር እየተቆጠረ ነው፣ ከጠላት ጋር እንደማሴር። ይሄ አካሄድ ስሜታዊ ሽፋን ስለተሰጠው እንጂ ውድቅነቱ ለማንም አይሰወርም። እነዚህ "የሰው ስም አታንሱ" የሚሉ አካላት ራሳቸው የሚጠሉትን ሰው ትልቅ ዓሊም እንኳ ቢሆን ስሙን ጠርተው ከማብጠልጠል የማይመለሱ ናቸው። እነዚህ አካሄዳቸው እርስ በርሱ የሚጣረስ የሆኑ ሰዎችን ወደ ጎን እንተውና ጥንት በጉዳዩ ላይ የሰለፎች ፈልግ ምን ይመስል እንደነበር እንመልከት። ቀጥሎ የተዘረዘሩት በሙሉ ከሞቱ ከአንድ ሺህ አመት በላይ ያለፋቸው ቀደምት የኢስላም ሊቃውንት ናቸው።
1. ዐብዱላህ ብኑ ሙባረክ
በአንድ ወቅት “ሙዐላ ብኑ ሂላል ጥሩ ሰው ነበር በሐዲሥ ላይ ይዋሻል እንጂ” ይላሉ። በዚህን ጊዜ የሆነ ሱፊይ ሰማቸውና “የዐብዱረሕማን አባት ሆይ! እንዴት ሰው ታማለህ?” አላቸው። ኢብኑ ሙባረክ ታዲያ፡ “ዝም በል! ግልፅ ካላደረግን ሐቅና ባጢል እንዴት ይልለያል?!” አሉት። [አልኪፋያህ፡ 9]
2. ኢብራሂም አነኸዒይ
“ለቢድዐ ሰው ሃሜት የለውም!” ብለዋል። [አልኢባናህ፡ 2/449]
3. ሰዒድ ብኑ ጁበይር
“ጦልቅ ጋር አትቀመጡ” ብለዋል። የኢርጃእ ቢድዐ አራማጅ ስለሆነ ነው ይህን ያሉት። [አልኢባናህ፡ 2/450]
4. ሐሰን አልበስሪይ
“ለቢድዐ ሰው ሃሜት የለውም! አመፁን ባደባባይ ለሚያወጣ አመፀኛም ሃሜት የለም” ብለዋል። [ሸርሑ ኡሱሊ ሱናህ፣ ላለካኢ፡ 1/158]
5. አቡ ኢድሪስ አልኸውላኒይ
“አዋጅ! አቡ ጀሚላ በቀደር አያምንም። እንዳትቀማመጡት!” ብለዋል። [አልኢባናህ፡ 2/449]
6. ቀታዳህ
ዓሲም አልአሕወል እንዲህ ይላሉ፡- “ቀታዳ ዘንድ ተቀምጬ ነበር። ዐምር ብኑ ዑበይድ ስሙ ሲወሳ በክፉ አነሳው። 'ዑለማዎች ከፊሉ በከፊሉ ላይ እንደሚናገር አላውቅም ነበር' ስለው 'አሕወል ሆይ! አንድ ሰው ቢድዐ ሲያንፀባርቅ ሰዎች ይጠነቀቁት ዘንድ ስሙ ሊጠቀስ እንደሚገባ አታውቅም'ንዴ?' አለኝ።” [አልሚዛን፡ 5/330]
7. የሕያ ብኑ ሰዒድ አልቀጧን
እንዲህ ይላሉ፡- “ሱፍያኑ ሠውሪይን፣ ሹዕባን፣ ማሊክ ብኑ አነስን፣ ሱፍያን ብኑ ዑየይናን 'የሆነ (ተሻጋሪ) ጥፋት ወይም የዘገባ ድክመት ስላለበት ሰው ሁኔታ ዝም ልበል ወይስ ግልፅ ላድርግ?' ብየ ስጠይቃቸው 'ግልፅ አድርግ' አሉኝ።” [ሸርሑ ዒለሊ ቲርሚዚይ፡ 1/49]
8 - 9. አርጣህ ብኑ ሙንዚር እና አውዛዒይ
ዑቅባህ ብኑ ዐልቀማህ እንዲህ ይላሉ፡-
“በአንድ ወቅት ከአርጣህ ብኑ ሙንዚር ጋር ነበርኩኝ። በቦታው ከነበሩ ሰዎች አንዱ ‘ከአህሉ ሱና ጋር እየተቀመጠ፣ እየተቀላቀላቸው ስለ ቢድዐ ሰዎች ሲወራ ግን ‘ተውን እንግዲህ ስማቸውን አታንሱ’ ስለሚል ሰው ምን ትላላችሁ’ ሲል ጠየቀ። የዚህን ጊዜ አርጣህ ‘እሱ እራሱ ከነሱ ነው። እንዳያታልላችሁ!’ አለ። ይሄ የአርጣህ ንግግር አልተመቸኝምና ወደ አውዛዒይ ሄድኩኝ። አውዛዒይ እንዲህ አይነት ነገሮች ሲደርሱት ገላጭ ነበር። ጠየቅኩት። ‘አርጣህ እውነት ተናግሯል። ሐቁ እሱ ያለው ነው። ይሄ ሰውየ ስማቸው እንዳይነሳ ይከለክላል። ስማቸው ካልተገለፀ እንዴት ሰዎች ይጠነቀቋቸዋል?!’ አለ።” [ታሪኹ ዲመሽቅ፡ 8/15]
10 - 12. ሐማድ፣ ማሊክ እና ሸሪክ
አቡ ሰለማ አልኹዛኢይ እንዲህ ይላሉ፡- “ሐማድ ብኑ ሰለማን፣ ማሊክ ብኑ አነስን፣ ሸሪክ ብኑ ዐብዲላህን ቢድዐ ስለሚፈጥር ሰው 'ነገሩ ግልፅ ይደረጋል' ሲሉ ሰምቻለሁ።” [ሸርሑ ዒለሊ ቲርሚዚ፡ 1/49]
13. ኢማሙ አሕመድ
“ለቢድዐ ሰው ሃሜት የለውም!” ብለዋል። [ጦበቃቱል ሐናቢላ፡ 2/274]
ሙሐመድ ብኑ በንዳር፡ “በውኑ እኔ እከሌ እንዲህ ነው፣ እከሌ እንዲህ ነው ማለት ይከብደኛል” ቢሉ አሕመድ እንዲህ ሲሉ መለሱ፡- “አንተም ዝም ካልክ እኔም ዝም ካልኩ መሀይም የሆነ ሰው ጤነኛውን ከበሽተኛው እንዴት ይለየው?!” [አልፈታዋ፡ 28/231]
አሁንም ኢማሙ አሕመድ “ትርፍ ፆም ከሚፆም፣ ትርፍ ሶላት ከሚሰግድ፣ ኢዕቲካፍ ከሚያደርግ ሰውና ስለ ሙብተዲዖች ከሚያወራ ሰው የትኛው ነው አንተ ዘንድ ይበልጥ የተወደደው?” ተብለው ቢጠየቁ “ቢሰግድ፣ ቢፆም እንዲሁም ኢዕቲካፍ ቢያደርግ ለራሱ ነው። ስለ ሙብተዲዖች ሲያወራ ግን ጥቅሙ ለሙስሊሞች ነውና ይሄኛው ይበልጣል” ብለዋል። [አልፈታዋ፡ 28/231]
እስካሁን የተዘረዘሩት ሰዒድ ኢብኑ ጁበይር፣ አቡ ኢድሪስ አልኸውላኒይ፣ ሐሰን አልበስሪይ፣ ኢብራሂም አነኸዒይ፣ ኢብኑል ሙባረክ፣ ኢማሙ ማሊክ፣ ሸሪክ ብኑ ዐብዲላህ፣ አውዛዒይ፣ ዐርጧህ ብኑ ሙንዚር፣ ሐማድ ብኑ ሰለማ፣ ሸሪክ ብኑ ዐብዲላህ፣ ሱፍያኑ ሠውሪይ፣ ሹዕባ፣ ሱፍያን ብኑ ዑየይና፣ ቀታዳ እና ኢማሙ አሕመድ ናቸው። በእርግጠኝነት ከዚህ በላይ ብዙ መዘርዘር ይቻላል። ይህንን የምጠቅሰው ዲን ከሚንዱ አጥፊዎች ማስጠንቀቅ ከጥንት ዑለማዎች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ሐቅ እንጂ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ጉዳይ እንዳልሆነ ለመጠቆም ነው።
እንዲያውም ከነዚህ ሁሉ ፈለጎች በላይ ከነብዩ ﷺ ሱናዎች በቂ መረጃ አለ። ለምሳሌ ያክል ፋጢማህ ቢንት ቀይስ - ረዲየላሁ ዐንሃ - ሙዓዊያህ ብኑ አቢ ሱፍያንና አቡ ጀህም ለትዳር እንደጠየቋት ለነብዩ ﷺ ብታማክራቸው፡
“አቡ ጀህም ዱላውን ከትከሻው አያወርድም። ሙዓዊያም ድሃ ነው፣ ገንዘብ የለውም። ይልቅ ኡሳማህ ብኑ ዘይድን አግቢ” ብለው ነው የመለሱላት። ዘገባው ላይ ጣትህን እንዳትቀስር ሙስሊም ናቸው የዘገቡት። [ሙስሊም: 3770]
ልብ በሉ! ሰዎቹን በሌሉበት ነው ስማቸውን ያወሱት። በአንዲት ሴት የትዳር ጉዳይ አስፈላጊ ሲሆን የሰዎችን ስም ማንሳት ከተቻለ፣ ዲንን የሚያጠለሹ፣ ወደ ቢድዐ የሚጣሩ ሰዎችን ስም ጠቅሶ ማስጠንቀቅ ደግሞ የበለጠ ተገቢ ነው።
ከግለሰቦች በላይ ለእምነታችን ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። እርግጥ ነው፡
* ፍትህ በጎደለው መልኩ በግል ጥላቻ ተነሳስተን በደለኛ ንግግር ልንናገር አይገባም።
* በትንሽ በትልቁ አደብ የቀለለው ትችት ውስጥ ከመግባትም ልንቆጠብ ይገባል።
* የሚታለፉና የማይታለፉ ርእሶችንም መለየት አለብን።
* ከዲን በመከላከል ሽፋን ተሻጋሪ ያልሆኑ የግለሰቦችን ነውሮች መዘክዘክም ነውረኝነት ነው።
እነዚህን ነገሮች ከጠበቁ በኋላ ዲን የሚበክሉ፣ ደካሞችን የሚያሳስቱ ሰባኪዎችን አትንኩ ማለት ግን የእውነት ዲናችንንም፣ ወገኖቻችንንም የሚጎዳ ነው። ሙብ ^ ተዲዖች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ስማቸውን እያነሱ ጭምር መልስና ማስጠንቀቂያ ባይሰጥባቸው ኖሮ ዲኑ የማንም መጫወቻ በሆነ፣ ህዝብም ገደል በገባ ነበር።
ደግሞም አስተውሉ! ከነዚህ የሰው ስም አታንሱ ከሚሉ ሰዎች ውስጥ የሰው ስም የማያነሳ አለ?! በጭራሽ! “ስም አታንሱ” የሚሉት ራሳቸው በቢድዐ ቁንጮዎች ላይ የሚሰጠውን ሂስ ዝም ለማሰኘት እንጂ አነሰም በዛ ራሳቸውም የሰው ስም ከማንሳት የሚቆጠቡ አይደሉም።
ማሳሰቢያ፦
ያወራሁት ስለ አጠቃላይ መርሁ ነው። እንጂ “ጉዳዩ ጤነኛ ባልሆነ መልኩ የሚያዝበት ሁኔታ አልበዛም ወይ?” ከተባለ “እንዴታ!” ነው መልሱ። በርግጠኝነት ውጥንቅጡ የወጣ፣ ከልክ ያለፈ፣ መረን የለቀቀ፣ ባላሰበው አቅጣጫ በሱና ስም ሱናን የሚዋጋ ብዙ ሰው አለ። እንዲህ አይነቱን አካል ሚዛን እንዲጠብቅ መታገል እንጂ የትኛውም አጥፊ ስሙ እንዳይነሳ ብሎ በር ለመከርቸም መሞከር አይሳካም እንጂ ቢሳካ ጉዳቱ ከባድ ነው የሚሆነው።
(ኢብኑ ሙነወር፣ የካቲት ዐ4/2009)
https://t.me/dawudyassin