ትክክለኛ ደዕዋ ወደ ላ ኢላሃ ኢለላህ መጣራት ነው
“ትክክለኛ ደዕዋ ማለት ሰዎችን ወደ አላህ ብቻ መጣራት፣ የተውሒድን እውነት ማብራራት እና “ላ ኢላሃ ኢለላህ” የሚለውን ቃል በትክክለኛ ትርጉሙና በሚገባው መልኩ ለሰዎች ማስተማር ነው። ደዕዋ ዓላማው ሰዎችን ወደ ፈጣሪያቸው ማቅረብ እንጂ የራስን ስም ማሳደግ ወይም ሌሎችን ማዋረድ አይደለም።
ነገር ግን ዛሬ ነገሩ መልኩን ቀይሮ የምናየው ነገር አለ። ወደ ላ ኢላሃ ኢለላህ የሚጣሩ፣ ተውሒድን የሚያስተምሩ ወንድሞችን ማጥላላት፣ ማዋረድ፣ ስማቸውን ማጥፋትና ሰዎችን ከእነሱ ማራቅ እንደ ደዕዋ ወይም እንደ መንሀጅ የሚታይበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ይህም ደዕዋ ወደ ምን እንደተለወጠ በጥልቀት እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
ወንድማችን ላ ኢላሃ ኢለላህን እየጣራ ከሆነ፣ የተውሒድን አስፈላጊነት እያስተማረ ከሆነ፣ የሽርክን አደገኛነት እያስጠነቀቀ ከሆነ፣ ልዩነት ቢኖረን እንኳን በማስረጃና በፍትሕ መወያየት ነው የሚገባው፤ ማጥላላትና ማዋረድ ግን የደዕዋ ዓላማ ሊሆን አይገባም።
የደዕዋ ሰው ራሱንም ጭምር መፈተሽ አለበት። “ሰዎችን ወደ አላህ እየጣራሁ ነው? ወይስ ሰዎችን ወደ ራሴና ወደ ቡድኔ እየጣራሁ ነው?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። እውነተኛ ደዕዋ ሰውን ወደ አላህ ታስጠጋለች፤ ልብን በእውቀት፣ በተውሒድ፣ በኢኽላስ ታሳድጋለች።
ስለዚህ ዛሬ የሚያስፈልገን የሌላውን ስም ማውረድ ሳይሆን ወደ አላህ መመለስ፣ የተውሒድን እውቀት ማስፋፋት፣ በቁርኣንና በሱንና ላይ በማስረጃ መናገር እና በመካከላችን ፍትሕንና መልካም ምክርን ማስፈን ነው።
ደዕዋ ወደ አላህ እንጂ ወደ ሰው አይደለም፤ የደዕዋ መለኪያም ሰዎችን ማዋረድ ሳይሆን ሰዎችን ወደ ተውሒድና ወደ አላህ ታዛዥነት መጣራት ነው።
ᏃᗩᏦᏆᖇ’Official Channel”