#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)
ብዙ ነገር አጥቼ እንደነበር የተሰማኝ አሁን ላይ ነው። የእማዬን አልጋ ከበን ቡና ተፈልቶ ቆሎ እየቆረጠምን አንዱን ወሬ ስናነሳ አንዱን ስንጥል በብዙ ሳቅ እና ደግሞ በደስታ ለቅሶ የታጀበ ቀን እየዋልን ያለፉ አመታቴን አስቤ ብዙ እንደጎደለኝ ገባኝ።
ደግሞ በዚህ ሁሉ የቤተሰብ ፍቅር ታቅፌ ልቤ ክንፍ አውጥታ ጎንጥ ጋር ስትሄድ፣ የያዘኝን አያያዝ ፣ የሳመኝን መሳም ፣ የጠራኝን መጥራት አሰብ አድርጌ ብቻዬን ፈገግ ስል ባለፉት ዓመታቶቼ ብዙ እንዳለፈኝ ገባኝ። ብዙ እንዳልኖርኩ ገባኝ!!
«እትዬ ዛሬ ሌላ ሰው ሆነው በንፁህ ልብ ስለተቀበሉት ነው የሚያጎብጥ ሸክም የሆነብዎት። ቂም ባቄመና በጠለሸ ልብ ሆነው ሲቀበሉት እንዲህ አልተሰማዎት ይሆናል።» ነበር ያለው ጎንጥ እንዴት ይሄን ሁሉ ጥላቻ ተሸክሜ ኖርኩ ስለው?
በንፁህ ልብ አይደለም። በፍቅር ልብ ሳየው ነው ዓለምን እና ዙሪያዬን የማይበት መነፅር የተቀየረው። በፍቅር ዓይን!! ሁሉ እንዳለኝ የተሰማኝ፣ መኖር ደስ የሚል ነገር መሆኑን ማሰብ የጀመርኩት በፍቅር ልቤ ማየት ስጀምር ነው።
እናቴን አቀፍኳት፣ ኪዳንዬ አለኝ፣ አጎቴን አለኝ፣ ጎንጥ ይኑረኝ አይኑረኝ ባላውቅም አዎ በልቤ ውስጥ ግን ከነጥጋቡ አለኝ!! ምን እጠይቃለሁ ሌላ? አጎቴ እናታችን ስለደከመች ካጠገቧ ባንርቅ መልካም መሆኑን ስለነገረን በአካሌ ላለመሄድ ወሰንኩ። ግን ልትሞት ቀናት የቀራት እናቴን አቅፌ ልቤ አዲስአበባ መሸምጠጡ ራስወዳድነት ነው? እንደዛ እየተሰማኝኮ ራሴን እገስፃለሁ። ልቤ አልሰማኝ አለኝ እንጂ!!
የገባን ቀን ማታ ምናልባት ለጥንቃቄ በሚል። በኪዳን ስልክ ዋትሳፕ መልዕክት ላኩለት። ሁለት መስመር ለመፃፍ ከ20 ደቂቃ በላይ ፈጀብኝ። ለኪዳን ካልሆነ በቀር ፅፌ የማውቀው ማስፈራሪያ ወይ ቢዝነስ ነክ ነገር አልያም የሆነ መልእክት እንጂ ፍቅር ነክ ነገር እንዴት እንደሚፃፍ አላውቅም። ምን ተብሎ ነው የሚጀመረውስ? ሀይ ጎንጥ? ስሙ ደግሞ ሲጠራ ምንም የፍቅር ቅላፄ የለውም!! እንዴት ዋልክ ዓለሜ? ልበለው? አይሆንም እሱ ሲል ነው እንደሱ የሚያምርበት! ሀኒ ልበለው? ሆ ጎንጥን ሀኒ? ራሴኑ አሳቀኝ!! ያቺ የድሮ ሚስቱ እንደጠራችው ጎኔ ልበለው? ኡፍፍፍ
«ሰላም ዋልክ? እኔ ነኝ!! በጠዋት ላይህ ሳልችል ቀርቼ እማዬጋ መጥቻለሁ!! ደህና አድረህ ዋልክ?» በቃ መፃፍ የቻልኩት ይሄን ብቻ ነው። ምን አይነቷ ነፈዝ ነኝ በፈጣሪ!! ከዛማ ስልኩን አቅፌ የፃፍኩለት መልዕክት ሰማያዊ የራይት ምልክት እስኪያሳየኝ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።
«ዓለሜ ናፈቀሽ እንዴ?» ይለኛል ኪዳን ሲያበሽቀኝ
«ለምን ግን አታርፍም?» እላለሁ
«ጎንጤን ነው?» ይላል አጎቴ
«እንዴ? እኔ ብቻ ነኝ የማላውቀው ማለት ነው? አንደኛውን ሽማግሌ ልኳል አትይኝም እንዴ?»
«እዚህ ከርሞ አይደል እንዴ የሄደው? ዓይነውሃው ያስታውቃልኮ ፍቅር እንዳለበት! መች አይኑን ከርሷ ላይ አንስቶ! ብለው ይለኛል። ብለው ይለኛል። ኋላማ እለዋለሁ ቆጣ ብሎ አለኛ» እናቴን ጨምሮ ሁሉም ይስቃሉ። እንደኮረዳ እሽኮረመማለሁ።
ስልኩ መልዕክት መቀበሉን የሚገልፅ ድምፅ ሲያሰማ ከመቀመጫዬ እንደመዝለል ሁሉ ሲያደርገኝ ቡና የምታፈላው ትንሽዬ ዘመዳችን ሳትቀር በአንድ ላይ አውካኩብኝ። የትልቅ ሰው ያልሆነ ማፈር አፍሬ መልዕክቱን ለማየት ሁሉ ስግደረደር ቆየሁ።
ነው የሚለው መልዕክቱ! አሁን ይሄ እሺ ምኑ ነው የሚያስቦርቀው? በፍቅርሽ ሞቻለሁ የተባለች ኮረዳ እንኳን እኔ የምሆነውን መሆን አትሆንምኮ! ትቻቸው ወደበር ወጣሁ እና ደወልኩለት። ቶሎ አውርተሽ መጨረስ አለብሽ የተባልኩ ይመስል የተፈጠረውን ለምን ሳላየው እንደመጣሁ እማዬ ስለደከመች ወደከተማ እንደማልመለስ በጥድፊያ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ አውርቼ ሳበቃ ሳቅ ብሎ
«ለመዝጋት ተቻኮልሽ እንዴ?» አለኝ
«አይ!» እያልኩ በቆምኩበት በጫማዬ መሬቱን እየቆፈርኩ መሆኑን አየሁ
«ደግ! ያሻሽን ያህል ጊዜ ቆይ!! » አለኝ
«አንተስ?»
«እኔ ምን እሆናለሁ?» አለኝ እኔ ማወቅ የፈለግኩት ከዛስ የሚለውን….. እኔ ያሻኝን ያህል ጊዜ እዚህ ስቆይ እሱስ? ከሆስፒታል ሲወጣ ቤት ሄዶ ይጠብቀኛል? ወይስ ያለሁበት ይመጣልኛል? ወይስ እኔ ወደማላውቀው ቤቱ ይሄድብኛል?
ያናደደኝን ወይ የተጣላኝን ሰው በጉልበት እንዴት እንደማግተው አውቅ ነበርኮ! የወደድኩትን ሰው እንዴት አባቴ አድርጌ ነው የራሴ የማደርገው? እሱን አልችልበትም!! በጉልበት ባገቱት ሰው ላይ ሙሉ ስልጣን ማራመድ ይቻላል። በፍቅር የወደቁለትን ሰው ራሱ ፈቅዶ ወደእኔ ካልቀረበ ምንድነው የማደርገው? ዝም አልኩ!!
«ዝም አልሽኝ እኮ ዓለሜ?» አለኝ ጠብቆ
«ምን እንደምል አላውቅበትም!! ያለፍከውን አላውቅም! ወደፊት ምን እንደምታስብ አላውቅም! ነገ ምን እንደምንሆን አላውቅም! አሁንም ምን እንደሆንን አላውቅም!! አላውቅህምኮ ጭራሽ! እኔ ግን እዚህ ልትሞት ያለች እናቴን አቅፌ ካንተ ሌላ ሀሳብ የለኝም!! ይሄ እንዴት ያለ መሸነፍ ነው ቆይ?» አልኩት።
«የት እሄድብሻለሁ? አለሁ አደል? ሁሉን ትደርሽበት የለ? አንች ብቻ የተሸነፍሽ አታድርጊው እንጅ!!» ብሎ ግማሽ መልስ ምን ግማሽ እሩብ መልስ ይመልስልኛል።
«እንዲህ እንድትለኝ አይደለም የምፈልገው!» ስለው እየሳቀ
«እንዴት እንድልሽ ነው የምትፈልጊ? ቁጣው የምንድነው ታዲያ?» ሲለኝ ነው እየተቆጣሁ እንደሆነ ያስተዋልኩት
«እንደምትወደኝ ነው ማወቅ የምፈልገው!! እንዳልነሳ ሆኜ በፍቅርህ ከመውደቄ በፊት እየተሰማኝ ያለው ስሜት የእኔ ብቻ እንዳልሆነ ነው ማወቅ የምፈልገው! አይሆኑ አሸናነፍ ከመሸነፌ በፊት እንደማላጣህ እርግጠኛ መሆን ነው የምፈልገው? እ?» ስለው መሳቁን ሳያቆም
«ፍቅርሽም ቁጣ ነው? እንደምወድሽማ ታውቂያለሽ! መስማቱን ከሆነ የፈለግሽ እወድሻለሁኮ ዓለሜ!! ነገ ምን እንደሚሆን ከፈጣሪ ጋር እናበጀዋለን!! ዛሬን ልውደድሽ ዓለሜ ዛሬን ውደጂኝ!!»
እንኳን ፊት ሰጥቶኝ ዘጭ ለማለት እየተንደረደረ የነበረ ልቤ ዝርፍጥ ብሎ በፍቅር ነሆለለ። ከዛን ቀን በኋላ በየቀኑ ተደዋወልን!! በየቀኑ እንደሚወደኝ ነገረኝ። በየቀኑ ደጋግሜ ተሸነፍኩ። በየቀኑ ከእማዬጋ ሳቅን። በየቀኑ ድሮ ያጣነውን እቅፏን ናፍቆት መሬት ላይ አንጥፈን ለሶስት እቅፏ ውስጥ አደርን። በየቀኑ ደስ አላት!! በአስራ ሶስተኛው ቀን ጠዋት እኔና ኪዳን በቀኝና በግራዋ ሙቀቷን እየሞቅን እማዬ ዝም አለች።
እማዬን ስላጣኋት ከፋኝ። አግኝቻት ስለሞተች ደግሞ አመሰገንኩ። ኪዳንም ተመሳሳይ ስሜት ነበር የተሰማው ግን ከእኔ በላይ የእርሱ ሃዘን በረታ!! ምናልባት እኔ ለእርሱ ለመሆን ስታትር ዘመኔን ስለኖርኩ አጎደልኩበት ብዬ እንዳላስብ ዝም ብሎኝ እንጂ ሁሌም የእናቱ ናፍቆት ያንገበግበው ነበር ይሆናል። በኖረችልኝ ብሎ ሲመኝ ይሆናል የኖረው። እኔና አጎቴ ከእርሱ በርትተን እሱን ማበርታት ጀመርን።
የቀብሯ ቀን ሬሳዋ ከቤት ሲወጣ አይኖቼን ደጋግሜ አሸሁ ያየሁትን ሰው ለማጣራት። አቶ አያልነህ! ፈገግ አልኩ! ይቅር ብለውኛል ማለት ነው።