ልብወለዶች፣ መፅሀፎች


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል።
የተለያዩ መፅሀፎችን፣
ትረካ በድምፅ፣

በፅሁፍ እናቀርባለን።።
ከናንተ ሚጠበቀው ከኛ ጋር መሆን ብቻ ነው😍😍
ለማንኛውም አስተያየት @kiyuly አለሁላቹ።
መልካም ጊዜ

Related channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter


ይህ አይገባትም ሀገር ለሰራችው ሀገር ላቆመችው
ድምጿን ስትቀንስ ዝም ያለች መስሏችሁ
የነኳት አልፈዋል እሷ ግን ፀንታለች
ይሄንንም አልፋ ገና ትኖራለች❤️


ትሞታለህ አለኝ ሞት እምፈራ መስሎት .

አርድሃለው አለኝ የምርድም መስሎት

የናቀው አባቴን የጠላው እምነቴን

የተከፋው እኔ ያነባች እናቴ

ማእተቤን ይዞ ስለሞት ያወራል

ጐልያድ ነኝ ብሎ ሲፎክር ይውላል


«ከዚያስ!»

«ከዚያማ ምን የማታውቂው ቀረ?»

«ይቀራል እንጂ! መች ነው የወደድከኝ? የተመታሁ ቀንኮ ግን ትተኸኝ ልትሄድ ነበር ለነሱ ትተኸኝ!»

«መች እንደወደድኩሽ ምኑን አውቄው? ስገቢ ስትወጭ ስትገለምጭ ስትሰድቢኝ!! አንዳንዴ ነገረ ስራሽ አፍሽ እንጅ የከፋ ልብሽ ደግ መሆኑን ሲነግረኝ አላውቅም!! እነርሱ የሚፈልጉትን መረጃ ሁላ አግኝቼ ለእነርሱ አሳልፌ ልሰጥሽ አቃተኝ!! ጥላሽን የማታምኝ ሴት እኔን ግን ከነጭርሱ አለመጠርጠርሽ አሳዘነኝ!! እንጃ ካስታወሽ የሆነ ቀን ለሊት ገብተሽ በር ስከፍትልሽ አልሽኝ።»
ብሎ ፈገግ አለ። አስታወስኩት።

ትንሽም ቢሆን ደስታዬ የነበረው ከእሙጋ በማሳልፈው ጊዜ የነበረ ጊዜ እሷ የማያገባት ነገር የመቆስቆስ ሱሷ አላስቀምጥ ብሏት ለአምስተኛ ጊዜ የታሰረች ቀን ነው። (እኔ እስር ቤት ለ6 ዓመት እያለሁ እሷ ሁለቴ ገብታ ወጥታለች። ስትገባ አብረን ጊቢውን እናምሳለን። ከጋዜጠኝነቷ ባሻግር ታቱ መስራት በልምድ ተምራለች። እስር ቤት ውስጥ እንኳን ዘመናዊ ንቅሳት ልትነቀስ ፀጉሯን ከሁለት ጉንጉን የዘለለ የማትሰራ የገጠር ልጅ ሁላ ሳትቀር በጋዜጠኛ ምላሷ አዋክባ አሳምና ትነቅሳታለች። የጀርባዬን እና የቂጤን ንቅሳት ግማሹን መጀመሪያ የገባች ጊዜ የተቀረውን ቀለም ያልደረሰው ቦታ እየፈለገች ሁለተኛ ስትመለስ የነቀሰችኝ እሷ ናት።) የዛን ቀን መታሰሯን ሰምቼ የበረደው ልቤን ይዤ ስባዝን አምሽቼ ስገባ ጎንጥ ከእንቅልፉ ነቅቶ በር ከፈተልኝ። በረንዳው ጠርዝ ላይ ተቀምጬ እያየሁት በህይወቱ ምንም ግድ የሚሰጠው አይመስልም ነበር።

«አንተ ግን ደስተኛ ነህ?» አልኩት በመገረም እያየሁት! እንደገመትኩትም ቁልል ብሎ

«ፈጣሪ ይመስገን!!» አለኝ

«ምን ማለት ነው ፈጣሪ ይመስገን? መልስኮ አልሰጠኸኝም!! ነህ አይደለህም? ነው ጥያቄው ! ነኝ ወይም አይደለሁም! ነው መልሱ»

«ምን ለየው!! ፈጣሪ ይመስገን ማለቴ ደስተኛ በመሆኔም አይደል?» ብሎ አሁንም መልስ ያልሆነ መልስ ይመልስልኛል።

«አንተ ግን መቼ ነው ቀጥተኛ ወሬ የምታወራው? ምናለ አሁን ነኝ ወይ አይደለሁም ብትል!! ምንህ ይቀነሳል?»

«እሽ ካሻዎት! አዎን ደስተኛ ነኝ!! ምነው? እርሶ ደስተኛ አይደሉም እንዴ?» አለኝ መልሴ የጨነቀው አይመስልም። እኔ ግን ውስጤ መከፋቴ ሞልቶ ስለነበር መተንፈስ ለማልፈልገው ሰው ገነፈለብኝ።

«ደስታ ምን እንደሚመስል ስለማላውቅ ደስ ቢለኝም ማወቄን እንጃ!! አላውቅም!! ደስታ ማለት መሳቅ ከሆነ ስቄኮ አውቃለሁ። በህይወት ውስጥ ምን ያህሉን ፐርሰንት ደስተኛ ስትሆን ነው ደስተኛ ነኝ የሚባለው? እኔእንጃ! አላውቅም ደስተኛ ሆኜ ማወቄን! ሰው የሚፈልገው ሁሉ ኖሮት እንዴት ደስታ አይኖረውም አይደል?» አልኩት እና ጎንጥ መሆኑን ሳስብ ትቼው ገባሁ!!

«የዚህን ቀን አንጀቴን አላወስሽው!!» አለኝ አሁን ሳቅ ብሎ! «ከዛ ወዲህ ያለውን አላውቅም በጣም ብዙውን ቀን ታናድጅኛለሽ ለራሴ በቃ እተዋለሁ ይህን ስራ እላለሁ መልሼ ግን ያቅተኛል። የልጄ እናት በደንብ ስለምታውቀኝ ጠረጠረች። እየለገመ ነው እንጂ ይህን ያህል ጊዜ ምንም ፍንጭ ሳያገኝ ቀርቶ አይደለም ብላ ሰው ልትቀይር ነበር። ከዛ በላይ ምክንያት ደርድሬ ብቆይም አንች ፍቅሬን የምታይበት ልብ አልነበረሽም እና ደጅሽ መክረሜ ትርጉም አጣብኝ ለዛ ነው ልሄድ የነበር!! እንደው ጥሎብሽ ስታይኝ ትበሰጫለሽኮ!! ምን በድዬ ነው ግን እንዲያ የምትጠይኝ?»

«ኸረ አልጠላህም!! አላውቅም!! እሙ ስለምትወጂው ነው እንደዛ የምትሆኝው ነው ያለችኝ!» ስለው አይኑን አፍጥጦ ሲያየኝ አብራራሁ «ከፀብ ውጪ የምታውቂው ፍቅር ስለሌለ ፍቅርሽን የምትገልጪበት መንገድ ነው የምትናደጂውና የምትቆጭው አለችኝ! እሷ ናት ያለችኝ!» አልኩኝ!! ሳቅ ብሎ ዝም ተባብለን እንደቆየን እህሉ ሳንነካው መቀዝቀዙን አየን!! ሁለታችንም የመብላት ፍላጎት አልነበረንም!! እኔ የምበላው መዓት ነገር አቀብሎኝ እንዴት ነው እህል የማስብ የነበረው። ልክ እንደቅድሙ አጠገቤ መጥቶ ተቀመጠ እና አገጬን ከፍ አድርጎ አይኖቼን እያየኝ።

«መድሃንያለም ምስክሬ ነው! የደበቅኩሽ የለኝም!! ከፍቅርሽ ውጪ አንቺጋ ያኖረኝ ምንም ሰበብ የለም!! አሁን ሁሉን አውቀሻል!! አልሻህም እሄዳለሁ ካልሽኝም በግዴ የእኔ አላደርግሽም!! ብትተይኝም ከአፌ የሚወጣ ሚስጥር የለም!! በልጄ እምልልሻለሁ!! እ? ዓለሜ? ፍቅሬ ከጥላቻሽ ከበለጠ ንገሪኝ!! እሽ በይኝና የኔ ሁኝ በደልሽን በፍቅር እንድትረሽ አደርግሻለሁ!!» ሲለኝ ለተወሰነ ደቂቃ የእነሱ ወገን እንደሆነ ረስቼው እንደነበር አስታወስኩ። አባቴ ከወንድሙ ገዳዮች አንዱ ወይም አዛዡ እንደነበር አውቆ እንዴት ቻለበት ማፍቀሩን!

«ስትጠፋብኝ ስላንተ መረጃ እንዲያቀብሉኝ አድርጌ ነበርኮ!!» አልኩት የተጠየቅኩት ሌላ የምመልሰው ሌላ እንደሆነ እየገባኝ

« እየተከተሉሽ ነበር። ከኪዳን ጋር ከተማ ስትገቡ እንዴት እንደሆነ መረጃ ደርሷቸው ነበር። ኪዳን በሰላም እንዲወጣ እኔ ጣልቃ መግባት ነበረብኝ!! (ፍጥጥ ብዬ ሳየው) ምንም አልሆንኩም!! » አለኝ እጁን ከአገጬ አውርዶ

«ምንድነው ያደረግከው?» አልኩት

«ብዙም አይደል! ዋናው ኪዳን መውጣቱ ነበር ያንቺ እዳው ገብስ ነው!!» አለኝ

«ይሁን ንገረኝ ምንድነው ያደረግከው?» ብዬ ጮህኩ

«ከረፈደ ነው መኪና እንደተመደበባችሁ የሰማሁት!! ምንም ማድረግ የምችለው ስላልነበር መኪናውን ተጋጨሁት!! ምንም አልሆንኩም!! ማንም አልተጎዳም!! ትራፊክ መጥቶ ስንጨቃጨቅ እናንተ ተሰውራችኋል። እኔን ተከትለው ሊደርሱብሽ ስለሚችሉ ካንቺ አካባቢ መጥፋት ነበረብኝ! ለጊዜው የሚያቆሙ ይመስለኛል። ሌላ መላ እስኪያገኙ!! አንቺን መከተል ካላቆመች ለልጄ ማንነቷን እንደምነግራት ነግሪያታለሁ!! መረጃዎች እንዳሉኝ ስለምታውቅ ለጊዜው አትሞክረውም!! ስጋታቸው አሁን ለምርጫው የሆነ ነገር ታደርጊያለሽ ብለው ፈርተው ነው!! የምታደርጊውን እስክታስቢ ፋታ ይኖርሻል!! (ትንሽ ፋታ ወስዶ)መች ነው ግን አንቺ የምታምኝኝ? ምን ባደርግ ነው ትቶኝ ይሄዳል ወይ ይከዳኛል ብለሽ የምታስቢውን የምታቆሚው?» አለኝ

«አላውቅም!! እኔ እንዲህ የምወደው ነገር ኖሮኝ አያውቅም! እንዲህ የተሸነፍኩለት ነገር ኖሮኝ አያውቅም!! እንዲህ የተንሰፈሰፍኩለት ሰው ኖሮኝ አያውቅም!! ባጣው የምሞት መስሎ የተሰማኝ ሰው ኖሮኝ አያውቅም!! የምወደውን ስጠብቅ የኖርኩት በመጠራጠር እና በጉልበት ነው!! ማመን እንዴት እንደሆነ አላውቅማ!!» አልኩት አስቤ የተናገርኩት አልነበረም!!

ፈገግ ብሎ ፊቱን አዞረ እና መልሶ በተመስጦ ሲያየኝ ቆይቶ ሁለቱን እጆቹን በአንገቴ ዙሪያ ልኮ አንገቴን እንደመደገፍ ፣ ከአገጬ ቀና እንደማድረግ አድርጎ ከንፈሩን ከንፈሬ ላይ አሳረፈው። ስሞኝ እጆቹ እዛው እንዳሉ ከመልሴ በኋላ መልሶ እንደሚስመኝ ነገር

«ያ ማለት ምን ማለት ነው? አለሽልኝ ማለት ነው? እ? ንገሪኛ?» ከንፈሩ ከንፈሬን ከነካው በኃላ እንኳን ዘሩን ያለሁበትን የማላስታውስበት ስካር ውስጥ ከቶኝ ነው የሚጠይቀኝ? በጭንቅላቴ ንቅናቄ አዎ!! አልኩት!! ከንፈሩን እቦታው መለሰው!!

......... አሁን ጨርሰናል!!..........


«እሺ ታዲያ እንዴት ከእነርሱ ጋር መስራት ጀመርክ?» አልኩት የነገሩን ጅማሬ ውል እየፈለግኩ

«ተዚያማ ትልቄ ሲሞት እምዬን ማስተዳደር በኔ ላይ ወደቀ። ያሸተ እህላችንን በእሳት ስላጋዩት ለከርሞ የሚቀመስ አልነበረም!! ቀዬው በጠኔ ደቀቀ። ይህኔ እምዬን ለወንድሟ አደራ ብዬ ወታደር ቤት ገባሁ!! ከዛ በምልክላቸው ፍራንክ እንደሆነው እንደሆነው አድርገው ከራረሙ።ወታደር ቤት ዓመታት ከቆየሁ ኋላ ወደቀዬ ተመልሼ መኖሪያዬን ቀለስኩ!! ምሽት አገባሁ ልጄን ወለድኩ!! ሚሽቴ ከ9 አቁማ የነበረውን የቀለም ትምህርት የመቀጠል እና በትምህርቷ ከፍ ያለ ቦታ የመድረስ ምኞቷ ትልቅ ስለነበር ከተጋባን ኋላ አስተምራት ነበር። የ12 ክፍል ትምህርቷን ስትጨርስ ሸጋ ውጤት አመጣች!! አዲስአበባ ዩንቨርስቲ ለትምህርት ተመደበች እና የ6 ዓመት ጨቅላ ልጃችንን ትታ መምጣት ግድ ሆነ!! ገና ከወራት ግን የልጇ ናፍቆት አቅቷት ተመልሳ መጣች። እሷ ከህልሟ አጓጉል ከምትሆን ምናባቱ ያገኘሁትን ሰርቼ እኖራለሁ ብዬ ልጄን ምሽቴን ይዤ አዲስአበባ ገባሁ!! ስራውንም ሳላማርጥ እየሰራሁ ባጀሁና ትንሽ ስደላደል እምዬንም አመጣኋት እኔጋ!! እንዳያልፍ የለም መቼም እንዴትም እንዴትም እሷ ተመረቀች። ይሄኔ እሷ ናት ይሄን ስራ በሰው አገኘሁልህ ብላ ደሳለኝጋ ያገናኘችኝ። እሷ ተመርቃ ከፍ ያለ ስራ ይዛ ከፍ ካሉ ሰዎች ጋር መዋል ስትጀምር ከእኔጋ መኖሩን እየተጠየፈችው መጣች። የምለብሰው አይጥማት ፣ አካሄዴ አይጥማት ፣ የማወራው አይጥማት …… ትምህርት ሚሽቴን ቀየራት ….. ትምህርት ሚሽቴን ነጠቀኝ!!» አለ ከደረቱ ቀና እንደማለት ብሎ በቁጭት ነገር የሆነ መፅሃፍ ትረካ ነገር በሬድዮ እየሰማሁ ያለሁ ነው እየመሰለኝ ያለው።


«ኋላማ ትዳራችን እንደማይሆን ሆነ። አቶ ደሳለኝ ጋር በጥበቃ ሰርቼ የማገኛት ገንዘብ ለሚስቴ ከራሷ ደመወዝ ጋር ተደምሮላትም የሚበቃትን ኑሮ አላኖር አለኝ። ኋላ ላይ አቶ ደሳለኝ በሷ ጥቆማ የግሉ ጠባቂ አደረገኝ። መድሃንያለም በሚያውቀው የዚህን ጊዜ ሁለቱ የሆነ ነገር ይኑራቸው የማውቀው የለኝም!! አይኔ ስር የሚሰሩትን ቆሻሻ ስራ አያለሁ!! ንፁህ ሰው አግተው ሲዝናኑ አያለሁ!! ቤቴን አቆም ብዬ አንገቴን ደፋሁ። ሰውየው የሚላቸው አሉት!! ስራው ጥበቃ አይደለም! ቆሻሻ ስራዎችን መስራት ነው!! የሚፈልገውን ሰው ከመሰለል እስከማገት ፣ መረጃ መስረቅ ፣ …… እነርሱን ተቀላቀል ሲለኝ አሻፈረኝ አልኩ። ሚሽቴ ብዙ ብር የሚያስገኝልኝን ስራ እንቢ ማለቴን ደሳለኝ እንደነገራት ነግራኝ ስትቆጣ የዚያኔ እምነቴ ሙሉ ስለነበር አልጠረጠርኳትም!! ብሩ ቢያስፈልጋት ነው ብዬ ስራውን ተቀበልኩ!! እሷን ካስደሰተልኝ እና በሷ ፊት ሞገስ ከሆነኝ ምናባቱ ብዬ ገባሁ!! ብዙ ወዳጅ አፈራሁ!! ስለከተማ ሰው ብዙ አወቅኩ!! እንዲያ ህሊናዬን አቆሽሼ ብዙ ብር ባመጣላትም ሚሽቴን አላቆየልኝም!! ፍታኝ አለችኝ!! በግድ ይዤ ላቆያት አልችል ለቀቅኳት።»

«ትወዳት ነበር!»

«ሚሽቴ አይደለች እንዴ? ቤቴ እኮ ናት የልጄ እናት! እንዴት አልወዳት?» አለኝ እንደመቆጣት ብሎ

«አይ እንዴት ሆነልህ ብዬ ነው! ባለፈው ሳያችሁ የሌላ ሴት ሚስት ሆና ምንም የመሰለህ አትመስልም ነበር።»

«ያልፋልኮ! ያልፋል! ቅናቱም ፣ ህመሙም ፣ እህህ ማለቱም ያልፋል!»

«እና ደሳለኝን ካገባችው በኋላ እሷን እያየህ ስራ እዛው እንዴት ቀጠልክ?»

«እኔና እሷ ከተፋታን ኋላ ትንሽ ቆይቶ እምይ በጠና ታመመችብኝና ለህክምና 10 ዓመት ብሰራ የማላገኘው ፍራንክ ተጠየቅሁ!! አቶ ደሳለኝ ብሩን ሊያበድረኝ እና በምትኩ ለ3 ዓመት የታዘዝኩትን ልሰራ ያቀረበልኝን ሀሳብ ለማለፍ ምርጫዬ የእምዬ ህይወት ነበርና ፈርሜ ገባሁበት!! እምዬን አዳንኩበት እኔ የማልወጣው ሀጥያት ውስጥ በየቀኑ ሰመጥኩ እንጅ!! ከዚያማ የልጄ እናት የአለቃዬ ሚስት ሆና መጣች። ትቼ አልሄድ ቃሌ ፣ ፊርማዬ ….. አልቀመጥ ሽንፈት ፣ ቅናት ፣ መከዳት ፣ መታለል ፣ መዋረድ አንገበገበኝ። ያልፋል አልኩሽ አይደል? አለፈ። እሷን ወይ አብራኝ እያለች አላውቃት ይሆን ወይ ከትምህርቱ በኋላ ተቀይራ : ጭራሽ የማላውቃት ሰይጣን ሴት መሆኗን አለቃዬ ስትሆን አወቅኩ። ለእኔ እንዲያ ብትሆንም ለልጄ ወደር የሌላት እናት ናት!! ልጄ በቋሚነት እኔጋ ብትሆንም ከአርብ እስከእሁድ እሷጋ ትሆናለች። አብረሽኝ ሁኝ ብትላት ልጄ እኔን መረጠች» አለ ኮራ ብሎ በፈገግታ ቀጥሎ

«አንቺጋ ስቀጠር ያገናኘን ሰውዬ ያንቺ ወዳጅ ቢሆንም በድብቅ የእነርሱ ወዳጅ ነው!! ያው ዘበኝነት ገብቼ የፈለጉትን መረጃ እንዳመጣ ነበር። ልጄ የታመመች ጊዜ » ብሎ ጊዜውን በማስታወስ ነገር ፍዝዝ አለ። «ልክ ያሁን ያህል አስታውሳለሁ። በረንዳው ላይ ተቀምጠሽ!

«ቤተሰብ ነኝ ብዬ ከቀበሌ የሆነ ወረቀት እናሰራ እና የእኔ ከሆናት የኔን ኩላሊት እሰጣታለሁ!» ስትይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደስራዬ ሳይሆን እንደሰው ያየሁሽ!! የዚያኔ ነው ለምን እንደሆን እንጃ ስላንች ማወቅ ናፈቅኩ። እናቷ ያንች ኩላሊት መስማማቱን ስነግራት አይሆንም አለች። ፈጣሪ ደግ ነው ሌላ ሰው ተገኘና ልጄ ዳነችልኝ! በሰው በሰው ሳጠራ ማን እንደሆንሽ ደረስኩበት። ስራዬን ልልቀቅ ካልኩሽ በኋላ ለእነርሱም ሄጄ ሌላ ስራ እንዲቀይሩልኝ ጠየቅኳቸው። በእኔ ምትክ እንዲገባ አናግረሽው የነበረውን ሰውዬ እነርሱ ናቸው የላኩልሽ!! የሰው ተፈጥሮ ያልፈጠረበት የሰይጣን ቁራጭ አረመኔ ነው!! ምንም እንኳን የምጠላው ጎሳ ፣የወንድሜ ገዳዮች ልጅ ብትሆኝም ለልጄ ስትይ አካልሽን ልትሰጭኝ ስስት አልነበረብሽም እና ለዚያ አውሬ አሳልፌ ልሰጥሽ አልሆነልኝም!! መልሼ ሀሳቤን አንስቻለሁ እሰራለሁ በቃ ብዬ ተመለስሁ!!» ብሎ ነግሮኝ እንደጨረሰ ነገር ዝም አለ።


«አባቴንኮ የገደሉብኝ ያንተ ወገኖች ናቸው፤ ማን ያውቃል ወይ አጎትህ ወይ አባትህም ሊሆን ይችላል፤ እናቴን መሳሪያ ይዘው የደፈሩብኝኮ እነዛው ያንተ ወገኞች ናቸው፤ ልጅነቴን ፣ወጣትነቴን ፣ ጉልምስናዬን ያመሳቀሉብኝኮ ያንተ ወገኖች ናቸው ፤ አምርሬ ስጠላቸው እና ላጠፋቸው ስመኝኮ ነው የኖርኩት። በህይወቴ አንድ ጥሩ ነገር ቢከሰት ፣ አንዴ ፍቅርን ባገኝ ፣ አንዴ ብሸነፍ …… እሱም የእነሱ ወገን ይሁን?» እያልኩት ውስጤኮ ቁጭት ነው የሞላው ቃላቶቹ ከአፌ ሲወጡ ግን እንባዬን አስከትለው ሀዘን የተሸከሙ ነበሩ።

«አንዴ ሁሉን ስሚና ፍረጅኝ!! ሰምተሽ አሻፈረኝ ከአሁን ፍቅሬ ያለፈ በደሌ ይበልጣል ካልሽ ምን ማድረግ ይቻለኛል? ልብሽ ያለሽን አድርጊ!! እ? እ ዓለሜ?» ከፊት ለፊቴ ተነስቶ አጠገቤ ወንበር አድርጎ ተቀመጠ። እንዳያቅፈኝም እንዳይነካኝም የቸገረው መሰለ። እንዳየው በዓይኖቼ ዓይኖቼን ያሳድዳል።

«እሺ ንገረኝ! ሁሉንም ልስማህ!! የእነሱ ወገን መሆንህን ግን የትኛው ታሪክ ይቀይረዋል?»

«ፍቅር! ፍቅር ይቀይረዋል! ፍቅር ጎሳ ብሄር ሀገር የለውምኮ ዓለሜ? እኔስ አስቤ እና አቅጄ በፍቅርሽ የወደቅኩ ይመስልሻል? ላንች እስከተንንበረከኩባት ሰዓት ድረስ እኔምኮ ያንቺን ጎሳ እንገሸገሸው ነበር። ሁሉም ቤትኮ እሳት አለ ዓለሜ!? ከጥላቻዬ አስበልጬ ወድጄሽ ነው! ከቂሜ አስበልጬ ወድጄሽ ነው፣ ፍቅርሽ ልቤ ሲሞላ መበደሌን ይቅር ብዬ ነውይ!» ብሎ ጀርባዬ ላይ አንድ እጁን ደገፍ አደረገ።

«የአባትን ሞት ያህል በደል አልተበደልክማ! የእናትን መደፈር ያህል ቂም አልያዝክማ! እድሜህን ሁሉ የቀማህ ጥላቻ አልጠላህማ!!» አልኩት ማልቀሴን ሳላቆም! ከተቀመጠበት ተነስቶ እንደገና ወደነበረበት ተመልሶ

«ህም!!» አለ እና በረዥሙ ተንፍሶ ቀጠለ። « እኮ የእኔ ህመም ይተናነስ እንደው ሰምተሽ ፍረጅኛ!! አብይ ህፃን ሳለሁ ነው የሞተው!! እንደመጎርመስ ብዬ ድምጤ የሻከረ ጊዜ እምይ ታማ ካልጋ ዋለች። ህመሟ እንዲህ ነው ሳይባል ወሰድ መለስ እያደረጋት እድሜ ቆጠርን!! እኔ እና ትልቅ ወንድሜ ነበርን እርሻውኑም ከብቱንም ብለን እምዬን የምናኖራት። ትልቄ እንደታላቅነቱ ሀላፊነት አለብኝ ብሎ ትምህርቱን ተወው!! እኔ በቀለሙ ትንሽ ፈጠን ያልኩ ስለነበርኩ እኔን ከትምህርት እንዳልጎድል አገደኝ። 10 ክፍል ስማር ሳለሁ አንድ እለት ተማሪ ቤት እየተማርን ሳለ ከተማው በጩኸት ሰከረ። በላይ በላያችን እየተረጋገጥን ብቅ ስንል ከተማው ይንቦለቦላል። ያልነደደ ቤት ያለ አይመስልም ነበር። ሁሉም የራሱን ቤተኞች ደህንነት ሊያጣራ ሲሮጥ መደሚጤሰው ከተማ ገባ። የምማርበትን ደብተር በትኜ ስበር ወደቤት ሄድኩ። በመንገዴ ከከተማው ግማሽ የሚያህለው ቤት እየነደደ መሆኑን ሳይ አልጋ ላይ የዋለች እምዬን እሳት በላብኝ ብዬ ነፍሴ ስትጨነቅ ደረስኩ። ቤታችን ሲነድ ደረስኩ። እምይ በደረቷ ስትሳብ ከበሩ ደርሳ ነበር።» ብሎኝ ፊቱ በሀዘን ተውጦ ከንፈሩን ነከሰ።

« እሳት የጀመረው ቀሚሷን አፈር በትኜ አጥፍቼ እሷን በክንዴ ላይ አቅፌ ከጎረቤት የነበረ እሳት ያላገኘው የወንድሟ ቤት አስቀምጫት ለወንድሜ ሚስት ሀደራ ብዬ እንዲህ ካለ ግርግር መሃል አይጠፋም እና አንዳች ነገር እንዳይሆንብኝ ብዬ ወንድሜን ፍለጋ ወጣሁ። ሰፈርተኛው እሳቱ የባሰ እንዳይዛመት ሊያጠፋ ደፋ ቀና ይላል። ደመኞቻችን እጃቸው የደረሰውን ታህል ቤት አንድደው ፣ የደረሰው እህል ላይ እሳት ለቀውበት ወደገበያ መሃል መግባታቸውን ከመንገድ ስሰማ በአሳላጭ ቅያስ በርሬ ደረስኩ። (ክብድ ያለው ትንፋሽ ግንባሩን አኮሳትሮ ተነፈሰ እና ቀጠለ) ያንች ዘመዶች ገበያው ዳር የተፋለሟቸውን የከተሜውን ወንዶች ሬሳ አጋድመው ሲጨፍሩ ደረስኩ። ትልቄ ለስራ ከለበሰው ቡት ጫማውጋር በእጁ የአብዬን ጠብመንጃ እንደያዘ ተዘርግቷል።» ሲለኝ ሳላስበው

«ሞተ?» አልኩኝ

«እህ!! (ጭንቅላቱን ወደላይ እና ወደታች እየነቀነቀ) እንደዋዛ ድፍት ብሎ ሞተ። አድብተው እንደሌባ አጥቅተውን እንደጀግና እየጨፈሩ መሪያቸውን ትከሻቸው ላይ ተሸክመው በሽለላ እያወደሱት ያጋደሙትን ሬሳ ሲዞሩ ቆይተው ከተማውን ለቀው ወጡ!! ድምፃቸው ከጆሮዬ ብዙ ጊዜ ዋለ - የወንድ ዋርካ የጀግና አድባር
የአምሳል አባት ባለዝናር …… » እሱ ድሮ በልጅነቴ ለአባቴ ሲገጠም የማውቀውን ግጥም በቃሉ ወረደልኝ። እኔ ግን የአምሳል አባት ከሚለው በኋላ ያለውን አልሰማሁትም!! ሰውነቴ ቀዘቀዘ። ሁሉም ቤት እሳት አለ ያለኝ ይሄን ነበር? ታዲያ ይሄን እረስቶ ወዶኝ ነው? ሊበቀለኝ ፈልጎ እንጂ!!!

«እኔጋ መቀጠርህ ከቀዬህ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም አላልከኝም?» አልኩት ሳላስበው

«የሚያያይዘው የለም!! ያ ሰው አባትሽ መሆኑን ያወቅሁት ራሱ አንቺጋ ከገባሁ ከወራት በኋላ ነው!!» አለኝ ረጋ እንዳለ። ዝም አልኩኝ!!

«ታምኚኛለሽ? እንድዋሽሽ የሚያደርግ አንዳች ምክንያት የለኝም! አለመንገር እችል አልነበር? የምፈልገው በቀል ከነበር እጄ ላይ ነበርሽኮ ዓለሜ!! በብዙ መንገድ ላደርገው እችል ነበር። ለእነደሳለኝ መረጃውን እስኪያገኝ ነው ያልተበቀለኝ ብለሽ ታስቢ ከሆነ ልንገርሽ!! ሁሉንም አውቃለሁ!! ባንክ ያስቀመጥሽውን ኮፒ ፣ እሙጋ ያስቀመጥሽውን ፣ ሴትየዋጋ ያለውን!! እቤትሽ መታጠቢያ ቤት መስታወት ጀርባ ያለ ድብቅ ካዝናሽ ውስጥ ያሉ መረጃዎችሽን፣ ኮዱን ልነግርሽ እችላለሁ። የቀረኝ አለ? ሁሉን ደርሼበታለሁ!!! በቀል ከነበር ዓላማዬ እጄ ላይ ነበርሽ!! ታምኚኛለሽ? እርግጥ ነው ብዙ ጥላቻ እና ቂም ነበረኝ ግን የበቀል ሰው አልነበርኩም!!» ሲለኝ የማስበው ተምታቶብኝ የነገረኝን ትርጉም ልሰጠው እታገላለሁ!! ይሄን ሁሉ ካወቀ ምንድነበር የሚሰራው በሬ ላይ? ያሰብኩትን ያወቀ ይመስል

«አላውቅም!! ለምን እንደቆየሁ አላውቅም!! መች በፍቅር እንዳየሁሽ አላውቅም!! ብቻ አንቺን መጠበቁን ወደድኩት!! የዚያን ቀን መሄዴ ነው ስልሽ ከልቤ ነበር!! ወረቀት አኑሬልሽ ልሄድ ነበር። እውነታውን ፅፌ አኑሬልሽ ልሄድ ነበር። እንደማይባል እንደማይባል ብለሽ ታች ላይ አድርሰሽ ሰድበሽኝ ወጣሽ!! ስዘገጃጅ ፖሊስ በሩን አንኳክቶ መመታትሽን ነገረኝ!! ልቤ ሁለት ሆነ። ከሆስፒታል እስክትወጪ ታግሼ እቤትሽ ስትገቢ ጠብቄ ልሂድ ብዬ ጠበቅኩ!! ስትመጭ ጭራሽ ሌላ ሰው ነበርሽና ትቼሽ መሄድ አልቻልኩም!!» (የዛን ቀን ያለውን ቀን እኔ እየከተለኝ የነበረ መኪና አስተውዬ ልለው ስወጣ ነበር ስራዬን መልቀቄ ነው ያለኝ። ምን እንደዛ እንዳናደደኝም አላውቅም!! እሱ ክብሩ ከሚነካ ሞቱ እንደሆነ አውቃለሁ ግን ተናገርኩት!! ስወጣ ማለቴን አስታውሳለሁ።


የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሰላሳ (የመጨረሻ ክፍል)
(ሜሪ ፈለቀ)

ብዙ ጥያቄዎች ስለእርሱ እያብሰለሰልኩ አልነበር? ቅድም ተበሳጭቼበት ባገኘው የምጮህበት ሲመስለኝ አልነበር? ታዲያ ገና ሳየው እንኳን ልቆጣ የማወራውም የማስበውም ጠፍቶኝ አባን ጉልበት ስሜ እሱን እጁን ጨብጬ ተቀመጥኩ። እየመላለስኩ ስል ቆየሁ አባን!!

«ተገናኛችሁም አይደል? እኔ የምፈፅማት ጉዳይ አለችኝ!» ብለው ተነሱ። እሳቸው ከአጠገባችን ከራቁ ከደቂቃዎች በኋላ እንኳን ዝም ተባብለናል። የሆነ በነዚህ ባልተገናኘንባቸው ቀናት በመሃከላችን መራራቅ የተፈጠረ ዓይነት ስሜት አለው።

«ቸር ባጀሽ?» አለኝ እኔ ቀድሜ እንዳወራ ሲጠብቅ ቆይቶ! ቸር ነው የባጀሁት? እሱ ምን ሆኖ እንደዘጋኝ የሀሳብ ካብ ስከምር እና ስንድ እንቅልፍ እንቢ ብሎኝ የተሰቃየሁት ፣ እወድሻለሁ እያለ አንሶላ አብሮኝ ሲጋፈፍ የነበረው ሰው ከምድረገፅ ሊያጠፋኝ እስኪሻ አምርሮ የሚጠላኝ ሰው ሆኖ ማግኘቴ ፣ አሁን ወደዚህ እየመጣሁ በብዙ ባዶነት መዋጤ …… ይሄ ቸር ከተባለ አዎ ቸር ነው የባጀሁት!!

«መሄድ ነበረብኝ!!» አለኝ እኔ ምንም ሳልጠይቀው! ዝም አልኩ!

«አናግሪኝ እንጅ ዓለሜ?» ሲለኝ ኩርፊያዬን ትቼ ማለት ነበር ያሰኘኝ ደጀ ሰላም ሆንኩ እንጂ!!

«ምን ልበል? መሄድ ኖሮብኝ ነው አልከኝ አይደል? የማለት መብት አለኝ? ከመሄድህ በፊት ልታሳውቀኝ እንኳን ግድ ያልሰጠህ አያገባትም ብለህ አይደል? ያስኬደህ ነገር ከእኔ በላይ ያንተን ትኩረት የሚሻ ነገር ቢሆን አይደል ሀሳብ አሳቅፈኸኝ የጠፋኸው? ዝም ከማለት ውጪ ምን አቅም አለኝ?» ስለው በጣም ስፍስፍ ባለ አስተያየት አይቶኝ ከተቀመጠበት ተነሳ

«ተነሽ እንሂድ?» አለኝ

«የት?»

«እኔእንጃ! ቁጭ ብለን የምናወጋበት ቦታ!!» ሲለኝ ለምንድነው ከተናገረው ዓረፍተ ነገር የተለየ የገባኝ? ማውጋቱንማ እያወጋን አይደል? እየነካሁሽ፣ እያቀፍኩሽ እየሳምኩሽ የማወጋሽ ቦታ እንዳለ ነው የሰማሁት። ተነሳሁ!! ደጁን ስመን ወጣን እና መኪናዬን ወዳቆምኩበት ልሄድ ስል ታክሲ ይዘን እንሂድ ሲል ለምን ብዬ አልጠየቅኩም!!

«አባጋ እንደምመጣ በምን አወቅህ?»

«ጭንቅ ጥብብ ሲልሽ የምትመጭ እዚሁ አይደል? ደሞ አርብ አይደል? አርብ አርብኮ ለወትሮም አባጋ ታዘወትሪ ነበር!»


ከዋናው መንገድ ደርሰን ከቆሙት ላዳዎች አንዱን ወደሱሉልታ ይዞን እንዲሄድ አናግሮት ከኋላ ወንበር ገባን። መንገድ ስንጀምር እጁን በትከሻዬ አሳልፎ አመልጠው ይመስል ተሽቀዳድሞ ስብስብ አድርጎ ደረቱ ላይ አደረሰኝና ጭምቅ አድርጎ አቀፈኝ።

«እኔ ላይ ሙሉ መብት አለሽ!! የልቤ አዛዡ አንቺ አይደለሽ? ያንቺን ያህል እኔ እንኳን መች በገዛ ልቤ አዝበታለሁ? አያገባሽም ብዬ አይደለም ሳልነግርሽ የጠፋሁ።» አለኝ። ካቀፈኝ በኋላ ምክንያቱን ቢነግረኝም ባይነግረኝም ግድ አልነበረኝም። ተናድጄ የነበረውን ፣ ከፍቶኝ የነበረውን ፣ ተቆጥቼ የነበረውን ፣ መጠየቅ እፈልግ የነበረውን ……… ሁሉንም ረሳሁት!! እጄን በሆዱ ላይ አሳልፌ ወገቡን አቀፍኩትና በቃ ዝም አልኩ!! እንደዚህ ታቅፌ አላውቅማ!! ደረት ከዝህች ዓለም ውጥንቅጥ መጠለያ ቤት መሆኑን አላውቅማ!! የሰው ልብ ማዘዝ እንደሚቻል አላውቅም ነበራ!! ብዙዙዙዙ ከፍቅር ጎድዬ ነበራ!! ሲጠፋብኝ ሳቄንም ሀሳቤንም ይዞብኝ የጠፋ ፣ ሲመጣልኝ ዓለምን ያስጨበጠኝ ሰው ኖሮኝ አያውቅማ!! በዚሁ ሱሉልታ አይደለም ከሀገር ይዞኝ ቢጠፋ ፣ እንዲሁ ደረቱ ላይ በክንዱ ታቅፌ ብቻ ብዙ ዓመት መሽቶ በነጋ!! ያለፈው ዘመኔ ፍቅር ያልጎበኘው ምነኛ ባዶ ነበር? ፀጉሬን ሳም አድርጎ

«እየተከተሉሽ ነበር!! …… » ብሎ ሊቀጥል ሲል

«ዝም ብለህ እቀፈኝ!! በኋላ ትነግረኛለህ!! አሁን ዝም በለኝ!!» አልኩት ከእርሱ ፍቅር ውጪ ቢያንስ ሱሉልታ እስክንደርስ መስማት የፈለግኩት ነገር የለም!! ክትትል ፣ ፀብ ፣ በቀል ፣ ሴራ ….. የት ይሄድብኛል ሲሆንብኝና ሳደርገው የኖርኩት አይደል? እንዲህ የታቀፍኩት ግን ዛሬ ብቻ ነው! እንዲህ ልቆይና የሱን የልብ ምት የእኔን የልብ ፈንጠዝያ ልስማ!! ከዛ በኋላ የሚከተሉኝ ሰዎች እንኳን አጊንተው ቢገድሉኝ ታቅፌ ነበር ፣ የእናትን ሞት በሚያስረሳ እቅፍ ታቅፌ ነበር፣ የበረደው ልብ በሚያሞቅ እቅፍ ታቅፌ ነበር፣ መኖር ጀምሬ ነበር።


«እሽ» ብሎ ባላቀፈኝ እጁም ደርቦ አቅፎኝ አንዴ ጨመቅ አንዴ ላላ ሲያደርገኝ ፣ አሁንም አሁንም ፀጉሬን ሲስመኝ ደረስን። ልጁን መንገድ እንደሚያሻግር አባት እጄን ይዞኝ የገባው ሪዞርት ውስጥ ካሉት ትንንሽ ጎጆ ቤት መሳይ አንደኛው ጋር ገብተን ፊት ለፊት ለፊት ለፊት ተቀመጥን። ጎጆ ቤትዋ ውስጥ እኛ ከተቀመጥንበት ጠረጴዛ በተጨማሪ ሌላ አንድ ጠረጴዛ ቢኖርም ሰው የለውም ነበር እና እኔና እሱ ብቻ ነበርን። አስተናጋጁ የሚታዘዘውን ጨራርሶ እንዲሄድልን አጣድፈን አዘን ሸኘነው። መብት አለሽ ተብዬ የለ? ሁለቱንም እጄን ጠረጴዛው ላይ ዘርግቼ እንዲይዘኝ ሰጠሁት። በሁለቱም እጆቹ ያዘኝ።

«እሺ አሁን ንገረኝ!!» አልኩት በስስት የሚያዩኝን አይኖቹን(መሰለኝ) እያየሁት

«ከወየት ልጀምር?»

«እኔ እንጃ!! ማነህ? ምንም ሳይቀር ስላንተ ማወቅ እፈልጋለሁ!» ስለው ዓይኖቹ ውስጥ መከፋት ነገር ያየሁ መሰለኝ ወይም ፍርሃት እኔንጃ

«እሽ! ምንም ሳላስተርፍ አወጋሻለሁ!! ግና የቱ ነው ማን መሆኔን የሚገልጥልሽ? ያለፈ ህይወቴ? የመጣሁበት ብሄር ጎሳዬ? አባት አያት ቅድመአያቴ? እምነቴ? የእስከዛሬ በጎ ምግባሬ ወይስ ሀጥያቴ? ወይሳ አሁን የሆንኩት እኔ? በየትኛው ነው አንት ይህ ነህ ብለሽ ምትቀበይኝ?» አለኝ ያለፈው ህይወት አድካሚ እንደነበር በሚያሳብቅ መልኩ።

«ሁሉም መሰለኝ!! የሁሉም ድምር መሰለኝ አንተን አንተ የሚያደርግህ!! ሁሉንም ልወቀው!!»

«ደግ!! ከማን ጎሳ መገኘቴ ፍቅርሽን ያሳሳብኛል?» አለኝ ሲሆን አይቼው እንደማላውቅ ሽንፍ ብሎ በልምምጥ

«የእነሱ ወገን አትሁን እንጂ ….. » ብዬ የአባቴን ገዳዮች ጎሳ ከመጥራቴ መልሱን ፊቱ ላይ አገኘሁት!! ማድረጌን ሳላውቀው እጄን ቀማሁት። ልቤ ድው ድው ማለቱን ያቆመ መሰለኝ። ከዛች የተረገመች ቀን ጀምሮ እድሜዬን ሙሉ ስጠላቸው ኖሪያለሁ። ያለፉትን ወራት ግን ልቤን የሞላው የሱ ፍቅር ጥላቻዬን ከድኖት ክፋትን እየሸሸሁ ፣ በቀልን እና ጥላቻን ከልቤ እያስወጣሁ ሌላ ሰው ልሆን እየሞከርኩ አልነበር? ለምን እንዲህ ተሰማኝ ታዲያ? የሱ ፍቅር ሌላው ላይ ያለኝን ጥላቻ እንጂ ማጥፋት የሚችለው እሱ የምጠላውን ሆኖ ሲመጣ ፍቅሩ አያሻግረኝ ይሆን? ዝም ብዬ መሬት መሬቱን ሳይ አስተናጋጁ የታዘዘውን ይዞ መጥቶ ጠረጴዛው ላይ መዋከብ ጀመረ። ቀና ብዬ አየሁት። እያየኝ ነው። ዓይኔን በዓይኑ ሲይዘው በሚለምን አስተያየት አየኝ!!

«እሺ አንድ ነገር ንገረኝ? እኔጋ መስራት መጀመርህ የእነሱ ወገን ከመሆንህ ጋር ተያያዥነት አለው?»

«የለውም ዓለሜ!!» አለኝ እንደተጨነቀ እያስታወቀበት።


«ተነሺ ከእግሬ ላይ!!» ብዬ ጮህኩባት

«በእመቤቴ ይዤዎታለሁ!! እንደው በሚወዱት ይሁንብዎ!! እጆት ላይ ይሞታል!! ኸረ እንኳን አንጠልጥለውት በአንድ ጥፍ ባህር የሚሻገር ነፍሰ ቀጭን ሰበብ ይሆንብዎታል።»

«ተነሺ ከእግሬ ላይ አልኩኮ!! እንዲሞት አይደል እንዴ ታዲያ!» ጮህኩኝ ድጋሚ

«እኔንም እንደፈለጉ ያድርጉኝ ከፈለጉ አልነሳም!!» ብላ አንድ እግሬ ላይ ተጠመጠመች። ሌላን ሰው ለመታደግ መሬት መንበርከኳ ገረመኝ። ትንፋሽ አጥሮት ሲልሞሰሞስ እያየሁት አሰብኩ!! ንዴት ላይ ሆኜ በፍፁም የማስብ ሰው አልነበርኩምኮ!! የድሮዋ እኔ ብሆን እጄ ላይ ይህችን ደቂቃ አይቆይም! ገና ሲመጣ ዘግቼው ነበር። ሆኖልኝ ቆይቶ እንኳን ቢሆን እግሬ ስር የተደፋችውን ሴት ታግሼ ተነሺ አትነሺ ግብ ግብ አልገጥምም! ይሄኔ ገንብሬ ጥያት ነበር!! አሁን ተቀይሬያለሁ ወይም ለመቀየር እየሞከርኩ ነው! መሬቱ ላይ ለቀቅኩት!! ሴትየዋ ከእግሬ ላይ ተነሳች። እየተንከባለለ አስሎ ሲያበቃ! መሬቱ ላይ ቁጢጥ ብዬ

«ለምን? ለምን እንዳደረግከው ብቻ እውነቱን ንገረኝ!! ከዋሸኸኝ ኪዳንን ይንሳኝ እጨርስሃለሁ!!» አልኩት! ለገንዘብ ብሎ እንደማያደርገው አውቃለሁ። የገንዘብ ችግር የለበትም!!

« ግልፅ አይደል እንዴ? ስለምጠላሽ!» አለኝ እስከዛሬ አናግሮኝ በማያውቀው ጥላቻ እና ድፍረት። ደነገጥኩ። ወዲያው ከአፌ ቃል አልወጣም!!

«ልትገድለኝ እስከሞከርክ ቀን ድረስ እወድሻለሁ ስትለኝ አልነበር? እየጠላኸኝ ነው አብረኸኝ የነበርከው? ደግሞስ ምን አድርጌህ ነው እስከመግደል የምትጠላኝ?» ስለው ተነስቶ እዛው መሬቱ ላይ ተቀመጠ እና ቆመው ሲያዩን የነበሩትን ሴቶች አያቸው። እየተሯሯጡ ወደ ውስጥ ገቡ።

«ከአባቴ ቀጥሎ እንዳንቺ ያዋረደኝ ፣ ትንሽ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ፣ ራሴን እንድጠላ ያደረገኝ ሰው የለም። ከዛሬ ነገ ትወጂኛለሽ፣ በፍቅርሽ እፈወሳለሁ ብዬ ጠበቅኩሽ። በየቀኑ ናቅሽኝ!! ለፍቅሬ ምላሽሽ ሁሌም እንደበረዶ የቀዘቀዘ ቃላት ነው የምትወረውሪልኝ። ያላልሽኝን ቀን ብቆጥረው ከእጄ ጣት አይበልጥም!! ለአባቴ እንደልጅ እንደሰው ነው የከሸፍኩበት። አንቺ ግን ወንድነቴንም ነው የቀማሽኝ!! አብሬሽ ባሳለፍኩት እያንዳንዱ ቀን ትንሽ በትንሽ በራስ መተማመኔን እየሸረፍሽ ካንቺ ሌላ ሴት እንደወንድ እንኳን የማትቆጥረኝ እየመሰለኝ አብሬሽ ቆየሁ። ምክንያትሽን ሳትነግሪኝ ለወራት ስትዘጊኝ እጠብቃለሁ። ምክንያትሽን ሳትነግሪኝ ስትመለሺ እቀበልሻለሁ። ላንቺ ምንም ነኝ!! በፈለግሽ ሰዓት ሄደሽ ስትመለሺ የምታገኚኝ እቃሽ ነኝ!! እኩል ድርሻ ባለን ቤት ላይ እንኳን ፈላጭ ቆራጯ አንቺ ነሽ!! አንቺ አለቃ እኔ ባሪያሽ ነኝ!! ንገሪኝ ለመጥላት በቂ ምክንያት አይደለም?»

አልመለስኩለትም። ቁጢጥ ካልኩበት ተነሳሁ!!!! ቆሜ ምን እንደማስብ አላውቅም ግን ፈዝዣለሁ። እሱ ከአሁን አሁን ምን ታደርገኛለች ብሎ በሰቀቀን እየጠበቀኝ ነው።

«ይቅርታ!!! ይሄ ሁሉ አይገባህም ነበር። እንዲህ እንዲሰማህ ማድረጌንም አላውቅም ነበር። ስቀህ ማለፍህ ልክ የሆንኩ እንዲመስለኝ አድርጎኛል። ይቅርታ አድርግልኝ!! ከልቤ ነው አንተ ጥሩ ሰው ነህ!! ቢያንስ ለእኔ ጥሩ ሰው ነበርክ!! አይገባህም ያልኩህ የእውነቴን ነው። » አልኩት። ሞቶ መንግስተሰማያት ደርሶ ይሁን በእውኑ እዚህ ምድር ላይ ሆኖ ይሄን ከእኔ አፍ መስማቱ እያወዛገበው አይኑን ጎልጉሎ ያየኛል።

«ሙከራህን ብትደግመው የምምርህ እንዳይመስልህ!! ቤቱን ልሸጠው እፈልጋለሁ!! ህገወጥ ስራውን የምታቆም ከሆነ የእኔን ድርሻ ልሽጥልህና የቤት ኪራይ እየከፈልክ ስራበት። አይ ካልክ ግን ቤቱን ለቀህ ትወጣለህ!! እኔ ጨርሻለሁ!!» ብዬው ወጣሁ።

ከወጣሁ በኋላ ያ ስሜት ተሰማኝ!! ባዶ የሆነ ስሜት!! ጣዕም አልባ ስሜት!! የምሄድበትን ሳላውቅ እየነዳሁ ስዞር ቆይቼ አመሻሽ ላይ አባ መልከፃዲቅ ያሉበት ቤተክርስቲያን ሄድኩ!! እግራቸው ላይ ተደፍቼ ማልቀስ ፈልጌ ነው።ኮቴን ክለብ እረስቼው የለበስኩት እጁ የተጋለጠ ነገር ስለነበረ ሱቅ ገብቼ ነጠላ እና ሹራብ ደርቤ ቀጠልኩ።
በሩን አልፌ ቦታዬጋ ስደርስ አይኔ ከቆቡ ውስጥ ተጎልጉሎ ሊወጣ ደረሰ። አባ የሚቀመጡባት ጉቷቸው ላይ ተቀምጠው ጎንጥ እኔ በምቀመጥበት ቦታ እግራቸው ስር ተቀምጦ ያወራሉ። እግሬ ተወለካከፈብኝና ቆምኩ። አየኝ!! ምንም ቀን እንዳልዘጋኝ!! ልቤ በመከፋት ተኮማትራ ከእጄ ጭብጥ እንዳላሳነሳት፣ መከፋት እና ተስፋ መቁረጥ እንዳላሸከመኝ ሁሉ ፈገግ አለ።

........... አልጨረስንም!! ..........


ወጥቼ ብዙም ሳይቆይ አንድ ባንክ ውስጥ በራሱ ፣ በእህቱ ፣ በአንድ የሩቅ ዘመዱ …… ደማምሮ የያዘውን 48% አክሲዮን ተቀበልኩት። እኔም በራሴ ፣ በኪዳን እና በእሙ ስም አደረግኩት!! የዚህን ጊዜ ብሎ ፎክሮ ነበር። እንደባለስልጣን ሳይሆን እንደተራ መናኛ ሰው ራሱ የሚጠብቀው ነገር ቅሌት መሆኑን እየደጋገምኩ ማስታወስ ነበረብኝ። ይፎክራል እንጂ እንደማያደርገው አውቃለሁ። የስልጣን ፍቅሩ ነፍሱን እስከመገበር የሚያደርሰው ነው። ቀስ በቀስ ሀብቱን ስቀበለው። የሚልበት ቀን ብዙ ነበር!!

ከዚህ በኋላ ግን ሁሉም ሲኖረኝ ፣ ከህፃንነቴ ጀምሮ የኖርኩለትን ጠላቶቼን የመግደል ህልም ሳሳካ ፣ ካሰብኩት በላይ ገንዘብ እና አቅም ሲኖረኝ ………. ሁሉም ቀስ በቀስ ጣዕሙን እያጣብኝ መጣ!!! የምኖርበት ህልም አጣሁ!! ለራሴ ስል የምለው ምንም ነገር ጠፋኝ!! ለካንስ በበቀል ስካሬ ውስጥ ወጣትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ ሴትነቴን ሰውቼዋለሁ፣ እናት የመሆን እድሌን ቀርጥፌዋለሁ ፣ ሚስት የመሆን መንገዴን ዘግቼዋለሁ ፣ ከሁሉ በላይ ግን ሰው መሆንን ገብሬ ከሰውነት ወርጃለሁ!! ………… ከዛማ በህይወቴ ከኪዳን እና በጥቂቱ ከእሙ ውጪ ምንም ነገር ፈገግ የማያስብለኝ ፣ ልኩን ከስህተቱ ያደበላለቅኩ ፣ ባህልን ከዘመናዊነት ያቀላቀልኩ ፣ ብልግናን ከጨዋነት ያጣረስኩ ፣ ምን ለምን እንደማደርግ የተወናበደብኝ ሆንኩ!! ሲረጥቡ መበስበስ ለምጄ የለ? ተበሳበስኩት!!

ሙሉሰውም ጭንቅላቱ የተዛባ እስኪመስለኝ ድረስ የሚሰራው ሁሉ የሚበላሽበት ፣ ከቀን ወደቀን የደጋፊዎቹ መወድስ እየቀነሰ የሚተቸው ሰው ቁጥር እየበዛ ጭራሹኑ አስተካክሎ የሚከውነው ነገር ጠፋው!! እዚህ ነጥብ ላይ እየፈራሁት መጥቼ ነበር። የሆነ ቀን ገድሎኝ ራሱን ሊገድል ይችላል ብዬ ማሰብ ጀምሬ ነበር። ግን ለምንድነው የማልረካው? እሱን በቁሙ ገድዬው ሌሎቹን ጨርሼ አሁንም የተሸነፍኩ ዓይነት ስሜት የሚሰማኝ ለምንድነው? ያ ሁሉ ቁስል እነርሱን ስበቀል የሚድን መስሎኝ አልነበር? ለምን አሁንም እንደድሮ ያመኛል? ያደረግኩት ክፋት እና በቀል ጥያቄዬን እንዳልመለሰ ወይም ህመሜን እንዳልፈወሰ እያወቅኩም በክፋት መቆመሬን ቀጠልኩበት።

ገንዘብ ካለ ሲደመር ስልጣኑ ያለው ሰው ካወቅኩ የማላገኘው ነገር ጥቂት መሆኑን ስረዳ የማይጣሱ ብዙ መስመሮች ጣስኩ። ከአንድ ባልደረባው ጋር በአንድ ውሳኔ ሳይግባቡ ቀርተው እራሱ ስንቴ መጥቶ የባለገበትን ቤት እንደማስፈራሪያ ተጠቅሞ የሙሉ ሰውን እጅ ጠመዘዘው። ሙሉሰው አይደለም የማይፈልገውን ውሳኔ መወሰን ቢሞት ራሱኮ ግድ አይሰጠኝም ግን ሰው መበቀል እና ክፋት ደሜ ውስጥ ያለ ነገር መሰለኝ። ሰውየው ሲባልግ በድብቅ ቀረፅኩት። የተከበረ ባለትዳር እና የልጆች አባት ስለሆነ የቀረፅኩትን ቪዲዮ ሳሳየው ሽንቱን ሱሪው ላይ ሊሸናው ምንም አልቀረውም። የሚገርመው ግን ብሎ ይሆን አልገባኝም። እየመጣ መባለጉን አላቆመም!! በድብቅ ካሜራ እንደቀረፅኩት ለአንድ ሰው ትንፍሽ ቢልና አንድ ደንበኛ ባጣ በራሱ እንዲፈርድ አስጠንቅቄዋለሁ። እውነትም ለማንም ትንፍሽ ሳይል ቀርቶ ይሆን ወይም የነገራቸውም ሰዎች እንደእርሱ ሱሳቸው በልጦባቸው አላውቅም የቀረ የለም። ለምናልባቱ የምፈልጋቸውን ሰዎች የፖርን ፊልም ማስቀመጤ አልቀረም። አስፈልጎኝ የምጠቀምበት ቀን እስኪመጣ ድረስ

የሙሉ ሰውን ከቀልቡ አለመሆን ተከትሎ ህዝቡ በሱ ላይ እንዲነሳ አጋጋይ በዛ!! ጨዋ ናቸው የሚባሉት እንኳን እሱን ለመጣል ተወለካከፉ!! ጨዋታው ስላዝናናኝ ብቻ ቆሻሻቸውን እየፈለጉ ሲሸነፉ ማየት የበላይነት ስሜት ስለሚሰጠኝ ወደድኩት። ለእኔ ቀላል ጨዋታ እንደሆነው ለእነሱ አልነበረም እና ከሙሉሰው ጀርባ ነገር የምቀምረው እኔ መሆኔን ሲያውቁ ሁለት ተቃራኒ ጠላቶች አፈራሁ። የተወሰኑት ሊያጠፉኝ የሚያደቡ ሲሆኑ የተቀሩት መዝራት የፈለጉትን ክፋታቸውን እና ወጥመዳቸውን በእኔ ተከልለው መከወን የሚፈልጉ ጥቅመኞች (አጋጣሚውን ካገኙ በራሴው ወጥመድ የሚያጠምዱኝ ሴረኞች ናቸው።) ሁለቱም ወገን በአይነቁረኛ የሚፈራኝ እና የሚጠላኝ ሰውም ሆንኩ። ባሎች ለሚስቶቻቸው ስለእኔ አሙላቸው። ሚስቶች ተሰብስበው ስጋዬን በሉት። በውስጣቸው ግን እነርሱ በባላቸው ላይ የሌላቸው ስልጣን እኔ ስላለኝ ቀኑ!! ተሰብስባ በመንገሽገሽ ስሜን የምትጠራ ለብቻዋ ስትሆን ልታገኘኝ ትፈልጋለች።

እኔም ሲሰለቸኝ እሱም ሲታክተው አንድ ቀን ቤቱ ሄድኩ!! ባልገድልህም ሞተሃል ይበቃሃል ልለው ነበርኮ አካሄዴ! ከልቤ በቅቶኝ በቃህ ካሁን በኋላ የምፈልገውን አግኝቻለሁ እና በቀሌ በቅቶኛል!! ትቼሃለሁ!! ልለው ነበርኮ!!

ሞትን ራሱ በዓይኑ ያየ የሚመስል ህፃን እያባበለ ደረስኩ!! በፊት እቤቱ የነበረው ዘመዱ እኛ መረጃ ከያዝንበት በኋላ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲያስገባው ያስገደድኩት እኔ ነበርኩ። የህፃኑን መንሰፍሰፍ ሳይ ዘንግቼው የነበረው ያኔ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ የመለሰው መጣብኝ። ሲያየኝ ከመደንገጡ፣ መቀበጣጠሩ፣ ውክቢያው፣ ህፃኑ እንዲሄድ ማካለቡ ……. የሆነው ነገር ያልገባኝ መስዬ ተረጋጋሁ!! ህፃኑ የጎረቤት ልጅ መሆኑን አረጋግጬ ልጁን አባብዬ ወደቤቱ መልሼ ምንም እንዳልተፈጠረ ወይም እንዳልገባኝ መሰልኩ። እስኪረጋጋ እና ድንጋጤው እስኪለቀው ጠበቅኩት። ስመጣ አስቤው የመጣሁትን ነገርኩት።

«እውነትሽን ነው? በምን አምንሻለሁ? ቪዲዮዎቹን ካልሰጠሽኝ በምን አምናለሁ? የሆነ ቀን ሀሳብሽን ብትቀይሪስ?» አለኝ

«ከቃሌ ውጪ ምንም ማስተማመኛ የለህም!! ግን ሁሉንም ነገር ወስጄብሃለሁ ከዚህ በኋላ ምን ቀረኝ ብዬ ካንተጋ አኩኩሉ እጫወታለሁ? ግን እኔስ በምን አምንሃለሁ? ማረችኝ ብለህ ልትገድለኝ ብትሞክርስ? ማረችኝ ብለህ አሁንም የሌላ ለጋ ህፃን ህይወት እንደማታበላሽ በምን አውቃለሁ?» ስለው ከተቀመጠበት ዘሎ ተነሳ!! የዚህ ቀን ነው እንደአጓጉል አድርጌ ገድዬው እጄን ለፖሊስ የሰጠሁት!!!

* * * * * * * * *

ዳዊት በሩን አልፎ ሲገባ ዋናው የጭፈራ ወለል መሃል ቆሜ ቤቱን እየቃኘሁ ነበር። ሌባ አይኖቹ እየተቁለጨለጩ ወደኋላም ወደፊትም ከማለቱ በፊት ፊቴን ማጥናት ያዘ።

«አለቃ የለብኝም ብለህ በፈለግክ ሰዓት ነውኣ የምትገባ የምትወጣው?» አልኩት ሊገድለኝ የድሮ ፍቅረኛውን እንደላከብኝ ምንም ፍንጭ እንደሌለኝ መስዬ

«የኔፍቅር አትደውይልኝም ነበር? መጥቼ እጠብቅሽ ነበርኮ» ብሎ በመገላገል እየተነፈሰ ሊያቅፈኝ ተጠጋኝ!! አንገቱን አንቄ ወደላይ አንጠለጠልኩት እና እግሩ አየር ላይ ሲወራጭ ፣ የግንባሩ ደምስር ሲፈጥ እያፀዱ የነበሩት ሁለት ሴቶች መሄድም መቆምም ተወዛግቦባቸው ሲያዩኝ ቆይተው አንዷ መጥታ እግሬ ስር ወድቃ ትለምነኝ ጀመር።


የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሀያ ዘጠኝ
(ሜሪ ፈለቀ)

ሰውነቴን ያጋራሁት ወንድ ሊያስገድለኝ ከመሞከሩ በላይ የተሸነፍኩለት ሰው ስልኩን ዘጋግቶ መጥፋቱ ልቤን ሊያበድነው ይገባ ነበር? ክህደት ያውም ለመግደል እስከመሞከር የደረሰ ክህደት ይበልጣል ወይስ መተው? ጭፈራ ቤቱ እስክደርስ በዳዊት ከምናደደው እኩል በጎንጥም እየተናደድኩ ነበር የምነዳው! እንደደረስኩ በሩን በረጋግጄ ስገባ ለወትሮው የሚውልበት ቢሮው ዳዊት የለም። እሱ እስኪመጣ እየጠበቅኩ ቤቱን እየተዘዋወርኩ ማየት ጀመርኩ። ገና ረፋድ ስለሆነ ከሚያፀዱት ሰዎች ውጪ ማንም የለም!! ምንድነው የማደርገው አሁን? መቼም እንደድሮው ስራ ብዬ አልቀጥልበትም! ወይም ቢያንስ የአገልግሎቱን ዝርዝር ማስተካከል ይኖርብኛል!! ከዋናው ጭፈራ ቤት ይልቅ ከሀያ እጥፍ በላይ ገቢ የሚያስገኙት ባለሀብቱ እና ባለስልጣናቱ የሚያዘወትሯቸው በድብቅ የሚከወኑት የሴቶቹ ገላ እና የሚሸጡት አደንዛዥ እፆች ናቸው!! እነዚህ አገልግሎቶች ከተቀነሱ እንደማንኛውም የከተማዋ ጭፈራ ቤቶች ሰካራም የሚራገጥበት ወለል ብቻ ነው የሚቀረው!

እዚህ ቤት ስንቷ ወጣት የሀብታም እና የባለሀብት መዝናኛ ሆናለች!! (ስንቷ ክብሯን ሸጣ ሆዷን ሞልታለች! ወይም እናቷን አሳክማለች።) እዚህ ቤት ስንቱ ወጣት የማይወጣበት ሱስ ውስጥ ተዘፍቋል! (VIP ደንበኛ የሚባሉት ኮኬይን የሚገዙት ናቸው!! ሺሻ እንዲሰራላቸው ያዛሉ ኮኬይን ተደባልቆ ያጨሱታል። ኪሳቸውም ጤናቸውም አብሮ ይጨሳል።) እዚህ ቤት ስንቱ ባለጌ በሚስቱ ላይ ማግጧል (ስንቷ ምስኪን ሚስት እቤቷ ልጆቿን አቅፋ አልቅሳለች) ፣ እዚሁ ቤት ስንቱን ብልግና ማየት ተለማምጄ እንደ ጤንነት ቆጥሬዋለሁ!

ከሙሉሰው ጋር ተጋብተን ትንሽ እንደቆየን ፣ እንግዳ ወይ ጓደኞቹ እቤቱ ሲመጡ እቤቱ ሄጄ እንደሚስት ስብር ቅንጥስ ብሉልኝ ጠጡልኝ ማለት የለመድኩ ጊዜ ፣ እኔ ጠባቂ መሆኔ ቀርቶ በጠባቂ መታጀብ የጀመርኩኝ ጊዜ (አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም! ለምን ጠባቂ እንደሚያጅበውም አይገባኝም!! ታይታ ካልሆነ በቀር) ፣ በቴሌቭዥን እንኳን ለማየት ወራት ከምንጠብቃቸው ባለስልጣናት ጋር የተለያዩ ክስተት እና ድግሶች ላይ የባሌን እጅ ቆልፌ መታየት የለመድኩ ጊዜ ፣ አንቱ የምለው ባለስልጣን ሚስት ባሏን ስታማልኝ የለመድኩ ጊዜ ፣ ራሴን ከእነርሱ እንደአንዳቸው ስቆጥር ያልታየ ድግስ ደግሼ እቤት እንዲታደሙልኝ ማድረግ የጀመርኩ ጊዜ፣ ………. ያኔ ጭፈራ ቤቱን በእኔ ስም እንዲያዞርልኝ አስደረግኩት። (እንደ ዓረፍተነገሩ እጥረት ሂደቱ ቀላል አልነበረም!! ትልቁ የገቢ ምንጩ ነው!! ባለስልጣናቱ የሚመጡት እሱን ስለሚያምኑት ነው!! )

ሌላው ጭንቅላቱን የምዘውርበት ጉድፉ ጭፈራ ቤቱ ነው! ራስምታት የሚቀሰቅስበት ርዕስ ነው።) ስራውን ለመልመድ ትንሽ ወራት ፈጀብኝ ግን ስለምደው ከእርሱ በተሻለ ያዝኩት ምክንያቱም እኔ ሙሉ ሀይሌን ተጠቅሜ እንጂ እንደእሱ ድብብቆሽ እየተጫወትኩ እና በትርፍ ጊዜዬ አልነበረም የምሰራው። ወደአካውንቴ ከሚያስገባልኝ ጠርቀም ያለ ገንዘብ በተጨማሪ ቁጭ ብዬ ራሴን የምሰማበት ጊዜ ስለማይሰጠኝ ወደድኩት።

እቅዴ በምፈልገው መንገድ እየሄደ ያልሞላልኝ ያን እናቴ ስትሞት መሳሪያ ዘቅዝቆ ይዞባት ተራ ሲጠብቅ የነበረ ደመኛዬን መድፋት ነበር። የሚኖረው አዲስአበባ ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ማዕረግም ሀብትም ያለው ሰው አልነበረም!! ከሙሉሰው ጋር ግን በየእለቱ የሚገናኙ ሰዎች ባይሆኑም ቢያንስ የአንዳቸውን ፌስቡክ ፖስት አንዳቸው ሼር የሚደራረጉ ወዳጃሞች ናቸው!! እቅዴ ግልፅ ነበር ለሁለታችንም!! አንድ ቅዳሜ ብሎ ሙሉሰው እንዲቀጥረው፣ ከዛ ሲገናኙ እኔ ባለሁበት ምሳ ልንበላ! (የመጨረሻዋን ምሳ) ስንጨርስ መኪናውን እኔ ልሾፍር ፣ ከዛማ ከከተማ አርቄ ወስጃቸው ትክክለኛ ማንነቴን ነግሬው ሬሳውን ለጅብ ጥዬ መምጣት ነበር እቅዴ!! ይሄን ከ10 ጊዜ በላይ ለሙሉሰው ነግሬዋለሁ!!

የዚህን ወቅት ከእኔ የሚያመልጥበት መንገድ መሞከሩን ተስፋ አልቆረጠበትም ነበር። በእቅዱ መሰረት መጥተን ከምሳ ወጥተን ወደመኪናችን ስንሄድ ሙሉሰው ለሰውየው እኔ ያልሰማሁትን ግን ሲመስለኝ እራሱን እንዲከላከል ወይ ልገድለው እንደሆነ አልያም ማን እንደሆንኩ ብቻ አላውቅም የነገረው መልዕክት አደባባይ ላይ ሽጉጥ አስመዝዞታል!! (ሙሉሰው አስቦበት ያደረገው ነገር መሆኑ በሚያቃጥርበት መልኩ ሰውየው መሳሪያ ስላልታጠቀ የሱን ሽጉጥ መውሰድ የሚችልበት አቋቋም ላይ ኮቱን ገልጦለት ነበር የቆመው) ሀሳቡ እሱ ማድረግ ያልቻለውን ሰውየው እኔን እንዲገድልለት ነበር። ተቀደመ እና ሰውየው እዛው ሞተ። በሰውየው ሞት ከማዘን በእኔ አለመሞት ሲበሳጭ ላየው ግራ ያጋባ ነበር። አደባባይ ላይ ስለነበር የሆነው ሁሉ የሆነው ታሰርኩ!! የዚህን ጊዜ ነው እስር ቤት ከእሙጋ የተዋወቅነው። ነገር የማትፋታ ጋዜጠኛ ነበረች። ያልሆነ ነገር እያነፈነፈች አላፈናፍን ስትላቸው ነው እረፍት እንድታደርግ ያስገቧት!! እሷ እስር ቤቱን ለምዳዋለች። ሲፈቷት ደግሞ ሲያስሯት፣ ደግሞ የሆነ ነገር ትቆፍራለች ደግሞ ይከቷታል። ለመጀመሪያ ጊዜ በህይወቴ ሳይከብደኝ ያወራኋት ፣ ሳልደብቅ ያጫወትኳት ፣ ሳትፈርድብኝ የሰማችኝ ፣ ውርደት እና ክፋቴን እንኳን የተረዳችኝ የመጀመሪያ ጓደኛዬ ሆነች። ከሶስት ወር በኋላ ምርጫ ስላልነበረው ሙሉሰው በሚኬደው ሄዶ እራሱ አስፈታኝ። እሙም ከወራት በኋላ ተፈትታ ከእስር ቤት ውጪ ጓደኝነታችን ቀጥሎ ነበር።


በሁለተኛው ቀን መስማማቱን ላከብኝ!! በአደባባይ ሀገር ጉድ ያሰኘ ሰርግ ደግሶ አገባኝ!! ኪዳን ዩንቨርስቲ ገብቶ ነበር። ማንን እንደማገባ ሲያውቅ ለብዙ ሳምንታት አኩርፎኝ ነበር።

ተጋባን እንጂ አብረን አንኖርም ነበር። በአደባባይ እሱ የሚገኝባቸው ቦታዎች ግን እገኛለሁ። በዚህ አጋጣሚ ከባለስልጣኑ ማህበረሰብ ጋር የመቀላቀል እድል ኖረኝም አይደል? ሳይወድ በግዱ እየገለፈጠ ይላል። ሰዎቹን ማጥናት ተጨማሪ ስራዬ ሆነ። የመጀመሪያ ስራዬ የነበረው ሌሎቹን የአባቴን ገዳዮች ራሱ እንዲነግረኝ ማድረግ ነው። የድሮ አብሮአደጎቹጋ ሁሉ ደውሎ የዛን ቀን አብረውት የነበሩትን አጣራ!! የምፈልገው አንድ እሱን ሁለት እናቴ ስትደፈር መሳሪያ ይዞ ቆሞ የነበረውን ሶስት የአባቴን ሬሳ ተሻግሮት ያለፈውን አራት እኔ በመልክም በስምም የማላውቀው አባቴ ላይ የተኮሰው ሰውዬ!! አባቴ ላይ የተኮሰውን ሰውዬ እራሱ ሙሉሰው እንዲገድለው አደረግኩ! ተጨማሪ ወንጀልም እንደማስረጃ ለመያዝ!! ሰውየው ተብሎ ተቀበረ። የአባቴን ረሳ ተሻግሮት ያለፈው ኮቴውን ብቻ የማስታውሰው ሰውዬ ከልጅነት ቀዬዬ እልፍ ብሎ ያለች ሰፋ ያለች ከተማ ውስጥ ሹም ሆኖ ነበር የሚሰራው!! እሱን ፀጥ ለማድረግ ግርግር አላስፈለገም ነበር።

እናቴ ስትደፈር መሳሪያ ይዞ ቆሞ ሲያያት የነበረውን ሰውዬ ለራሴ ቆጥቤ አስቀመጥኩት!!
እየቆየ ቀን ቀንን ሲተካ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚደነግጥ፣ ወኔው የተሰለበ ድንዙዝ እየሆነ መጣ። ያልሞተም ህያው ያልሆነም ድንዙዝ ሆነ። ባልደረቦቹ ብለው እኔን ይጠይቁኛል። እላለሁ!!

ከአረቡ አለቃዬጋ እዚህጋ ተፋታን!! አንዳንዴ የሆነ ነገር ስፈልግ እደውልለታለሁ። የሚፈልገው ነገር ሲኖር ይደውልልኛል። ሊያስፈልጉኝ የሚችሉ ቁልፍ ሰዎችን መቆለፊያ ተንኮል የጠቆመኝ እሱ ነው!! ወሳኝ ስልጣን ላይ ያሉትን ሰዎች ቆሻሻ መያዝ!! እዚህ ነጥብ ላይ ከእርሱ የተሻለ ለመረጃ ቅርብ የነበርኩት እኔ ነበርኩ። ምክንያቱም የከፍተኛ ባለስልጣን ሚስት ነኛ!! የታዘዘውን ያቀርባል!! የደሳለንኝ ከውጪ ሀገር ባለሃብት ጋር ተሻርኮ የወርቅ ማዕድን የተገኘበትን መሬት ለአበባ ልማት አንድ ሀገር ሄክታር የተፈራረመበትን ከሰዎቹ ጋር የነበረውን ኮንፍራንስ የሚያሳይ ቪዲዮ ጭምር ያቀበለኝ እራሱ ነው!!!

በዚህን ወቅት ነው ብዙ ክፋቶችን ፣ ብዙ ተንኮሎችን ከዛም ዛሬ መረጃ እንዲያቀብለኝ የምጠብቀውን ሰዌን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ያወቅኩት።

**********
ከጎንጥ በፊት ህይወት ያልነበረኝ ይመስል የምሄድበት ወይ የምሰራው ጠፋኝ!! ቀኑ አልገፋ ብሎኝ እሙጋ ሄጄ የተፈጠረውን አንድ በአንድ ነግሪያት ራሱ ጊዜው አልሄደም። ወደከተማ ተመልሼ ደጋግሜ ብደውልለት ስልኩ አይሰራም!! እንዲህ በአንድ ቀን ሳቄንም ተስፋዬንም ይዞብኝ እብስ የሚለው ምን ቀን ነው እንዲህ ልቤን ለራሴ ሳላስቀር የሰጠሁት? ምን ቀን ላይ ዓለሜ በእርሱ ውስጥ የታጠረው? ማልቀስ አማረኝ ከዛ ደግሞ ሽንፈት መሰለኝና ዋጥኩት። ሲመሻሽ ቤተክርስቲያን ገባሁ ግን ግራ ተጋባሁ!! ለእግዚአብሄር ስለወንድ ይፀለያል? ምን አድርግልኝ ተብሎ ነው የሚፀለየው? ተውኩት!! ዝምብዬ ለረዥም ሰዓት ተቀምጬ ወጣሁ!!

ውሸቱን ነበር! ቢወደኝ ኖሮ ሁለት ቀን ሙሉ እንደምጨነቅ እያወቀ ስልኩን አጠፋፍቶ አይጠፋም!! የእኔ መጨነቅ ይቅር እሱስ አልናፍቀውም? አሁንም እየሰለለኝ ይሆን? አዳር ያልሆነ አዳር አድሬ ጠዋት መረጃውን ላከልኝ!! መጀመሪያ ያየሁት የጎንጥን ነው!! ምንም የተለየ ነገር የለውም!! ተጨማሪ መረጃ ብሎ የጨመረው እኔ የማውቀው ነው!! ስልኩን ደወልኩ

«እንዴት ምንም ተጨማሪ ማስረጃ አታገኝም!?»

«አንቺኮ የፈረንጅ ፊልም ላይ እንደምታዪው ካልሆነ የምትይው ነገር አለሽ!! ሜላት ኢትዮጵያ ውስጥ ነን መረጃዎች በሙሉ አይመዘገቡም!! ከዛ ደግሞ ሰውዪሽ ሌላ ምንም ድብቅ ነገር የሌለው ከሆነስ?»

«ይኖረዋል!! ስለማታውቀው ነው ይኖረዋል!»

«የተቀሩትን መረጃዎች ግን አይተሻቸዋል?» አለኝ አይተሻቸው ቢሆን ኖሮ ስለሰውዬሽ አትጨቃጨቂኝም ነበር በሚል ለዛ። ስልኩን ዘግቼ የተቀረውን ፎልደር ከፈትኩ!!

«ይሄ የውሻ ልጅ አውቄዋለሁ!! እገለዋለሁ!!» አልኩ ለራሴ ጮክ ብዬ!! ኮቴን እንደነገሩ ደርቤ መኪና ውስጥ ገብቼ ወደክለቡ ነዳሁት!!

........ አልጨረስንም!! ............


«አላደርገውም!! ወንድ አልወድም ከወንድ ጋር መተኛትም አልወድም!! ሴት መሆኔን እርሳው!! ህፃን ሆኜ ነው እናቴን አይኔ ስር ሲደፍሯት ያየሁት!! እንደማንኛዋም ወጣት ሴት ያለ ስሜት አይደለም ያለኝ!! ሳስበው ራሱ ትዝ የምትለኝ እናቴ ናት!! ይዘገንነኛል። ምንም ነገር ይቀራል እንጂ አላደርገውም!!» ያልኩት እንዲያዝንልኝ ነው? ፣ እንዲረዳኝ ነው? ፣ ልዋጭ ሳይፈልግ ሙሉሰውን የማጠምድበት መላ እንዲዘይድልኝ ነው? ምን አስቤ እንደሆነ አላውቅም!! ከዚህ ሁሉ ውስጥ እሱ በድፍኑ የተሰማው ሌላ ነው።

«ጭራሽ ወንድ አላውቅም እያልሽ ነው?» ከማለቱ ዓይኖቹ ሰውነቴ ላይ በመቀላወጥ ተርመሰመሱ። በጣም እየቀፈፈኝ ተነስቼ እየቆምኩ

«አዎን ምነው?» ስለው ምንም ድንቅፍ ሳይለው ከዛኛው ሰውዬ ጋር የመተኛቱን ሀሳብ እንደቀየረ (ልክ እኔ የተስማማሁ ይመስል) እና በምትኩ ከእርሱ ጋር እንድተኛና ከፈለግኩ የሙሉሰውን ጭንቅላት ከሰውነቱ ቆርጦ እንደሚያመጣልኝ ነገረኝ። ማለት በቃ በምንም የማንግባባ የተለያየ ቋንቋ የምናወራ ሰዎች መሆናችን ሲገባኝ ተነስቼ ወደቤቴ ሄድኩ። ያወራሁትን አልሰማም?

ከዛን ቀን በኋላ በአፉ ምንም ባይናገርም አስተያየቱ ተቀየረ። ዓይኖቹን ሳይነቅል ሲያፈጥብኝ ቆዳዬን ያሳክከኛል። ተስተካክዬ መቆም ያቅተኛል። ከቀናት በኋላ ሆነ ብሎ እዛ ቤት እንድንሄድ አደረገ እና በሴቶቹ ፋንታ ሙሉሰው እንዲመጣ ጠየቀ። ሙሉሰው ከአንድ ጠባቂው ጋር መጥቶ በወዳጅ ሰላምታ ማሽቃበጥ ያበዛበት ዓይነት ሰላም ብሎት ተቀመጠ። ዘለሽ እነቂው እነቂው የሚለኝን ስሜቴን ተቆጣጥሬ ቆምኩ። ሆነ ብሎ እሱ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑን ሊያሳያኝ ያደረገው ነገር እንደሆነ ያስታውቅበታል። ቢገጣጠም የማይቀና አማርኛ እያወራ በአይኑ እኔን ያጠናል። ሙሉሰው ወጥቶ ሲሄድ «የዚን ያህል ቀላል ነበር።» ብቻ ብሎ ዝም አለ።

ለሳምንታት በራሴ መንገድ መረጃ ላገኝ ዳከርኩ። ሌላው ቀርቶ ጭፈራ ቤቱ እንኳን ድንገት የሆነ ሰዓት ነው እንጂ የሚመጣው ማንም ሰው የሚመጣበትን ሰዓት አያውቅም። ድንገት እድለኛ ሆኜ እንኳን ባገኘው ጠባቂ አለው!! ከዛ ግን ያ ሰይጣን ሰውዬ ያቀበለኝ ሀሳብ ውስጤ ቀስ በቀስ ማደጉን ያወቅኩት። ባገኘሁት አጋጣሚ ልገድለው አለመፈለጌ ገባኝ!! ቁጭ ብዬ አስቤ አስቤ ማሰሪያዬ የሚል ሆነ። ሊሆን የማይችል ቅዠት ይመስለኛል ግን ማሰብ ማቆም አቃተኝ። ግን እንዴት? አላውቅም!!!

«እሺ!» አልኩኝ ጠብ የሚል ነገር ከሌለው ብዙ ልፋት በኋላ!! «ነገር ግን በቅድሚያ የማገኘውን ነገር በዝርዝር ማወቅ እፈልጋለሁ!»

ክብሬን ሸጬ በቀል ሸመትኩበት!!! ካሰብኩት በላይ ነገሮች ቀለሉልኝና የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ ኖረኝ። እኔ ግን ጎደልኩ!! ለቀናት እራሴው እሺ ብዬ ተስማምቼ የተኛሁ ሳይሆን እንደእናቴ የተደፈርኩ አይነት ስሜት ተሰማኝ። በእንባ የማላጥበው ዓይነት መቆሸሽ ሆነብኝ!! ያለው ይሄን መሰለኝ። የገዛ ሰውነቴ የሆነ ቦታ አስቀምጬው መንቀሳቀስ ብችል አሰኘኝ። ይሄን የውስጤን ጩኸት ላለመስማት በነጋ በጠባ ሴራ መጎንጎን ሆነ ስራዬ!! ከረጠቡ አይቀር መበስበስ ነው በክፋት ተጠመቅኩ። ተንኮል አስራለሁ እፈታለሁ!! ደጋግሜ ረከስኩ!! ደጋግሜ ራሴን ረሳሁ።

ሙሉሰውን እንዲወደኝ አድርጌው አይደለም ያገባሁት!! እጁ ባይያዝበት የመጀመሪያ መግደል የሚፈልገው ሰው እኔ ነኝ!! እንዲያገባኝ አስገድጄው እንጂ!! አብዛኛው ባለስልጣን አንድ የሆነ ድክመት ወይ አንድ የሆነ ቆሻሻ ይኖረዋል። ወይ በሚስቱ ላይ ሲማግጥ ወይ በሃገር ላይ ሲማግጥ ብቻ የሆነ መረጃ ይገኝበታል። ሙሉሰው አስለፋን!! ጭራሽ ምንም ማግኘት ከበደ። በዘመድ አዝማዱ ስም ጭምር የያዛቸው ንብረቶች እና ከሀገር የዘረፋቸው ሀብቶች ማስፈራሪያ ሊሆን ቢችልም በቀላሉ በገንዘብ ሃይል መረጃዎቹን ድራሻቸውን ማስጠፋት ይችላል። የራቁት ጭፈራ ቤቱ ውስጥ በጓሮ ተሹለኩልከው የሚገቡትን ባለስልጣናት በቀላሉ በሴቶቹ ማጥመድ ይቻላል። እሱ ግን ከሴት ጋርም በፍፁም ምንም አይነት ንኪኪ የሌለው ሆኖ ተገኘ። ምናልባት ቤቱ የሱ ስለሆነ ሰራተኞቹ ባሉበት መልከስከስ ስለማይፈልግ ነው ብለን አስበን። (በሃሳቡ ተስማማሁ እንጂ ሀሳቡን የሚያመነጨው አለቃዬ ነው) እቤቱ የምትሰራዋን ሰራተኛ ያዝናት። ጭራሽ እንደውም በበጎ አድራጎት የሚታወቅ ከላዩ ላይ ዝንቡን እሽ ብል ግር ብሎ የሚወጣለት ህዝብ ያሰለፈ ሰው ነው። እጅ ወደመስጠቱ ስንቃረብ ከስንት መላምትና ልፋት በኋላ ማንም ሰውጋ የማይሰማ ማንም ሰው የማይገምተው ብልግና እቤቱ ሸሽጎ እንደሚኖር ደረስንበት። ሊያሳድገው ከገጠር ያመጣው እቤት አብሮት የሚኖር ዘመድ አለው። ደፍሮት አሁንም እያስገደደው ያባልገዋል። ከዚህ ሰውዬጋ መዋል ከጀመርኩ በኋላ ብዙ ለጆሮ የሚሰቀጥጡ ብልግናዎች ሰምቻለሁኮ ይሄ ግን ወደር የማይገኝለት ነበር። ከብዙ ሙከራ በኋላ ብልግናውን ቀረፅነው!! ይሄ ነው እጄ ላይ የጣለው!!

ለዘመናት የናፈቅኩት ቀን ተከሰተ እና ፊት ለፊት ተገናኘን። ውርደቱ እጄ ላይ እንዳለ ስነግረው ፊቱን ማየት ለቀናት ሲያቅበጠብጠኝ ነበር። እዛው የራቁት ጭፈራ ቤቱ ከአለቃዬ ጋር ሄደን እሱ ሲመጣ እንዲጎበኘው መልዕክት አስቀመጠ። እዚህ ጋር የማይገባኝ አለቃዬ በእኔ በቀል የሚሰክረው ጉዱ ነበር። ልክ መጥቶ እንደተቀመጠ።

«ሜላት እባላለሁ! ወይም ደግሞ አባቴ ባወጣልኝ ስም አምሳል!» አልኩት እና የአባቴን ማንነት ቀዬዬን እና የዛን ቀን ተፈጥሮ የነበረውን ሳላዛንፍ ነገርኩት። ምንም ታክል የፀፀት ስሜት ሽው ባላለው አነጋገር

«ጦርነት ነው የገጠምነው!! ልንስማችሁ አልነበረም የመጣነው!! እንኳን አንቺ ማን እንደሆንሽ አባትሽንም አላስታውሰውም!» ሲለኝ እሱን ለመበቀል የሄድኩት መንገድ ልክ ነው ብዬ አመንኩ። ቪዲዮውን ላኩለት እና ምንም ከማሰቡ በፊት አንድ ቅጂ አለቃዬ ጋር ፣ ሌላ ቅጂ ተቀባብሎ ሌላ ሰው ጋር መኖሩን ነገርኩት!! አንድ ነገር ሊያደርገኝ ቢያስብ መረጃውን ከመውጣት እንደማያግደው ሲያውቅ ተሰበሰበ።

«እሺ ምንድነው የምትፈልጊው? ምን ያህል?» ብሎ ራሴን የሸጥኩበትን በቀሌን በገንዘብ ተመነብኝ

«ገንዘብ አይደለም የምፈልገው!! እንድታገባኝ ነው የምፈልገው!!» ስለው በቁሙ ቃዠ።

«ቀልድ ነው የያዝሽው? ጤነኛ ነሽ?» ሲል አለቃዬ በወልካፋ አማርኛ ቅልብ አድርጎ
«ውነቷን ነው! ቀልድ የለም!» አለው።
«ምን አስበሽ ነው?»

«አታስብ ጠዋት ከእንቅልፋችን አንድ ላይ ተነስተን ፣ ደህና አደርሽ ፣ ደህና አደርክ የምንባባል፣ ቁርስ አንድ ላይ የምንበላ ሰዎች አንሆንም!! አንድ ቤትም አንኖርም! ሚዲያዎች የሚዘግቡት ሰርግ ደግሰህ እንጋባለን!! አብረን አንኖርም እንጂ የትም ቦታ ስትሄድ እጄን እጅህ ውስጥ ሻጥ አድርገህ ትሄዳለህ!! ከዛ የቀረውን እያኖርን እንመካከራለን!! ውሳኔህን እንድታሳውኝ 2 ቀን እሰጥሃለሁ። ያው አማራጭ የምትለውን በሙሉ አይተህ እንደማያዋጣ ትደርስበታለህ!!» ተወራጭቶ ወጣ!! እንደምገምተው አማራጭ ሊሆን ይችላል ብሎ የሚያስበውን ሁሉ አስቧል። ጉዱን ለማንም እንደማያዋየው ግልፅ ነው!!

ቪዲዮው ቢወጣ በመድፈር ወንጀል ብቻ አይደለም የሚከሰሰው በፍቅር ከፍ አድርጎ የሰቀለው ራሱ ህዝብ በድንጋይ ወግሮ እንደሚገድለው ያውቃል። ሰው ገደለ፣ ሀገር ከዳ ፣ ሰረቀ …… ምንም ቢባል ኸረ ምንም ጥፋት ቢሆን ይታለፍለታል። ይሄን ግን አያልፉለትም።


#የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል.......( ክፍል ሀያ ስምንት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«ታውቂዋለሽ እንዴ? ምነው?» ሲለኝ
ማለት ብፈልግም …. እንኳን ከዚህም ከዛም ቃርሜ እና በ6 ወር ከስልጠናው ጋር ተምሬ የምኮላተፍበት አረብኛ ቀርቶ የራሴው አማርኛ እንኳን የህመሜን ያህል ገላጭ ቃል የለውም።

«ክፉ ሰው ነው!» ብዬ ብቻ አለፍኩት። ከዛን በኋላ ግን ለሰዓታት መረጋጋት እስኪያቅተኝ ሰውነቴ ምሬት ተፋ። ፊቴ እስኪያስታውቅበት ድረስ ያለፈው ሁሉ መጠቃት፣ እልህ ፣ ቁጣ ……. እንደአዲስ በደምስሬ ከደሜ ጋር ተዘዋወረ። እቤት ደርሰን መውጫ ሰዓቴ ደርሶ ልወጣ ስል ሌሎቹን ጠባቂዎች አስወጥቶ ብቻዬን ሊያወራኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። ከትዕዛዝ ውጪ ምንም አይነት ነገር አውርተን ስለማናውቅ ግር እያለኝ ተቀመጥኩ።

«ምን አድርጎሽ ነው? የሞት መልዓክ ያየሽኮ ነው የመሰልሽው!» አለኝ

«በልጅነቴ ወላጆቼን ያሳጣኝ ሰው ነው!» አልኩት በደፈናው።

«ጥላቻ ከፍቅር ያይላል። በቀልም ከወሲብ እርካታ በላይ ፍሰሀን ያጎናፅፋል!» አለ ለእኔ ይሁን ለራሱ የተናገረው መለየት በሚቸግር አነጋገር። ቀጠል አድርጎ «ድፍረትሽ ያስታውቃል። ሞትን እስካለመፍራት የሚደፍረው ውስጡ የሚገፋው ጥላቻ እና ያረገዘው በቀል ያለው ሰው ነው። ፍቅር እና ተስፋ ልቡን የሞላው ሰው ፈሪ ነው። ነገን ይፈራል፣ ማጣትን ይፈራል ፣ ሞትን ይፈራል!! በልምድ ብቻ ያገኘሽው ድፍረት እንዳልሆነ ያስታውቃል።» ያለው በትክክል የገባኝ ከብዙ ጊዜ በኋላ በቀልም ጥላቻም ገፍትረው ልቆም ያላቀድኩበት ውሳኔ ላይ ሲያቆሙኝ ነው!! ይሄን አጀንዳ አንስቼ አይደለም ከሱ ጋር ከኪዳን ጋር እንኳን የምጋራው ባላመሆኑ ዝም አልኩ።

«ብዙ ሰው ባያውቅም ሰውየው የቤቱ ባለቤት ነው! ከዚህ በኋላም ተደጋጋሚ ጊዜ ልትገጣጠሚ ስለምትችዪ እንደፕሮፌሽናል ጠባቂ የግል ስሜትሽን ውጠሽ ስርዓት ባለው መልኩ ለመታየት ሞክሪ!!» አለኝ እንደትዕዛዝ ነገር! ከዛ ሁሉ ትኩረት የሰጠሁት የሚለውን ነው። ያውቀዋል ማለት ነው!!?? « ምን ልታደርጊው ነው የምታስቢው?» ሲለኝ ለምን ወይም እንዴት ይሄን ጥያቄ እንደጠየቀኝ አላሰብኩትም። «እገድለዋለሁ!» ያልኩት ጮክ ብዬ መሆኑን ከእርሱ እኩል ነው የሰማሁት። የሆነ የፌዝ ነገር (ቀሽም! የሚል ዓይነት ነገር) ሳቅ ብሎ

«አትቸኩዪ! በቀል የሚጣፍጠው ሰውየው ሲሰቃይ የማየት እድል ሲኖርሽ ነው!! ከገደልሽውማ ገላገልሽው! ስንት ዓመታት ተሰቃይተሻል? ስንት ዓመታት ባሰብሽው ቁጥር ህመም ተሰምቶሻል? ለዓመታት የተሰቃየሽው ስቃይ በሱ ቅፅበታዊ ሞት ይካካሳል? ይድናል? ገደልሽው! ከዛስ? እድሜ ልክሽን እስር ቤት ትማቅቂያለሽ!! በህይወት እያለም ደስታሽን ቀምቶሽ በሞቱም ደስታሽን ቀምቶሽ! ይሄ ፍትህ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ?» ቃላቶቹን ረጋ ብሎ የሚያወራበት ለዛ ልቡ ቀዝቃዛ እና ክፉ መሆኑን ያሳብቅበታል። ያልገባኝ ለምን እኔን እንደሚያቀሳስረኝ ነው!! ሲያወራው ግን እውነትም በቀል እሱ አፍ ላይ ትጣፍጣለች። በቀልን ሳስብ የማስብ የነበረው መግደልን እንጂ በቀል እንዲህ ተሽሞንሙና እና ረቅቃ አስቤያት አላውቅም!!! ሲያዩትኮ ሰውየው ፍፁም ትሁት እና ሳቂታ፣ ካገኘው ሁሉ ጋር ጨዋታ ወዳድ ነው የሚመስለው። ከሴት ጋር ተያይዞ ካለው ስድነቱ ውጪ እቤቱ እንግዳ ጠፍቶ የማያውቅ ቸር ነው ብዬ ነበርኮ የማስበው!

«ለድፍረቴ ይቅርታ ይደረግልኝና አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ? ቤተሰብህን ፣ ህይወትህን ፣ ቤትህን ፣ ልጅነትህን የቀማህን ሰው ምን ታደርገዋለህ? በድጋሚ ስለድፍረቴ ይቅርታ!»

« ድክመቱን ማግኘት ነው!! በዛ ድክመቱ ገብተሽ የሚወደውን ነገር አንድ በአንድ መንጠቅ! ልክ በቁሙ እያለ መጀመሪያ ተራ በተራ ጣቶቹን፣ ቁስሉ ደርቆ ተሻለኝ ሲል ክንዱን ፣ ቆየት ብለሽ ሙሉ እጁን ፣ ከዛ የሌላኛው እጁን ጣቶች ፣ ክንድ ፣ ሙሉ እጅ ….. እያደረግሽ አካሉን እንደመክተፍ!! ግደዪኝ ብሎ እስኪለምንሽ ወይም ራሱን ለመግደል እስኪወስን ያለውን ማሳጣት!» ሲል የተናገረውን እያንዳንዷን ድርጊት ተግብሮት እንደሚያውቅ ነው። በትክክል እንዲገባኝ የፈለገ ይመስል ወሬውን በምልክት አጅቦ ነው አስረግጦ ያስረዳኝ። አወራሩ የጭካኔ ጥግ የሆነ ወሬ እያወራ ሳይሆን የልደት ኬክ ስለመቁረስ ዓይነት ያለ ጨዋታ እንደሚያወራ ቃላቶቹን በፍቅር ነው ምላሱ ላይ የሚያሽሞነሙናቸው። ለሆነ ቅፅበት አጠገቡ መሆኔን ሁሉ ፈራሁት!!! መልሼ ፍርሃቴ ራሴኑ አሳቀኝ እንጂ! እኔ ከእርሱ በምን ተሽዬ ነው? በተናገረው ነገር ተስቤ በቀልን እሱ በገለፀው መንገድ ጭንቅላቴ ውስጥ ላጣጥመው እኮ ሞክሬያለሁ።

«እርዳታዬን ከፈለግሽ መጠየቅ ብቻ ነው የሚጠበቅብሽ!! ስለሰውዬው ማወቅ የምትፈልጊው ነገር ካለ የሀገሩ ዜጋ አለመሆኔን አትዪ ሁሉም ቦታ አይን አለኝ፣ የሚያስፈልግሽ ገንዘብ ወይም ፋሲሊቲ ምንም ቢሆን !!» አለኝ።

«እውነትህን ነው? ለምን ልትረዳኝ ፈለግክ?» ጥርጣሬም መገረምም ጨረፍ አድርጎኝ የጠየቅኩት ጥያቄ ነበር።

«ፍትህ ሲዛባ ደስ አይለኝም!! የተፃፉ ህጎች ለሁሉም ሰው እኩል ፍትህ አይሰጡም!! ጉልበተኞችን ያሾልካሉ።» ሲለኝ የከተማው ብልጣብልጥነት ብዙም ያልዘለቀው ልቤ አመነው። ወይም ድክመቴን አግኝቶብኛል። አመስግኜው ስለሰውየው ሊጠቅመኝ የሚችል መረጃ ምንም ቢሆን እርዳታውን እንደምፈልግ ነግሬው አቋራጭ መንገድ በማግኘቴ ተደስቼ ሳልጨርስ በምትኩ ከእኔ የሚፈልገው ነገር መኖሩን ነገረኝ። በጅልነቴ ብግን ያልኩት ሰውየው እውነተኛ ማነነቱን በግልፅ አሳይቶኝ እንኳን የሚቀጥለው ጥያቄ ከደግ ልብ የመነጨ እንደሚሆን መጠበቄ!!

ልክ ልከኛ ነገር ያወራ ይመስል፣ ልክ ከእዛጋ ያን ወረቀት አቀብዪኝ እንደማለት ነገር ቀለል አድርጎ …… አንድ ከየትኛው አረብ ሀገር እንደሆነ የማላውቀው አዘውትሮ እሱጋ የሚመጣ ሰውዬ ስለሚቋምጥልኝ ከእርሱ ጋር በመተኛት ውለታውን እንድከፍለው ነገረኝ። በተጨማሪ ሰውየው የምፈልገውን የሚያደርግልኝ ሀብታም መሆኑን አከለበት። ለሆነ ደቂቃ ምንም የምለው ቃል ራሱ ቸግሮኝ ዝም ብዬ እንደሆነ መዓት ሳየው ቆየሁ። ትንሽ ቆይቼ ግን ከአፌ ከወጣ በኋላ የፀፀተኝን ወሬ አወራሁ!!


ሁላችንም የተቀላቀሉንን እንግዶች ችላ ብለን የተቀረነውን ዙሪያ ገባችንን በንቃት እየቃኘን ትንሽ እንደሄድን ባልታሰበ ቅፅበት ፍጥንጥን ያለ ፊልም የሚመስል ክስተት ሆነ። የሰማይ ስባሪዎቹ አንደኛው የኛን ሰውዬ ሌሎቹ ሁለቱን ወንዶች ጨምሮ ምናልባት ፈጣን ናቸው ያሏቸውን ጠባቂዎች ያዙ። የሚያወሩት አረብኛ ስለሆነ ጥቁሩ ባለሀብት የሚያወራው ባይገባኝም የሆነ የፈለገውን ነገር በጣም በንቀት እያየው ለኛ ሰውዬ እያስረዳው በችኮላ እየነገረው እያለ አውርዳቸው የነበረችው መኪና ዞራ አጠገባችን መጣች እና እንዲገባ ገፈታተሩት። መሳሪያ ያልተደገነብን እና አንገታችን ያልተቆለፈብን ሁላችንምኮ ሽጉጣችንን መዘናል። ግን መተኮስ እንዳንችል አለቃችን ተይዟል። በፍጥነት ለማሰብ ሞከርኩ። ከሰውየው ሁለት እርምጃ የማይሞላ እርቀት ላይ ደርሻለሁ። ግን ከፌቴ በቁመቱ ሙሉ የሚከልለኝ ሰውዬ የፊት ጠባቂዋን አንገት ይዞ ሽጉጡን ጭንቅላቷ ላይ ይዞታል። ምንም ያህል ብፈጥን አደጋ ያለው እርምጃ እንደምወስድ ቢገባኝም ፍርሃት አልተሰማኝም። እንቅስቃሴዬን ትኩረት የሚስብ ዓይነት ሳላደርግ ሽጉጤን የእኛን አለቃ ለያዘው ሰውዬ ግንባር አደረግኩ። ከጀርባ ከተያዘው ወንድ ጠባቂ ጋር ተያየን። እርምጃ ልወስድ እንደሆነ ገብቶታል። አባዬ ፣ አጎቴ ፣ እዚህ ስራ ልቀጠር ስል ደግሞ ቋንቋቸው ሳይገባኝ የተደናቆርኳቸው የሰውየው ሰዎች …… ያስተማሩኝን ኢላማ የምተገብርበት ሰዓት ሆነ። አልፈራሁም!! ምናልባት ብስት ሊፈጠር የሚችለውን ስለማላውቅ ወይም የመጀመሪያዬ ስለሆነ አላውቅም! ምንም ፍርሃት አልተሰማኝም። አለማወቅ አንዳንዴ ጥሩ ድፍረት ነው። ከኋላ የነበረው ልተኩስ እንደሆነ የገባው ጠባቂ ወከባ እና ሁከት ፈጥሮ ትኩረት ሲቀንስልኝ የሰውየውን ግንባር አገኘሁት እና በፍጥነት ከፊቴ የነበረው እግር ስር ዝቅ ብዬ በክንዴ ጉልበቱን ገጨሁት። ከጀርባ የነበረው የእኔን እርምጃ ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር አለቃችንን መሬት ላይ ጥሎት እላዩ ላይ ወድቆ ከደነው። ሁለት ከኛ ወገን (እኔን ጨምሮ) ተመትቶ ቆስሎ አንድ ከእነርሱ ወገን ሞቶ ሁለት ቆስሎ አካባቢው በፖሊስ እና በህዝብ ግርግር ተዋክቦ እነሱ ሬሳቸውን ትተው በመጡበት መኪና አመለጡ። የተመታ ክንዴን ታክሜ ወደስራ ስመለስ ከዛን ቀን በኋላ የሰውየው የጎን ጠባቂ ሆንኩ!!

በሰውየው ዙሪያ ከገንዘብ ነክ ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ብልግናዎች እንደሚከወኑ ያወቅኩትም በጎን መቆም ስጀምር ነው። አዲስአበባ ሲመጣ ሳሎኑ መጂልሱ ላይ ተቀምጦ የከተማው እምቡጥ እምቡጥ የመሳሰሉ ሴቶች እየመጡ እንደሚታረድ በግ ሽንጥና ዳሌያቸውን እያገላበጠ ፈትሾ ይመርጥ እና የወደዳትን ለራሱ የተቀሩትን እቤቱ መጥተው አብረውት ሲቅሙ እና ሲያጨሱ ለሚቆዩት እንግዶቹ ልክ ብሎ እንደሚያቀርበው ምግቡ ያቀርባቸዋል። መጀመሪያ ቀን ነውርነቱ አሳፈረኝ። የሴቶቹ ምንም የማፈር ስሜት ፊታቸው ያለመኖር እኔን መሬት ተሰንጥቃ እንድትውጠኝ እስከመመኘት አሳፈረኝ። ሲቆይ ልምድ ነው አላልኳችሁም? ለመድኩት። ሴቶቹ አንዱ ባለሃብት ላይ አይኔ እያየ ለሁለት የማይኮን ሲሆኑ አይኔን ሳላርገበግብ መቆም ለመድኩበት። ከዛ በኋላ እይዘዋለሁ ብዬ የማላስበውን ያህል ገንዘብ እየኖረኝ መጣ። ከሰውየው ጋር በየሀገሩ መዞርም ለመድኩ። በዞርንበት በተለይ እግሊዝኛ የሚነገርበት ሀገር ስሄድ ያለመማሬ የምር አስቆጨኝ እና እንግሊዝኛ ለመማር እቤቴ አስተማሪ ቀጠርኩ። ከዓመት በኋላ እየተመላለሰ ሰውየው ካስተማረኝ እንግሊዝኛ በላይ በልምድ በዙሪያዬ እነርሱ የሚያወሩት አረብኛ ይገባኝ እና መናገር መሞከር ጀመርኩ።

የጎን ክንፍ አጃቢ ከሆንኩ ከዓመት በኋላ የሰውየው የቅርብ ጠባቂዎች በሙሉ ሰልጥነውት እኔ ያልሰለጠንኩት ስልጠና መኖሩ ተነግሮኝ የመን ለስልጠና ሄድኩ። በየጊዜው ለቀናት ከኪዳን መራቁን እየተላመድነው መጥተናል። እስከአሁንም ቦታው የግለሰብ ይሁን የመንግስት በማይገባኝ ካምፕ በመሰለ ቦታ ስልጠና ለ6 ወር ወሰድኩ። አብዛኛው ስልጠና የወታደር ስልጠና ምን እንደሚመስል ባላውቅም እንደዛ ዓይነት ይመስለኛል። በየቀኑ ፈሴ ጢጥ እስኪል ከብዙ ወንዶች እና በጣት ቁጥር ከማይሞሉ ሴቶች ጋር የሚሰጡኝን የቴክኒክ እና የጉልበት ስልጠናዎች መውሰድ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ለስለላ የሚያሰለጭኑኝ እስኪመስለኝ በሰዓቱ በስርዓቱ የማይገቡኝን የጭንቅላት ስልጠናዎች እና ፈተናዎች ወሰድኩ።

ከስድስት ወር በኋላ ስመለስ የሰውየው ቀኝ እጅ ከመሆኔ በተጨማሪ የሚከፈለኝ ደሞዝ በህልሜ እንኳን አስቤው የማላውቀው ነበር። በዛ ላይ ጭኔን የሚያሳዩትን ብጣቂ ሚኒዎች ያለመልበስ መብት ተሰጠኝ እና በምትኩ ሙሉ ሱፍ በሱሪ መልበስ ጀመርኩ። በገንዘቤ ሳይሆን በሰውየው ገንዘብ መኪና ተገዛልኝ እና የመኪና ባለቤት ሆንኩ። አንድ ቀን እስከዛ ቀን ድረስ ሲሄድ ያልገጠመኝ ቤት አጅቤው ሄድኩ (አሁን የእኔ የሆነው የራቁት ጭፈራ ቤት) ከፊት የሚታየውን የአዘቦት ጭፈራ ቤት የሚመስል በሙዚቃ አንድ ገበያ ህዝብ የሚውረገረግበትን አዳራሽ የሚያክል ሳሎን አልፈን ወደውስጥ በሚስጥር በር ዘለቅን። ኮሪደሩ ላይ የተቀበለን አስተናጋጅ ወደተዘጋ ክፍል ወሰደን። አራት የምንሆን ሴት ጠባቂዎቹ አጅበነው ስንቆም ክፍሉ ከእርሱ ውጪ ማንም አልነበረበትም። ተራ በተራ ሴቶቹ እየገቡ የቆመው ፖል ላይ ሲጥመለመሉ ሲያስቀይር ሌላ ስትመጣ ሲያስቀይር ሌላ ስትመጣ ቆይቶ ሁለቱን መረጠ እና ፓንት ለማለት የሚያስቸግር ክር ነገር ነገራቸው ላይ ጣል አድርገው፣ የጡታቸውን ጫፍ ብቻ የሚሸፍን ጨርቅ ጩታቸው ላይ አገልድመው ይቀነጣጠሱ ገቡ። ለምጄው የለ? እየቆየ የለበሱትን እንዲያወልቁለት አዘዘ እና ረብጣ ብር አስቀመጠ። እኛን ዞር ብለው ሳያዩ እርቃናቸውን ሆኑለት። ……

ከፖላቸው ወርደው አጓጉል ቦታ እየነካኩት ሰውየው ላይ መደነስ ጀመሩ!! እኔ ብቻ ስቀር ሌሎቹን ጠባቂዎቹን እንዲወጡ አድርጎ እንኳን በእውኔ በፊልም ባየው የሚያስመልሰኝ የሚመስለኝን ብልግና ሴቶቹን አስደረጋቸው። የዛን ቀን እየወጣሁ በሴቶቹ ፍርድ አይደለም የፈረድኩባቸው እያልኩ አሰብኩ። የሰውየውን ምናምን ባደረጉበት አፋቸው ምግብ ይበሉበታል? እላለሁ።

እዛ ቤት መመላለስ ያዘወትር ጀመር። አንድ ቀን ታዲያ ይገጥመኛል ብዬ በምንም አጋጣሚ ያላሰብኩት ሰው ገጠመኝ። አለቃዬን አጅቤ ከክፍሉ ስወጣ ሙሉሰው በጋርድ ታጅቦ ወደሌላ ክፍል ሲገባ አየሁት። ደንዝዤ ቆምኩ። ሰውየው እንኳን እስኪያስተውለኝ ተደነባበርኩ። እሱ አላየኝም። ምናልባት ቢያየኝም አያውቀኝም። እኔ ግን ደንግጬ እግሬ ከቆመበት አልንቀሳቀስ አለኝ!!

.......... አልጨረስንም ........


አዲስ አበባ እንደአደግኩበት ክፍለሀገር በጉልበቴ ብቻ የምከበርበት ሀገር አለመሆኑን ከረፈደም ቢሆን አውቄያለሁ። ከኛ ሰፈር የአባቴ ገዳዮች ሰፈር እኩዮቼን አጅቤ ሄጄ ጠላቴን አደባይቼ ልምጣ ብዬ እንደማቅደው የስልጣን ሽልማታቸውን የሚያጣጥሙ ያባቴን ገዳዮች በር አንኳኩቼ እንደማልገድላቸው አውቄያለሁ። ሁሉም ነገር ከባድ እንደሆነ ያወቅኩት እንኳን እኔ ቀርቶ ገጠር ሲመጣ እያለ የሚበጠረቀው የካራቴ አሰልጣኛችን እንኳን የሚንስትሩ ቤት ሰማይ ይሁን ምድር ካለማወቁ ቤተሰቦቹ እንኳን ያለምክንያት የማያገኙት ሩቅ ሰው መሆኑን ስረዳ ነው። ከሀገሬ ስወጣ እገድላቸዋለሁ ብዬ ስም ዝርዝራቸውን የፃፍኳቸው እና ስማቸውን ማወቅ ሳልችል በምልክት ጭንቅላቴ ውስጥ የመዘገብኳቸው ሰዎች ዋና ዋናዎቹ እዚሁ አዲስአበባ ተሿሹመው ሲኖሩ የተቀሩት የት እንዳሉ አላውቅም!!!! ብቻ ማናቸውንም ማግኘት ትንሽዬ ማስታወሻዬ ላይ ስማቸውን ፅፎ እንደመያዝ ቀላል እንዳልሆነ ገብቶኛል። በየቀኑ ግን ወደቤቴ ስገባ ያቺን በመተሻሸት ብዛት ቀለሟን የቀየረች ማስታወሻ ደብተር ገልጬ በኑሮ ደፋ ቀና ጠላቶቼን እንዳልረሳ አስታውስባታለሁ። ቀኑ እንጂ የሚረዝመው እስከእድሜዬ ማለቂያ ድረስም ቢዘገይ እነርሱን ሳላገኝ እንደማልሞት ለራሴ በየቀኑ እነግረዋለሁ።

ህልሜን ለማሳካት (በቀልን ህልም ማለቴ አይግረማችሁ!! ያው ለማሳካት እስከምንም ጥግ የምትደክሙለት ዓላማ መግደልም ቢሆን ህልም አይደል?) አዲስአበባ ላይ ጎበዝ አላሚ ተኳሽ እና እንደንፋስ የፈጠንኩ ካራቲስት መሆን ብቻውን እንደማይበቃኝ አውቄያለሁ። አዲስ አበባ ላይ ከምንም ነገር በላይ እነዚህ ሶስቱ ወይም ከሶስቱ አንዱ ያለው አቅም አለው። ሀብት ፤ ስልጣን እና ዝና!! ከሶስቱ በጥቂቱም ቢሆን ተስፋ ያለኝ ሀብት የሚለው ላይ ቢሆንም እንዴት? የሚለውን ግን እስክደርስበት ድረስ እቅዱ አልነበረኝም። ምንም ዓይነት የቅብጠት ምኞት ስላልነበረኝ የማገኘውን ገንዘብ ለኪዳን ያስፈልገዋል የምለውን ነገር ከማሟላት የተረፈኝን አስቀምጣለሁ። ጎን ለጎን መኪና መንዳት መማር እና ከሰባተኛ ክፍል የተውኩት ትምህርት አማርኛ ከማንበብ እና መሰረታዊ የሂሳብ ስሌት ከመስራት የማያሻግር በመሆኑ ቢያንስ መሰረታዊ የቴክኖሎጂ ትሩፋቶችን መጠቀም የሚያስችለኝ እውቀት ለመገብየት ሰውየውን ተከትዬ ሆቴል እና ጭፈራ ቤት ደጅ በምገተርባቸው ቀናት እየቀረሁም ቢሆን የማታ ትምህርት ቤት ገባሁ። ውሉ ሲጠፋብኝ ኪዳን እቤት እቤት ያስጠናኛል።

ለዓመት ከ6 ወር ደላላው እንዳለው ሰውየው በአጀብ ከመሄድ ልክፍቱ ውጪ ሀገር ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድም አይደለም ሊያጠቃው ጮክ ብሎ የተናገረው ሰው አልሰማሁም። ከዚህ በኋላ የሆነ ቀን ዱባይ ትልቅ ስብሰባ መኖሩን እና እዛ ሲሄድ ሀብትና ጉልበቱን ማሳየት ስለሚፈልግ ሁላችንንም አስከትሎ እንደሚሄድ ተነገረን። ፓስፖርት እንኳን ስላልነበረኝ በሰውየው ጉዳይ አስፈፃሚዎች በኩል ያለቀጠሮ ፓስፖርቴ አልቆ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰውየው የግል አውሮፕላን ተሳፈርኩ። ይሄን ጊዜ የግድ ቀሚስ መልበስ እንዳለብኝ ሲነገረኝ ከሀገር የመውጣት ጉጉቱ ስለበለጠብኝ ተስማማሁ!! ለመጀመሪያ ጊዜ ለረዥም ቀናት ከኪዳን ተለይቼ የቆየሁበት ጊዜ ስለነበር ትቼው መሄዱ ሀሳቤን ለመቀየር እስኪፈታተነኝ ከብዶኝ ነበር። የሚከፈለኝ ብር ብዙ ማድረግ የሚያስችለኝ በመሆኑ ከኪዳን ጋር ተነጋግረን እቤት የምታግዘው ሰራተኛ ቀጥሬለት ሄድኩኝ። እስከዛ ሰዓት ድረስ ሰውየው ምን ይስራ፣ ምን ይኑረው፣ ለምን ኢትዮጵያ ይኖራል? የማወቅ ፍላጎት ኖሮኝም አያውቅም!! የግሉ አውሮፕላን እንዳለው ሳውቅ ግን የገቢ ምንጩን የማወቅ ፍላጎት ኖረኝ። ዱባይ ስንደርስ የአንድ ምግባቸው ዋጋ የእኔን የወር ደመወዝ የሚሆን ሆቴል ብቻውን የያዘው እስኪመስል አንድ ፍሎር ላይ ሰፈርን። አስተናጋጆቹ መሬት በግንባራቸው ሊነኩ እስኪቀራቸው ሰግደው ነው ሰላምታ የሚያቀርቡት።

ሰውየው በሀብቱ የተፈራ እና የተከበረ ልጥጥ ነው። የተለያዩ ሀገራት ላይ ለቁጥር የታከቱ ንብረቶች እና ኢንቨስትመንቶች ባለቤት ነው። በአረብ ሀገራት ውስጥ ታላቅ የተባለ የነዳጅ ካምፓኒ ውስጥ ትልቅ ስቶክ ያለው ባለስልጣኖቹ ሁሉ የሚሽቆጠቆጡለት ሰው መሆኑን ስብሰባው አዳራሽ ሲገባ አስተዋልኩ። አዲስአበባ የሚኖረው ሀገሪቷ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ፈልጎ የኢትዮጵያ መንግስት መንገዱን ስላላቀለለለት እግረመንገዱን በሴቶቻችን እየተዝናና ነው ገባ ወጣ የሚለው።

የዛን ቀን ማታ አንደኛውን አቅም (ሀብት) መገንባት እንደምችል እርግጠኛ ሆንኩ። ስብሰባውም ላይ እኔ ከውጭ ጠባቂ ነበርኩ። የተቀመሱት ናቸው አብረውት አዳራሽ የገቡት። የዛን ቀን የሚዘገንነኝን ሴትነቴን ለማሰብ በትንሹ ገርበብ ያለ ልብ ኖረኝ። ቢሆንም ሀሳቡን ለመፈፀም እሩቅ እንደሆነ እያሰብኩ በሚቀጥለው ማታ እድል ወይ አጋጣሚ ብቻ ክስተት ሆነ። ሰውየው የሁለተኛውን ቀን ስብሰባ ጨርሶ ሆቴሉ ካረፈ በኋላ ወክ ካልወጣው ብሎ ቀበጠ። እኔን ጨምሮ ስምንት ሴት እና ሁለት ጠብደል ወንድ አስከትሎ የተቀሩት ምን እንዲጠብቁ እንደሆነ ባላውቅም ሆቴል ውስጥ ሲጠብቁ እንዲቆዩ አስደርጎ ወጣ!! ከስር ከስሩ ጡል ጡል የሚል ትዕዛዙን የሚቀበል እና የሚያቀብል አንድ ሲያዩት ግዙፍ የሚመስል ሲሽለጠለጥ ቡችላ የሚያክል ሰውዬ ከስር ከስሩ አይለየውም። ከፊት አራት ሁለት ከጎን የተቀረነው ከኋላ ሆነን ከሆቴሉ ወጥተን ትንሽ እንደሄድን (እኔ መጨረሻ ላይ ነኝ) ሰው በበዛበት ጎዳና ሚኒባስ ከሚመስል ዝግ መኪና ውስጥ አንድ እንደእርሱ የለበሰ ባለሀብት የሚመስል ጥቁር ሰውዬ የሰማይ ስባሪ በሚያካክሉ ስድስት በኋላ ላይ ናይጄሪያውያን መሆናቸውን ያወቅኳቸው ወንዶች ታጅቦ ወረደ። የኛውን ሰውዬ ያጀብነው እኔን ጨምሮ ወደሽጉጣችን እጃችንን ላክን ……. ግማሾቻችንም ሰዎቹ ላይ ደቀንን!! የኛው ሰውዬ እንድንረጋጋ ምልክት ሰጥቶን ከሰውየው ጋር በወዳጅነት ሰላም ተባብለው የሰውየውም ጠባቂዎች ከኛ ጋር ተደባልቀው ሁለቱ እያወሩ መጓዝ ያዙ።


የመኖር አካፋይ የመሞት ሲሶ መንገድ መሃል........ ክፍል ሀያ ሰባት
(ሜሪ ፈለቀ)

የሰው ልጅ ለውጥ የአንድ ጀምበር ክስተት አይሆንም። ወይ ተሸርፎ ተሸርፎ የተጋተው ልምድ እየቆየ ይለውጠዋል አልያም በህይወቱ ከባድ ክስተት እንደሚወዱትን ማጣት ያለ ንዝረት 360 ዲግሪ ይቀይረዋል። የአባቴን ገዳዮች ለመጥላት የአባቴ ሞት እና የእናቴ አይኔ ስር መደፈር በቂ ነበር። የበቀል ጥንስሴን ከዜሮ መቶ ለማድረስ ለቁጥር የሚታክት ጊዜ አባቴ የሞተበት ደጃችን ላይ ተመላልሼ ክስተቱን በጭንቅላቴ ስያለሁ!! አንድ ቀን ባልሳቅኩ ቁጥር፣ ልጅነቴን ሁሉ እኔና ወንድሜ እናትና አባት እንደሌለን ባሰብ ቁጥር ሁሉ አምርሬ ጠልቼ አምርሬ ላጠፋቸው ሰውነቴ ጥላቻ ረጭቷል።

ሴት ልጅ እርቃኗን የወንድ መዝናኛ ሆና የምታስገኘውን ገንዘብ እንደገቢ ከመቁጠሬ ከዓመታት በፊት የሴት ልጅ ገላ ሲቀል አይቼ ዘግንኖኝ ነበር። ም ብዬ ፈርጄባታለሁ። ቀን በቀን በትንሽ በትንሹ ስጋተው ቀጭን ወገብ ሳይ ፖሉ ላይ ስትጥመለመል የሚስል ጭንቅላት ኖረኝ እና አረፈው።

ያኔ ታክሲ በር ላይ ተለጥፌ ፒያሳ ሜክሲኮ የምል ጊዜ ……. በጉልበቴ ተከበርኩ። ተራ አስከባሪውም ሹፌሩም ከዛን ቀን በፊት አይቶኝ በማያውቀው የክብር ዓይን አየኝ። ፀሃይ ሲያነደኝ ውዬ የማገኘው ገንዘብ ግን ኪዳንዬን እንደምፈልገው የሚያኖርልኝ አልነበረም። ያ ሰውዬ የሰጠኝን ቢዝነስ ካርድ ለማይቆጠር ያህል ጊዜ ካሸሁት በኋላ ደወልኩለት። ሰውየው ደላላ ነው። ሊያስቀጥረኝ ያጨልኝ ቦታ እንኳን ለእንደእኔ ዓይነቷ ከትንሽ ክፍለሀገር ለመጣች ሴት ቀርቶ የፈረንጅ ፊልም ስታይ ላደገች ከተሜም ቀላል አይመስለኝም። ከተማዋ ውስጥ እኔ ነኝ ያለ የመናዊ ሰውዬ ጠባቂ መሆን ነው። መጠበቁ ደግ ነበር። ሰውየው የጋዳፊ(ስለጋዳፊ ሳውቅ ነው የገባኝ ጉዳዩ) ታናሽ የሚሰራራው ወፈፌ ነው። ጠባቂዎቹ ሴቶች እንዲሆኑ ከመፈለጉ አንድ ደርዘን ሴት እንዲጠብቀው መፈለጉ ግራ ያጋባል። ብስራተ ገብርኤል ካለው ቤቱ ቦሌ ለመድረስ በአራት መኪና እና በ10 ሴት ጠባቂ በሁለት ወንድ አጃቢ መከበብ ጤንነት ነው?

የተገናኘን ቀን ዝርዝሩን ብዙም ሳይነግረኝ ሰውየው ቤት ይዞኝ ሄደ። የቤቱ ስፋትና ውበት ቤተመንግስት ራሱ እንደዚህ ይመስላል የሚል ምስል ጭንቅላቴ ውስጥ የለም። የአጥሩ በርጋ ብቻ ወንድ ሁለት ጠባቂዎች ሲኖሩ በተረፈው ሱፍ ኮት እና ሚኒ ጉርድ የለበሱ በለበስኩት የመነቸከ ሸሚዝና ጅንስ ሱሪ የሚያሸማቅቁኝ የሚያማምሩ ሴቶች ሲቀባበሉ ብዙ ኮሪደር እና ክፍሎች አልፈን አንደኛው ቢሮ የሚመስል ክፍል አደረሱኝ። ሴቶቹ ምናልባት ከሁለቱ ውጪ ሀበሻ አይደሉም!! ሰውየው ፊቱ ከመንጣቱ የተነሳ የሰው ቆዳ ሳይሆን ነጭ ሸማ የመሰለ ፊት ያለው አረብ ነው። ጭንቅላቱ ላይ በቄንጥ የታሰረ ሻርፕ ነገር አድርጎ እንደወተት የነጣ ቀሚስ ለብሷል። ከደላላው ጋር በአረብኛ ሲነጋገሩ እንዳልወደደኝ ያስታውቅበታል። ከእግሬ እስከራሴ በማጣጣል እያየኝ ቁጣ የመሰለ ነገር ይንጣጣል። ደላላው ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ሳይገባኝ አይኔን ከሰውየው ወደ ደላላው እያቁለጨለጭኩ ሳይ ከየት መጣ ያላልኩት የሆነ ጠባቂ መሰለኝ ከጀርባዬ ሳላስበ በእጁ ቆልፎ አንቆኝ ወደላይ አነሳኝ። እነርሱ ጭቅጭቃቸውን ቀጠሉ። ደመነፍሴን እየሆነ ያለው ሳይገባኝ በቀኝ እጄ ያነቀኝን እጁን ጠምዝዤ በግራ እጄ ፍሬውን አጎንኩት። እጁን ጠምዥዤ ወደፊት ስደፋው ነው ሆነ ብለው የፈጠሩት ድራማ መሆኑን ያወቅኩት። ሰውየው አይነት ንቅናቄ ጭንቅላቱን ነቀነቀ።

እዚህ ድረስ ሰላም ነበር። እንድለካው ያመጡልኝን ልብስ ስለብሰው የለበስኩት ፓንት ሊታይ ትንሽ የቀረው ከመሆኑ ለፋሲካ የሚገዙትን በግ አዟዙረው እንደሚያዩት እየዞረኝ ሲገረምመኝ
«ምንድነው እሱ? ስራው ጥበቃ ነው አላልክም? ደግሞ ይሄን ብጣሽ ነገር አገልድሜ አንድ እርምጃ አልሄድም!! አልፈልግም ስራውን!» ብዬ ልብሱን እንድቀይር የወሰዱኝ ክፍል ሄጄ የራሴን ልብስ ስቀይር አሁንም እነርሱ እንደጭቅጭቅ ያለ ወሬ ሲያወሩ ይሰማኛል። ደላላው በኋላ ሲገባኝ ለሚከፈለው ጠርቀም ያለ ገንዘብ ነው ሽንጡን ገትሮ እንድቀጠር ሲከራከር የነበረው። ሰውየው ስራውን አልፈልግም በማለቴ ተናዶ መሆኑን በኋላ ሰማሁ። ብሎ ነበር የደነፋው። ስንወጣ ደላላው ደሞዙን ሲነግረኝ ጠጅ እንደጠጣ ሰው ጉልበቴን ያዘኝ። ግን እንዲያውቅብኝ ስላልፈለግኩ መግደርደሬ እንዲታወቅልኝ

«የምሰራ ከሆነም ያን ቀሚስ አልለብስም። ሱሪ ከተደረገልኝ እሰራለሁ!! ደግሞ ቆይ ሴቶቹስ እግራቸውን ማንሳት ቢኖርባቸው በዛ ቀሚስ እንዴት ነው የሚሆኑት?»

«ሰውየው በሴት የመከበብ ልክፍት ስላለበት እንጂ አሁን ማን ይሙት አዲስአበባ ውስጥ እንዲህ ተከቦ የሚያስኬድ ስጋት ኖሮበት ነው? የሀብታም ነገር ብሩን የሚጥልበት ሲጨንቀው ነው።» አለኝ። ከቀናት በኋላ ሱሪ መልበስ እንደተፈቀደልኝ ነገረኝ እና ስራውን ጀመርኩ። ጀመርኩ እንደዋዛ አይደለም። ከሰውየው ጠባቂዎች ጋር ኢላማ ተፈትኜ…… መጀመሪያ ሰሞን በየሄደበት በር ጠባቂ ካደረገኝ በኋላ ….. ከሀገር ውጪ ሲወጣ ባዶ ቤት ክፍሎች ጠባቂ ከሆንኩ በኋላ ….. ከኪዳን ጋር የተሻለ ቤት ተከራይተን መኖር ከጀመርን በኋላ ……. የግል ትምህርት ቤት ካስገባሁት በኋላ …… የሆነ ጊዜ ደላላው ሲመጣ በር ጠባቂ መሆኔን ሲያይ

«አንቺ ከእነዚህ እሳት ሴቶች ጋር እየዋልሽ ዛሬም በር ላይ ነሽ? አትማሪም? ምንድነው እንዲህ ማካበድ? ይሄኔ ብታቀምሺው ስንት ሀገር አይተሽ ነበር! ያንቺ የተለየ ነው እንዴ ይሄን ያህል?» ሲለኝ እስከዛን ቀን ዙሪያዬ እየሆነ ያለውን አለማጤኔ ገባኝ። አትማሪም ወይ? አለኝ እንጂ ሴቶቹ ከእኔጋ ጊዜ ኖሯቸውም አያወሩ ቢኖራቸውም የእነርሱ ዓይነት አራዳ ስላልነበርኩ ትዝም አልላቸውም። በዛ ላይ ከሁለቱ ሀበሾች ውጪ በቋንቋም አልግባባም!! ደላላው ከሄደ በኋላ ነው ከእኔ ውጪ ሁሉም ሴቶች ባለመኪና የመሆናቸው ሚስጥር እኔ ቅርብ ስራ ጀማሪ መሆኔ ሳይሆን እነርሱ መቀመሳቸው መሆኑ የተገለጠልኝ። እስከዛን ቀን ድረስ ሴትነትን ወይም ድንግልናን አስቤው የማውቅ ባልሆንም ነገሩን አስቤው ዘገነነኝ። ሴትነትን ሳስብ ትዝ የሚለኝ መሬት ላይ ቀሚሷ ተገልቦ የተኛች እናቴ ናት!! ሴቶቹም ዘገነኑኝ!! ሴትነቴም ዘገነነኝ!! ለውጥ የልምድ ውጤት ነው አላልኳችሁም? ለዛን ሰዓት ከመኪናው እና ሴቶቹ ሲይዙ ከማያቸው ውድ ስልኮች እና ሲያደርጉ ከማያቸው ዘናጭ ቦርሳና ጫማዎች በላይ የከዳሁት ሴትነቴን ክብር ማስጠበቅ መረጥኩ!! በየሄደበት በር ላይ መቆሙን ቀጠልኩበት!!


«አዲስአበባ ከሄድን እዛ አንድ ቀን እንኳን እንድታድር አልፈልግም!! ሳይውል ሳያድር እንድትወጣልኝ ነው የምፈልገው ምን ያደርጉብኝ ይሆን ብዬ ማሰብ አልፈልም!!»

«አውቃለሁ!! ግን አንቺስ?»

«እኔ ምን? እኔ ራሴን መጠበቅ አያቅተኝም!!»

«ሜል ብዙ ነገር ተቀይሯል። ምን ያህል እንዳስተዋልሽው አላውቅም እንጂ አንቺም ራሱ ፍፁም ተቀይረሻል። ወደኋላ ተመልሰሽ ያለፈ ህይወትሽን መኖር የምትችዪ አይመስለኝም! እሱን ነው የምታስቢው? ምንድነው የምታስቢው?» አጠያየቁ የእኔ ኪዳን አይመስልም በጣም ተኮሳትሮ እንደታላቅ ነው የሚያወራው

«አላውቅም! ራሴ እንደተቀየርኩ አውቃለሁ ነገር ግን ያለፈውን ህይወቴን ሙሉ ለሙሉ ተፋትቼ መኖር እችል እንደሆነ አላውቅም! ምክንያቱም እኔ ብቻ እንጂ የተቀየርኩት በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችም ሁኔታዎችም እንዳሉ ናቸው። የቱን ጥዬ የቱን ይዤ እንደምቀጥል አላውቅም!»

«ለምን ከሀገር መውጣትን አታስቢበትም? ሁሌ ጀርባሽን መጠበቅ ሳይኖርብሽ አዲስ ህይወት አዲስ ማንነት ትገነቢያለሽ!»

«እኔእንጃ የኔ ኪዳን!!»

«በጎንጥ ምክንያት ነው? የነገ አብሮነታችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል ተነጋግራችኋል?»

«አይደለም! ስለነገም ያወራነው የለም! ስለምንም ያወራነው የለም!»

«ሜልዬ እስኪ ዛሬ እንደ ትንሹ ወንድምሽ ሳይሆን እንደ 31 ዓመት ትልቅ ሰው አውሪኝ! እንደምትዋደዱ ግልፅ ነው!! እኔ ሳውቅሽ ለማንም ሆነሽ የማታውቂውን ነው ለሱ እየሆንሽ ያለሽው! ማንንም ሰው ባላቀረብሽው ልክ ነው እሱን ያቀረብሽው! ወደፊትሽን ስታስቢ እሱ አለበት? ያወራችሁት አይኑር! አንቺ ምንድነው የምታስቢው?»

«እኔ እንጃ ኪዳንዬ የእውነቴን እኮ ነው እኔንጃ የምልህ!! ታውቃለህ እኔ ፍቅር አላውቅም!! ፀብ ቢሉኝ አውቃለሁ፣ በቀል ቢሉኝ አውቃለሁ ……. ፍቅር ግን አዲሴ ነው!! ስምጥ ብዬ ከዋኘሁ በኋላ ነውኮ እንደወደድኩት እንኳን የነቃሁት! ደግሞ እኔ ብቻ የማስበው ምን ይፈይዳል? እኔ ስላሰብኩህ ና ወደፊቴ ውስጥ ላካትህ ይባላል?»

«ጠይቂዋ!»

«ምን ብዬ?»

«ምንድነው ስለወደፊት የምታስበው? አብሮነታችን ምን ድረስ ነው የሚዘልቀው? ብለሽ ነዋ!»

«እህ እሱ አይደል እንዴ ወንዱ! ይሄን መጠየቅ ያለበት እሱ አይደለም? በግድ እየገፋፋሁት ቢመስልብኝስ?» ስለው ከቀናት በፊት ሲስቅ የሰማሁትን ሳቅ ሳቀ።

«አይመስልም ዓለሜ (ልክ ጎንጥ በሚልበት ለዛ) ዘመኑ ተቀይሯል!! ሴት ተንበርክካ አግባኝ የምትልበት ዘመን ላይ ነን!»

« ምንስ ፍቅር ብርቄ ቢሆን ጥንቅር ይላታል እንጂ ተንበርክኬማ አግባኝ አልለውም! ጭራሽ? ለተሸነፍኩትም መደበቅ ቢቻለኝ በዋጥኩት! እንቢ እያለኝ እያመለጠኝ እንጂ!!» ተሳሳቅን!!

በሚቀጥለው ቀን ኦንላይን ትኬቱን ቆርጦ አጎቴን ተሰናብተን (ስንብቱ በእንባ የታጀበ ነበር።) ወደ አዲስ አበባ መጣን!! የዛኑ ቀን በረራው ነበረ። ስንሰነባበት

«ሜል አስብበታለሁ በይኝ ከሀገር መውጣቱን?»

«አስብበታለሁ ሙት!!»

«ለዓለሜ እንደምትዪው ብሎሃል በይልኝ። የምሬን ነው ንገሪው!»

«ሂድ አሁን አርፈህ!! እነግርልሃለሁ!!»

እሱን ሸኝቼው ስመለስ ህይወቴን ካቆምኩበት መቀጠል እንደማልችል ገባኝ። ቤቴ እንኳን ያለስጋት መሄድ እንደማልችል ሳውቅ መኪናውን መንገድ ዳር አቁሜ ውስጥ እንደተቀመጥኩ ብዙ ቆየሁ። የእውነት ምንድነው አሁን የማደርገው? እንደድሮው ባር ሄጄ ወገበ ቀጫጭን ሴቶች የቆመ ፖል ላይ ሲውረገረጉ ፣ ለፍዳዳ ሰካራሞች ለሀጫቸውን እያዝረከረኩ ብራቸውን ሲረጩ …. .፣ አቅላቸውን የሳቱ ሱሰኞች ሀሺሺን ከሺሻው እያደባለቁ ሲያጨሱ …… እያየሁ እየተዘዋወርኩ ብሉልኝ ፣ ጠጡልኝ ፣ አጭሱልኝ ፣ ተዝናኑልኝ እያልኩ ብሬን መምታት ይቻለኛል?

ከአንድ ሰዓት በላይ ከቆምኩ በኋላ የሆነኛው ገስት ሀውስ ይዤ ለዛሬ እርፍ ብዬ መተኛት ፈለግኩና ከዛ በፊት የጎንጥን ድምፅ መስማት ፈለግኩ። አንዱ ሱቅ ገብቼ ደወልኩ። ስልኩ ዝግ ነው። ገስትሀውስ ገብቼ ለማረፍ ሞከርኩ እና ተገላበጥኩ። ራሴን አሁንም ወጥቼ የሱቅ ስልክ ላይ ስደውል አገኘሁት። ዝግ ነው!! ተመልሼ ገብቼ ለጥ ብዬ አድራለሁ ያልኩትን ለሊት ስገላበጥ አደርኩ። ይሄኛው ስሜት ደስ አይልም!! ስልኩን ባይከፍተው የት ብዬ ነው የማገኘው? የድሮ ሚስቱ ቤት ሄጄ ነው የምላት? ደግሞ ለራሴ እላለሁ። ዛሬ እንደምመጣ እያወቀ ስልኩን የዘጋው ሊያገኘኝ ስላልፈለገ ቢሆንስ? ምን እየሆንኩ ነው ስንት ሀሳብ እያለብኝ ስለእርሱ ብቻ የማስበው? ……. ስወራጭ ቆይቼ ሊነጋ ሲቃረብ እንቅልፍ ወሰደኝ!!

እንደነቃሁ ተጣጥቤ ስልኩን ሞከርኩ። አሁንም ዝግ ነው። ወደሰፈሬ ነዳሁ እና ተናኜን ቅያሪ ልብሶች ተቀብያት ጎንጥ ብቅ ብሎ እንደው ስጠይቃት አለመምጣቱን ነገረችኝ። ልብሴን እዛው መኪና ውስጥ ቀይሬ ሻለቃው ቢሮ ሄድኩ። የሰዎቹን ፎቶ ከተገበያየሁ በኋላ እንደማላውቃቸው ሳውቅ መረጃ የሚያቀብለኝ ሰው ጋር ደወልኩ።

«ኢሜል የማደርግልህን ፎቶ ተመልከተውና መረጃ አቀብለኝ» ካልኩት በኋላ የሁለቱን ሰዎች ፎቶ እየላኩለት ልክ እንዳልሆነ የማውቀው ሀሳብ ጭንቅላቴን ወጠረኝ። ላለማድረግ ከራሴ ጋር ታገልኩ። ግን አቃተኝ!! ከስልኬ ውስጥ ጎንጥን ስቀጥረው ይዤው የነበረውን ፎቶ አብሬ ላኩለት። መልሶ ደወለልኝ እና

«ይሄን ሰውዬኮ ከዚህ በፊት ጠይቀሽኝ ነበር።»

«አውቃለሁ!! ተጨማሪ መረጃ ፈልግ!! በጓሮ ሂድ!» አልኩት (ሰውየው በግልፅ ከተመዘገበው መረጃ በላይ የተደበቀ መረጃ አለው ለማለት ነው በጓሮ ሂድ የምንባባለው)

ስልኩን ዘግቼው ኮምፒውተር ቤቱ ውስጥ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ!!!

………… አልጨረስንም …………..


#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ስድስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

የእማዬ ቀብር ላይ የአባቴ ገዳዮች ዘመድ አዝማድ እና ልጆች ሁሉ ሊቀብሯት ሲያጅቧት ፤ አንዳንዱም ሲያለቅሱላት እያየሁ የተሳከረ ስሜት ወረረኝ። የዛን እለት ከአቶ አያልነህ ጋር የነበሩት ሰውም አረፋፍደው ተቀላቀሉ። የኛም ወገን የእነሱም ወገን የተፈጠረውን እልቂት ይቅር ተባብለው ተሻግረውት እኔ ብቻ ነበርኩ በጥላቻ የሰከርኩት? አይደለም! እዚህ ያሉት ናቸው በይቅርታ የተሻገሩት!! ጥላቻ እና ቂማችንን ይዘን ከተማ የገባን እኔና መሰሎቼ በየሶሻል ሚዲያው በቃላት ተዋግተናል፣ ካለመንደራችን በተገናኘንበት ተጠማምደን ተጠላልፈናል፣ የደማችንን ምንጭ ተጠያይቀን ለአባቶቻችንን ፀብ እኛ ተሰነካክለናለን ተጫርሰናል፣ እኛ እንደአባቶቻችን በጥይት ተጫርሰን ባናሳያቸውም ለወለድናቸው ልጆቻችንን እና ታናናሾቻችን ጥላቻችንን አጋብተናል። እነርሱ ግን እረስተውትም እንኳን ባይሆን አልፈውት የአንዳቸውን ለቅሶ ይላቀሳሉ። እኔ ግን ከወራት በፊት እንኳን የእነእርሱን የልጅ ልጅ እንኳን ባገኝ በማያውቀው የአያቱ በደል ጥላቻዬ ውስጤ ይፈላ ነበር።

ከቀብር መልስ ሰው እየተሰናበተን ሲወጣ አቶ አያልነህ ከሚስታቸው ጋር ተሰናብተው ሊወጡ ሲሉ እጄን ያዝ አድርገው።

«እግዜሃር ያፅናሽ!» ሲሉኝ እጃቸውን በደንብ ጨብጬ ይዤ

«ዛሬ ነው የፈቱኝ!! እስከዛሬ የእርሶ እስረኛ ነበርኩ።» ስላቸው ቁጥብ ያለ ፈገግታ ፈገግ ብለው

«እኔ ይቅር ብያለሁ እርሱ ጨርሶ ይቅር ይበልሽ!! በርቱ!!» ብለውኝ ወጡ!!

በኋላ ላይም ወዳጃቸው የተቀመጡበት ሄጄ እጃቸውን ያዝ አድርጌ (በአካል ስላላገኘኋቸው ሁሌ ይከነክነኝ ነበር) «የማይገባኝን ይቅርታ ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ!!» አልኳቸው። እሳቸው ከአቶ አያልነህ በላይ በተፈታ መንፈስ

«እግዜር ያፅናሽ ልጄ!! እቤቴ በተውሽው መልዕክት የልጆቼን ህይወት ነው የቀየርሽው!! ልብሽ ቀና ነው የእኔ ልጅ ቂምና ጥላቻ ለማንም አይበጅ! ለአባትሽም ለእኛም አልሆነን!! ልብሽን ከክፉ ጠብቂው!» ብለው ጭራሽ እኔኑ አበረቱኝ።

የቀብር ቀን ማታ ፍራሽ ላይ ተቀምጠን ሊያማሽ የመጣውን ለቀስተኛ እየተቀበልን ስንሸኝ በሚገባ እና በሚወጣው ሰው መሃል ጎንጥ በሞላ ሞገሱ ጎንበስ ብሎ ድንኳኑን ሲዘልቅ ሳየው የእማዬን መሞት አሁን የተረዳሁ ይመስል ድንኳኑን በለቅሶ ደበላለቅኩት። እስከአሁን ሲገባ ሲወጣ ከነበረው ሰው የበለጠ ፣ እስከአሁን ሊያፅናናኝ ከሞከረው ህዝብ በበለጠ ፣ እንደነፍሴ ከምወደው ኪዳኔ እንኳን የበለጠ ፣ ከአጎቴም የበለጠ ……. እሱ ብቻ የበለጠ ህመሜ የሚገባው ዓይነት ነው የመሰለኝ። ድንኳኑ እንደአዲስ በለቅሶ ተናጠ። ሌላ ሰው መኖሩን ረሳሁ!! ዘልዬ እቅፉ ውስጥ ገባሁ!! አላባበለኝም አብሮኝ አለቀሰ። ሽማግሌዎች ብለው ሊያረጋጉ ሲሞክሩ አጎቴ ከውጭ ብቅ ሲል ጎንጥን ሲያየው ከእኔ ብሶ አረፈው። ልክ የሆነ ታናሽ ወንድሙን ያገኘ ወይ ታላቅ ልጁን አልያም የብዙ ጊዜ ወዳጁን ያገኘ ይመስል

«አመለጠችኝኮ! አትከብጅኝም ትንሽ ቆይ እያልኳት አሻፈረኝ ብላ ሄደች! እንብኝ አለች! ናፍቆቴ አልወጣልኝም እያልኳት ተሸነፍኩ አለች!» እያለ ሲያለቅስ ድንኳኑ ተተራመሰ። ጭራሽ ሁለቱ ተቃቅፈው ሲላቀሱ የተወሰኑ ቀናት አብረው ያሳለፉ ሳይሆን ሳይነጋገሩ የሚግባቡ ቤተሰቦች ነው የሚመስሉት። እኔስ ስለወደድኩት ወይ ይወደኛል ብዬ ስላሰብኩ ለልቤ አቅርቤው መሰለኝ ሳየው ሀዘኔ የፈነቀለኝ። አጎቴስ? ምናልባት እኔ ያልሰማኋቸውን ቅፅበት የልብ የልባቸውን አውግተውበት ተናበው ይሆን? ወይስ ለልብ ለመቅረብ የተለየ ነፍስ ያለው ሰው አለ?

ለቅሶው ሲበርድ አጠገቤ መጥቶ ፍራሽ ላይ ተቀመጠ። ለቀስተኛው ማን ስለመሆኑ ግራ እየተጋባ ሲጠያየቅ አጎቴ «ቤተሰብ ነው!» እያለ ይመልሳል። አንድ ዘመዳችን

«የአባትሽ ቤተሰብ ነው? የእነርሱ ደም ይመስላል!» ስትለኝ በደንብ አስተዋልኩት። በጭንቅላቴ ውስጥ ሊጠፋ የደበዘዘ የአባቴን መልክ ለማነፃፀር እየታገልኩ ….. ቁመቱ ፣ ትከሻው ፣ ግርማ ሞገሱ ፣ ጥይምናው ፣ ጅንንነቱ …… ከአባቴ ጋር ይመሳሰላል። ለአፍታ ብዬ አሰብኩ። ሳይታወቀኝ አፍጥጬ እያየሁት ስለነበር

«ምን አስፈልጎሽ ነው?» አለኝ

«ምንም! ስለመጣህ ደስ ብሎኛል።» አልኩት

«እንዴት ይቀራል ብለሽ አሰብሽ?» ብሎ ወደትከሻው አጥብቆ ከያዘኝ በኋላ የህመም ትንፋሽ ተነፈሰ። ከሆስፒታል የሚወጣበት ቀን ቀናት እንደሚቀሩት እያወቅኩ እሱን አለማሰቤ አሳፈረኝ። እሱ አጠገቤ መሆኑን እንጂ የእርሱን ቁስል አላሰብኩለትም።

«ውይ! ይቅርታ!» ብዬ ከትከሻው ቀና ስል መልሶ ከቅድሙ በላላ ሁኔታ ትከሻው ላይ አስደግፎኝ
«ደህና ነኝ!!» አለኝ

«ሆስፒታል መቆየት ነበረብሃ?»

«አንድ ሁለት ተጨማሪ ቀን ነበረብኝ! የእኔ ሀሳብ አይግባሽ!! ደህና ነኝ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? አንች መድሃኒቴ አይደለሽ? ሆስፒታል ምናባቱ?» ብሎ ከደቂቃዎች በፊት ስንሰቀሰቅ የነበርኩትን ሴት ያሽኮረምመኛል? እያየኝ ያለ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ አይኔን የተቀመጠው ለቀስተኛ ላይ አንቀዋለልኩ።

እናቴ የሞተችብኝ እኔ ከዛ ደግሞ የተሽኮረመምኩትም እኔ …… ለሰው የሀዘኔን ጥልቀት አሳይቼ መሽኮርመሜን መደበቅ ያለብኝም እኔው!! ምክንያቱም ምንም እንኳን ሊያፅናኑ ቢመጡም ስፅናና እንደሚዳኙኝ አውቃለሁ። እንደሚሉኝ አውቃለሁ። ግራ የሚገባኝ ሊያፅናኑኝ የሚሞክሩት የውሸት ነው ማለት ነው? ሀዘን ማብዛት ጥሩ አይደለም የሚሉት ስለሚባል ነው ማለት ነው? ስፅናና ወይ ስስቅ ታዲያ ለምን ይከፋቸዋል? ሁሉ እንደሚባል አውቃለሁ!!

ስለዚህ ተሰብስቤ ተቀመጥኩ። እኔ ትቼው የምሄደው ህዝብ እና መንደር ቢሆንም ለአጎቴ ወሬ ትቼለት መሄድ አልፈለግኩም!! በሁለተኛው ቀን ጎንጥ የምጨራርሰው ጉዳይ አለኝ ብሎ ወደከተማ ተመለሰ።

ከእማዬ ቀብር በኋላ ቤቱ ውስጥ የሚተራመሰው ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት እየተመናመነ ሄዶ ድንኳኑ ከተነሳ በኋላም ኪዳን መሄድ የፈለገ አይመስልም። «ትንሽ ቀን እንቆይ!» ሲል ብዙ ቆየን። ሁሉም ወደቤቱ ገብቶ ሶስታችን ብቻ የቀረን ቀን ማታ ሀዘናችን በረታ እና እንደአዲስ መላቀስ ያዝን። ኪዳን ከሁለታችን ብሶ «ምናለ ትንሽ ቀን ብትሰጣት? ፣ ምናለ ትንሽ ቀን ብጠግባት? ፣» እያለ ከአምላኩ ጋር ሲሟገት አንጀቴ ልውስ ብሎብኝ ተንሰፈሰፍኩ። አጎቴ እንደልማዱ «እህቴ ፤ ክፋዬ ፣ አንድ ደሜ …. » እያለ እንዳልተነፋረቀ እንባውን በፎጣው አደራርቆ

«ተው ደግም አይደል። የፈጣሪን አይን አትውጉ! ሳናያት ሳናውቅ አልፋስ ቢሆን? የልጆቿን ዓይን ዓይታ ፤ ጠረናችሁን ስባ በትውልድ ቀዬዋ ሀገሬው ቤቱን ነቅሎ ወጥቶ በፍቅር የሸኛት እሰቡት አምላክ እንዴት ቸር እንደሆነ? ደግም አይደል?» ብሎ ተቆጥቶ አረጋጋን!! እንባችንን አቆምን እንጂ ለሚቀጥሉት ቀናት እንደተኳረፈ ሰው በመሃከላችን ብዙም የቃላት ልውውጥ አልነበረም። የሆነ ቀን ውጪ ሳሩ ላይ ተቀምጠን

«የኔ ኪዳን? አሁንም ከዚህ በላይ መቆየት ትፈልጋለህ?» አልኩት

«እኔ እንጃ ሜል! ወደ አዲስአበባ መመለስ ከፈለግሽ እንመለስ! እኔ አሁን ምን እንደምፈልግ ራሱ አላውቅም!!» አለኝ።


አዲስ አበባ ከገባሁ ከአመታት በኋላ ባለገንዘብ የሆንኩ ጊዜ ወደእሳቸው መንደር ላገኛቸው ተመልሼ ነበር። አፈላልጌ በጥቆማ እቤታቸውን ፈልጌ ሳገኝ እኔ አወቅኳቸው። ከዘራ ይዘው እያነከሱ ከበራቸው ወደቤት እየገቡ። እሳቸው ግን አላወቁኝም ነበር። ከአመታት በፊት ካየኋቸው አርጅተው። ተጎሳቁለው ነበር። ሰላም ካልኳቸው በኋላ ከከተማ መምጣቴን ስነግራቸው ወደቤታቸው ጋበዙኝ።

«ያስታውሱኝ ይሆን?» አልኳቸው

«ዓይኔ እያስቸገረኝ ነው ልጄ አላስታወስኩሽም! የማን ልጅ ነሽ?»

«ማን እንደሆንኩ እነግሮታለሁ! መጀመሪያ ግን ማንነቴን ስነግርዎት የምለውን ሰምተው እንደሚያስጨርሱኝ ቃል ይግቡልኝ!!»

«ልጄ እያስጨነቅሽኝኮ ነው!!»

«ቃል ይግቡልኝ!! የምለውን ሁሉ ይሰሙኛል?»

«እሽ ቃሌ ነው!!»

«ከብዙ ዓመት በፊት ከገበያ ሲመለሱ አንዲት ሴት እንደዘረፈችዎት አይጠፋዎትም መቼስ!»

«እንዴት ይጠፋኛል! ቤቴን እኮ ነው ያፈረሰችው! » ብለው በደንብ አዩኝና « አምሳል ነኝ እንዳትይኝና እዚህ ደም እንዳንፋሰስ!!»

«እስከመጨረሻው እሰማሻለሁ ብለው ቃል ገብተውልኝ የለ?»

«በይ ልስማዋ!!»

እግራቸው ላይ ወደቅኩ!! «ከዛን ቀን በኋላ ሳላስቦት የዋልኩ ያደርኩበት ቀን የለም! አንዲት ቀን እንኳን ፀፀት ሳይፈጀኝ አልፎ አያውቅም!! ይቅር አይበሉኝ! ግን ከዚህ በላይ አይቅጡኝ!! የምሰጦትን ገንዘብ ይቀበሉኝ!» አልኳቸው

ተነስተው በፍፁም አሉ!! ሚስታቸው ከጓዳ ትሰማ ነበር እና

«ደግም አይደል አያል! ይህች ልጅ ተጠጥታ መጣችም አይደል? እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል አቤቱ በደላችንን ይቅር በል ብለንም አይደል የምንጠልይ? ተነሽ ይበሏት በቃ!» አሉ። ከስንት ልምምጥ በኋላ እንዳኩረፉ ያመጣሁላቸውን ገንዘብ ተቀበሉኝ። አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች አንደኛው ማረፋቸውን ነገሩኝ! ሌላኛውን እቤታቸው ሄጄ ስላላገኘኋቸው መልዕክቴን ከገንዘቡ ጋር አስቀምጬ ተመልሼ ለአቶ አያልነህ ይቅርታዬን እንዲነግሩልኝ ለምኜ ልወጣ ስል እንዲህ አሉኝ

«ጨርሶ ይቅር ያልኩሽ እንዳይመስልሽ!! ድህነት አይኑ ይጥፋ ዛሬም ለልጆቼ ፍራንካው ስለሚያስፈልግ እንጂ ለራሴ ቢሆን እመቤቴ ምስክሬ ናት ፍንክች አላደርገውም!!» ብለውኝ ነበር። ከዓመታት በኋላ ለቅሶዬን ሊደርሱኝ የመጡት በልባቸው ይቅር የሚሉበት ፍቅር አጊንተው ቢሆን አይደል? ይቅር መባል እንዲህ ደስ እንደሚል ባውቅ ስንት ይቅርታ የምጠይቀው ነበረኝ!!


........ አልጨረስንም ......,


#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

ብዙ ነገር አጥቼ እንደነበር የተሰማኝ አሁን ላይ ነው። የእማዬን አልጋ ከበን ቡና ተፈልቶ ቆሎ እየቆረጠምን አንዱን ወሬ ስናነሳ አንዱን ስንጥል በብዙ ሳቅ እና ደግሞ በደስታ ለቅሶ የታጀበ ቀን እየዋልን ያለፉ አመታቴን አስቤ ብዙ እንደጎደለኝ ገባኝ።

ደግሞ በዚህ ሁሉ የቤተሰብ ፍቅር ታቅፌ ልቤ ክንፍ አውጥታ ጎንጥ ጋር ስትሄድ፣ የያዘኝን አያያዝ ፣ የሳመኝን መሳም ፣ የጠራኝን መጥራት አሰብ አድርጌ ብቻዬን ፈገግ ስል ባለፉት ዓመታቶቼ ብዙ እንዳለፈኝ ገባኝ። ብዙ እንዳልኖርኩ ገባኝ!!

«እትዬ ዛሬ ሌላ ሰው ሆነው በንፁህ ልብ ስለተቀበሉት ነው የሚያጎብጥ ሸክም የሆነብዎት። ቂም ባቄመና በጠለሸ ልብ ሆነው ሲቀበሉት እንዲህ አልተሰማዎት ይሆናል።» ነበር ያለው ጎንጥ እንዴት ይሄን ሁሉ ጥላቻ ተሸክሜ ኖርኩ ስለው?
በንፁህ ልብ አይደለም። በፍቅር ልብ ሳየው ነው ዓለምን እና ዙሪያዬን የማይበት መነፅር የተቀየረው። በፍቅር ዓይን!! ሁሉ እንዳለኝ የተሰማኝ፣ መኖር ደስ የሚል ነገር መሆኑን ማሰብ የጀመርኩት በፍቅር ልቤ ማየት ስጀምር ነው።

እናቴን አቀፍኳት፣ ኪዳንዬ አለኝ፣ አጎቴን አለኝ፣ ጎንጥ ይኑረኝ አይኑረኝ ባላውቅም አዎ በልቤ ውስጥ ግን ከነጥጋቡ አለኝ!! ምን እጠይቃለሁ ሌላ? አጎቴ እናታችን ስለደከመች ካጠገቧ ባንርቅ መልካም መሆኑን ስለነገረን በአካሌ ላለመሄድ ወሰንኩ። ግን ልትሞት ቀናት የቀራት እናቴን አቅፌ ልቤ አዲስአበባ መሸምጠጡ ራስወዳድነት ነው? እንደዛ እየተሰማኝኮ ራሴን እገስፃለሁ። ልቤ አልሰማኝ አለኝ እንጂ!!


የገባን ቀን ማታ ምናልባት ለጥንቃቄ በሚል። በኪዳን ስልክ ዋትሳፕ መልዕክት ላኩለት። ሁለት መስመር ለመፃፍ ከ20 ደቂቃ በላይ ፈጀብኝ። ለኪዳን ካልሆነ በቀር ፅፌ የማውቀው ማስፈራሪያ ወይ ቢዝነስ ነክ ነገር አልያም የሆነ መልእክት እንጂ ፍቅር ነክ ነገር እንዴት እንደሚፃፍ አላውቅም። ምን ተብሎ ነው የሚጀመረውስ? ሀይ ጎንጥ? ስሙ ደግሞ ሲጠራ ምንም የፍቅር ቅላፄ የለውም!! እንዴት ዋልክ ዓለሜ? ልበለው? አይሆንም እሱ ሲል ነው እንደሱ የሚያምርበት! ሀኒ ልበለው? ሆ ጎንጥን ሀኒ? ራሴኑ አሳቀኝ!! ያቺ የድሮ ሚስቱ እንደጠራችው ጎኔ ልበለው? ኡፍፍፍ

«ሰላም ዋልክ? እኔ ነኝ!! በጠዋት ላይህ ሳልችል ቀርቼ እማዬጋ መጥቻለሁ!! ደህና አድረህ ዋልክ?» በቃ መፃፍ የቻልኩት ይሄን ብቻ ነው። ምን አይነቷ ነፈዝ ነኝ በፈጣሪ!! ከዛማ ስልኩን አቅፌ የፃፍኩለት መልዕክት ሰማያዊ የራይት ምልክት እስኪያሳየኝ ስልኩ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።

«ዓለሜ ናፈቀሽ እንዴ?» ይለኛል ኪዳን ሲያበሽቀኝ

«ለምን ግን አታርፍም?» እላለሁ

«ጎንጤን ነው?» ይላል አጎቴ

«እንዴ? እኔ ብቻ ነኝ የማላውቀው ማለት ነው? አንደኛውን ሽማግሌ ልኳል አትይኝም እንዴ?»

«እዚህ ከርሞ አይደል እንዴ የሄደው? ዓይነውሃው ያስታውቃልኮ ፍቅር እንዳለበት! መች አይኑን ከርሷ ላይ አንስቶ! ብለው ይለኛል። ብለው ይለኛል። ኋላማ እለዋለሁ ቆጣ ብሎ አለኛ» እናቴን ጨምሮ ሁሉም ይስቃሉ። እንደኮረዳ እሽኮረመማለሁ።

ስልኩ መልዕክት መቀበሉን የሚገልፅ ድምፅ ሲያሰማ ከመቀመጫዬ እንደመዝለል ሁሉ ሲያደርገኝ ቡና የምታፈላው ትንሽዬ ዘመዳችን ሳትቀር በአንድ ላይ አውካኩብኝ። የትልቅ ሰው ያልሆነ ማፈር አፍሬ መልዕክቱን ለማየት ሁሉ ስግደረደር ቆየሁ።

ነው የሚለው መልዕክቱ! አሁን ይሄ እሺ ምኑ ነው የሚያስቦርቀው? በፍቅርሽ ሞቻለሁ የተባለች ኮረዳ እንኳን እኔ የምሆነውን መሆን አትሆንምኮ! ትቻቸው ወደበር ወጣሁ እና ደወልኩለት። ቶሎ አውርተሽ መጨረስ አለብሽ የተባልኩ ይመስል የተፈጠረውን ለምን ሳላየው እንደመጣሁ እማዬ ስለደከመች ወደከተማ እንደማልመለስ በጥድፊያ ትንፋሽ እስኪያጥረኝ አውርቼ ሳበቃ ሳቅ ብሎ

«ለመዝጋት ተቻኮልሽ እንዴ?» አለኝ
«አይ!» እያልኩ በቆምኩበት በጫማዬ መሬቱን እየቆፈርኩ መሆኑን አየሁ

«ደግ! ያሻሽን ያህል ጊዜ ቆይ!! » አለኝ

«አንተስ?»

«እኔ ምን እሆናለሁ?» አለኝ እኔ ማወቅ የፈለግኩት ከዛስ የሚለውን….. እኔ ያሻኝን ያህል ጊዜ እዚህ ስቆይ እሱስ? ከሆስፒታል ሲወጣ ቤት ሄዶ ይጠብቀኛል? ወይስ ያለሁበት ይመጣልኛል? ወይስ እኔ ወደማላውቀው ቤቱ ይሄድብኛል?

ያናደደኝን ወይ የተጣላኝን ሰው በጉልበት እንዴት እንደማግተው አውቅ ነበርኮ! የወደድኩትን ሰው እንዴት አባቴ አድርጌ ነው የራሴ የማደርገው? እሱን አልችልበትም!! በጉልበት ባገቱት ሰው ላይ ሙሉ ስልጣን ማራመድ ይቻላል። በፍቅር የወደቁለትን ሰው ራሱ ፈቅዶ ወደእኔ ካልቀረበ ምንድነው የማደርገው? ዝም አልኩ!!

«ዝም አልሽኝ እኮ ዓለሜ?» አለኝ ጠብቆ

«ምን እንደምል አላውቅበትም!! ያለፍከውን አላውቅም! ወደፊት ምን እንደምታስብ አላውቅም! ነገ ምን እንደምንሆን አላውቅም! አሁንም ምን እንደሆንን አላውቅም!! አላውቅህምኮ ጭራሽ! እኔ ግን እዚህ ልትሞት ያለች እናቴን አቅፌ ካንተ ሌላ ሀሳብ የለኝም!! ይሄ እንዴት ያለ መሸነፍ ነው ቆይ?» አልኩት።

«የት እሄድብሻለሁ? አለሁ አደል? ሁሉን ትደርሽበት የለ? አንች ብቻ የተሸነፍሽ አታድርጊው እንጅ!!» ብሎ ግማሽ መልስ ምን ግማሽ እሩብ መልስ ይመልስልኛል።

«እንዲህ እንድትለኝ አይደለም የምፈልገው!» ስለው እየሳቀ

«እንዴት እንድልሽ ነው የምትፈልጊ? ቁጣው የምንድነው ታዲያ?» ሲለኝ ነው እየተቆጣሁ እንደሆነ ያስተዋልኩት

«እንደምትወደኝ ነው ማወቅ የምፈልገው!! እንዳልነሳ ሆኜ በፍቅርህ ከመውደቄ በፊት እየተሰማኝ ያለው ስሜት የእኔ ብቻ እንዳልሆነ ነው ማወቅ የምፈልገው! አይሆኑ አሸናነፍ ከመሸነፌ በፊት እንደማላጣህ እርግጠኛ መሆን ነው የምፈልገው? እ?» ስለው መሳቁን ሳያቆም

«ፍቅርሽም ቁጣ ነው? እንደምወድሽማ ታውቂያለሽ! መስማቱን ከሆነ የፈለግሽ እወድሻለሁኮ ዓለሜ!! ነገ ምን እንደሚሆን ከፈጣሪ ጋር እናበጀዋለን!! ዛሬን ልውደድሽ ዓለሜ ዛሬን ውደጂኝ!!»

እንኳን ፊት ሰጥቶኝ ዘጭ ለማለት እየተንደረደረ የነበረ ልቤ ዝርፍጥ ብሎ በፍቅር ነሆለለ። ከዛን ቀን በኋላ በየቀኑ ተደዋወልን!! በየቀኑ እንደሚወደኝ ነገረኝ። በየቀኑ ደጋግሜ ተሸነፍኩ። በየቀኑ ከእማዬጋ ሳቅን። በየቀኑ ድሮ ያጣነውን እቅፏን ናፍቆት መሬት ላይ አንጥፈን ለሶስት እቅፏ ውስጥ አደርን። በየቀኑ ደስ አላት!! በአስራ ሶስተኛው ቀን ጠዋት እኔና ኪዳን በቀኝና በግራዋ ሙቀቷን እየሞቅን እማዬ ዝም አለች።

እማዬን ስላጣኋት ከፋኝ። አግኝቻት ስለሞተች ደግሞ አመሰገንኩ። ኪዳንም ተመሳሳይ ስሜት ነበር የተሰማው ግን ከእኔ በላይ የእርሱ ሃዘን በረታ!! ምናልባት እኔ ለእርሱ ለመሆን ስታትር ዘመኔን ስለኖርኩ አጎደልኩበት ብዬ እንዳላስብ ዝም ብሎኝ እንጂ ሁሌም የእናቱ ናፍቆት ያንገበግበው ነበር ይሆናል። በኖረችልኝ ብሎ ሲመኝ ይሆናል የኖረው። እኔና አጎቴ ከእርሱ በርትተን እሱን ማበርታት ጀመርን።

የቀብሯ ቀን ሬሳዋ ከቤት ሲወጣ አይኖቼን ደጋግሜ አሸሁ ያየሁትን ሰው ለማጣራት። አቶ አያልነህ! ፈገግ አልኩ! ይቅር ብለውኛል ማለት ነው።


የነቃሁት የቧንቧ ውሃ ሲወርድ ሰምቼ ነው። ኪዳን ቀድሞኝ ነቅቷል ወይም አልተኛም! አልጋው ጫፍ ላይ እንቅልፍ እንደወሰደኝ ልብስ ደርቦልኛል። ምናልባት እንቅልፍ አልወስድ ብሎት የነበረ ይሆን ብዬ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። በደቂቃዎች ውስጥ እናትህ አለችም ልትሞትም ነው የሚል መርዶ አርድቼው እኔ እንቅልፌን ስለጥጥ አደርኩ። እናቴን አግኝቻት ልትሞት መሆኑን ሳውቅ ለወራት መቀበል አቅቶኝ የሆንኩትን መሆን አስቤ ያጠፋሁ መሰለኝ። ብቅ ሲል

«ይቅርታ ቀሰቀስኩሽ እንዴ?» አለኝ

«ነግቶ የለ! ምነው እንቅልፍ አልወሰደህም እንዴ?»

«አይ ተኝቻለሁ!» ይበለኝ እንጄ የእኔን ኪዳን መች አጣሁት እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር ነው ያደረው። አስር ጊዜ እለዋለሁ። ይለኛል።

«ማውራት ትፈልጋለህ ኪዳንዬ?»

«አልፈልግም! ዝም ብለን እንሂድ!» አለኝ።

ከመሄዴ በፊት ብዙ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩኝ። ሆስፒታል ሄጄ ጎንጥን ማየት። ሻለቃው ጋር መደወል፣ ሴትየዋ ማን መሆኗን አውቄ ማግኘት….. ብዙ!! ከኪዳን የሚበልጥ ነገር የለኝም አይደል? እሱ እንዲህ በዝምታ ተለጉሞ የሚሰማውን እንኳን ሳላውቅ ራሴን ማስቀደም አልሆንልሽ አለኝ!! ክፍላችን የመጣውን ቁርስ እንደነገሩ እየለኳኮፍን መኪና ስፈልግ የሚያዘጋጅልኝ ሰው ጋር ደውዬ መኪና እንዲያመጣልኝ ካደረግኩ በኋላ የዳዊትን መኪና ሌላ ቦታ ወስዶ እንዲያቆምልኝ አደረግኩ። ለዳዊት ደውዬ መኪናውን ከቆመበት እንዲወስድ ስነግረው ምንም እንዳልጠረጠርኩ ለመምሰል ከራሴ ታገልኩ። መንገድ ከጀመርን በኋላ ሻንበሉ ደወለ። የመኪናው ባለቤት እና ልትገድለኝ የሞከረችው ሴት የተለያዩ ናቸው። ግን ሁለቱም በስማቸው የማውቃቸው አይደሉም!!

«ቢሮ ብቅ ካልሽ የሁለቱንም ፎቶ ላሳይሽ እችላለሁ!!» ብሎ ስልኩን ዘጋው!! መልዕክቱ አንድም ለመላክ አላምንሽም ነው ሁለትም ፎቶውን ለማየት ተጨማሪ ዋጋ አለው ነው። ስልኩን ዘግቼ ዝም አልኩ! ኪዳንም ምንም አልጠየቀኝም!! ዝምታው አስጨነቀኝ!! ልቤ ድንጋይ የተጫነበት እስኪመስለን ድረስ እንደከበደኝ ተጉዘን ከሰዓታት በኋላ እነእማዬጋ ደረስን!! አጎቴ ከበር እንደተቀበለን ኪዳንን እያገላበጠ ስሞ አልጠግብ አለው!!

«አቤት አንተ መድሃንያለም ምን ይሳንሃል!! አስካል ልጅሽ መጣልሽ!» እያላት ወደ ውስጥ ገባ!! እማዬ ለመነሳት በዛለ ጉልበቷ ተፍጨረጨረች። ከሁለት ቀን በፊት ካየኋት በላይ ገርጥታለች። ይብሱን የከሳችም መሰለኝ። ዝም እንዳባባሉ ፣ እንደማታው አጠያየቁ ከኪዳን ጋር ሲተያዩ አሁን የሚሆኑትን የሚሆኑ አይመስልም ነበር። ጉልበቷን አቅፎ ተንሰቀሰቀ። ፀጉሩን እየደባበሰች ተንፈቀፈቀች። እኔና አጎቴ የሁለቱን መሆን እያየን ስንነፋረቅ ቆይተን! አጎቴ ፊቱ ላይ የተዝረከረከ እንባውን ጠራርጎ ሲያበቃ ደግሞ እንዳላለቀሰ ሰው ኮስተር ብሎ

«አይ ደግም አይደል የምን ለቅሶ ነው?» አላለም?

............ አልጨረስንም!! ..............

20 last posts shown.

766

subscribers
Channel statistics