#የመኖር አካፋይ ፣ የመሞት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል ሀያ ስድስት)
(ሜሪ ፈለቀ)
የእማዬ ቀብር ላይ የአባቴ ገዳዮች ዘመድ አዝማድ እና ልጆች ሁሉ ሊቀብሯት ሲያጅቧት ፤ አንዳንዱም ሲያለቅሱላት እያየሁ የተሳከረ ስሜት ወረረኝ። የዛን እለት ከአቶ አያልነህ ጋር የነበሩት ሰውም አረፋፍደው ተቀላቀሉ። የኛም ወገን የእነሱም ወገን የተፈጠረውን እልቂት ይቅር ተባብለው ተሻግረውት እኔ ብቻ ነበርኩ በጥላቻ የሰከርኩት? አይደለም! እዚህ ያሉት ናቸው በይቅርታ የተሻገሩት!! ጥላቻ እና ቂማችንን ይዘን ከተማ የገባን እኔና መሰሎቼ በየሶሻል ሚዲያው በቃላት ተዋግተናል፣ ካለመንደራችን በተገናኘንበት ተጠማምደን ተጠላልፈናል፣ የደማችንን ምንጭ ተጠያይቀን ለአባቶቻችንን ፀብ እኛ ተሰነካክለናለን ተጫርሰናል፣ እኛ እንደአባቶቻችን በጥይት ተጫርሰን ባናሳያቸውም ለወለድናቸው ልጆቻችንን እና ታናናሾቻችን ጥላቻችንን አጋብተናል። እነርሱ ግን እረስተውትም እንኳን ባይሆን አልፈውት የአንዳቸውን ለቅሶ ይላቀሳሉ። እኔ ግን ከወራት በፊት እንኳን የእነእርሱን የልጅ ልጅ እንኳን ባገኝ በማያውቀው የአያቱ በደል ጥላቻዬ ውስጤ ይፈላ ነበር።
ከቀብር መልስ ሰው እየተሰናበተን ሲወጣ አቶ አያልነህ ከሚስታቸው ጋር ተሰናብተው ሊወጡ ሲሉ እጄን ያዝ አድርገው።
«እግዜሃር ያፅናሽ!» ሲሉኝ እጃቸውን በደንብ ጨብጬ ይዤ
«ዛሬ ነው የፈቱኝ!! እስከዛሬ የእርሶ እስረኛ ነበርኩ።» ስላቸው ቁጥብ ያለ ፈገግታ ፈገግ ብለው
«እኔ ይቅር ብያለሁ እርሱ ጨርሶ ይቅር ይበልሽ!! በርቱ!!» ብለውኝ ወጡ!!
በኋላ ላይም ወዳጃቸው የተቀመጡበት ሄጄ እጃቸውን ያዝ አድርጌ (በአካል ስላላገኘኋቸው ሁሌ ይከነክነኝ ነበር) «የማይገባኝን ይቅርታ ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ!!» አልኳቸው። እሳቸው ከአቶ አያልነህ በላይ በተፈታ መንፈስ
«እግዜር ያፅናሽ ልጄ!! እቤቴ በተውሽው መልዕክት የልጆቼን ህይወት ነው የቀየርሽው!! ልብሽ ቀና ነው የእኔ ልጅ ቂምና ጥላቻ ለማንም አይበጅ! ለአባትሽም ለእኛም አልሆነን!! ልብሽን ከክፉ ጠብቂው!» ብለው ጭራሽ እኔኑ አበረቱኝ።
የቀብር ቀን ማታ ፍራሽ ላይ ተቀምጠን ሊያማሽ የመጣውን ለቀስተኛ እየተቀበልን ስንሸኝ በሚገባ እና በሚወጣው ሰው መሃል ጎንጥ በሞላ ሞገሱ ጎንበስ ብሎ ድንኳኑን ሲዘልቅ ሳየው የእማዬን መሞት አሁን የተረዳሁ ይመስል ድንኳኑን በለቅሶ ደበላለቅኩት። እስከአሁን ሲገባ ሲወጣ ከነበረው ሰው የበለጠ ፣ እስከአሁን ሊያፅናናኝ ከሞከረው ህዝብ በበለጠ ፣ እንደነፍሴ ከምወደው ኪዳኔ እንኳን የበለጠ ፣ ከአጎቴም የበለጠ ……. እሱ ብቻ የበለጠ ህመሜ የሚገባው ዓይነት ነው የመሰለኝ። ድንኳኑ እንደአዲስ በለቅሶ ተናጠ። ሌላ ሰው መኖሩን ረሳሁ!! ዘልዬ እቅፉ ውስጥ ገባሁ!! አላባበለኝም አብሮኝ አለቀሰ። ሽማግሌዎች ብለው ሊያረጋጉ ሲሞክሩ አጎቴ ከውጭ ብቅ ሲል ጎንጥን ሲያየው ከእኔ ብሶ አረፈው። ልክ የሆነ ታናሽ ወንድሙን ያገኘ ወይ ታላቅ ልጁን አልያም የብዙ ጊዜ ወዳጁን ያገኘ ይመስል
«አመለጠችኝኮ! አትከብጅኝም ትንሽ ቆይ እያልኳት አሻፈረኝ ብላ ሄደች! እንብኝ አለች! ናፍቆቴ አልወጣልኝም እያልኳት ተሸነፍኩ አለች!» እያለ ሲያለቅስ ድንኳኑ ተተራመሰ። ጭራሽ ሁለቱ ተቃቅፈው ሲላቀሱ የተወሰኑ ቀናት አብረው ያሳለፉ ሳይሆን ሳይነጋገሩ የሚግባቡ ቤተሰቦች ነው የሚመስሉት። እኔስ ስለወደድኩት ወይ ይወደኛል ብዬ ስላሰብኩ ለልቤ አቅርቤው መሰለኝ ሳየው ሀዘኔ የፈነቀለኝ። አጎቴስ? ምናልባት እኔ ያልሰማኋቸውን ቅፅበት የልብ የልባቸውን አውግተውበት ተናበው ይሆን? ወይስ ለልብ ለመቅረብ የተለየ ነፍስ ያለው ሰው አለ?
ለቅሶው ሲበርድ አጠገቤ መጥቶ ፍራሽ ላይ ተቀመጠ። ለቀስተኛው ማን ስለመሆኑ ግራ እየተጋባ ሲጠያየቅ አጎቴ «ቤተሰብ ነው!» እያለ ይመልሳል። አንድ ዘመዳችን
«የአባትሽ ቤተሰብ ነው? የእነርሱ ደም ይመስላል!» ስትለኝ በደንብ አስተዋልኩት። በጭንቅላቴ ውስጥ ሊጠፋ የደበዘዘ የአባቴን መልክ ለማነፃፀር እየታገልኩ ….. ቁመቱ ፣ ትከሻው ፣ ግርማ ሞገሱ ፣ ጥይምናው ፣ ጅንንነቱ …… ከአባቴ ጋር ይመሳሰላል። ለአፍታ ብዬ አሰብኩ። ሳይታወቀኝ አፍጥጬ እያየሁት ስለነበር
«ምን አስፈልጎሽ ነው?» አለኝ
«ምንም! ስለመጣህ ደስ ብሎኛል።» አልኩት
«እንዴት ይቀራል ብለሽ አሰብሽ?» ብሎ ወደትከሻው አጥብቆ ከያዘኝ በኋላ የህመም ትንፋሽ ተነፈሰ። ከሆስፒታል የሚወጣበት ቀን ቀናት እንደሚቀሩት እያወቅኩ እሱን አለማሰቤ አሳፈረኝ። እሱ አጠገቤ መሆኑን እንጂ የእርሱን ቁስል አላሰብኩለትም።
«ውይ! ይቅርታ!» ብዬ ከትከሻው ቀና ስል መልሶ ከቅድሙ በላላ ሁኔታ ትከሻው ላይ አስደግፎኝ
«ደህና ነኝ!!» አለኝ
«ሆስፒታል መቆየት ነበረብሃ?»
«አንድ ሁለት ተጨማሪ ቀን ነበረብኝ! የእኔ ሀሳብ አይግባሽ!! ደህና ነኝ አልኩሽ እኮ ዓለሜ? አንች መድሃኒቴ አይደለሽ? ሆስፒታል ምናባቱ?» ብሎ ከደቂቃዎች በፊት ስንሰቀሰቅ የነበርኩትን ሴት ያሽኮረምመኛል? እያየኝ ያለ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ አይኔን የተቀመጠው ለቀስተኛ ላይ አንቀዋለልኩ።
እናቴ የሞተችብኝ እኔ ከዛ ደግሞ የተሽኮረመምኩትም እኔ …… ለሰው የሀዘኔን ጥልቀት አሳይቼ መሽኮርመሜን መደበቅ ያለብኝም እኔው!! ምክንያቱም ምንም እንኳን ሊያፅናኑ ቢመጡም ስፅናና እንደሚዳኙኝ አውቃለሁ። እንደሚሉኝ አውቃለሁ። ግራ የሚገባኝ ሊያፅናኑኝ የሚሞክሩት የውሸት ነው ማለት ነው? ሀዘን ማብዛት ጥሩ አይደለም የሚሉት ስለሚባል ነው ማለት ነው? ስፅናና ወይ ስስቅ ታዲያ ለምን ይከፋቸዋል? ሁሉ እንደሚባል አውቃለሁ!!
ስለዚህ ተሰብስቤ ተቀመጥኩ። እኔ ትቼው የምሄደው ህዝብ እና መንደር ቢሆንም ለአጎቴ ወሬ ትቼለት መሄድ አልፈለግኩም!! በሁለተኛው ቀን ጎንጥ የምጨራርሰው ጉዳይ አለኝ ብሎ ወደከተማ ተመለሰ።
ከእማዬ ቀብር በኋላ ቤቱ ውስጥ የሚተራመሰው ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት እየተመናመነ ሄዶ ድንኳኑ ከተነሳ በኋላም ኪዳን መሄድ የፈለገ አይመስልም። «ትንሽ ቀን እንቆይ!» ሲል ብዙ ቆየን። ሁሉም ወደቤቱ ገብቶ ሶስታችን ብቻ የቀረን ቀን ማታ ሀዘናችን በረታ እና እንደአዲስ መላቀስ ያዝን። ኪዳን ከሁለታችን ብሶ «ምናለ ትንሽ ቀን ብትሰጣት? ፣ ምናለ ትንሽ ቀን ብጠግባት? ፣» እያለ ከአምላኩ ጋር ሲሟገት አንጀቴ ልውስ ብሎብኝ ተንሰፈሰፍኩ። አጎቴ እንደልማዱ «እህቴ ፤ ክፋዬ ፣ አንድ ደሜ …. » እያለ እንዳልተነፋረቀ እንባውን በፎጣው አደራርቆ
«ተው ደግም አይደል። የፈጣሪን አይን አትውጉ! ሳናያት ሳናውቅ አልፋስ ቢሆን? የልጆቿን ዓይን ዓይታ ፤ ጠረናችሁን ስባ በትውልድ ቀዬዋ ሀገሬው ቤቱን ነቅሎ ወጥቶ በፍቅር የሸኛት እሰቡት አምላክ እንዴት ቸር እንደሆነ? ደግም አይደል?» ብሎ ተቆጥቶ አረጋጋን!! እንባችንን አቆምን እንጂ ለሚቀጥሉት ቀናት እንደተኳረፈ ሰው በመሃከላችን ብዙም የቃላት ልውውጥ አልነበረም። የሆነ ቀን ውጪ ሳሩ ላይ ተቀምጠን
«የኔ ኪዳን? አሁንም ከዚህ በላይ መቆየት ትፈልጋለህ?» አልኩት
«እኔ እንጃ ሜል! ወደ አዲስአበባ መመለስ ከፈለግሽ እንመለስ! እኔ አሁን ምን እንደምፈልግ ራሱ አላውቅም!!» አለኝ።