ዕንቁላል እና ፋሲካ
═══🥚═══
🥚
በእኛ ሀገር ዓመት በዓል ሲታሰብ ዶሮ ወጥ፤ ዶሮ ወጥ ሲባል ደግሞ ዕንቁላል አብሮ መነሳቱ አይቀርም። በእርግጥ በኛ ሀገር የዶሮ ወጥ ውስጥ ዕንቁላል ለመጀመሪያ ጊዜ የጨመረችው ወይዘሪት/ወይዘሮ ማንነት ባይታወቅም፣ በመላው ዓለም በተለያዩ ባህሎች ለዓመት በዓል ከዕንቁላል የተለያዩ ምግቦችን ማዘጋጀት የተለመደ ነው።
🥚
በዚህ በኩል በተለይም በክርስትናው ዓለም ከፋሲካ ጋር የተያያዘ ዕንቁላልን የማስዋብ፣ ዕንቁላል የመገባበዝና የመመገብ ባህል እንዳለ የታወቀ ነው። በተለይ በምሥራቅ አውሮፓ በተለያየ ሁኔታ ያሸበረቁ ዕንቁላሎችን ለፋሲካ በዓል ማዘጋጀት የተወደደ ተግባር ነው።
🥚
ለፋሲካ ዕንቁላልን አሸብርቆ መስጠትን በተመለከተ የተለያዩ መላ ምቶች ያሉ ሲሆን፣ ከእነሱ ውስጥ አንዱ ከሮማ ኢምፓየር ንጉሥ ከማርክ አውሬሊዮ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ አፈ-ታሪክ ንጉሡ በተወለደበት ቀን፣ አንድ የእናቱ ዶሮ ቀይ ነጠብጣብ ያለበት ዕንቁላል በመጣሏ ይህም ልክ የመልካም ብሥራት መገለጫ ወይም አመላካች ተደርጎ በመወሰዱ፣ ከዚያን ወዲህ ሕዝቡ ለመልካም ምኞት መግለጫ ተጠቀመበት የሚል ሲሆን፤ ሌላኛው ከክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ጋር የተያያዘ ነው።
🥚
በዚህም ታሪክ ክርስቶስ እንደሞተ አንድ ይሁዳዊ ቤተሰብ ግብዣ ላይ የተለያዩ ምግቦች ቀርበው፣ (ዶሮም ዕንቁላልም ከምግቡ ውስጥ ነበሩ) ሲጨዋወቱ ከታዳሚዎቹ፣ ስለ ክርስቶስ አንስቶ 'ከሦስት ቀን በኋላ ይነሳል' ማለት፤ ሌላኛው ደግሞ 'አሁን ፊታችን ያለው ዶሮ ነፍስ ከዘራ ዕንቁላሎቹም ቀይ ከሆኑ፣ ያኔ በክርስቶስ መነሳት አምናለሁ' ብሎ ሳይጨርስ ያኔውኑ ዶሮዋ ነፍስ ዘራች ዕንቁላሉም ቀይ ሆነ።
🥚
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀይ ዕንቁላል የትንሣኤ ምልክት ማረጋገጫ ተደርጎ ተወሰደ፣ ባህልም ሆኖ ተዛመተ። እኛም ምንም እንኳ ቀይ ቀለም ባንቀባውም፣ እንደ አቅሚቲ ቀይ ወጥ ውስጥ በመጨመር የጀመርነው ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሆን?
━━━━━━━━
✍ ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ
📔 ጤና ነገር እና ጉዳይ
🗓 2007 ዓ.ም.
📄 85
📖 📖 📖 📖 📖
https://t.me/Ethiobooks