በአምስተኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ 60 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ ማቅረቡን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነገ ረቡዕ በሚያካሄደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ፤ 60 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ ማቅረቡን አስታወቀ። በጨረታው መሳተፍ የሚፈልጉ ባንኮች የሚያቀርቡትን ዋጋ ነገ ከረፋድ አራት ሰዓት እስከ እኩለ ቀን እንዲያስገቡ ብሔራዊ ባንክ ጥሪ አቅርቧል።
ለነገ የታቀደው ጨረታ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለውጥ ካደረገች ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ወዲህ አምስተኛ ነው። ብሔራዊ ባንክ ባለፉት አራት ዙሮች ባካሄዳቸው ጨረታዎች፤ በድምሩ 355 ሚሊዮን ዶላር ለተሳታፊ ባንኮች አቅርቧል።
አቶ ማሞ ምህረቱ በገዢነት የሚመሩት ብሔራዊ ባንክ፤ “በየሁለት ሳምንት” ልዩነት ተመሳሳይ ጨረታ እንደሚያካሄድ ያስታወቀው ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ገደማ ነበር። በዚህ መልኩ የሚካሄደው ጨረታ እስከ 2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደሚካሄድ ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ አይዘነጋም።
በእነዚህ ጨረታዎች የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ መጠን፤ “በወቅቱ ያለውን የውጪ ምንዛሬ ፍላጎት በማገናዘብ” እንደሚሆን አቶ ማሞ ምህረቱ በዚሁ ወቅት ተናግረው ነበር። በዚህ መሰረት ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ በተካሄደው ጨረታ 50 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታ የቀረበ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ለአንድ ዶላር የቀረበው አማካይ ዋጋ 131.7 ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
በተመሳሳይ መልኩ በሚዝያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት በተካሄደ ጨረታ 70 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታ ቀርቧል። ለአንድ ዶላር በአማካይ 131.1 ብር በቀረበበት በዚህ ጨረታ፤ በጥያቄያቸው መሰረት ለ26 ባንኮች የውጭ ምንዛሬ መከፋፈሉን ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። የነገው ጨረታ ውጤት አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ይፋ እንደሚደረግ ባንኩ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
@EthiopiaInsiderNews