🌺
ክፍል ሁለት [፪] 🌺
✝ለምን ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ ወጣ?1⃣ጌታ "እሞታለሁ፤ እሰቀላለሁ" ባለው ጊዜ ጴጥሮስ "ልትሞት አይገባም፤ ይህ ላንተ አይገባም" ብሎ ተቃውሞት ነበርና በአብ ቃል "እርሱ ያላችሁን ስሙት፤ ይህ ለአንተ አይገባም አትበሉት፤ አትቃወሙት" ለማለት፡፡
2⃣ ጌታ "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ብሎ ደቀመዛሙርቱን በጠየቃቸው ጊዜ ጴጥሮስ "አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ" ብሎት ነበርና አሁንም አብ "አዎ ልክ ነህ! እመለክበት ዘንድ ለተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው ልጄ ይህ ነው" ብሎ ለማረጋገጥ፡፡
3⃣ ለፍቅሩ ስለሚሳሱ ነው፡፡ ይህም በዕብራይስጡ ኬፋ ፤ በግሪኩ ጴጥሮስ ፤ በግዕዙ ኰኲሕ (ዐለት) የተባለው የዮና ልጅ ስምዖን ጌታችን "እሞታለሁ" እያለ ሲናገር "እሞታለሁ" ማለቱ አስቀድመን እንደተናገርን "ለጌታ ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ ነው" ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡
ዮሐንስም በወንጌል "የጌታ ወዳጅ" ተብሎ ተጽፏል፡፡ ያዕቆብ ደግሞ ጌታን በእጅጉ እንደሚወደው በኋላ ታውቋል፡፡ ይኸውም "እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ?" ማቴ ፳፥፳ ሲባሉ "አዎ" ብሎ መመለሱና በዚህም በሄሮድስ ዘአግሪጳ ሰማዕት ሆኖ መሞቱ ምስክር ነው፡፡
4⃣በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ "ኃጥእ ሰው የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ያርቁታል" እንዲል ኢሳ ፳፮፥፲፫ እርሱን ጥሎ አሥራ አንዱን ወደ ተራራ ይዞ ቢወጣ ከምሥጢር ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት እንዳይል፡፡ ያም ባይሆን ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ለምን ይከለከላሉ ቢሉ አልተከለከሉም በርእሰ ደብር (በተራራው አናት) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጸው ምስጢር በእግረ ደብር (በተራራው ግርጌ) ለነበሩት ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል፡፡
ይህም በደብረሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠ ምሥጢር በከተማ ለነበሩት ለኤልዳድና ሙዳድ እንደተገለጠ ማለት ነው ዘኁ፲፩፥፳፮
✝ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?1⃣ በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን "በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀው" ሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም "ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም" ብሎት ነበር ዘጸ ፴፫፥፲፫-፳፫ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡
እንዲህ ማለቱ "አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ" ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡
2⃣ ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- "አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ" ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ "የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ" ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡
3⃣ በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?" ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል" ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡
4⃣ አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ ዮሐ፱፥፲፮ ፣ ፲፥፴፫ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡
5⃣ ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም ደግሞ አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡
6⃣ የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡
6⃣ ጽድቃቸው ከእነዚህ ከሙሴና ከኤልያስ የበለጠ ሊሆን እንደሚገባ ለማሳየት ማቴ፭፥፳ ምክንያቱም ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ቢመራ ምድረ ፍልሥጥኤምን ለማውረስ ነው፡፡ እነዚህ ግን ሕዝቡን መርተው የሚያስገቡት መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ኤልያስ ሰማያትን ቢለጉምም ከጊዜአዊ ዝናም ነው፡፡ እነዚህ ግን ለዘለዓለም መንግሥተ ሰማያትንም የመለጎም ሥልጣን አላቸውና፡፡
ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" ሲል ተደምጧል፡፡ ይህም የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ ቃል በቃል (Literaly) ስናየው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ "አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ እነዚህ መከራ ያደርሱቡኛል ይገድሉኛል ያልካቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዳይመጡ በደመና እየጋረደ፣ ቢመጡም አልያስ እሳት እያዘነመ እያባረራቸው በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው" ማለቱ ሲሆን ምሥጢራዊው መልእክቱ ግን.....
ክፍል ሦስት ይቀጥላል.....