የሴትልጅ ቁንጅና ምንድነው?
_______
(ውበትና ደም-ግባትስ?)
"ቁንጅና ምንድነው ሰዎች አስረዱኝ
እኔ እሷን ወድጄ ታምሜያለሁኝ...
ውበትና ቁንጅናሺ፣ ይማርካል ለሚያይሺ.."
- ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ
በየዘመኑ "የሴት ልጅ ውበት" የሚባለውን አስተሳሰብና መስፈርት ማን ፈጠረው? "ቆንጆ" ሴት ከቆንጆ ሰው በምን ትለያለች? ሴቶች በ"ሽንጥና ዳሌሽ ሲታዩ..." ዓይነት መስፈርቶች እንዲለኩ የበየነላቸው ማነው?
ወንዶች ሴቶችን የሚስሉበት መንገድ ከስሜት ጋር የተያያዘ ለምን ሆነ? ከወሲባዊ መስህብ አሊያም ከመራባትና ከእናትነት አስተሳሰቦች ውጭ ሊታሰብ የሚችል የሴት ልጅ ሰብዓዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ከየማኅበረሰቡ አንጎል የተነነው በምን ምክንያት ነው?
ውበት ምንድነው? ደርባባነትን ከሴት ልጅ ለምን እንድንጠብቅ ሆንን? በዘመናት ውስጥ የተቸራቸውን ማኅበራዊ ተክለሰብዕናና የተሰጣቸውን ሚና ለመጫወት እምቢ ያሉ ሴቶች ዕጣፈንታ ምንድን ነበር? አሁንስ ምንድነው?
ወንዶች በጥቅሉ ለሴቶች ያለን ዝንባሌ በጎችንና ፍየሎችን ሽንጣቸውን ለክተን፣ ጥርሳቸውን ፈልቅቀን፣ ሸሆናቸውን መትረን ለመግዛት ከምንሄድበት መንገድ ብዙም ያልተለየ ሆኖ የሚገኘው በምን የተነሳ ነው? ተፈጥሯዊ ነው? ወይስ ማኅበራዊ?
የሴቶች ተፈጥሯዊ ሰዋዊ አገልግሎት ምንድነው? ብለን ነው የምናስበው? ለምን?
የሴትን ልጅ አካላት ዕርቃን እያወጡ የተሳሉ አያሌ ክላሲካልና ሞደርን የጥበብ ሥራዎች (ሥዕሎች፣ ቅርፃቅርፆች፣ ስነፅሑፎች፣ ሙዚቃዎች፣ ወዘተ.) ለምን በየዓለሙ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኑ?
የሰውልጅ ሴትን ልጅ ከsensual pleasure ውጭ ለማሰብ ያልቻለበት አብይ ምክንያቱ ምንድነው? ሴቶችስ ራሳቸውን ከመኳኳልና ከማጊያጌጥ፣ ሽንጥና ዳሌያቸውን ከማጉላት፣ ፀጉራቸውን ከመሾረብና በአልባሳት ከመሸለም ውጭ ያለውን ጥልቅ የራስ ማንነታቸውን ለመፈለግ ብዙ ዝንባሌ የማያሳዩት ለምንድነው?
በሴትነት ውስጥ ከማኅበራዊው መስፈሪያ ሚዛን የማፈንገጥ ዋጋው ምን ያህል ነው? ይህች ዓለም የማን ዓለም ነች?
እውን It's a man's man's world እንደሚባለው.. ዓለማችን የወንዶች ብቻ ዓለም ነች? ከሆነች ሴቶች የተነጠቀ ሙሉ የሰውነት ክብራቸውንና ዋጋቸውን ለማስመለስ ምን ያድርጉ?
የፆታ አስተሳሰባችን በምን በምን ነገሮቻችን ውስጥ ሥር እንደሰደደ፣ እስከ ምን ከፍታ እንዳሻቀበና እንዴትስ ተብሎ እንደተድበሰበሰና እንደተሸነገለ ልብ ብለን አስተውለነዋል?
ሴትነት ምንድነው? ወንድነትስ? ውበትስ? የሴት ልጅ ውበት ምንድነው? ሴትን ልጅ ያለ ጭንና ባቷ ለማሰብ ፈቃደኝነቱ ያለው ወንድ ከመቶ ስንት ፐርሰንት ነው? ራሷን ከቀሚሷ ውጭ አድርጋ ማሰብ የምትችልስ ሴት ከመቶ መሐል ስንት ትገኛለች?
የነዳጅ ዘይትን የሚተኩ በርከት ያሉ የኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂ ተገኝተዋል በዘመናዊዋ ዓለማችን። ግን የዔለም ኢንዱስትሪ ሁሉ ከነዳጅ ጋር የተያያዘ ነው። ዲዛይኑ፣ ሸቀጡ፣ ንግዱ፣ ኢኮኖሚው፣ ቴክኖሎጂው፣ መኪናው፣ መርከቡ፣ አውሮፕላኑ... ሁሉ ከነዳጅ ጋር የተሳሰረ ነው። በዚህ የተነሳ ዓለም የሚያውቀውንና ህልውናውን የመሠረተበትን ኋላቀሩን ነዳጅ ዘይት መተው አይፈልግም። የሴት ልጅ ውበትስ ተመሣሣይ ነገር ይኖረው ይሆን?
በዓለም ሁሉ "የሴቶችን ውበት" መሠረት አድርገው የሚመረቱ ምርቶች፣ ዲዛይኖች፣ ፅሑፎች፣ ሳይንሶች፣ ፊልሞች፣ ኢንደስትሪዎችና ማኅበራዊ አወቃቀሮች... ባንዴ ተንደው እውነተኛ የሴቶችን ሙሉ ሰውነትና ክብር ወዳረጋገጠ ዘመናዊ አስተሳሰብ መሻገር ይችላሉ? የሚቻል ነው? ሴቶች ቂጥና ፊታቸው እየታየ የሚመዘኑበት ዘመን እስኪያበቃስ ስንት ዓመት ይፈጃል?
ይህ የናዖሚ ዎልፍ መፅሐፍ ላለፉት 3ሺህ ዓመታት የተቀነቀኑ የስነውበት ፍልስፍናዎችን፣ ሳይንሶችንና አስተሳሰቦችን እጅግ ጥልቅ በሆነ መንገድ ይቃኛል። አጥብቆ ይሄሳል። እና የውበትን ትርጉም እንድንፈትሽ ያስገድዳል።
ሴቶች ከወንዶች የውበት መስፈርት ራሳቸውን ማላቀቅ አለባቸው፣ ነፃ መውጣት አለባቸው ትለናለች።
በምጥን ፈገግታዋና በመርገፍ ቀሚሷ ዓለምን የምታማልለው ሞናሊዛ የኋላቀሩ ዘመን ማስረጃ ሆና ተቀድዳ የምትጣልበት፣ የፒካሶና የሌሎች በዓለም የተደነቁ የእርቃን ሴቶች ሥዕሎችና ኃውልቶች ተጠራርገው ወደ ቆሻሻ ቅርጫት የሚጣሉበት፣ የሴት ልጅን ሉዓላዊነት ያከበረ፣ ኮርማዊውን የወንዶች ዓለም የገረሰሰ፣ አዲስ የሴቶች ነፃነት ዘመን መበሠር አለበት ትላለች።
ከዚህ በፊት "ዘ ሴክስ ኦፍ ቲንግስ" የሚል አስገራሚ መሠል ይዘት ያለው በአንዲት ጀርመናዊት-እንግሊዛዊት ሪሰርቸር ዶክተር የተፃፈ አንድ ዳጎስ ያለ መፅሐፍ አግኝቼ ስገረምና የያዝኳቸውን ሁሉ የሴትልጅ አስተሳሰቦች ስሞግት ቆይቼ ነበር።
ይህን መፅሐፍ ካነበብኩ በኋላ ደግሞ ብርቱካን ከንፈርሽ፣ ብርንዶ ትንፋሽሽ፣ የዘንባባ ማር ይመስላል ፍቅርሽ፣ ፅጌረዳ ስላንቺ ልጎዳ፣ ሐር ይመስላል ፀጉርሽ፣ ሎሚ ተረከዝሽ፣ ስልታዊ ውዝዋዜሽ፣ ዓይናፋርነትሽ፣ ችቦ አይሞላም ወገብሽ፣ ካንቺ ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት፣ እና አንቺን ያለውን በቴስታ ጥርሱን🤩... የመሣሰሉትን የምወዳቸውን የሙዚቃ ስንኞች ከአዕምሮዬ ለማጥፋት ምን ዓይነት ላጲስ መጠቀም እንዳለብኝ በማሰላሰል ላይ ነኝ🤓!!!
ይህች ደራሲና ተመራማሪ፣ ሶስተኛው የፌሚኒዝም አብዮት ተብሎ የሚጠራውን አስተሳሰብ ያፈለቀችና ለዓለም ያስተዋወቀች ጉምቱ ምሁር ስለመሆኗ ከተለያዩ ዜና መወድሶች ለመረዳት ችዬአለሁ።
ለማንኛውም ሃሳቦቿ የያዝካቸውን የሴት ልጅ ውበት ኮተቶች ሁሉ ያስጥሉሃል። ግን ፍራቻዬ ያለንን አስጥላን... በምትኩ የምትሰጠን ውበት ምን ዓይነት እንደሆነ ደራሲዋም ራሷ በትክክል ያወቀችው አልመሠለኝም።
ሽንጥና ዳሌሽ ሲታዩን ትተን... ወደ ምን እንሻገር? ውብ የምንላትን ሴት ከየት እናግኛት? ከስንደዶ አፍንጫና ከማር ከንፈር ውጭ ያለችዋ ቆንጆ ሴት ማነች? ከወዴትስ ትገኛለች? እውን አለችስ ወይ በዓለም ላይ? ሴቶቹ ራሳቸውስ ይቀበሏታል?
ደራሲዋ የምትሰብከን ሴቶች ከሙክትነትና ከጌጥነት አሊያም ከስሜት ማስተንፈሻነት የወረደ የወንዶች አስተሳሰብ ነፃ የሚወጡባት ዓለምስ እውን በዚህ የቅርብ ዘመን ትውልድ እውን ሆና እናያት ይሆን? ...
የወንዶች አሽኮርማሚነት፣ እና የሴቶች ተሽኮርማሚነት አብቅቶ፣ ማንም ማንንም የማያሽኮረምምባትን ዓለም የምናየው መቼ ነው? መቼ ነው ያቺ የፍፃሜ (ዋንጫ) ቀን መምጫዋ? ምን ምልክትስ እንጠብቅ?
ወንድሜ (እና እህቴ🤩)... በበኩሌ ጥይቴን ጨርሼያለሁ!
አሰፋ ሀይሉ ✍