ጥር ፭ /5/
በዚች ቀን በከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን የከበረ አውስግንዮስ ምስክር ሁኖ ሞተ።
ይህም ቅዱስ አውስግንዮስ እድሜው መቶ ዐሥር ዐመት እስከ ሆነው ከቈስጠንጢኖስና ከልጆቹ ዘመነ መንግሥት በኋላ እስከ ከሀዲው ዑልያኖስ ዘመን ኖረ።
በአንዲት ዕለትም በአንጾኪያ ከተማ በአደባባይ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አግኝቷቸው ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላም ሊያአደርግ ወዶ አስታረቃቸው በመታረቃቸውም ደስታ አደረጉ እርሱ የከበረ አረጋዊ ሰው ነውና።
ከዚያም አንድ ክፉ ሰው ወደ ንጉሥ ዑልያኖስ ሒዶ ነገር ሠራበት እንዲህም አለው አውስግንዮስ በራሱ ፈቃድ ገዥና ፈራጅ ዳኛ ሆነ። ንጉሥም ይህን ቅዱስ ወደርሱ አቅርቦ ገሠጸው ገዥና ፈራጅ ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማነው አለው።
የከበረ አውስግንዮስ መልሶ ነፍስህ በእጁ የተያዘች የእግዚአብሔርን አምልኮት ትተህ አንተ ለረከሱ ጣዖታት ለምን ሰገድክ ከአንተ በፊት የነበሩ ነገሥታትን ለምን አልተከተልካቸውም እኔም እንዳንተ ወታደር ሁኜ ከቈስጠንጢኖስ ጋር ሃያ ዓመት ኖርኩ ከልጆቹም ጋር ነበርኩ ከእነርሱ ውስጥ እንዳንተ ያለ ጠባየ ክፉ የለም አለው።
ዑልያኖስም በቅዱስ አውስግንዮስ ላይ እጅግ ተቆጣ ይሰቅሉት ዘንድ በጐኖቹም ውስጥ መብራቶችን አስገብተው እንዲለበልቡት አዘዘ እርሱም ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህን ሁሉ ታገሠ።
ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ወታደሮችም ሊቆርጡት በመጡ ጊዜ እስኪጸልይ ይታገሡት ዘንድ ለመናቸው ጸሎቱንም ሲፈጽም የከበረች ራሱን ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
💚 @ortodoxmezmur 💚
💛 @ortodoxmezmur 💛
❤️ @ortodoxmezmur ❤️