ጾመ ነነዌ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአጽዋማት ቀኖና መሠረት ሰባት የዐዋጅ ጾም አጽዋማት አሉ። ከሰባቱ አጽዋማት አንዷ በዕለታት ተወሳክና በዓመቱ መጥቅዕ ድምር ውጤት ወይም በመባጃ ሐመር የምትውለዋ ጾመ ነነዌ ናት።
ጾመ ሰብአ ነነዌ (የነነዌ ሰዎች ጾም) የምትጾመው ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሙ የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፉ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ድረስ ነው፡፡ በእነዚህ ፴፭ ቀናት/ዕለታት/ ስትመላለስ ትኖራለች፡፡ ከተጠቀሱት ዕለታት አይወርድም፤ አይወጣም ማለት ነው፡፡ በዚህም ቀመር መሠረት የ፳፻፲፯ ዓ.ም ጾመ ነነዌ የካቲት ሦስት ጀምሮ በአምስት ያበቃል፡፡
ጾመ ነነዌን የጾሙት በነነዌ የሚኖሩ ሰዎች በአምላካችን እግዚአብሔር ትእዛዝ እና በነቢዩ ዮናስ ነጋሪነት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ በኃጢአታቸው ምክንያት ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት አምላካችም ነቢዩ ዮናስ መክሮ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ሕዝብ እንዲሄድ አዘዘው፡፡ (ዮናስ. ፬፥፲፩)
እግዚአብሔርም “ሄደህ በነነዌ ላይ ስበክ” ባለው ጊዜ “አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔር ግን ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩት ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ “በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ” ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም “የሰው ደም በእጃችን እንይሆንብን አይሆንም” ብለው ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ነጋድያኑም ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያው የእግዚአብሔርን የማዳን መልእክት ዮናስ እንዲያደርስ፣ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ነነዌ አደረሰው፡፡
ዮናስም ከእግዚአብሔር መኮብለል አለመቻሉን ሲረዳና ነነዌ መሬት ላይ መድረሱ ሲነገረው ለነነዌ ሰዎች “ንስሐ ግቡ” ብሎ መስበክ ጀመረ፤ (ዮናስ ፩ እና ፪)፡፡ መጀመሪያ ከተልእኮው ቢያፈገፍግም “ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፦ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ” እንደተባለው ነቢዩ ዮናስ የኋላ ኋላ ወደ ነነዌ ሄዶ የእግዚአብሔርን መልእክት ዐውጇል። (ዮናስ ፴፫፥፬) በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎችም እንዲህ አደረጉ፤ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም ዐዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ” (ቁጥ.፭) እንዲል፡፡
መጽሐፉ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር እንደማራቸው ይገልጻል፡፡ (ዮናስ ፫) ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መሆኑን አምላካችን ቅልን ምሳሌ በማድረግ አስረዳው፡፡ (ዮናስ ፬) ነቢየ ሐሰት እንዳይባልም ለቅጣት የመጣው እሳት እንደ ደመና ሆኖ ታይቶአል፡፡ የታላላቅ ዛፎች ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ የእሳቱ ወላፈን ነክቷቸው ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ በንስሐ በጾምና ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ከጥፋትና መዓት ድነዋል።
እኛንም ካለንበት መከራ፣ ችግርና ሥቃይ እንዲያወጣን፣ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንዲያኖረን እንደ ነነዌ ሰዎች ንስሐ እንግባ፤ በጸሎት፣ በጾምና በበጎ ምግባር ተወስነን በሃይማኖት እንጽና!
አምላካችን እግዚአብሔር ቸርነቱን ያብዛልን፤ አሜን!
#ጸሎተ ዮናስ ነቢይ
ጸራኅኩ በምንዳቤየ ኀበ እግዚአብሔር አምላኪየ
ወሰምዐኒ በውስተ ከርሠ ሲኦል
ወሰምዐኒ ቃልየ
ወገደፈኒ ውስተ ማዕምቀ ልበ ባሕር
ወአፍላግኒ ዐገቱኒ
ኵሉ ማዕበልከ ወሞገድከ እንተ ላዕሌየ ኀለፈ
ወእቤ ተኀጐልኩኑ እንጋ እምቅድመ አዕይንቲከ
ሀሎኩኑ እርአይ ጽርሐ መቅደስከ
አኅዘዘኒ ማይ እስከ ነፍስየ
ወቀላይኒ መልዐኒ
ናሁ ርዕስየ ውስተ ጥንቃቃተ ደብር
ወወረድኩ ውስተ ምድር ከመ መልሕቅ ታሕተ
ትዕርግ ሕይወትየ ዘእንበለ ሙስና ኀቤከ እግዚኦ አምላኪየ
ሶበ ኀልቀት ነፍስየ ተዘከርክዎ ለእግዚአብሔር
ትብጻሕ ጸሎትየ ቅድሜከ ጽርሐ መቅደስከ
እለሰ ዐቀቡ ከንቶ ወሐሰተ ገደፉ ሣሕሎሙ
አንሰ ምስለ ቃለ ስብሐት በተጋንዮ እሠውዕ ለከ
መጠነ ጸለይኩ በሕይወትየ አዐሥዮ ለእግዚአብሔር
https://t.me/mkpublicrelationበማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀና edit የተደረገ
✝ኦርቶዶክስ ተዋህዶ✝
#መልካም_እለት
https://t.me/OrtoPicturehttps://t.me/OrtoPicturehttps://t.me/OrtoPicture