👉 የመሬት መንቀጥቀጥ
የመዲናችን አዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢ ነዋሪዮች ለሊቱን በጭንቀትና በስጋት ከህንፃዎች ወርደው መሬት ላይ ሆነው የሚሆነውን እየተጠባበቁ እንደ ነበር ሚዲያዎች ዘግበዋል ። ይህም የሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክት በመታዩቱ መሆኑን አስረድተዋል ።
የመሬት መንቀጥቀጥ ማለት መቅሰፍት ሲሆን ሚዲያ ላይ አንብበንና ሰምተን ከሚሰማን ስሜት ፍፁም የማይገናኝ አላህ ባሮቹን ሊያስፈራራበት ፣ ወደርሱ እንዲመለሱና ካሉበት የአመፅ ማእበል ወጥተው ከሱ ጋር እንዲታረቁ የሚያደርግበት ነው ። ሲከሰት ነገሮችን በሽርፍራፊ ሰከንዶች ውስጥ ወደ አለመኖር ፣ የሰዎች መኖሪያዎችን ወደ ቀብርነት ፣ ሽማግሌ ህፃናት እናቶችና አረጋዊያን የጣር ድምፅ እያሰሙ የዘረጉት የአድኑኝ እጃቸው ደራሽ አጥቶ በሲቃ የሞት ፅዋ ተጎኝጭተው በፍርስራሽ ስር እንዲቀሩ የሚያደርግ ፣ ሰው መሸሻና መግቢያ አጥቶ የሚያተርፍና የሚተርፍ ሳይኖር ሁሉም በተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ሆኖ ወዳልተቆፈረ ቀብር መግባቱን የሚያረጋግጥበት ፣ ማንም ማንንም ማዳን የማይችልበት ከተማ ከያዘችው ነገር ጋር ላይዋ ታች ታችዋ ላይ የሚሆንበት አስፈሪ መቅሰፍት ነው ።
ለፉጡራን አንድ እናት ለጨቅላ ልጇ ከምታዝነው በላይ አዛኝ የሆነው አምላካችን አላህ እንዲህ አይነት መቅሰፍት የሚያመጣው አመፅና ሀጢያት ሲበዛ መሆኑን በተለያዩ መለኮታዊ ቃሉ ይነግረናል ። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተለው ቃሉን እንመልከት :–
« ظَهَرَ الْفَسَادُ فِي الْبَرِّ وَالْبَحْرِ بِمَا كَسَبَتْ أَيْدِي النَّاسِ لِيُذِيقَهُم بَعْضَ الَّذِي عَمِلُوا لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ»
زالروم ( 41 )
" የሰዎች እጆች በሠሩት ኃጢኣት ምክንያት የዚያን የሠሩትን ከፊሉን ያቀምሳቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባሕር ተገለጠ፤ (ተሰራጨ) ፡፡ እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና " ፡፡
እንደዚህ አይነት ምልክቶችን የሚልከው ሰዎች ፈርተው ከሀጢያት ርቀው ወደርሱ እንዲመለሱ መሆኑንም እንዲህ ብሎ ይነግረናል : –
« وَمَا مَنَعَنَا أَن نُّرْسِلَ بِالْآيَاتِ إِلَّا أَن كَذَّبَ بِهَا الْأَوَّلُونَ ۚ وَآتَيْنَا ثَمُودَ النَّاقَةَ مُبْصِرَةً فَظَلَمُوا بِهَا ۚ وَمَا نُرْسِلُ بِالْآيَاتِ إِلَّا تَخْوِيفًا »
الإسراء ( 59 )
" ታምራቶችንም ከመላክ የቀድሞዎቹ ሰዎች በእርሷ ማስተባበልና (መጥፋት) እንጂ ሌላ አልከለከለንም፡፡ ለሰሙድም ግመልን ግልጽ ተዓምር ኾና ሰጠናቸው፡፡ በእርሷም በደሉ፡፡ ተዓምራቶችንም ለማስፈራራት እንጂ አንንልክም " ፡፡
አላህ በዚህ አንቀፅ በመካ ከሀዲያን ላይ ተአምራትን ከመላክ የከለከለው ከዛ በፊት የነበሩ ህዝቦች ተአምር መጥቶላቸው አለማመናቸውና በዚህም ምክንያት መጥፋታቸው መሆኑና የመካ ከሀዲያንም ተአምር መጥቶላቸው ካላመኑ ሊጠፉ መሆኑን ከነገረን በኋላ ተአምር የሚልከው ሰዎች ፈርተው እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሆነ ነው ።
በምድር ላይ የመሬት መንቀጥቀጥም ይሁን አውሎ ንፋስ ወይም የውሀ ሙላት አሊያም ወረርሽኝ የሚከሰተው በግልፅ የሚሰራ ወንጀል ሲበዛ ነው ። ሰዎች ወንጀልን በግልፅ ሲሰሩና ተዉ የሚል ሲጠፋ አላህ መቅሰፍትን ያመጣል ። መቅሰፍት ሲመጣ ወንጀለኞቹን ብቻ ነጥሎ አይመታም ። በወንጀል ላይ ምንም አስተዋፆ ያልነበራቸውንም ህፃናትን ፣ እንሰሳትንና ንፁሀንንም ጭምር ነው ።
ይህንንም አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ብሎ ይነግረናል : –
« وَاتَّقُوا فِتْنَةً لَّا تُصِيبَنَّ الَّذِينَ ظَلَمُوا مِنكُمْ خَاصَّةً ۖ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ »
الأنفال ( 25 )
" ከናንተም ውስጥ እነዚያን የበደሉትን ብቻ ለይታ የማትነካን ፈተና ተጠንቀቁ ፡፡ አላህም ቅጣቱ ብርቱ መኾኑን እወቁ " ፡፡
በመሆኑም ይህ በመዲናችን የታየው የመሬት መንቀጥቀጥ ምልክት የማንቀያ ደወል ነውና እንጠንቀቅ ። መጠንቀቅ ማለት በሙሶሶ ስር መደበቅ ሳይሆን ከግልፅ ወንጀልና ሀጢያት በመራቅ ወደ አላህ መመለስ ነው ። በግልም በጀማዓም ከሚሰራ ሀጢያት መራቅ የሚሰሩትን ተዉ ማለት ብቸኛው አማራጭ ነው ።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ላይ እየተሰራ ያለው ሀጢያት ህዝቡ ተዉ ብሎ ማስቆም ካልቻለ ራሱን ከአላህ ለሚመጡ መቅሰፍቶች ማዘጋጀት ይኖርበታል ። ከእነዚህ መቅሰፍት ከሚያመጡ ሀጢያቶች ዋና ዋናዎቹ የጣኦት አምልኮ ፣ የወንድ ለወንድ ወይም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ፣ የግፍ ግድያና የመሳሰሉት ይገኝበታል ።
አላህ በመልካም አዞ ከመጥፎ ከልክሎ ከሚድኑት ያድርገን ።
http://t.me/bahruteka