"ሲጥል" የእንዳለጌታ ከበደን ልብወለድ በጨረፍታ
ሽብሩ ተድላ (ኤመረተስ ፕሮፌሰር)
በእንዳለጌታ ከበደ (PhD.) የተደረሰው "ሲጥል" ተብሎ የተሰየመው ልብወለድ፣ ርእሱን ያገኘው፣ በመጽሐፉ ውስጥ የተወሱ ገጸ-ባህርያት፣ "ደብረ ሠምራ" ለመሄድ አስበው "ዐሊይ" ወደ ምትባል ትንሽ የገጠር ቀበሌ ስለተጓዙ ይመስለኛል፣ ያንን ዓይነት ስያሜ (ቀን ሲጥል ዓይነት) የተሰጠው፡፡ ደራሲው አሥራ ሁለት ገደማ በሆኑ ቀጥተኛ ገጸ-ባህርያት፣ በተጓዳኝ የጎላ ሚና ያሏቸው ስድስት ገደማ እና በጨረፍታ የሚወሱ አሥር ገደማ የሚሆኑ ገጸ-ባህርያት፣ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን በጎ እንዲሁም ኋላ ቀር ተብለው የሚፈረጁ ጎኖችን ሁሉ ያመላክታል፡፡
በ"ሲጥል" ልቦለድ ያልተዳሰሰ የሰው ልጅ ባህርይ ያለ አይመስልም፡፡ ባህርያቱ ሁሉ የሚገለጡት ለሃያ አንድ ቀናት ሳይፈልጉ አብረው በሰነበቱበት ሁኔታ ነው፡፡ ማታ ማታም፣ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ባለመኖሩ፣ እማምሻ ሻይ ቤታቸው ተሰባስበው ዕጣ እየተጣጣሉ፣ በደረሳቸው ዕጣ አማካይነት በትረካ መሳተፋቸው፣ እርስ በርስ የመተዋወቅ አድማሶቻቸውን አስፍቶላቸዋል፡፡
በቆይታቸው ከተሜዎችን የገጠር አባባል ዘይቤዎች ሳያስገርሟቸው አልቀሩም፣ የገበሬ ማኅበር ሊቀመንበሩ "ቢከፋም ቢለማም አታምሹ"፣ "ቢከፋም ቢለማም ከፀጉረ-ልውጦች ጋር አትገናኙ...."፣ "ቢከፋም ቢለማም…."፡፡ የሴቶች ፀጉር አሠራርም ከእድሜ ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንዷ ለገጠር እንግዳ ስታስረዳት ስናነብም ባህል በየፈርጁ…ያስብለናል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸው አጥር ሳይኖረው፣ አጥር እንዳለው አድርገው አስበው ለትምህርት ቤቱ ደንብ መገዛታቸው…የዐሊይ ማኅበረሰብ ለመራቂነትና አስታራቂነት የሚመርጠው ከዚህ ቀደም ወንጀል ሰርቶ በበቂ ፍርዱን ጨርሶ የወጣ ሰው መሆኑ… ‹‹ተፈርዶበት ከሆነና ቅጣቱን በሰላም ማጠናቀቁ ከተረጋገጠ ማኅበረሰቡ ለእሱ አድሮበት የነበረውን ቅሬታ ማንሳቱን የሚያሳምነው እንዲህ ባለው አጋጣሚ ከበሬታ ሲቸረው ነው፡፡›› ይለናል "ሲጥል"፡፡ ሌላም ሌላ…ያልተለመዱ አኗኗሮችና ጥልቅ ህይወት ፍልስፍናዎች…
ገጸ-ባህርያቱ የየራሳቸው የዓለም እይታ አላቸው - ዓለም ጉራማይሌ ናት እንደሚባል፡፡ እንዲያም ሆኖ የሚያገናኛቸው ጉዳዮች አሉ፣ በጉዞ ላይ የነበረ ሥጋትና በባልፈለጉት ቦታ አንድ ላይ መገኘታቸው፡፡
የተለያዩ ገጸ-ባህርያትን ለምሳሌ ፍቅርና ጥላቻ፣ ሃይማኖታዊ እምነትና በአንፃሩ ምትሃታታዊ አምልኮት፣ የወቅቱ የመታገት ስጋት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት ወሲባዊ፣ አንዲሁም በስልጣን መባለግ፣ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የብሔር ጋብቻ፣ ክፋትና ደግነት፣ መከፋትና መደሰት፣ አክብሮትና ንቀት፣ በራስ መተማመን እና በራስ እምነት ማጣት፣ የወገን ፍቅር ጥማት (ራሷ እየገዛች የምትለብሰውን ወንድሜ የላከልኝ ነው እያለች ለጎረቤት የምታሳውቀዋን እናት ልብ ይሏል)፣ ሌሎችም የእኛ መጥፎ እድል ገጥሟቸዋል ብሎ የምስራች ማብሰር መሯሯጥ፣ ወዘተ፣ የሚወክሉ ግለሰቦችም በውይይት ላይ ባህሪዎቻቸውን ገላጭ የሆኑ አረፍተ ነገሮች ሲሰነዝሩ፣ እንደ ተራ ጉዳይ፣ የቀን ተቀን ሁኔታ፣ ተግባር አድርገው ነበር የሚያወሩ፡፡
ግለሰቦች ቦድነው በማይረባ ጉዳይ መነታረክ፣ "የቴዎድሮስ ሳልሳዊ ጉዳይ"፣ የኛ ነው የኛ ነው የማለት ብሎም ስር የሰደደ ጸብ መቀስቀስ፡፡ በፖለቲካ ተዋናይነት ከሚገባ በላይ ራሱን አንቱ ብሎ፣ ያንን ለዘላለም ሲያነሱ መገኘት አንዱ የዘመናችን ችግር ነው፣ ያም ተወስቷል (አቶ ሥዩም በሟች በአቶ ዘላለም ተነጠቅሁ የሚሉት ዝና)፡፡ የፍቅር መግለጫ ሆኖ የተሰነደው ቤርሳቤህ ለተለያት ፍቅረኛዋ ለምንተስኖት ጥላለት የሄደችው፣ እሱ ይወደው የነበረ እርሷም የምትኩራራበትን ዘንፋላ ፀጉሯን ተላጭታ ከመቃብሩ አፈር ጋር ቀላቅላ መሰናበቷስ? ሁሉንም ሁኔታዎች ደራሲው በአጫጭር አረፍተ ነገሮች፣ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡
ለአዲሱ ትውልድ እንግዳ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ ኋላ ቀር እምነቶችም ተወስተዋል፣ ለምሳሌ የመሪጌታ ሐብቴ እና የኢዩዔል ተግባራት፣ "የትኩስ የመቃብር አፈር በመበተን የተኛን ከእንቅልፉ እንዳይነቃ ማድረግ"፣ "ጅብ ጋላቢ ቡዳ"፣ "የድመት ቂመኝነት፣ እንዲሁም መጥፎ ዕድል አመልካችነት"፣ "ለአንድ ግለሰብ የመጣን የሞት እጣ ወደ ሌላ ግለሰብ ማሸጋገር"፣ "ትላልቅ ወንዞች የመናፍስት ሰፈሮች ስለመሆናቸው"፣ የሞተን ሰው ቀስቅሶ እንዴት እንደተገደለ ራሱን ሟቹን ቀስቅሶ ስለመጠየቅ …ወዘተ፡፡ አንዱ ኩነት፣ ኩነቱ በሚነካቸው ገጸ-ባህርያት ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ማድረስ፣ ለእናት የስጋት ምንጭና ምስጢራዊነት፣ ላልወለደ አባት የጥንካሬ ምንጭ፣ ልጁ የእሱ አለመሆኑን እያወቀ ሚስቱን እንዳይከፋት፣ ብሎም ልጇን ይዛበት እንዳትሄድ፣ እንዳላወቀ ሆኖ መታየት፣ ለልጅ የዘላለም ጠንቅ ሆኖ የዘለቀ፣ በመጨረሻ ራሱን ለማጥፋት ምክንያት መሆን፡፡
ብዙ ፍልስፍና አዘል ጥልቅ አስተያየቶችም ቀርበዋል፣ ለምሳሌ "ከቁርበት ጋር መምከር (ይደር እንደማለት)"፣ ለማኙ ለተለማኝ የወረወረው አረፍተ ነገር "አንተ እንድትረዳኝ የግድ መዝረክረክ፣ መንገፍገፍ.....መቆሸሽ... ነበረብኝ?" … "መዋደድ ብቻውን አብሮ ለመኖር በቂ አይደለም"፣ "ፍቅር ብቻውን ግጥም የሌለው ዜማ ነው"፣ "ያልተፈተነ አያልፍም"፣ የደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር "የነፃነት" ግንዛቤ፣ ወዘተ፡፡
ብዙ ዱብዳዎችም ተወስተዋል፡፡ ለብዙ ዓመት እናቷን ያላየች ልጅ፣ እናቷን ስታገኛት የእናቷን ሴት አዳሪ መሰል ሆና መታየት፣ ያም ሁኔታ በቅናት መንስዔ በራሷ ጓደኛ የተቀናጀ ሴራ መሆኑን ከጊዜ በኋላ መገንዘብ… ከሃያ ዓመት በላይ አባቴ እገሌ ነው ብሎ የኖረ ልጅ፣ ድንገት አይቶት የማያውቀው ሰው አባትህ ነኝ ብሎ መምጣት ወዘተ፡፡
አልፎ አልፎ አረፍተ ነገሮች፣ ሙዚቃ አዳባሪ መሰል፣ ከሩቅ የሚሰማ አታሞ/ከበሮ ድምጽ ስሜትን በአንባቢው ላይ ይጭራሉ፡፡ "ድፍረት እንደ አንበሳ፣ ስርቆት እንደ ቁራ፣ ፍጥነት እንደ ንስር…"፣ "የተፋታ ሁሉ የተጣላ፣ አብሮ የሚኖር ሁሉ ፍቅረኛ…"፣ "ከምላስ ላይ ምራቅ፣ ከአንገት ላይ ንቅሳት…"፣ "እናቷን ስታገኝ፣ የዛገ ብረት እንደማሽተት፣ የሻገተ እንጀራ እንደመብላት፣ ክፍቱን ያደረ ውሃ እንደመጠጣት ዓይነት ስሜት…" ... መሰል የቃላት ስብጥሮች፡፡
አንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎችም ተወስተዋል፡፡ "ቀውስጦስ" የተባለ መልዓክ፣ የፈጣሪውን ትዕዛዝ፣ ለመፈጸም ርህራሄው ስለገታው በአምላክ ተቀጣ፤ ክንፉ ተሰበረ፤ ብሎም የመብርር አቅሙን ተነጠቀ፤ በአማላጅ ከዓመታት በኋላ በፊት እንደነበረው ለመሆን በቃ፡፡ ይህን ስናነብ ምነው ብዙ "ቀውስጦስ" መሰሎች የፈጣሪ መልእክተኞች በዚህ ዓለም ቢኖሩ ኖሮ? ያሰኛል፡፡
አንባብያን የእንዳለጌታ ከበደን "ሲጥል" በጥሞና ካነበቡ፣ ስለ ሕይወት ገጠመኞች ብዙ ግንዘቤ፣ ብሎም ስለ ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች የሕይወት መመሪያ ሊሆን የሚችል ዕውቀት እንደሚያገኙ አምናለሁ፡፡ መጽሐፉን ማንበብ ይጠቅማል፤ ይበጃልም፣ እላለሁ!
ከአዘጋጁ፡-