ለቸኮለ! ዓርብ፣ መስከረም 15፣ 2019 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች
1፤ ሕወሃት፣ በትግራይ ክልል የኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ትዕዛዝ መስጠቱን ከታማኝ ምንጮች መስማቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘገበ። በክልሉ ከትናንት ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ የኢትዮ ቴሌኮም የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ተቋርጠዋል። የኢንተርኔት ነጻነትን የሚከታተለው ኔት ብሎክስም፣ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ መስተጓጎሉን ገልጧል። ኾኖም ኢትዮ ቴሌኮምም ኾነ የትግራይ ባለሥልጣናት የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ለምን እንደተቋረጡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ምሽት ድረስ ማብራሪያ አልሠጡም።
በሌላ በኩል፣ የትግራይ ቴሌቪዥን ከዛሬ ጧት ጀምሮ የበይነ መረብ ሥርጭቱን አቋርጦ ውሏል። በክልሉ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች መቋረጣቸውን ተከትሎ፣ ጣቢያው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዛሬ ምሽት 2 ሰዓት ድረስ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዜናዎችንም ኾነ ሌሎች ዝግጅቶችን አላሠራጨም።
2፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከወልድያ ወደ ጋሸና እና ደሴ ከተሞች የሚወስደው ዋናው የአስፓልት መንገድ ከትላንት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደተዘጋ ዋዜማ ሠምታለች። የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በአፋር በኩል ያለውን መንገድ በአማራጭነት እየተጠቀሙ መሆኑንና ይህም ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጋቸው ነግረውናል። መንገዱ የተዘጋው፣ በሰሜን ወሎ ዞን በመንግሥት ወታደሮች እና በሕወሃት ኃይሎች መካከል ከሚካሄደው ግጭት ጋር በተያያዘ መኾኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከረቡዕ ጀምሮ፣ ወልድያ የሚገኙ ባንኮች ለደንበኞቻቸው ጥሬ ብር መስጠት ማቆማቸውንና የጥሬ ብር ክምችታቸው መመናመኑን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የባንኩ ሠራተኞች ተናግረዋል። የባንኩ የጥሬ ብር ክምችት የተመናመነው፣ በአካባቢው ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት ደንበኞች ተቀማጭ ገንዘባቸውን ቀደም ብለው በማውጣታቸው ተረድተናል።
3፤ ዓለማቀፍ አጋሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ድጋሚ ግጭት መቀስቀሱ በጥልቀት እንዳሳሰባቸው መግለጥ ቀጥለዋል። ብሪታንያ፣ የትግራይ ኃይሎች በደቡባዊ ትግራይ እና በአፋር ክልል ጥቃት መክፈታቸውን አውግዛለች። ብሪታንያ፣ ሁሉም ወገኖች ግጭቱ እንዳይባባስና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል እንዲያደርጉ ጠይቃለች። ፈረንሳይ በበኩሏ፣ የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ሲቪሎችን ከጥቃት የመጠበቅና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል የማድረግ ዓለማቀፍ ግዴታቸውን እንዳይዘነጉ አሳስባለች። ሰብዓዊ እርዳታን ማስተጓጎል፣ ለሌላ ጥቅም ማዋል ወይም በእርዳታ ላይ ጥቃት መፈጸም ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑንም ፈረንሳይ አጽንዖት ሠጥታለች።
4፤ ኢሰመኮ፣ በትግራይና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን ለተቀሰቀሱ የትጥቅ ግጭቶች በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሠጣቸው ዛሬ ጠየቀ። ኢሰመኮ፣ የትጥቅ ግጭቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ፣ ልዩነቶች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ፣ ሲቪሎችና የሲቪል መሠረተ- ልማቶች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስቧል። በአካባቢው በድጋሚ የትጥቅ ግጭት መቀስቀሱ በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ተደራራቢ ጉዳትን ሊያሳድር የሚችል መሆኑ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ኢሰመኮ ገልጧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የኾኑ ወገኖች በተለይም የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ፈራሚ አካላት ስምምነቱን እንዲያከብሩ፣ በዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች ላይ የተደነገጉ ግዴታዎቻቸውን እንዲወጡና በሲቪሎችና መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ ርምጃዎች እንዲታቀቡ አሳስበዋል። ዓለማቀፉ ኅብረተሰብም የግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ወደ ንግግር እንዲመለሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን እንዲቀጥልም ብርሃኑ ጥሪ አድርገዋል።
5፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ የሠላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ወዳጄ አስማረ ትናንት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ተገደሉ። የወረዳው የጸጥታ ሀላፊ የተገደሉት፣ በጸጥታ ሥራ ላይ ሳሉ መኾኑን የወረዳው አስተዳደር ገልጧል። የወረዳው አስተዳደር፣ የሀላፊው ሕይወት ያለፈው "ጽንፈኛ" ሲል የጠራቸው ታጣቂዎች ባጠመዱት ጸረ-ተሽከርካሪ ፈንጅ መኾኑን ጠቅሷል።
6፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ፤ አሜሪካዊያን በማንኛውም ምክንያት ወደ ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች እንዳይጓዙ አስጠነቀቀ። ኢምባሲው፤ በአማራ ክልል በላሊበላ ከተማ አቅራቢያ ውጊያ እንደሚካሄድ መረጃ እንዳለው ጭምር ዛሬ ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ላይ ገልጧል። አሜሪካዊያን ላሊበላን ጨምሮ ወደ አማራ ክልል ሌሎች አካባቢዎች እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀው ኢምባሲው፣ በትግራይ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ስለመቋረጣቸው መረጃ ማግኘቱንም ጠቅሷል።
እስራኤልም፣ ዜጎቿ ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ አስጠንቅቃለች። ትግራይ ውስጥ የሚገኙ እስራኤላዊያንም፣ ከወታደራዊ ተቋማት እንዲርቁ እና አላስፈጊ የኾኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መክሯል።
7፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከዛሬ ዓርብ መስከረም 15 ጀምሮ የሠሌዳ ቁጥር 4 ካላቸው እና ከፖሊስ ሞተር ብስክሌቶች ውጭ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌቶችን በከተማዋ ማሽከርከርን አገደ። ፖሊስ፣ በሞተር ብስክሌቶች አማካኝነት በከተማዋ የቅሚያና የሥርቆት ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የገለጠው ፖሊስ፣ ወንጀለኞች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወርና የተሠረቁ እቃዎችን ለማጓጓዝ ሞተር ብስክሌቶችን በብዛት ይጠቀማሉ ብሏል። ፖሊስ፣ ትራፊክ መብራት የሚጥሱ፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ገጭተው የሚያመልጡና ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ የሠሌዳ ቁጥሮችን የሚጠቀሙ የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነም ጠቅሷል። ኾኖም እገዳው እስከመቼ ጸንቶ እንደሚቆይ ፖሊስ አልጠቀሠም።
እንዲሁም፤
1፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የመስቀል ቅርሶችን የሚያሳይ ልዩ የመስቀል በዓል ዐውድ ርዕይ ከዛሬ መስከረም 15 እስከ 24 ድረስ ለተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሙዚየም ለዕይታ ክፍት ሆኗል።
2፤ ድምጻዊት ሙኒት መስፍን ሙሉ የሙዚቃ አልበሟን ለአድማጮች ልታደርስ መሆኗን አስታውቃለች። ሙኒት፣ ከሙሉ አልበሟ መውጣት አስቀድሞም፣ "መንገድ" የተሠኘ አዲስ የሙዚቃ ሥራዋን ይፋ አድርጋለች። [ዋዜማ]