አልዋሸሁም
==============
22 ማዞሪያ፡፡
መንገዱ በሰው ተወሯል፡፡
ለታክሲ በተሰለፉ መአት ሰዎች፣ ከጣሪያ በላይ እየጮሁ ይሄንንም ያንንም በሚሸጡ ነጋዴዎች፣ አጎንብሰው ከነጋዴዎቹ ጋር በሚከራከሩ ገዢዎች፣ በሁሉም አቅጣጫ በቀስታ፣ ቶሎ ቶሎ በሚራመዱ እግረኞች፡፡ ቆመው ስልክ በሚያወሩ ሰዎች፡፡
እኔስ ምን እያደረግሁ ነው?
እየሮጥኩ ነው፡፡ በፍጥነት፡፡ ጠና ካለች ሴትዮ ነጥቄ የያዝሁትን ቅንጡ ቦርሳ በቀኝ እጄ ደረቴ ላይ አጣብቄ ይዤ በግራ እጄ አየሩን እየቀዘፍኩ እሮጣለሁ፡፡
ሁኔታዋ ደህና ብር እንደያዘች ነግሮኛል፡፡
ልክ ኦሎምፒክ ላይ ቀነኒሳ የሐይሌን መቅረት ባለማመን አስሬ ወደ ኋላ እየተገላመጠ እንዳየው አንድ ሁለቴ ዞር ብዬ የተከተለኝ ሰው አለመኖሩን እያየሁ ነው የምሮጠው፡፡
ቦርሳዋን የነጠቅኳት ሴት እንጥሏ እስኪቃጠል እየጮኸች ነበር፡፡
አንድ ወጠምሻ እየተከተለኝ ነበር፡፡ በጎ አድራጎት መሆኑ ነው፡፡ እኔ የምለው…ሰዉ ግን ለምን የራሱን ኑሮ አይኖርም…? ምነው በየጎዳናው የበጎ ሰው ሽልማት ካልሸለማችሁኝ ባዩ በዛ፡፡ ሆ!
ዞር አልኩ፡፡
የለም፡፡
ኡፎይ፡፡
ወያላ ‹‹ፒያሳ በላዳ!›› እያለ ከሚጮህላቸው ተደርድረውና በር ከፍተው ከሚጠብቁ ላዳዎች አንዱ ጋር ስደርስ የሁዋላ ወንበሩ ላይ ገብቼ ዘ---ፍ እንዳልኩኝ እዛው አገኘኋት፡፡
ቦርሳዋን የወሰድኩባት ሴትዮ አይደለችም፡፡ የፊዚክስ ህግ እዚህ ቀድማኝ እንድትገኝ አይፈቅድላትም፡፡
ግን እሷ ብትሆን ይሻለኝ ነበር፡፡
ሳሮን ነበረች፡፡ ሳሮን ገላልቻ፡፡ የሃይስኩል ጓደኛዬ፡፡ የሃይስኩል ፎንቃዬ፡፡ ከአስር ዐመት በላይ ያላየኋት፣ ዛሬም በሚያፈዝ ሁኔታ የምታምረው ሳሮን፡፡
በቁልቢው! ካልጠፋ ቀን፣ ካልጠፋ ሰዐት፣ ካልጠፋ ቦታ ዛሬ፣ እዚህ፣ እንዲህ ላግኛት?
የሰረቅኩትን ቦርሳ ኪሴ ውስጥ አጣጥፌ አስቀምጬው የነበረ ጥቁርና ከውጪ የማያሳይ ፌስታል ውስጥ በፍጥነት ጎሰርኩና ፊት ለፊት ገጠምኳት፡፡
ሳቀች፡፡
‹‹ኤርሚዬ! እውነት አንተ ነህ?›› ብላ አቀፈችኝ፡፡
ስታምር፡፡ መአዛዋ ሲጥም፡፡
አዬ መከራዬ!
ደማቅና ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋውጠንና ላዳው ሞልቶ መንገድ ስንጀምር ዛሬ ስላለንበት ሁኔታ ማውራት ጀመርን፡፡
‹‹እሺ…ሳሮንዬ እንደተመኘሽው አሪፍ ዶክተር ሆንሽ…?›› አልኳት ፌስታሉን ጠበቅ አድርጌ እየያዝኩ፡፡
በጣም እንዳላበኝ ያስተዋለች አትመስልም፡፡ ምናልባት ከረጅም ጊዜ በኋላ በድንገት በመገናኘታችን የደነገጥኩት መስሏት ይሆናል፡፡
‹‹ሃሃ…አዎ…ጎንደር ዩኒቨርስቲ ህክምና ተምሬ ዶክተር ሆኜልሃለሁ›› አለች ያንን የሚያምር ፈገግታዋን ይበልጥ አድምቃ፡፡
ሆኜልሃለሁ፡፡ ግራ እጇን የጋብቻ ወይ የቃልኪዳን ቀለበት ለማግኘት በአይኖቼ ፈተሸኩ፡፡
ባዶ፡፡
ልቤ ቀለጠ፡፡ የባሰ አላበኝ፡፡
ሹፌሩ ጋቢና የተቀመጠውን ተሳፋሪ ሂሳብ ሰብሳቢ አድርጎ እንደሾመ ቶሎ ብዬ ብር አወጣሁና የእሷንም ከፈልኩ፡፡ ሳትግደረደር ፈገግታዋን ለገሰችኝ፡፡
መልስ ተቀብዬ አየት አደረግኋትና ልክ እንደእሷ ፈገግ ለማለት እየጣርኩ፣
‹‹ጠብቄ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ባይሎጂ ላብ ስንገባ እነዚያን ምስኪን እንቁራሪቶች እየሳቅሽ ስትሰነጣጥቂያቸው፡፡ ሌሎቻችን ላለማስመለስ ስንታገል አንቺ ግን ደስ ይልሽ ነበር …›› አልኩ፡፡
በጣም ሳቀችና ‹‹አንተስ ኤርሚዬ? ሁሌ እንደምልህ ህግ አጠናህ አይደል?›› አለችኝ፡፡
ጥያቄዋ የጥፊ ያህል አመመኝ፡፡
እዚህ ላዳ ውስጥ ዘልዬ ከመግባቴ በፊት፣ እሷን ከማግኘቴ በፊት የተፈጠረው ነገር ሁሉ ልክ እኔ ሳልሆን ሌላ ሰው ሲያደርገው ቆሜ የታዘብኩ ይመስል ትእይንቱ በዐይኔ ላይ ዞረ፡፡
ይህቺ የልጅነት ህልምና ተስፋዬን የምታውቅ፣ ግን ደግሞ ያለፉት አስር አመታት እንዴት አድርገው ተስፋዬንም ህልሜን እንደቀሙት የማታውቅ ከድሮ ሕይወቴ በድንገት ተወንጭፋ የመጣች ልጅ ጥያቄዋ አሳመመኝ፡፡
ስሰርቅ ዛሬ የመጀመሪያዬ ሆኖ አይደለም፡፡
ስርቆትን መቁጠር እስካቆም፣ የጥፋተኝነት ስሜት ሽው እንኳን እስካይለኝ ለአመታት ሰልጥኜበታለሁ፡፡
አሁን ግን፣ ያኔ ማንም ሳያየኝ በፊት አይታኝ፣ ‹‹ኤርሚዬ አንተ ንግግርና ክርክር ላይ…ቋንቋ ላይ ጎበዝ ስለሆንክ አሪፍ ጠበቃ ወይ ዳኛ ይወጣሃል፡፡ ህግ ነው ማጥናት ያለብህ›› ካለችኝ ልጅ ጋር ተቀምጨ የሆንኩትን ነገር ሳስበው ሃፍረት ወረረኝ፡፡
ቢሆንም ፈገግ አልኩና ‹‹ አዎ…ህግ አካባቢ ነኝ›› አልኳት፡፡
መልሴን አጢኖ ለመረመረው አልዋሸኋትም፡፡
By Hiwot Emishaw
@wegoch
@wegoch
@paappii