"የሕመማቸውን ልክ መናገር የማይቻለን" ሲሉ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ጦርነት እንዲቆም፤ ህዝቡ የሰላም አየርን እንዲተነፍሱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ጥሪ አቀረቡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው አባታዊ የሰላም ጥሪ አስተላለፉ!
የመልእክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው፦
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
‹‹ወዝንቱ ውእቱ ዘነገርኩክሙ ከመ በኀቤየ ሰላመ ትርከቡ፡-
በእኔም ሰላምን እንድታገኙ ይህን ነገርኳችሁ›› (ዮሐ. 16÷33)
ዘመናትን እያፈራረቀ በድንቅ መግቦት ሕዝቡን የሚመራ ፣ በአባታዊ ምክሩ ዕረፍትን ፣ በቃሉ ትምህርት ጥበብን ፣ በመንፈሱ ምሪት መንገድን የሚሰጥ ፤ ሰውንም ከፍጥረት ሁሉ አልቆ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረ፣ ሞትና ድንጋጤን የሚያስወግድ ፈቃድና ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር አምላካችንን እያመሰገንን፤ በሩቅ ሀገራችሁን በልባችሁ ተሸክማችሁ የምትኖሩ፣ በቅርብም የሀገራችሁን ደስታና ኀዘን እየተካፈላችሁ በከተማ ውስጥ በሥራ፣ በዳር ድንበር በሀገር ጥበቃ ላይ የተሰማራችሁ፣ እንዲሁም በሕመም ሆናችሁ ፈውስን፣ በእስር ቤት ነፃነትን እየጠበቃችሁ የምትገኙ መላው ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ልጆቻችን ከሁሉ በማስቀደም ለዘመኑ ህልፈት፣ ለመንግሥቱ ሽረት በሌለበት በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊ ሰላምታችንን እናስተላልፋለን፡፡
የሰላም ትርጉሙ ተረጋግቶ መኖር፣ ወደ ዓላማ ፍጻሜ መድረስ፣ መርቆ ማለፍ ነው። ወልዶ ለመሳም፣ አሳድጎ ለመዳር፣ ዐርፍተ ዘመን የገታቸውን በክብር ለመሸኘት ሰላም አስፈላጊ ነው ። እስካሁን ድረስ የብዙ ነገሮች ዋጋ ታውቋል፤ የሰላም ተመን ግን አልታወቀም ። ሰላም ከሌለ ልጅነቱ መቦረቅ፣ ሽምግልናው ማረፍ የሌለበት ነው ። ሰላም ጠብን መግደል፣ ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ይድላው ብሎ የልብ ስፋት ማግኘት ነው ። ሰላም የኑሮና የሞት ፍርሃትን የሚያስወግድ ነው ። በትክክል ኖረ የሚባለው ሰላማዊ ሰው በኑሮው ድንጋጤ፣ በሞቱም ፍርሃት የሌለበት ነው ። ሰላም ከሌለ ምድር ትታወካለች፣ አራዊት መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገር ይሰደዳሉ ። በዚህም ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን ። ሰላም በሌለበት ሰጪ ባለጠጋ፣ ጠያቂ ተመጽዋች ማግኘት አይቻልም ።
ሰላም ሁለንተናዊ መገዛትን ትፈልጋለች ፣ የሰላም ልብ ፣ የሰላም ቃል ፣ የሰላም ተግባር ያስፈልጋል ። ሰላምን አስቦ ካልተናገሩትና ካልተገበሩት ሁከት እንደ ነገሠ ይቀጥላል ። ሰላምን ተናግረውት ካላሰቡበትና ካልተገበሩት በድብብቆሽ ብዙ ሰው ያልቃል። ሰላምን በሁለንተናችን መልበስ አጭሩን ዘመናችንን ለማጣፈጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ።
በዓለም ላይ ብዙ ሺህ የሰላም ስምምነቶች ሲደረጉ ኖረዋል ። የሰው ልጅ ግን ሟች መሆኑን ረስቶ ገዳይ በመሆኑ፣ ራሱንም በራሱ ለማወክ በመፍቀዱ የሰላም ስምምነቶች ተፈርመው ፊርማው ሳይደርቅ እንደገና ሁከት ይሆናል ። በዚህም “ወይፌውሱ ቅጥቃጤሆሙ ለሕዝብየ ወይቤሉ ሰላም ሰላም ወአልቦ ሰላም፡- የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ።” (ኤር. 6፡14) የሚለው ቃለ መጽሐፍ እየተፈጸመ ይመስላል፡፡
በዘመናችን ሰዎች በትዳር፣ በቤተ ዘመድ፣ በሀገር ሰላም ያጡ እንደሆነ እየተመለከትን ነው ። ሰው የራሱን ክፉ ጠባይ መግዛት ባለመቻሉ ወዶ የሸኘውን ሲፈልገው ይኖራል ። የሕጎችም ብዛት መፈራራትን እንጂ እውነተኛ ሰላምን ማምጣት አይችሉም ። ሰላም በማጣታችን በዘገየች ሀገር ዛሬም ስለምግብ የሚጨነቅ ሕዝብ አገልጋይ በመሆናችን በታላቅ ትካዜ ውስጥ ሆነን መልእክት እንድናስተላልፍ አድርጎናል።
እግዚአብሔርን ለሚወዱ የተሰጠች ጸጋ ሰላም ናት ። ታዲያ ይህ ሰላም ርቆን ሳለ እርሱን መውደዳችን እውነተኛ ነው ወይ( ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል ። አንድ ዓይነት መልክና ማንነት ያለው ሕዝብ መተላለቁ ሰውነትንም መንፈሳዊነትንም መክሰር እንደሆነ የተረዳነው አይመስልም ። በእውነቱ ካየነው ነጭ ለብሰን ሳይሆን ማቅ ለብሰን የምናለቅስበትና በንስሐ ምሕረተ ሥላሴን የምንናፍቅበት ጊዜ ነው ።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
ትዕግሥተኛዋ መሬት እንኳ እየተናወጠች፣ ዓለም የቅጽበት ዕድል ብቻ እንዳላት እየጠቆመች ነው ። የመሬት መንቀጥቀጡ የዘመኑን ፍጻሜ የሚያስረዳ ሲሆን የምናያቸው ምልክቶች ሁሉ በተሰበረ ልብ እግዚአብሔርን እንድንፈልግ የሚያሳስቡን ናቸው ።
በመሆኑም በሀገራችን በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያሉ ጦርነቶች ቆመው ልጆቻችን በሰላም መኖር እንዲችሉ፤ በጦርነት እየተሰቃዩ የሕመማቸውን ልክ መናገር የማይቻለን የኦሮሚያና የአማራ ክልል ነዋሪዎች ሰላምን እንዲያገኙ አባታዊ ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን ።
በትግራይ ክልል ያለው የአስተዳዳሪዎች አለመግባባት በሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ችግርና ጭንቀት እያመጣ ስለሆነ በትሕትና መንፈስ እርስ በርስ መገናዘብ ተፈጥሮ ዕረፍት ያጣው ሕዝብ መረጋጋት እንዲችል ታደርጉ ዘንድ አደራችን የጠበቀ ነው ።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የምትገኙ የሃይማኖት አባቶች መበደላችሁን እናውቃለን ፣ በኀዘናችሁ ሰዓት አብረን መቆም ባለመቻላችን ማዘናችሁም እርግጥና ተገቢ ነው ። ነገር ግን ሁሉም ነገር የሚካሰው በእርቅ ሲሆን እኛ የገፋነውን እርቅ ዓለም ሊቀበለው ስለማይችል፤ በእጃችንም የያዝነው መስቀለ ክርስቶስ የሰላም ዓርማ ነውና ልባችሁን ለሰላም፣ ለአንድነት እንድታዘጋጁ እንጠይቃለን ።
በመጨረሻም የመሬት መንቀጥቀጥ ባለበት አካባቢ እየተጨነቃችሁ ያላችሁ ልጆቻችን ረድኤተ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን በጸሎት የምታስባችሁ መሆኑን እየገለጽን መላው ኢትዮጵያውያን ለጉዳቱ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለሚኖሩት ወገኖቻቸው አቅማቸው በፈቀደው መጠን ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ